ሕዝቡ አክብሮ የያዘው ስነ ምግባር ሊከበርለት ይገባል

አንድ መንግሥት ሕዝቡ አክብሮ የያዛቸውን የስነ ምግባር እሴቶች የማክበር እና የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ አለበት። በሥልጣኔ ሽፋን፣ አልፎም በእርዳታ ሰጭዎች ተጽዕኖ የስነ ምግባር ድንበር ሲገፋ እያየ መንግሥት ዝም ካለ ግን ሕዝበ ምዕመን በመሪዎቹ፣ ካልሆነም በራሱ፣ ተነሳስቶ የመቃወም መብት አለው። በሁሉም ማኅበረሰብ እንደሚታወቀው፣ የሞራል ውድቀት ከኢኮኖሚ ውድቀትና ከማኅበራዊ ቀውስ ይቀድማል።

የፊታችን ቅዳሜ ዓለም አቀፍ የ“ኤይድስ ቀን” በአዲስ አበባ ላይ እንደሚከበርና በዚያው ዕለት ከየአገሩ የሚመጡ ግብረሰዶማውያን የራሳቸው ፕሮግራም እንደሚኖራቸው በ”አሜሪካ ድምጽ” ጋዜጣ [ቪኦኤ፣ ሕዳር 19/2004] ተገልጿል። ይህንኑ በመቃወም ኦርቶዶክሳዊት፣ ካቶሊካዊት፣ ወንጌላውያንና የእስልምና ሃይማኖት መሪዎች ያሳዩት ትብብር እጅግ የሚያስመሰግን ነው። ለሁሉም ድንበር አለው። አንድ ሲባል ዝም ከተባለ ሁለትና ሦስት መከተሉ አይቀርም። ከንግዲህም የሃይማኖት መሪዎች ሰዶማውያኑ ከአዳራሽ ወደ ዝግ ስብሰባ እንዛወር የሚል ድርድር እንዳያመጡ መከታተልና ተቃውሞአቸውን ማሰማት ይኖርባቸዋል።

ክፉን እንድንቃወም የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። ሕዝቡን በቀናው መንገድ እንዲመሩ ክርስቶስ የሠየማቸው ተቀዳሚ ተግባራቸው ይኸው ነው። መሪዎች፣ ወዮላችሁ! የተባሉት ቸልተኝነት የሚያስከትለውን ፍርድ እንዳይዘነጉ ነው። እንግዳ ማስተናገድ ባሕላችን ነው ማለት፣ የምናስተናግደውን አንለይም ማለት አይደለም።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ የሃይማኖት መሪዎች ለውጭ ጋዜጠኞች ሊሰጡ የተዘጋጁበትን የተቃውሞ መግለጫ ጣልቃ ገብተው ማስቀረታቸውን ይኸው ጋዜጣ ዘግቧል። ሚኒስትሩ በአጣብቂኝ ውስጥ መግባታቸው ያስታውቃል። እንግዶችን ቅር ማሰኘት ለ “ኤይድስ”ና ለጤና ጥበቃ የሚመጣውን እርዳታ ሊያስተጓጉል እንደሚችል የተገነዘቡ ይመስላል። ሆኖም የኢትዮጵያ ሕዝብ በሌሎች ዕይታ “ተራማጅ” ሆኖ አለመገኘቱ ባለሥልጣኖቻችንን ሊያሳፍራቸው አይገባም።  እርዳታ ሰጭ አገሮች በአሁኑ ወቅት በአዳጊ አገሮች ከሚያራምዱአቸው ተግባራት አንዱ ለግብረሰዶማውያን መድረክ ማሠጠትና እንዲህ የመሳሰሉ አጀንዳዎችን አያይዞ ማስፈጸም ነው። በዩጋንዳ ሞክረው ከሽፏል። እርዳታ ከፈለጋችሁ ይህንንም አብራችሁ ማራመድ ይኖርባችኋል ይላሉ። “ሰላማዊነትንና ተቻችሎ መኖርን” ለማስተማር በወጣቶች መማሪያ መጽሐፍ ውስጥ ይህንንም ጨምሩ ይላሉ። የጸና እምነት ከሌለው በስተቀር ለተቸገረ እምቢ ማለት ይህ ቀላል አይሆንም። እንደዚሁም አርቆ አስተዋይነትና በሞራል የታነጸ ስነ ልቡና የጎደላቸው መሪዎች ሕዝቡን መቀመቅ ይከቱታል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የራሱ ባሕል አለው፤ እንደሌሎቹ አገራት እንዲሆን ግን አይገደድም። በሥልጣኔ ተገን ወይም በእርዳታ ሰጭዎች ተጽዕኖ ብዙ ዝባዝንኬ እየተስተናገደ ትውልድን ማራቆት አይገባም። የሃይማኖት መሪዎች በአማርኛና በእንግሊዝኛ የጋራ መግለጫ አውጥተው ተቃውሞአቸውን አሁንም በዜና አውታሮች ማሠራጨት ይኖርባቸዋል።

አቡነ ጳውሎስና ቄስ ኢተፋ ጎበና በትክክል እንደገለጹት ግብረሰዶም የእግዚአብሔርን የተፈጥሮ ሕግ የሚጻረር ነው። “ከፍጥረት መጀመሪያ እግዚአብሔር ወንድና ሴት አደረጋቸው” ይላል [ማርቆስ 10፡6]። ባሕላችን ጥብቅ ነው ይሉናል። ጥብቅ የሆነው በማን ሚዛን ነው? ጥብቅ ቢሆን ታዲያ ምን ወንጀል አለበት? የተፈጥሮን ሥርዓት መጠበቅ መረን ከመውጣት አይመረጥም? መረን የወጡ አገራትስ በነፍሳቸው እየከፈሉ ይገኙ የለ? ድምፃቸው እንደ ፌንጣ እንደ እንጭራሪት ስለሆነ ምድርን የሞሉ ያስመስላሉ እንጂ፣ ለነገሩ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ የሞራል ልቅነትን የሚያስተናግዱ አገሮች ቁጥር በጣም አናሳ ነው።

ባሕል ቢላላ ሥልጣኔ ወይም ነጻ የመውጣት ምልክት፤ ቢጠብቅ ግን ኋላ ቀርነት አይደለም። ነውር በጓዳ ይሁን በአደባባይ ክብር የለበትም። “የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት ስለ ለወጡ … እግዚአብሔር ለሚያስነውር ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባውን ሥራ ለባሕርያቸው በማይገባው ለወጡ፤ እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ወንዶችም በወንዶች ነውር አድርገው በስሕተታቸው የሚገባውን ብድራት በራሳቸው ተቀበሉ። እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው” [ሮሜ 1፡26-28]።

ዘመኑ አስፈሪ ነው። እግዚአብሔርን አለመፍራት በጨለማ መዋጥ፤ እርም የሆነውን ከከበረው አለመለየት ነው። በወንጌል ብርሃን ግን ድቅድቁ ጨለማ ይገለጣል። እግዚአብሔርም ሕዝቡን በጽድቅ መንገድ ይመራል። “ሰው ከሞት ወጥመድ ያመልጥ ዘንድ እግዚአብሔርን መፍራት የሕይወት ምንጭ ነው። እግዚአብሔርን ከመፍራት ጋር ያለ ጥቂት ነገር ሁከት ካለበት ከብዙ መዝገብ ይሻላል” [ምሳሌ14፡27፤15፡16]

የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ አምላኩ ይጸልይ፤ በተግባር አቋሙን ያስታውቅ። የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ግዳጇን ትወጣ። መንግሥት ኃላፊነቱን ይወጣ፤ የሕዝቡን እሴቶች ያክብር ያስከብር!