ያ ዘመን፣ ያ ሠፈር

በጊዜ እና በሠፈር ታጥረናል። እድሜ የተመጠነልን፤ በአንዴ ሁለት ቦታ መሆን አንችል። የምናየው በከፊል። ትናንት፣ ዛሬ፣ ነገ እያልን እንቆጥራለን። ትናንትን በትዝታ እና በምስጋና፣ አንዳንዴም በፀፀት መረብ እናጠምዳለን፤ ነገን ደግሞ በተስፋ ወይ በሥጋት። እንዲያ እያልን ዛሬን እንሻገራለን። ጊዜ ወደሌለበት፣ በሕይወት ኃይል እንገሠግሣለን።

ልባችን በአብዛኛው ወደ ትናንት የዞረብን ነን። የአውሮጳ ልብ እይታው በአመዛኙ ወደ ነገ ነው። አውሮጳ ያለፈ ታሪኩን ችላ ማለት ያበዛል። እኛ፣ ካለፈ ታሪካችን የሚስማማንን ቆንጥረን፣ ብዥ ያለበትን ሁሉ ማደማመቅ እናዘወትራለን። ሚዛን መጠበቅ እያቃተን እንንገዳገዳለን። አሮጌ ያልናቸውን ጥለን መጤውን ሙጥኝ እንላለን። መ-ጣ-ል፣ መረሳት ያለበትን ግሣንግሥ ተሸክመን ግራ ተጋብተናል። ጆሮ ያለው ይስማ!

ከእንሥሣት ይልቅ ለሰው፣ የማስታወስ ችሎታ ተለግሦታል። መታሰቢያዎችን ያኖራል። ቀናቱን ይዘክራል፤ ለመልክዐ ምድሩ ስያሜ ይሰጣል። ልጅ ይወልዳል። ተረት ይተርታል፣ ይቀባበላል። ያንጎራጒራል፣ ይጽፋል፣ ይስላል። ወቅቶችን፣ እንጀራ የቆረሰባቸውን፣ ፅዋ የጠጣባቸውን ሠፈር ወዳጆቹን ያስባቸዋል። በዚህ ቀን፤ በዚህ ሥፍራ፣ እንዲህና እንዲህ ሆነ ይላል። ጊዜና ሠፈር ተጽእኖ ያደርጉበታል፤ እሱም አፃፋውን ይመልሳል። የጊዜ እና የሠፈር ድንበሮቹ እንዳይፈርሱበት ይሻል።

≈∞≈

“ጌታ ያውቃል” የምትለዋን ዝማሬ ባደመጥኩ ቊጥር፣ በትዝታ ጭነት ከመቅፅበት ያ ሠፈር ያ ዘመን ላይ ለመድረስ እጣደፋለሁ። አኮርዲዮኑን። የአኮርዲዮኑን ቀይ ጥቊር፣ ነጭ በቆሎ ጥርሠ ፍንጭት ብርቅርቅ ፈገግታና ጥልፍልፍ ማንገቻ። ባለ አፍሮው ዘማሪ፣ አኮርዲዮኑን ደረቱ ላይ ሲያኼደው። በተከሻ አዝሎ፣ ላባዎቹን እንደ አሞራ ሲያራግባቸው። እንደ አንጥረኛ ወናፍ ሲተረትረው፣ ሲሰበስበው፤ ቅይጡን ሊያጠራ የመንፈስን እሳት ሲያቀጣጥልባቸው። ከኳየሩ ዘርፋፋ ቀሚስ ላይ ቦግ ያለ ቀይ መስቀል ሲጣራ፤ ሰይጣንን፦ ጌታ ነግሷል። ስማ! ሥራህ ፈርሷል። ድኛለሁ። ስማ! ነፅቻለሁ። አገግሜአለሁ፤ ሲለው፣ አኮርዲዮኑ ባስነሳው ማእበል እንዲያ ስንንሳፈፍ። የዘማሪውን ድምፅ እንደ በረቅ ሲያደርገው፣ ውሃ እንደሚያጠጣ ቧንቧ ሲከፈት፣ አንድነት ሲያስገመግም። የነበርንበት አዳራሽ ካሁን አሁን ከመጋጠሚያው የሚላቀቅ ሲመስል፤ በዜማና በታዳሚ ብዛት፣ በመንፈስ ቅዱስ ደስታ ወደ ሰማይ ሲያንሳፍፈን። ዘንቦ አባርቶ፣ በፀሐይ ጨረር ደጁ ደምቆ ሲታይ። እፀዋት ጠግበው፣ ወደ ፈጣሪአቸው አንጋጥጠው እፎይታ ሲያሰሙ። እግረኛ፣ ጤዛን ረመጥ ላይ እንደ መራመድ ሲያስመስለው። አኮርዲዮኑን ተከትሎ የሠፈር አውራ ዶሮ ድምጹን በመስኮት አሾልኮ አምልኮውን ሲቀላቀል፤ የዘማሪውን ቃል በኲኲሉ ሲያደምቅለት።

ያ የሠፈር ዶሮ፣ ለኢየሩሳሌሙ አውራ ዶሮ ዘመዱ መሆኑ ነው። ጴጥሮስን፦ ጌታን አላውቀውም እንዴት ትላለህ? ጌታ ቀድሞ አውቆልሃል፣ እምነትህ እንዳይጠፋ ጸልዮልሃል ላለው “ወንጌላዊ” ዶሮ፣ የሥጋ ዘመዱ ነው። ይህንን እንዴት አወቅሁ? በድምፅ። ኲኲሉ! ኲኲሉ! በሁለት ሺህ ዓመት፣ እንኳን ሁለቴ፣ አንዴም አልተለወጠም!

የቅዱስ ዝማሬ አንዲት ሠበዝ፣ ብዙ ዘመን ታስታውሳለች፤ ብዙ ሠፈር ታካልላለች፤ የተረሳውንና የራቀውን ታቃርባለች።

≈∞≈

የከሰዓት ፕሮግራም ነው። ወንድም ደሳለኝን የኮንፈረንስ አዳራሽ ውስጥ በመገኘት የሚቀድመው የለም። ከመድረኩ ሥር እንደ ቄስ ተማሪ፣ አራት ባትሪ ጎራሽ ቴፕሪኮርደሩን፣ ግዳይ እንደ ቀናው እንደ አርበኛ ምንሽር፣ በአንድ እጅ ከፍ አድርጎ፣ መሬት ለመሬት በመንፏቀቅ የሚተካከለው የለም። የቀዳበትን ቢጫ ቴፕ ለማንም እንዳላውስ አስጠንቅቆ ያዋሰኝ እርሱ ነው። ቴፕሪኮርደሩ ሶኒ ነው፤ ቴፑ ሂታቺ። የነበረኝ ቴፕሪኮርደር ሳንዮ አንድ ጎራሹ፤ አንደኛውን ቊልፍ ሲጫኑት፣ እንደ ራበው አዞ አፉ ተስፈንጥሮ የሚከፈት። ታዲያ ወስፋት የለው፣ ከአንድ በላይ አይጎርስ። ደሴ ያዋሰኝን ለመቅዳት ሌላ አንድ ጎራሽ ፓናሶኒክ ቴፕሪኮርደር ከጎረቤቴ ተውሼ፣ እንደ መንታ ህፃናት ጎን ለጎን፣ መቅጃ እንደ ጡጦ በላዩ አጋድሜ፣ አንድነት ማስጀመር ነው። አንደኛው ይዘምራል፤ ሁለተኛው የተኛ መስሎ ይቀዳል። ከማስጀመሬ በፊት ግን ድንገት ደምሴ መጥቶ በሩን አንኳኩቶ አቀዳዱን እንዳይደመሥሥብኝ፣ በሩን ቀስ ብዬ ዘግቼ ከደጅ እቆማለሁ። ኮቴ እያሰማ እያፏጬ ከወዲያ እየተውረገረገ ሲመጣ፣ በጣት አፍ ላይ ምልክት የመናገር መብቱን እቀማዋለሁ።

ደሴ፣ እዚያው ሠፈራችን፣ አሥር አለቃ ደሴ የተባሉ ጡረተኛ ዘመድ ነበሩት። ዛሬ ሁለቱም የሉም። ቅጂውን ስንቴ ሰማሁት፤ ስንቴ ጂኒ ገብቶበት ተጠማዝዞ ሳስቶ፣ ተበጥሶ ቆርጬ ቀጣጠልኩት። መዘመር የማይሆንልኝ እኔም እንኳ ባቅሜ፣ ቅደም ተከተሉን በእንቅልፍ ልቤ ማወቅ ሁሉ ችዬ ነበር።

መተላለፌ ተደምሥሦ እንደ በረዶ ነጽቻለሁ፣ ተመልከተኝ
ሰይጣን እፈር በምን ትከሠኝ፣ ይቅር ባይ አምላክ ይቅር ካለኝ
ና ልጄ ብሎ እንደ ገና ታርቆኛልና ፈጣሪዬ፣ ጠንክሬአለሁ
አዲስ ሰው ሆኜ አገግሜአለሁ፣ ጠላቴ ዋይ! እኔ እስቃለሁ

ቀጥሎ፣ “ጌታ ያውቃል” ነው።

ይኸ በሆነ በሠላሳ ዓመቱ፣ ውጭ አገር ሠፈር ስቀይር ካሴቱን ያረግሁበት ጠፋኝ። ያ ደምሴ ተውሶ አስቀርቶት ይሆን? እርሱ እንደ ሆነ የተቀዳውን እንጂ ለራሱ መቅዳት አይሆንለት። ቅዱልኝ ብሎ ያሠለቻል፤ ወይም ቀዳሁ ብሎ ደህናውን ቅጂ ይደመስሳል፤ ወይም መቅጃውን ሳይከፍት ረስቶ፣ ካሴቱን ከመለሰ በኋላ፣ ቴፕሪኮርደሬ አልቀዳልኝም ብሎ ዳግም ይዋሳል። መላ የለውም። ለማንኛውም፣ “ጌታ ያውቃል” ን በቀደም’ለት ዩቱብ አደባባይ ላይ ተሰቅሎ አግኝቼ፣ ጠፍቶ የከረመ ወዳጅ እንዳገኘ ደስ አለኝ። ከተሰቀለበት ያወረድኩት ዝማሬ፣ ወደ ኋላ ይዞኝ ከነፈ። እኔም ሳላንገራግር ሳልግደረደር ወደ ኋላ ተጓዝኩለት። ወደ ጭጋጉ፣ ወደ ፀሐዩ፣ ወደ አዳራሹ፣ ወደ ጤዛው፣ ወደ ሠፈር ጭሳ ጭስ፣ ወደ አንድ ዘመን። ካራ ወደ ተሣለባቸው፣ በጒረኖአቸው እንደ ፋሲካ በግ እጅብ ወዳሉ አማንያን። ወደ ተቆለፈባቸው። መውጫቸውን ከሰማይ አምላክ ወደሚሹ ሰማእታት ክልል።

ወደ ኋለኛው ዘመን ተጓዝኩ። በዚያው የምቀር መስሎኝ ሠግቼ ነበር። ይመስገነው፣ ጒልበቴ ታድሶ ወደ ዛሬ ተመለስኩ እላችኋለሁ። ትናንት እና ዛሬን፣ ገና ነገ ሳሉ፣ ጌታ አውቆአቸዋል። ሁሌም ዛሬ የሆነ ጌታ ሁሉን ያውቃል። ጠፍቶ የተገኘው ካሴት፣ እነሆ፣ እንደ እግዜር ፖስታ፣ ሌላ ዜማ፣ ሌላ ብርታት ጭኖ፣ ደረሰልኝ እላችኋለሁ!

ወደ ኋለኛው ዘመን መጓዝ ደግሞ፣ እንደሚወዱት ወዳጅ ቶሎ አይለቅም። የያኔው ለምለም የቅኔ አዝመራ። የዛሬ ምድረ በዳ፤ ባብዛኛው ያሠለቸ ስንኝ፤ ዝማሬ ታይታ ስርቅርቅታ የሆነበት፤ በሪሚክስ የቀኙ ግራ፤ የላዩ ታች የሆነበት።

ሪሚክስ እንደ ወረርሺኝ መዛመቱን እንጂ (ቋንቋ እና ሥርዓት ሲለዋወጥ) ለየትውልዱ በሚገባው መንገድ መተርጎም አስፈላጊነት የለውም ለማለት አይደለም። ያለቅጥ ሪሚክስ፣ የጠራውን ማደፍረስ ነው። ዘመን እና ሠፈርን ማመሳቀል ነው። የትዝታ ዝርፊያ ነው። መዝሙራትን ማዘመን ነው ይሉናል። ነገሩ ግን ባመዛኙ ንግድ ነው፤ “እኛም አለን ሙዚቃ” ነው፤ ራስን መካብ ነው። የዝማሬ ቋት ሲደርቅ እርቃን መሸፈኛ ነው። አንዳንዴም፣ ባልዘመነችዋ፣ ነገር ግን በተቀባች ጥርሰ ወላቃ ጊታር የማፈር ያህል ነው።

የቀደመው ይሻላል ለማለት አይደለም። አዲስ ራእይ አይሠጥም አይደለም። ማነፃፀር ለምን አስፈለገ? በማን ሚዛን? ማዘመን በቂ ምክንያት ሊሆን አይችልም። መጤ ባህል በቴክኖሎጂ እገዛ ልንቋቋመው በማንችለው ፍጥነት ተጽእኖ እያደረገብን ነው። “ታላቅ፣ ታላቅነት” (በጒግል ቆጠራ 3 ሚሊዮን 1 መቶ ሺህ)፤ “ከፍታ” (1 ሚሊዮን 2 መቶ 30 ሺህ)፤ “ማዘመን” (270 ሺህ) መድረሱ የአስተሳሰባችንን መቀረፅ ይጠቊመናል። ማዘመን ያለፈውን መሻር ማዘናጋት ሊሆን አይገባም። በዘመኑ፣ ዘመናዊ ያልተባለ የለም! የዛሬ ዘመናዊ፣ የነገ ቅርስ ነው። ከዛሬ ዘመናዊ ውስጥ ተፈትኖ 1፣ 5፣ 10 ዓመት፤ 1፣ 2፣ 3 ትውልድ የሚሻገር ስንቱ ይሆን? ቅርሳችንን እንንከባከብ፣ አንበርዝ ነው። መንፈስ ቅዱስ ያሠመረውን ያሠማመረውን ድንበር አንግፋ ነው። ትውልድ ያለፈውን ታሪኩን እንዳያውቅ ሐውልቶቻችንን አናፍርስ ነው።

አንድ ነገር አንርሳ፦ ርቀው ወደ ኋላ ካልተመለሡ፣ ርቀው ወደ ፊት አይገሠግሡ። ስለ ሁሉም ግን ጌታ ያውቃል፤

ጌታ ያውቃል፣ ሁሉን እርሱ ያውቃል
ሰው በከንቱ ይጨነቃል፣ ጌታ ያውቃል
ጌታ ያውቃል፣ ሁሉን እርሱ ያውቃል
ሰው በከንቱ ይጨነቃል፣ ጌታ ያውቃል

የሃሳብ ውጣ ውረድ ምንድነው?
በጭንቅ መዋተቱ ከንቱ ነው
ጌታ ሁሉን ማድረግ ይችላል
ራስን አስጨንቆ ምን ይገኛል?

ጌታ ያውቃል፣ ሁሉን እርሱ ያውቃል
ሰው በከንቱ ይጨነቃል፣ ጌታ ያውቃል
ጌታ ያውቃል፣ ሁሉን እርሱ ያውቃል
ሰው በከንቱ ይጨነቃል፣ ጌታ ያውቃል

የሰቆቃውን ህይወት መልበሱ
እንደ ኢዮብ ካምላክ ጋር ሙግቱ
ረብ የለው አንዳች አይጠቅምም
በእምነት መቆየቱ ነው መልካም

ጌታ ያውቃል፣ ሁሉን እርሱ ያውቃል
ሰው በከንቱ ይጨነቃል፣ ጌታ ያውቃል
ጌታ ያውቃል፣ ሁሉን እርሱ ያውቃል
ሰው በከንቱ ይጨነቃል፣ ጌታ ያውቃል

ሥጋ መንፈስን እረግጦ
ሽብር ቢከበንም አፍጦ
ኢየሱስ ፈቃድህ ምንድነው?
ብሎ መጠበቊ ጥበብ ነው

ጌታ ያውቃል፣ ሁሉን እርሱ ያውቃል
ሰው በከንቱ ይጨነቃል፣ ጌታ ያውቃል
ጌታ ያውቃል፣ ሁሉን እርሱ ያውቃል
ሰው በከንቱ ይጨነቃል፣ ጌታ ያውቃል
ጌታ ያውቃል፣ ጌታ ያውቃል።

በ ታምራት ወልባ። አብሮ ለመዘመር፣ ጌታ ያውቃል

~ ምትኩ አዲሱ