ሐተታ ግምገማ፡፡ ትንቢትና ነቢይነት፤ በነቢዩ ሺመልስ፤ ተፈራ ሥዩም የሕትመት ሥራ አገልግሎት፣ አ/አ፤ 2008 ዓ.ም.፤ 157 ገጽ። 70 ብር| 20 ዶላር| 15 ኢዩ።

የመጽሐፉ መልእክት ምንድነው? የተጻፈው ለማን ነው? አጻጻፉ ግልጽ ነው? በቂ ማስረጃ አቅርቧል? ደራሲው በተለይ ባለፉት ሃያ አምስት አመታት በአገራችን ስለ ተከሰተው የነቢያትና የሐዋርያት አገልግሎት የማናውቀውን ለእርምት የሚሆን ምን አዲስ ነገር አስታወቀን? እነዚህንና ተመሳሳይ ጥያቄዎችን መጠየቅ ግድ ነው። እኛም ከመጽሐፉ እየጠቀስን በተለያዩ ጒዳዮች ላይ እንመካከር።

1/ ትንቢትና ነቢይነት:- ትንቢት፣ የትንቢት ሥጦታ፣ እና ነቢይነት በሚሉ ሦስት ክፍሎች ተከፋፍሏል። ንኡስ ክፍሎቹ ድግግሞሽ ይበዛቸዋል፤ ለምሳሌ፣ አጋቦስ የተባለ ነቢይ (የሐዋ ሥራ 11:27-30፤ 21:10-11) ገጽ 59፣ 77፣ 81፣ 89፣ 94፣ ወዘተ ላይ ተጠቅሷል። ገጽ 59 ላይ ይኸው አጋቦስ “አንጋፋ ነቢይ” ተብሏል። ደራሲው ከምን ተነስቶ “አንጋፋ” እንዳለ መረጃ ባያቀርብም፣ ዓላማው “ነቢይነት” ዋነኛ ነው ለማሰኘት የተደረገ ጥረት መሆኑ ግልጽ ነው። የመጽሐፉም ድክመት እዚህ ላይ ነው። “ትንቢትና ነቢይነት”ን ለቤተክርስቲያን ጥሪና ለአገልጋዮች ፍሬአማነት መመርመሪያ ማድረጉ የሙግቱን መሠረት አዛንፎበታል። እግዚአብሔርን በቅዱስነቱ፣ በፍቅሩ፣ እና በፈራጅነቱ ያልተገነዘበ አቀራረብ ሚዛናዊ ሊሆን አይችልማ! በትንቢትና በነቢይነት ላይ ማተኮር የ[አገራችን] ቤተ ክርስቲያን ዋነኛ ችግር ነው!

“አካል ብዙ ብልቶች እንጂ አንድ ብልት አይደለምና። እግር። እኔ እጅ አይደለሁምና የአካል ክፍል አይደለሁም ብትል፥ ይህን በማለትዋ የአካል ክፍል መሆንዋ ይቀራልን? ጆሮም። እኔ ዓይን አይደለሁምና የአካል ክፍል አይደለሁም ቢል፥ ይህን በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ ይቀራልን? አካል ሁሉ ዓይን ቢሆን መስማት ወዴት በተገኘ? ሁሉም መስማት ቢሆን ማሽተት ወዴት በተገኘ?” (1ኛ ቆሮንቶስ 12:14-17)።

2/ የትንቢትና የነቢይነት አስተምህሮ በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ አሜሪካን አገር (ብሎም በአፍሪካ) ከተስፋፋው “ኢንዲፔንደንት ኔትዎርክ ካሪዝማቲክ፣” “ኢንተርናሽናል ሃውስ ኦፍ ፕሬየር፤” “ሸፐርዲንግ ሙቭመንት፣” ወዘተ ጋር የተያያዘ ነው። የመድረክ መብራትና የሙዚቃ ስልት፣ የአምልኮ መልክ፣ የገንዘብ አሰባሰብ፣ የአገልጋዮች አሰባበክ፣ ግለኛ ታዋቂነት፣ አዘማመርና ቁመና የአሜሪካ ቲቪና ድርጅት ተጽእኖ እንዳለበት ያሳያል፡፡ በዚያም በዚህም ራሳቸውን የሰየሙ፣ እርስበርስ የተሰያየሙ ነቢያትና ሐዋርያት፣ የዘመን ፍጻሜን ትምህርት ከተዓምራትና ከጮሌ ንግድ ጋር አስማምተው ይዘውታል። ደራሲው በዋቢነት ዊምበርን፣ ፍሮስትን፣ ኬኔት ሄጊንን፣ መሆኒን፣ ማጣቀሱ ይህን ድምዳሜ ግድ ይላል። እግዚአብሔር ግን በዚህም ውስጥ ሥራውን አይሠራም ማለት ጥበቡንና ኃይሉን አለመረዳት ነው! እንግዲህ ከእነዚህ አብዛኛዎቹ ራሳቸውን የአምላክ አፈ ቀላጤ እንደ ሆኑ ቆጥረዋልና ያፈቀዳቸውን ቢናገሩ እግዚአብሔር ተናግሮ ነው፤ በፍቅረ ንዋይና በዝሙት ቢያዙ፦ እግዚአብሔር ፍቅር ነው፣ አትፍረድ ብሏል! የኔን ጒድፍ የምታይ የራስህን ምሰሶ ምነው? መንጋውን አንበትን፣ ለሰይጣን መንገድ አንክፈትለት፤ ለኔና ለጌታ ተውልን! እያሉ ያዋክቡናል! ይቅርታ ካልኩ ወዲያ ጭቅጭቁ ምንድነው? ለዚያውም እኔ ሆኜ ነው፤ ተውኝ፣ ሥራዬን ልሥራበት ማለት ይቃጣቸዋል! በዚህም የክርስቶስን ማህበር የግለሰብ ንብረት እንደ ሆነ ያስመስላሉ።

3/ ደራሲው፣ “ክርስቶስ ኢየሱስ የነቢያት አውራና ምሳሌ ነው” ይለናል (ገጽ 82)። ለዚህም፣ ሳምራዊቱ ሴት “አንተ ነቢይ እንደ ሆንህ አያለሁ” ማለቷን (ዮሐንስ 4:19)፤ ዓይኖቹን የከፈተለትን፣ ስለ እርሱ ምን ትላለህ? ቢሉት “ነቢይ ነው” ማለቱን (ዮሐንስ 9:17)፣ ወዘተ፣ እንደ መረጃ አቅርቦልናል። የጠቀሳቸው የመጽሐፍ ክፍሎች መደምደሚያ ግን የሚገልጹት ኢየሱስን “የነቢያት አውራና ምሳሌ” ሳይሆን መሲሕና የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ነው።

ዮሐንስ 4፡19- ሴቲቱ። ጌታ ሆይ፥ አንተ ነቢይ እንደ ሆንህ አያለሁ ... ሴቲቱ። ክርስቶስ የሚባል መሲሕ እንዲመጣ አውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ይነግረናል አለችው። ኢየሱስ። የምናገርሽ እኔ እርሱ ነኝ አላት ... ሴቲቱም እንስራዋን ትታ ወደ ከተማ ሄደች ለሰዎችም። ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑና እዩ፤ እንጃ እርሱ ክርስቶስ ይሆንን? አለች። ከከተማ ወጥተው ወደ እርሱ ይመጡ ነበር ... ሴቲቱም። ያደረግሁትን ሁሉ ነገረኝ ብላ ስለ መሰከረችው ቃል ከዚያች ከተማ የሰማርያ ሰዎች ብዙ አመኑበት ... ሴቲቱንም። አሁን የምናምን ስለ ቃልሽ አይደለም፥ እኛ ራሳችን ሰምተነዋልና፤ እርሱም በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደ ሆነ እናውቃለን ይሉአት ነበር።” ዮሐንስ 9፡17- ዕውሩን። አንተ ዓይኖችህን ስለ ከፈተ ስለ እርሱ ምን ትላለህ? ደግሞ አሉት። እርሱም። ነቢይ ነው አለ... እርሱ ክርስቶስ ነው ብሎ የሚመሰክር ቢኖር ከምኵራብ እንዲያወጡት አይሁድ ከዚህ በፊት ተስማምተው ነበርና... ወደ ውጭም አወጡት። ኢየሱስም ወደ ውጭ እንዳወጡት ሰማ ሲያገኘውም። አንተ በእግዚአብሔር ልጅ ታምናለህን? አለው። እርሱም መልሶ። ጌታ ሆይ፥ በእርሱ አምን ዘንድ ማን ነው? አለ። ኢየሱስም። አይተኸዋልም ከአንተ ጋርም የሚናገረው እርሱ ነው አለው። እርሱም። ጌታ ሆይ፥ አምናለሁ አለ፤ ሰገደለትም።

4/ ስለ ትንቢት ዓላማ ሲያስረዳ፣ “የሚተላለፈው መልእክት ፍርድን የተሞላ፣ ጨለማ የበዛበት፣ የሚያስፈራራ ወዘተ ከሆነ አጠራጣሪነቱን እያሰፋው ይመጣል” (ገጽ 36) ይለናል። ይህን የሚለው ትንቢት “ለማነጽ፣ ለመምከርና ለማጽናናት” የሚለውን ለማጽናት ነው። ሆኖም፣ ገጽ 77 (2ለ) ላይ ጴጥሮስ የአናንያን (እና የሰጲራን) በመንፈስ ቅዱስ ላይ መዋሸት ሲጠቅስ (የሐዋ. ሥራ 5:1-11)፣ ጴጥሮስ ይህን የተሰወረ ጉዳይ ያወቀው በመንፈስ ቅዱስ (በነቢይነት መንፈስ) እንደ ሆነ ለማስረዳት ነው። ደራሲው የዘነጋው ግን፣ ይኸ ሁኔታ የፍርድና የማጥራት እርምጃ መሆኑን ነው፤ ባልና ሚስቱ “መንፈስ ቅዱስን ሊያታልሉ፣ ሊፈታተኑ ተስማሙ” (5:3፣9)። ሁለቱም ተቀሠፉ። “በቤተ ክርስቲያን ሁሉና ይህንም በሰሙ ሁሉ ላይ ታላቅ ፍርሃት ሆነ” ብሏልና (የሐዋ ሥ 5:11)

5/ ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው ለመፍረድ እንዳይደለ ለማስረዳት፣ “ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና” የሚለውን ሲጠቅስ (ዮሐንስ 3:17)፤ ቀጥሎ፣ “በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል። ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ ነው” የሚለውን ሳይጠቅስ አልፎታል (3:18-19)

6/ ነቢያትና ሰባኪያንን ማወዳደር። “ቃሉን በጥልቅ የምናጠና ከሆነ ግን ነቢያቶች ከሰባኪያን ያለፈ አገልግሎት ያላቸው መሆኑን እንረዳለን” (ገጽ 76፣ አንቀጽ 4፣ መስመር 4-5)። ደራሲው “ነቢይ” እንደ ሆነ እናስተውል (በመጽሐፉ መጀመሪያ ገጽ ላይ “የትንቢት መልእክት” አስተላልፏል)። "ከሰባኪያን ያለፈ አገልግሎት" ምን ዓይነት ነው?
7/ ስለ ነቢያት ሲያወሳ፣ የዛሬዎቹን ነቢያት በነ ኤርምያስና ኤልያስ፤ የዛሬዎቹን ሐዋርያት፣ በነ ጴጥሮስና ጳውሎስ ልክ ያሰባቸው ይመስላል፤ እነዚያ ለዚያ ዘመን፣ እነዚህም ለዚህ ዘመን የሚል ይመስላል!!

ቃሉ፣ “በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፣ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ በእርሱም ሕንጻ ሁሉ እየተጋጠመ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል፤ በእርሱም እናንተ ደግሞ ለእግዚአብሔር መኖሪያ ለመሆን በመንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ” (ኤፌሶን 2:20-22) ሲል፣ የማይደገም ጥሪና አገልግሎትን አመልካች ነው። “ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፥ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” (1ኛ ቆሮንቶስ 3:11)“ወደ ተራራም ወጣ፥ ራሱም የወደዳቸውን ወደ እርሱ ጠራ፥ ወደ እርሱም ሄዱ። ከእርሱም ጋር እንዲኖሩና ለመስበክ እንዲልካቸው፥ ድውዮችንም ሊፈውሱ አጋንንትንም ሊያወጡ ሥልጣን ይሆንላቸው ዘንድ አሥራ ሁለት አደረገ” (ማርቆስ 3:13-15)። ኢየሱስ በታቦር ተራራ ላይ ሲጸልይ ሙሴና ኤልያስ ተገልጠው አነጋገሩት፤ ሐዋርያቱ ጴጥሮስ፣ ዮሐንስ፣ እና ያዕቆብ በዚያ ነበሩ (ማርቆስ 9:1-8)

8/ “የሐዋ ሥራ 21:9 ትንቢትን ስለሚናገሩ አራቱ የፊሊጶስ ሴት ልጆች ይናገራል። እነዚህ ደናግል ሴት ልጆች ትንቢትን ይናገሩ እንጂ ነቢያት አልነበሩም። እነዚህ የፊሊጶስ ደናግል ሴት ልጆች የማነጽ አገልግሎት ይሰጡ ነበር እንጂ የወደፊቱን አስቀድመው አልተናገሩም። ሁሌም የወደፊቱን አስቀድሞ የሚናገረው ነቢይ እንጂ የትንቢት ሥጦታ የወደፊቱን ፈጽሞ ሊተነብይ አይችልም፤ ወይም ስለ ወደፊቱ ሙሉ የሆነውን ዕይታ ሊሰጥ አይችልም” (ገጽ 30፣ አንቀጽ 3፣ 4)

ስለ ፊሊጶስ ሴት ልጆች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው በሐዋርያት ሥራ 21:8-9 ብቻ ነው፣ “በነገውም ወጥተን ወደ ቂሣርያ መጣን፥ ከሰባቱም አንድ በሚሆን በወንጌላዊው ፊልጶስ ቤት ገብተን በእርሱ ዘንድ ተቀመጥን። ለእርሱም ትንቢት የሚናገሩ አራት ደናግል ሴቶች ልጆች ነበሩት፤” “ከሰባቱም” ሲል ፊሊጶስ ማዕድ እንዲያገለግሉ በሐዋርያት ከተሾሙት ዲያቆናት መሓል መሆኑንና ከሐዋርያው ፊሊጶስ ሌላ እንደ ሆነ ለማስረዳት ነው (የሐዋ ሥ 6:1-6፤ ማር 3:13-19፤ ዮሐ 1:44-46፤ 12:20-22)። በሌላ አነጋገር፣ ደራሲው ስለ ደናግሉ የፊሊጶስ ሴት ልጆች "የማነጽ አገልግሎት ይሰጡ ነበር እንጂ የወደፊቱን አስቀድመው አልተናገሩም" ላለው ማስረጃ አላቀረበም፡፡ የትንቢት ሥጦታንና ነቢይነትን ለምን እንደ ነጣጠላቸው አላብራራም!

9/ “ስብከት በእግዚአብሔር መንፈስ ሊነሳሳ ወይም ሊቀባ ቢችልም የአእምሮ ሲሆን፣ ትንቢት ግን ሁሌም ከፍጥረታዊ ያለፈ የሰውን አእምሮ የማይጠይቅና ፍጹም መንፈሳዊ ነው” (ገጽ 30፣ አንቀጽ 4)። ይህም፣ አእምሮንና መንፈስን በመነጣጠሉ፣ አእምሮን በማሳነሱ ያልተጠበቀ ችግር ፈጥሯል፤ “የነቢያትም መናፍስት ለነቢያት ይገዛሉ” ተብለናል (1ኛ ቆሮ 14:32)። እንደ ባለ አእምሮ እንድናስብ፣ በአእምሮ እንድናድግ (ሕጻናት ሆነን እንዳንቀር)፣ ከአእምሮ እንዳንወጣ ተብለናል (1ኛ ቆሮ 14:12-25“ማንም መንፈሳዊ የሆነ ቢመስለው ይቺን የጻፍኩላችሁ የጌታ ትእዛዝ እንደ ሆነች ይወቅ፤ ማንም የማያውቅ ቢኖር አይወቅ14፡37-38)፤ “ሙሉ ሰው ወደ መሆን” እደጉ ሲለን በአእምሮ ጭምር ነው (ኤፌሶን 4:12-17)። አእምሮን ያገለለ መንፈሳዊነት መንፈሳዊ አለመሆን ብቻ ሳይሆን ተጠያቂነትን የሻረ ነው፤ አሁን ለምናየው ዝብርቅርቅ ዋነኛ መንስኤ “መንፈሳዊ” በሚል ሽፋን ሁሉም የሻውን በማድረግ መሠማራቱ ነው።

10/ “የትንቢት ሥጦታ ምሪትን ለማረጋገጫ እንጂ ለምሪት አልተሰጠንም” (ገጽ 33፣ አንቀጽ 1፣3) ሲል ምን ማለት ነው?
11/ በወጣቶችና “ቀደም ባሉት” መሓል የተከሰተውን ችግር ሲዳኝ፣ ወጣቱ ለውጥ ፈላጊ (ለውጡ ምን እንደ ሆነ ሳይጠቅስ)፣ “የቀደሙት” ግን “ትውፊት ላለማስነካት” የሚሹ ብሏቸዋአል። ስለ ተከሰተው ችግር በሰጠው ብያኔ፣ ሁለቱን ወገን ላለማስቀየም የሞከረ ይመስላል (ገጽ 32)! ለዚህ የጠቀሰው ኢያሱ 5:13-14ን ነው፤

“እንዲህም ሆነ፤ ኢያሱ በኢያሪኮ አጠገብ ሳለ ዓይኑን አንሥቶ ተመለከተ፥ እነሆም፥ የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ የያዘ ሰው በፊቱ ቆሞ ነበር፤ ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ። ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህን? አለው። እርሱም። አይደለሁም፤ እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ሆኜ አሁን መጥቼአለሁ አለ።”

ሰይፍ በእጁ የያዘው፣ ከእስራኤልም ከኢያሪኮም ወገን እንዳይደለ መናገሩ ነው ይለናል ደራሲው። ታሪኩን ባንረሳ፤ እስራኤል ዮርዳኖስን ተሻግረዋል፤ እግዚአብሔር በጄኔራል ኢያሱ መሪነት ኢያሪኮን መምታት እቅዱ ነበር (ኢያሱ 4-6)። የተመዘዘ ሰይፍ የያዘው ሰው፣ ከኢያሪኮ የወገነ አልነበረም፤ ሊወግንም አይችልም። የታየው ለኢያሱ ነው! ኢያሱ ከፊትለፊቱ ስለሚጠብቀው ዘመቻ እያሰበ ነው። የሙሴ ረዳት ሆኖ ሙሴ ሲሞት ሕዝቡን ከነዓን ለማግባት እግዚአብሔር የመረጠው ነው። ታላቅ ሸክም በትከሻው ላይ ነበረ። ከዚህ የተነሳ ሊያረጋጋው እግዚአብሔር እንዲህ ብሎት ነበር፦

“በሕይወትህ ዕድሜ ሁሉ ማንም አይቋቋምህም፤ ከሙሴ ጋር እንደ ሆንሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ አልጥልህም፥ አልተውህም። ለአባቶቻቸው። እሰጣችኋለሁ ብዬ የማልሁላቸውን ምድር ለዚህ ሕዝብ ታወርሳለህና ጽና፥ አይዞህ። ነገር ግን ጽና፥ እጅግ በርታ፤ ባሪያዬ ሙሴ ያዘዘህን ሕግ ሁሉ ጠብቅ፥ አድርገውም፤ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲከናወንልህ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል። የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፥ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም። በምትሄድበት ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና ጽና፥ አይዞህ፤ አትፍራ፥ አትደንግጥ ብዬ አላዘዝሁህምን?” ብሎታል (ኢያሱ 1:5-9)።

ደራሲው፣ ኢያሱም ወደ ምድር በግምባሩ ተደፍቶ ሰገደና። ጌታዬ ለባሪያው የሚነግረው ምንድር ነው? አለው። የእግዚአብሔርም ሠራዊት አለቃ ኢያሱን። አንተ የቆምህበት ስፍራ የተቀደሰ ነውና ጫማህን ከእግርህ አውልቅ አለው። ኢያሱም እንዲሁ አደረገ” የሚለውን አልጠቀሰውም (5:14-15)፤ በተጨማሪ ዘጸአት 3፡5፣ ራእይ 19:9-10፤ 22፡8-9 ይመልከቱ። ታሪኩ የሚያስረዳን፣ የጦሩ መሪ እግዚአብሔር እንጂ ኢያሱ እንዳይደለ፣ ሕዝቡን ወደ እረፍት ሊያገባ “የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ የያዘ ሰው” (ኢየሱስ፣ እውነተኛው ኢያሱ) እንደ ሆነ ሊያረጋግጥለት ነው! የዚህ ክፍል ቀዳሚ አሳብ፣ ሳይቀደስ የእግዚአብሔርን ሥራ መሥራት አይቻልም ነው፤

12/ ጳውሎስ “ግትር” በመሆኑ፣ “በትንቢትና በነቢያት ሊገዛ አልፈለገም፣ አልወደደም” (ገጽ 58-60)። ሐዋርያውን “ግትር” የሚል ቃል አይስማማውም። ጒዳዩ የሌሎችን አሳብ የመቀበልና ያለመቀበል አይደለምና። ደራሲው የሐዋርያት ሥራ 20:22ን ሲያነብ፣ ቀጥሎ ቊ. 23 እና 24ን አለማንበቡ ላልሆነ ድምዳሜ ዳርጎታል። አገልጋዮችና ምእመን በትንቢትና በነቢያት እንዲገዙ ማስጠንቀቂያ ቢጤ ይመስላል!

የሐዋ. ሥ 20፡22-24 “አሁንም፥ እነሆ፥ እኔ በመንፈስ ታስሬ ወደ ኢየሩሳሌም እሄዳለሁ፥ በዚያም የሚያገኘኝ ምን እንደ ሆነ አላውቅም፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ። እስራትና መከራ ይቆይሃል ብሎ በየከተማው ሁሉ ይመሰክርልኛል። ነገር ግን ሩጫዬንና ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን አገልግሎት እርሱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ወንጌልን መመስከር እፈጽም ዘንድ ነፍሴን በእኔ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር እቆጥራለሁ።”

“ከጌታ ኢየሱስ የተቀበልሁትን አገልግሎት” ሲል ሐዋ ሥ 9፡15-16 “ጌታም። ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ሂድ፤ ስለ ስሜ ስንት መከራ ሊቀበል እንዲያስፈልገው እኔ አመለክተዋለሁና አለው” የሚለውን መጥቀሱ ነው። በሌላ አነጋገር፣ ሐዋርያት ሥራ 20፣ ኢየሱስ ከዓመታት በፊት ጳውሎስን ደማስቆ መንገድ ላይ ሲገናኘው የሆነውን የሚተርክ ነው! ጉዳዩ ራስን ስለ ማዳን ሳይሆን የክርስቶስን ጥሪ በመፈጸም ውስጥ መስዋእት ስለ መሆን ነው፤ ሁለቱ በጣም የተራራቁ አስተሳሰቦች ናቸው። ጳውሎስ እንደ ጌታው “በከንቱ እንዳልሮጥሁ በከንቱም እንዳልደከምሁ በክርስቶስ ቀን የምመካበት ይሆንልኛል። ነገር ግን በእምነታችሁ መሥዋዕትና አገልግሎት ተጨምሬ ሕይወቴ እንኳ ቢፈስ፥ ደስ ብሎኛል ... በመሥዋዕት እንደሚደረግ፥ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፥ የምሄድበትም ጊዜ ደርሶአል” (ፊል 2:16-17፤ 2ኛ ጢሞ 4:6)
13/ “የእግዚአብሔር ሕዝብ የትንቢት ሕዝብ ነው” (መግቢያ ገጽ 9፣ አንቀጽ 1)። ምን ማለት ነው?
14/ “ማንም ሰው ምንጩ እንዳለው እስካላወቀ ድረስ ምንም ስሜት የለውም። እንዲያውም ቢረሳው ይሻላል እንጂ” ገጽ 99 ቁ.3 አንቀጽ 1፣ መስመር 1። ምን ማለት ነው?
15/ “ነቢያቶች የኃይማኖት መሪዎችንና ነገሥታትን ሲያርሙና ሲገሥጹ እንደዚሁም ሊመጣ ያለውን የእግዚአብሔርን በረከት ሆነ ቊጣ አስቀድመው በማወቅ ሕዝብን ሲያስጠነቅቁ እናያለን” (ገጽ 14፣ አንቀጽ 3፣ መስመር 3-5)። እውነታው ይኸ ከሆነ፣ ሀ/ የአገር መሪዎች በአምሳለ እግዚአብሔር የተፈጠረውን ሲያናክሱ፣ አገር ሲዘርፉ ነቢያት ምን ሲሉ ነበር? ለ/ ደራሲው የውጭ አገሩን ከመጥቀስ ይልቅ (ገጽ 103-107) ለምን በአገራችን ነቢያትና ሐዋርያት መሓል በገሃድ የታየውን አልጠቀሰም? ለጸሎት ሁለት መቶ ዶላር (አምስት ሺህ ብር) እጅ በጅ ሲጠየቅ፣ ወዘተ። መፍረድ ወይም የፍቅር ጒድለት እንዳይመስል ነው? ምእመንስ ስለ የትኛው ነቢይና ትንቢት እንደሚያወራ አውቆ ከጥፋትና ከስህተት ትምህርት ይታረምና ያምልጥ? የእግዚአብሔር ቃል ግን መንጋውን ከተኲላዎች ለማዳን ስምና ድርጊቱን ጠቅሶ ያስጠነቅቀናል፤

“ለሚወጣ ሁሉ በክርስቶስም ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት ለሚኖር አብና ወልድ አሉት። ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ ይህንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ሰላምም አትበሉት፤ ሰላም የሚለው ሰው በክፉ ሥራው ይካፈላልና” (2ኛ ዮሐንስ 9-11)፤ “የብርሃኑ ፍሬ በበጎነትና በጽድቅ በእውነትም ሁሉ ነውና ለጌታ ደስ የሚያሰኘውን እየመረመራችሁ፥ እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ፤ ፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ፥ ይልቁን ግለጡት እንጂ፥ እነርሱ በስውር ስለሚያደርጉት መናገር እንኳ ነውር ነውና፤ ሁሉ ግን በብርሃን ሲገለጥ ይታያል፤ የሚታየው ሁሉ ብርሃን ነውና” (ኤፌሶን 5:11-13)። ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን መለያየትንና ማሰናከያን የሚያደርጉትን ሰዎች እንድትመለከቱ እለምናችኋለሁ፥ ከእነርሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ፤ እንዲህ ያሉት ለገዛ ሆዳቸው እንጂ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አይገዙምና፥ በመልካምና በሚያቆላምጥ ንግግርም ተንኮል የሌለባቸውን ሰዎች ልብ ያታልላሉ (ሮሜ 16:17-18)። እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ፥ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞች ሠራተኞች ናቸውና። ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና። እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል (2ኛ ቆሮንቶስ 11:13-15)።

ማጠቃለያ፦ መጽሐፉ የአሳብ ድግግሞሽ ይታይበታል። በአንደኛው ክፍል ላይ የተሠመረበት አሳብ፣ በሌላኛው ክፍል ተፋልሶና ተድበስብሶ ይታያል። ይኸ ሊሆን የሚችለው፣ በተለያዩ ጊዜአት የተሰበኩ ትምህርቶች ሳይብላሉና ሳይገናዘቡ በአንድ ላይ መሰባሰባቸውን፤ ዋቢ የእንግሊዝኛ መጻሕፍትን ይዞታና አቀራረብ መከተሉና ማዋሃዱ እና የአርትዖት ሥራ መጓደሉን ነው። ደግሞ ጅምላ ድምዳሜ ይታይበታል። ጅምላ ድምዳሜ፣ ከአንዲት መነሻ ሁሉ አቀፍ እውነታን ማወጅ፣ ድምዳሜው የሚያስከትለውን አሉታዊ ተጽእኖ አለማስተዋል ነው። ትንቢትና ነቢይነት ለመማሪያ ጠቃሚ መጽሐፍ ነው። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች መጽሐፉን በጥንቃቄ አንብበው ለምእመን ቢያብራሩ። ደራሲ ጠያቂና ነጋሪ ብቻ ሳይሆን ተጠያቂና አድማጭም ነውና፣ ደራሲ ነቢዩ ሺመልስ ከላይ ላነሳናቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ቢልክልን በ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ለአንባቢ እናዳርሳለን። ክብር ሁሉ ለቤተ ክርስቲያኑ ጌታና አዳኝ ለክርስቶስ ኢየሱስ ይሁን!