sermononmount

 

አ ዲ ስ፣  አ ዲ ስ  ራ እ ይ

ወንጌላዊ ያሬድ ጥላሁን፣ ከሰባት ዓመት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ፣ ድኅነትን ከሥሩ የሚያስወግድ “አዲስ” ራእይ ይዞ መመለሱን ኒቆዲሞስ ሾው ላይ አስታውቋል። ራእዩ ለኢትዮጵያ ብቻ አይደለም፤ በድኅነት ለሚጨናነቅ ዓለም ሁሉ ነው። https://youtu.be/Xbmlix9U1a0?t=3 (ክፍል 1, September 17, 2022)። https://youtu.be/Arh-p-JUVdg?t=2 (ክፍል 2, September 21, 2022)

ወንድም ያሬድን ካሁን በፊት ሲያስተምር ሰምቼው አላውቅም። አንደበተ ርቱእ ነው። በ2008 ዓም ትህነግን ባስወገደው ሕዝባዊ አመፅ ወቅት፣ ለጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከአሜሪካ ግልፅ ደብዳቤ መፃፉን ብቻ አስታውሳለሁ። ጊዜ ወስጄ እንዳደምጥ የገፋፋኝ፣ ከአንደኛው ፌስቡክ ገጽ፣ ወንጌላዊው ባስተማረው ላይ፣ አግባብነት ያለው፣ ነገር ግን ከመስመር ወጥቷል የምለው ትችት ነው። ሁለተኛው ምክንያት፣ ወንድም ያሬድ የማስተማር ጸጋው ጒልህና ፍሬአማ ሆኖ ሳለ፣ እውቀቱም ልምዱም በሌለው በማኅበራዊ አገልግሎት መሳተፉን እና ያቀረባቸውን ማብራሪያዎች መንፈሴ ሊቀበለው ስላልቻለ ነው። በሌላ አነጋገር፣ ወንድም ያሬድ ከቃሉ አስተማሪነት ጥሪው እንዳይፈናቀል ማገዜ ነው። ድኆችን መርዳት በጎ ነገር ነው፣ እግዚአብሔርም የሚወደው ነው። ጥያቄው፦ ወንጌላዊ ያሬድ በተጠራበት ጥሪ ላይ ጨምሮ ይሆናል ወይ? ነው።

ቤተክርስቲያን የሾመቻቸው መሪዎች፣ ጸጋቸውን በፈቀዱት ሰዓት፣ ሥፍራና መንገድ መጠቀም እንደማይችሉ ይገነዘባሉ ብዬ አስባለሁ። እዚህም ጌታን ማገልገል ነው፣ እዚያም ጌታን (በሰፊው) ማገልገል ነው ሲሉ ምክንያቱ ጥሩ ሊመስል፣ ትክክለኛ ምሪት ግን ላይሆን ይችላል።

ወንጌላዊ ያሬድ ከተናገራቸው ውስጥ፣ ሁሉ ቢሰማው የምላቸው ሦስት ወቅታዊና ጠቃሚ ክፍሎች አሉ፦

1/ “ባልንጀራዬ ማነው?” (ክፍል 1፤ ከ22፡50 ደቂቃ እስከ 32፡35) 2/ “ዘር ቅዱስ፣ ዘረኝነት እርኲስ” “ፖለቲካና ኃይማኖት” (ክፍል 2፤ ከ 35፡20 ደቂቃ እስከ 49፡18) 3/ “በጥሪ ስለ ማገልገል፤” እያንዳንዱ በተሰጠው የመትጋቱ ውጤት (ክፍል 2፤ ከ1፡00 ሰዓት እስከ 1፡10)

ጥያቄ የሆኑብኝ፣ የኒቆዲሞስ ጠያቂ የዘነጋቻቸው ክፍሎች ደግሞ አሉ። ዘንድሮ፣ በዓለማውያን ቀርቶ በወንጌል አማኞች ዘንድ ጥያቄ ማንሳት ከየጎራው የሚያስነሳውን መዘዝ አልዘነጋሁትም። ጥያቄ ማንሳት ግን ግድ ይኖርብናል። ተከታይ ማፍራት በራሱ ክፋት ባይኖርበትም፣ ወንጌላዊ ያሬድም እንደ ሌሎቹ ሁሉ የራሱ ተከታዮች አሉት፦ ይህን በምጽፍበት ጊዜ፣ ሴፕቴምበር 21 የተለጠፈውን 60 ሺህ ያህሎች አድምጠው፣ 400 ያህል አስተያየት ሰጥተዋል። ሴፕቴምበር 17 የተለጠፈውን ከ80 ሺህ በላይ ሰዎች አድምጠው ከ500 በላይ አስተያየት ሰጥተዋል (ደጋግመው የተመለከቱ/ያደመጡ መኖራቸው ይህንን እውነታ አያሳንሰውም)። የሚገርመው፣ ከ1 ሺህ በላይ አስተያየት ውስጥ በይዘቱ ላይ አንዳች ቊምነገር ያዘለ አስተያየት አለመኖሩ ነው! ባጭሩ፣ አስተያየቱ በአብዛኛው የአገልጋዩ እና አልፎ አልፎ የኒቆዲሞስ ሾው አዘጋጅ አድናቆት ነው፣ እና በጣት የሚቆጠር ጣል ጣል ምሥጋና ለእግዚአብሔር። ሌሎችም ዘንድ የሚታየው ይኸው ነው! የጳውሎስ ነኝ፤ የአጵሎስ ነኝ፤ የኬፋ ነኝ፤ የክርስቶስ ነኝ ነው ነገሩ! (1ኛ ቆሮንቶስ 1፡12)። እንግዲህ፣ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት አንድ ገጽታችን ይህንን ይመስላል! የዚህ መንስኤው የቃሉ እውቀት መመናመን ነው፤ የቃሉ አስተማሪዎች ያለጥሪ ያለፀጋ መገኘት ነው፤ አስተማሪዎች ክርስቶስን እና መስቀሉን ሳይሆን ራሳቸውን መስበካቸው ነው። በሌላ ሥፍራ እንዳልኩት፣ የማንበብና የመፃፍ ብቃት በጌታ ሕዝብ መሓል መመናመን አስተዋጽዖ አድርጓል። ከማንበብና ከመፃፍ ይልቅ ባልተጣሩ አሳቦች በሚነዳ ቴክኖሎጂ ተወርረናል። ባጭሩ፣ መኃይምነትን ከጌታ ቤት ማስወገድ የስሕተትና የሚያቀጭጩ ትምህርቶችን ለመቃወም ፍቱን መሣሪያ ነው!

ወደ ጥያቄና ትዝብቶቼ ልመለስ፦
1/ ወንጌላዊ ያሬድ፣ (እንደ ተወራው) ሄጄ አልቀረሁም፤ ውጭ ሄጄ መቅረት ብሻ ኖሮ በደርግ ዘመን ከጂቡቲ ባልተመለስኩ። ከ2008 ዓም በፊት የዓለም ከተሞችን ስዞርባቸው አልነበር? ታዲያ ማ አስገድዶኝ ተመለስኩ? ለመቅረት የወሰንኩት፤ እግዚአብሔር፣ ያሳየሁህ ነገሮች እስኪፈጸሙ “አትመለስም” ስላለኝ ነው። ስለ አገርህ ያሳየሁህ ነገሮች የሚፈፀሙበት ጊዜ ተቃርቧል፣ (እስኪፈፀሙ) አትመለስ ብሎኝ ነው ብሎናል። ደጋግሞ፣ “በድፍረት” ያለእግዚአብሔር ምሪት "አንድም ጊዜ" ተንቀሳቅሼ አላውቅም፤ በእንቅስቃሴዬ በሙሉ መንፈስ ቅዱስ መርቶኛል፤ ከ1983 ዓም ጀምሮ በአገር ዋነኛ ጒዳዮች ላይ እግዚአብሔር ለእኔ ያልተናገረኝ አንድም የለም ብሏል (ክፍል 1፤ 4፡43 ደቂቃ እስከ 6፡00)። አባባሉን መንፈስ ቅዱስም እያደመጠ ስለሆነ፤ የእርሱም መንፈስና ኅሊና ስለሚያውቀው በዝምታ ማለፍን እመርጣለሁ። ጥያቄ ግን ፈጥሮብኛል፦ ወንጌላዊ ያሬድ፣ ሊያደርገው ስላቀደው “አዲስ ራእይ” የሰዎችን (የተከታዮቹን) ልብ እና አእምሮ እያዘጋጀ ይሆን? ወደ አገር የተመለሰው ዶ/ር ዐቢይ ሥልጣን ላይ ከወጡ በኋላ ነውና፤ በእርሳቸው አስተዳደር ውስጥ ወይም ከእርሳቸው አስተዳደር ጋር በተያያዘ ኃላፊነት ሊሰጠው ይሆን?

ጠያቂዋ ይህንን ክፍል ጨርሳ ዘንግታዋለች። ወንድም ያሬድ፣ ዶ/ር ዐቢይን በስም ሲጠቅስ ትውውቃቸው ምን ያህል እንደ ሆነ አልጠየቀችም (ከእኔ በቀር አገር ሁሉ አውቆ የጨረሰው ጒዳይ ሆኖ ሊሆን ይችላል! ይልቅ፣ ወንድም ያሬድ መጽሐፍት ጽፌአለሁ ማለቱን ተከትዬ ሳፈላልግ “እፎይታ” የጽሞና መጽሐፉን ከአንድ ወዳጄ ቤት አገኘሁ። ይኸው መጽሐፍ ሕንጸት መጽሔት ላይ ተገምግሞአል (ኦገስት 12/2017)። የክብር እንግዳ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ናቸው (ሥልጣን ከመያዛቸው አንድ ዓመት አስቀድሞ)። ዐቢይ፣ ለደራሲው ያላቸውን “ፍቅርና ክብር ለመግለጥ እንደ ተገኙ ገልጸዋል።”

ወንጌላዊ ያሬድ፣ ጥሪዬ ማስተማር፣ ማጥናት፣ መፃፍ ነው ካለ፣ ድኅነትን ከሥሩ ነቅሎ ለማስወገድ ከሚደረግ ግብግብ ተርፎት ለማጥናት፣ ለማስተማር፣ ለመፀለይ፣ ለመፃፍ ምን ያህል ጒልበትና ጊዜ ያገኝና ነው? (ክፍል2፤ ከ1፡00 ሰዓት ጀምሮ)። ጠያቂዋ፣ እንደ ብዙዎች በዲስኲራቸው እንደሚያደነቊሩን፣ ጣልቃ እየገቡ እንደሚያበሳጩን “ጋዜጠኞች” አለመሆኗ አቀራረቧን ለየት ያደርገዋል። በተገኘው አጋጣሚ ለተጠያቂው ያላትን አድናቆት መሸሸግ አለመቻሏ ግን ሚዛናዊነቷን አፋልሶታል። ጠንከር ያሉ ጥያቄዎችን ከመጠየቅ አዘናግቷታል። ለምሳሌ፣ ወንጌላዊው ከአገር በወጣበት ወቅት በአገራችን የነበረውን ሁኔታ ማስታወስ ነበረባት፤ ወንጌላዊው አሜሪካ ገብቶ ለጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ የፃፈውን ግልጽ ደብዳቤ ለአድማጭ ስትል ማስታወስ ነበረባት (ኢትዮረፈረንስ 01/09/2016)። ጥገኝነት የጠየቅኸው ግልጽ ደብዳቤ ከፃፍክ በኋላ ነው? ለመሆኑ ደብዳቤው ምን ይላል? ከአገር የወጣኸው፣ አገር ጠፋች በተባለበት ሰዓት ነውና ጥገኝነት ለመጠየቅ ምቹ በነበረበት ወቅት ነው ለሚሉ ምላሽህ ምንድነው? እግዚአብሔር “አትመለሰም” አለኝ ከምትለው ጋር ይኸ እንዴት ይታረቃል? ላንተ “አርዋን” ፈቃድ ተሰጥቶኛል ግሪን ካርድ እየጠበቅሁ ነው ብለሃል፤ ለቤተሰብህስ ምን ዓይነት ፈቃድ ጠይቀህ እየጠበቅህ ነው? ወይስ ተሰጥቶአቸዋል? [ወንጌላዊ ያሬድ፣ አጠንክሮ፣ ውጭ አገር ሄጄ ለመቅረት ብፈልግ ኖሮ ቀድሞ ብዙ እድል ነበረኝ፤ በእያንዳንዷ እርምጃዬ እግዚአብሔር መርቶኛል፤ ውጭ አገር ለመቅረት ስላልፈለግሁ ተመላልሻለሁ፤ አሁን ከሰባት ዓመት በኋላ መመለሴ ይህንኑ ያስረዳል ከማለቱ አኳያ እነዚህ ጥያቄዎች ግድ ሊጠየቊ ይገባል።]

2/ ድኆችን ማሰብ፣ ባልንጀራን መውደድ አዲስ ራእይ ነው? እርግጥ ነው፣ ወንጌላውያን በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት፣ በደርግም “ነፍሳትን ማዳን” ዓለምን መጠየፍ ዓይነተኛ አመለካከታችን ነበር። እርስ በርስ መተጋገዝ አልነበረም ማለት አይደለም። ከመካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን በስተቀር “ሙሉ” ወንጌል ያስተማሩ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትን መጥቀስ ግን ይቸግራል። የዚህ ድኀ አመለካከት ምንጮቹ አያሌ ናቸው፦ የተገኘንበት “ሰማይ ጠቀስ” ኃይማኖታዊ ባህል፤ “ለጥቊር ነፍስ” የሳሱ ሚሲዮናውያን፤ መሪዎቻችን፤ የ “መንፈሳዊ”ን ምንነት አለመረዳት፤ በእንግሊዛዊው ጆን ዳርቢ “ስኮፊልድ” መጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜ እና በአሜሪካ የጌታ ምጽአት አዋቂዎች ቀመር ላይ የተመሠረቱ አስተምህሮዎች።

ሚሲዮናውያን ትምህርት ቤቶችን የጤና ጣቢያዎችን የእርሻ እና የተግባረ እድ ማእከላትን አላቋቋሙም ማለት አይደለም። ትልቅ ሥራ ሠርተዋል፤ ትልቅ ምሥጋና ይገባቸዋል። የተቋማቱ ቀዳሚ ዓላማ ግን፣ ነፍሳትን ማጥመድ ነው፤ ዓለም እንደ ሆነች ጠፊ ነች፤ ሥጋ ከንቱ ነው፤ ነፍስ ዘላለማዊ ነች!

በማኅበራዊ ጒዳይ የምር መሳተፍ የጀመርነው በረሐቡ ዘመን “ክርስቲያን” እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ከምእራቡ ዓለም መጒረፍ ሲጀምሩ በ70ዎቹ መጀመሪያ ነው። አቶ መለስ ሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት፣ አገራችን የእርዳታ ድርጅቶች ፋብሪካ እስክትመስል ድረስ ቊጥራቸው 4,000 ያህል ደርሶ ነበር! ዶ/ር ዐቢይ በበኲላቸው “ማዕድ ማጋራት” ፕሮግራም ጀምረዋል። የመንግሥት እጅ ቆርሶ ማጒረሱ ነው ወይስ ዜጋ በገዛ እጁ እንጀራውን ቆርሶ መጒረሱ ነው የሚሻል? ወንጌላዊ ያሬድ፣ “የድኅነትን አዙሪት ለመስበር” መድኃኒቱ ሥራ (የሥራ ቲኦሎጂ) ነው ይለናል። ሥራን እንዴት መፍጠር እንደሚቻል (ከፍተኛ ሥራ አጥነት እንዴት ኖረ?) አላብራራም፣ አልተጠየቀም። “የሥራ ቲኦሎጂ” ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ያለውን ብዙሓኑን ዜጋ ይጨምር እንደ ሆነ አላብራራም፤ አልተጠየቀም። ወይስ፣ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ እና አጋሮቻቸው በተለያየ መልኩ እንደነገሩን፣ ክርስቲያን አገር እና መንግሥት እየተገነባልን ነው? (አዲሱ ትርክት፣ ዐቢይን፦ እስራኤልን ከግብፅ ባርነት ወደ ተስፋዪቱ ምድር ባሻገረው በህግ አውጪው በሙሴ ዐይን የሚያይ ነው። ወይም በግብፅ ጠ/ሚ ዮሴፍ፣ በጦረኛው ንጉሥ ዳዊት፣ የፈረሰውን ቅጥር ባነፀው በነህምያ። ኢትዮጵያን በእስራኤል፤ ኢትዮጵያውያንን በሕዝበ እስራኤል፣ ወዘተ። ዐቢይም ትርክቱን ሲያጠናክሩ እንጂ ሲያስተባብሉ አልተደመጡም። አንዱም ግን እውነትነት የለውም!) 

ለማንኛውም፣ ወንጌልን ለነፍስ ብቻ አድርገን የነበርን፣ ወንጌልን ለነፍስም ለሥጋም ማድረግ ጀመርን። ከዚያማ ተለቀቅንበት! ዛሬ፣ የግል ሚኒስትሪ ብለን፣ የየግላችንን ቤተክርስቲያን መሠረትን፤ ሳናስበው በየፊናችን ሮጠን ቤተክርስቲያንን አራቆትን (ስለ ቊጥር አይደለም፤ በዓለም ፊት ስለ ምስክርነታችን፣ ስለ ተዘበራረቀው አስተምህሮአችን ነው፤ ስለ ምድራዊ ሥልጣን  ጥመኛነታችን ነው)። እውን፣ ወንጌላዊ ያሬድ የማናውቀውን “አዲስ ራእይ” ይዞልን መጥቷል? ምናልባት በእምነት ጒዞው የደረሰበትን አዲስ እይታ ማስታወቊ ሊሆን ይችላል። አብያተ ክርስቲያናትስ ይህን “አዲስ ራእይ” እንዴት ይመለከቱታል? ምላሽ ይሻል። “ድኅነትን ከሥሩ ማስወገድ የሚቻልበትን መንገድ ነው እግዚአብሔር የሰጠኝ” አባባሉን ጆሮ ሰጥተን እናድምጠው። በተለይ፣ ድኅነትን እና ሥራ አጥነትን ለማስወገድ የሚጣጣረው የጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር!

በዚህ ረገድ፣ ብዙ ልምድ ያካበቱ በመሓላችን አሉ። ልምድ ሆነ ሥልጠና የሌለው ሰው “ድኅነትን ከሥሩ” ስለ ማስወገድ (እንደ እርሱ አባባል “ሪቮሉሽናይዝ” ስለ ማድረግ) ሲናገር በአንክሮ ሊሰሙት ይገባል። ራእዩ እንደ ዮሴፍ ራእይ (ዘፍጥረት 37)፣ ባለማስተዋል በወንድሞች/በቤተክርስቲያናት መሓል ቅሬታ ቅናት ነቀፌታና ክፍፍል እንዳያስከትል በጥንቃቄ ሊያዝ ይገባል።

… … 

የቅርባችን ምዕተ ዓመታት ያስተማሩን አንድ ነገር፣ ድኅነትን (ቢበዛ መቀነስ/መቅረፍ እንጂ) “ከሥሩ ማስወገድ” እንደማይቻል ነው። ከዓለም ባንክ አንስቶ እስከ ወንድማችን ያሬድ ድረስ፣ ችግሩ፦ የሰውን ባህርይና ባህሎችን አለመረዳት ነው፤ የማኅበራዊ፣ ዓለም አቀፋዊ፣ ተፈጥሮአዊ ኃይላትን አሠላለፍና አለማስተማመን አለመረዳት ነው። ጌታም እንኳ ደቀ መዛሙርቱን፣ “ድሆችስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፥ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም” ብሎአቸው ነበር። የጌታ አባባል መነሻው፣ ማርያም እግሩን ውድ ሽቱ መቀባቷን ተከትሎ፣ ደቀ መዛሙርቱ፦ ተሽጦ ስንት ድኀ የሚያበላ ንብረት በከንቱ ባከነ ብለው ባጒረመረሙበት ወቅት ነው (ዮሐንስ 12፡5-8)፤ ካጒረመረሙት መሓል አንደኛቸው ገንዘብ ወዳድና ሌባ ነበር። በዚህም ጌታ፣ ለሚወዱት ድርጊቶቻቸው ሁሉ በቀዳሚነት አምልኮአዊ መሆኑን አስረድቷል። ሌላም ጥያቄ ያስነሳል፦ ወንጌላዊ ያሬድ፣ “እኔ የቃሉ አስተማሪ ነኝ፣ ፀሐፊ ነኝ፤ እረኛ አይደለሁም፤ በሆንኩበት ላይ ብተጋ” ልኩ ነው ብሎን ነበር። ከሰባት ዓመት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ አዲስ ራእይ ተሰጥቶኛል ማለቱ ከቀደመው ጥሪው ጋር እንዴት ይታረቃል? እርግጥ ነው፣ አይነጣጠሉም። አይነጣጠሉም ማለት ግን ተሰጠኝ የሚለው አዲስ ራእይ፣ ቀዳሚ ጥሪው ወንጌል አስተማሪ ለሆነ ሁሉ ይሆናሉ ማለት አይደለም!

ለሌሎች አገልጋዮች አይሆኑም ማለትም አይደለም! ጳውሎስ፣ ክርስቶስ ወንጌልን ልሰብክ እንጂ ለሌላ አልላከኝም ብሏል (1ኛ ቆሮንቶስ 1፡17)። ወንድም ያሬድ ከቃለ ምልልሱ መነሻ ላይ በጠቀሰው የገላትያ መልእክት (2፡10) ላይ፣ ለሐዋርያው ጳውሎስ ድኆችን መርዳት፣ ቀድሞም ያደረገው እንጂ ተጨማሪ ወይም አዲስ ራእይ አልነበረም (የሐዋርያት ሥራ 12፡25፤ 15፤ ገላትያ 2)። ሌላም ጒዳይ አለ፦ በሐዋርያት ዘመን የነበሩትን የተገፉ የተናቊ ጥቂቶች ክርስቲያን ማህበራትን፣ በተደራጀችዋ፣ የግለ ሰቦችን እና የመንግሥታትን ማህበራዊ ግዴታና ስነ ምግባር፣ ፍትሓዊ ህግጋትን፣ ለምዕተ ዓመታት በቀረፀች በዛሬዋ ቤተክርስቲያን ዐይን ማየት ከሚያርም ይልቅ ያልተገባ ስሕተትን ይፈጥራል። ይኸ መረሳት የለበትም።

… … 

ወንድም ያሬድን በፌስቡክ ገጹ በውስጥ መስመር ላገኘው ሞክሬ ነበር። ለውይይት ይረዳሉ ከምላቸው ውጭ ሌሎች ጒዳዮችን እዚህ ማንሳት አስፈላጊነቱ ስላልታየኝ በዚሁ ላብቃ። ምትኩ አዲሱ

የፌስቡክ ገፃችንን እዚህ ያንብቡ። 

picture credit: pinterest.com