እ ን ዳ ለ ፈ  ው ሃ

በ አስቴር ተፈራ ቊ.3- 2019-12-25 | የኢት ወንጌላዊት ቤ/ክ ዴንቨር ኮሎራዶ | © 2019 ዮሐንስ ጦና

astercd

የእህት አስቴር ተፈራ ቊጥር ሦስት መዝሙር ለጌታ ልደት 2019-12-25 ለሕዝብ መቅረቡ በምክንያት መሆን አለበት። ለጌታ የቀረበ የዝማሬ ስጦታ መሆን አለበት። “መከራህንም ትረሳለህ፤ እንዳለፈ ውሃ ታስበዋለህ።” እንዳለ ኢዮብ (11:16)። “በውሃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ በወንዞችም ውስጥ ባለፍህ ጊዜ አያሰጥሙህም” እንዳለ ኢሳይያስ (43:2)። የምስጋና ስጦታ ይመስላል፤ “ሃሌ ሉያ። እግዚአብሔር የልመናዬን ድምፅ ሰምቶአልና ወደድሁት … ነፍሴ ሆይ፥ ወደ ዕረፍትሽ ተመለሺ፥ እግዚአብሔር መልካም አድርጎልሻልና … ስላደረገልኝ ሁሉ ለእግዚአብሔር ምንን እመልሳለሁ? የመድኃኒትን ጽዋ እቀበላለሁ፥ የእግዚአብሔርንም ስም እጠራለሁ … ለአንተ የምስጋና መሥዋዕትን እሠዋለሁ፥ የእግዚአብሔርንም ስም እጠራለሁ። ሃሌሉያ። እንዳለ መዝሙረኛው ዳዊት። (116:1፣7፣12-13፣17)

የአልበሙ መግቢያ፣ መተላለፊያና መደምደሚያ ምን ፍንጭ ይሰጠን ይሆን?

  1. እንዳለፈ ውሃ (መግቢያ)፦ ያንተን መንገድ ትቼ በራሴ መንገድ ላይ | ምኞቴን ስከተል ከፈቃድህ ስለይ | ሥፍራዬ እስክመለስ በረከት ቢርቀኝ | ነፍሴ ተጨነቀች አጣሁ የሚረዳኝ (2x) || እንዳለፈ ውሃ መከራዬን ረሳሁ | ክብር ላንተ ይሁን በፊትህ እሰግዳለሁ፤
  2. አልሆንም ለሌላ፦ አልሆንም፣ አልሆንም ለሌላ | ወዳጅ፣ ወዳጄ አንተ ነህ (አንተ፣ አንተ ወዳጄ ነህ) (የሱስ፣ አንተ ወዳጄ ነህ) በደም፣ በደምህ የሆነ | አለኝ፣ አለኝ ቃል ኪዳንህ
  3. ጆሮ ያለው ይስማ | 4. ሥራህ ግሩም ነው | 5. ደሙ እንደ ውሃ | 6. እኔስ ማን ልበልህ | 7. ላክብርህ | 8. ግን አለ | 9. ጎሕ ከበደ | 10. ብዙ አለ በልቤ (መደምደሚያ)

ዝማሬው፣ ስላሻገርከኝ ክብር ላንተ ይሁን ብሎ ይጀምራል። ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ወደማያዳግም ውሳኔ ይደርሳል፦ ወፊት ጎጆዋ ገባች፤ ነፍስ በፍቅረኛዋ ታሠረች። “ከእንግዲህ ለሌላ አልሆንም!” ትላለች! ለሚሰማ ሁሉ ይህን ታውጃለች!

መደምደሚያው፣ የክርስቲያን ጒዞ ቋሚ ገጽታ ነው። “ብዙ አለ በልቤ አጫውትሃለሁ |ትሑቱ ጌታዬ፣ አንዴ ዘንበል በል ሁሉን እነግርሃለሁ” ነው። ያመኑት ለጌታ የማይነግሩት እርሱን የማያማክሩት ሊኖር አይገባም። በሰው ልብ ብዙ አሳብ መኖሩ እግዚአብሔርን አይደንቀውም። አፈር እንደ ሆንን፣ አቅማችንን ያውቃል፤ ያለ እርሱ ተስፋ እንደሌለን ነግሮናል (ዮሐንስ 15፡5)። ዘንግተን እንዳይሆን እንጂ! እንግዲያውስ፣ ምሥጋና፣ ልመና፣ ንስሓ፣ ምልጃ፣ ጌታ እስኪመለስና ሁሉን አዲስ እስኪያደርግ የሚቀጥል ነው።

“አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፣ … እነሆ፥ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፥ … እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፥ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ …” (ራእይ 21:1-6)

እስከዚያች ቀን ድረስ ግን እንዘምራለን፤ በሌሊት ዝማሬን እንቀበላለን፤ በተጽናናንበት መጽናናት ሌሎችን እናጽናናለን፤ ሰዎችን ወደ መንግሥቱ እንጠራለን። “ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት” እንሮጣለን (ዕብራውያን 12:2)። ጌታ ሆይ ቶሎ ና! እንላለን።

የማንነት ጥያቄ፣ በዓለም ዙሪያ፣ በቤተ ክርስቲያንም የዘመኑ ዋነኛ ጥያቄ ነው። የሰው ማንነቱ በቋንቋው ወይስ በቀለሙ? በዙሪያ ገባው ወይስ በዜግነቱ? በውቀቱ ወይስ በሃብቱ? ሰው ራሱን ቋንቋውን ዘሩን አገሩን ብቸኛና ዓይነተኛ አድርጎ ማየቱ አደጋ አለበት፤ ያለሌላኛው የማንም ኅልውና ሙሉ አይሆንምና። የወንጌል ምላሽ ምድራዊውን በመካድ አይደለም፤ ፍትኅ ሲጓደል ችላ በማለትም አይደለም። ወንጌል ሙሉ ነው፤ ሙሉ ያደርጋል። “ሰውነትን ለሥጋዊ ነገር ማስለመድ ለጥቂት ይጠቅማልና፤ እግዚአብሔርን መምሰል ግን የአሁንና የሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው፥ ለነገር ሁሉ ይጠቅማል።” (1ኛ ጢሞቴዎስ 4:8) ምድራዊው ቀዳሚ ሥፍራ በተሰጠው መጠን፣ በአገራችን እንዳየነው ሁሉ፣ አለመረጋጋትን ያስከትላል። ሰው ፈጣሪው ከለገሰው ክቡር ማንነት ውጭ በአናሳ ሰው ሠራሾች ሲታመን ሲታበይ ወይም ራሱን ሲመዝን ቀልሎ ይገኛል።

ምርጥ ሕይወት እኮ ነው፣ ካንተ የተወለደ | መለኪያ የሌለው ከላይ የወረደ | ቤተ መቅደስ መሆን የጌታ ማደሪያ | ላንተ ክቡር ዕቃ ለስምህ መክበሪያ ። ። ላክብርህ ልውደድህ፣ ልውደድህ ከልቤ | ምንም ሳይቀርልኝ በመላው ሕይወቴ | ባፌ ብቻ ሳይሆን፣ በሁለንተናዬ | በማንነቴ ላይ፣ ገዢ ሁን ጌታዬ | ላክብርህ ልውደድህ፣ ልውደድህ ከልቤ (ላክብርህ፣ ትራክ 7፣ ስንኝ ለ)

ገዢዬ ማነው? ወቅታዊና ምላሽ የሚሻ ሩቅ አሳቢ ጥያቄ ነው! እውነተኛ ጸጥታና መታመን የሚገኘው ለኢየሱስ በመገዛት ውስጥ ብቻ ነው!

አታሚው ወንድም ዮሐንስ ጦና ሙዚቃና ቅኔ ግብግብ እንዳይገጥሙ አድርጎ አዋህዶአቸዋል። ዝማሬዎችን መቅኖ ከሚያሳጣቸው ነገሮች መሓል የማዋሃድ ጥበብ መመናመን አንደኛው ነው። ትኲረቱ ከጸሎት ይልቅ በቴክኒክ ርቀትና ገቢ በማሰባሰብ ላይ መሆኑ። የግጥሞቹ መወላገድ፣ አሰልቺ ድግግሞሽና ጥራዝ ነጠቅነት። ተሰምቶ የማያውቅ ሙዚቃና ትርዒት ለመፍጠር መቻኮል። የዝማሬ መነሻ ዓላማው ተስቶ ድምጽ ብቻ ሆኖ መቅረት። ዋናው ቊምነገሩ፣ ከነፍስ በመነጨ ጥሩ ቅኔ፣ በቃሉና በጸሎት የታነጸ፣ በጥሩ ሙዚቃ የታጀበ ውበትን መፍጠር ነው፤ የውበትን አምላክ ማወደስ ነው። ይኸ ሲሆን ብቻ ዝማሬ ያንጻል፤ ልብና አእምሮን ያነቃቃል፤ ግቡን ይመታል።

የሰው ሕይወት እንደ ወቅቶች የሚለዋወጥ ነው። ክረምት፣ በልግ፣ በጋ፣ ፀደይ። ለሁሉም ጊዜ አለው። አንድ ወቅት ለቅሶ፣ ከዚያ ዜማ፣ ከዚያ ወይ ዝምታ፣ ወይም ግርታ። “የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው፥ እግዚአብሔርም ከሁሉ ያድናቸዋል።” (መዝሙር 34:19) “ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለን።” (ሮሜ 8:22) “እነሆ፥ ክረምት አለፈ፥ ዝናቡም አልፎ ሄደ። አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፥ የዜማም ጊዜ ደረሰ፥ የቊርዬውም ቃል ተሰማ። በለሱ ጐመራ፥ ወይኖችም አበቡ መዓዛቸውንም ሰጡ።” (መኃልይ 2:11-13)። ምድራዊ ሕይወት ጣእመ ዜማ ብቻ ይሁንልኝ ማለት እውነታን መካድ ነው። ሁሉን አንድነት ማየት ያሻል። ዓመታቱን የሚያፈራርቀውን፣ በደሙ ቃል ኪዳን የገባውን መታመን ያሻል። ዘማሪት አስቴር ተፈራ እነዚህን ጒዳዮች እንዳንዘነጋቸው በቊጥር ሦስት አልበሟ አሳስባናለች። ቁጥር አራትና አምስትን በተስፋ እንጠብቃለን!

ምትኩ አዲሱ | በዓለ ትንሣኤ፤ 2012 ዓ.ም.