ስብሐት እና እኛ

sebhat2

ደራሲ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር በ76 ዓመቱ በዛሬው ዕለት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቶአል። ስብሐት የሚታወቀው “ሁሉን አፍረጥርጦ መግለጽ” በተሰኘው፣ ከፈረንሣዊው ኤሚል ዞላ በወረሰው የአጻጻፍ ስልት ነው። በጓዳ የሚወራው ሁሉ አደባባይ ይውጣ ወይም ማኅበራዊ ኃፍረቶች እሥራቶች ናቸው በሚለው አስተሳሰቡ ሙሉ ለሙሉ ባንስማማም፣ አጫጭርና ያልተወሳሰቡ ፈር ቀዳጅ ትረካዎቹንና አገላለጾቹን ሳናደንቅ አናልፍም። “አምስት፣ ስድስት፣ ሰባት” “ያዲሳባ ተረቶች” እና የመሳሰሉትን ጽሑፎቹን ማንበብ ለዚህ አስረጅ ሊሆን ይችላል።

ስብሐት በብዙዎች ዘንድ የማይታወቅበት ገጽታም አለው። በጋዜጠኛ ዘነበ ወላ “ማስታወሻ” [1993 ዓ.ም.] መጽሐፍ ላይ ስብሐት በስዊድሽ ሚሽን [እንጦጦ መካነ ኢየሱስ ትምህርት ቤት] እንደ ተማረ፣ ከአብሮ አደጉ ከኤፍሬም ሐጎስ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ተምሮ እንደ ተጠመቀ፣ ኤፍሬምም በትምህርቱ ገፍቶ ሳይንቲስት እንደ ሆነና “እግዚአብሔር የለም” ማለት እንደ ጀመረ፣ ጠጥቶ ሲነዳ የጭነት መኪና ሥር ገብቶ ከሞት እንደ ተረፈ እና “ያልሞትኩት እግዚአብሔር ስለአለ ነው” ብሎ የሕይወቱን አቅጣጫ እንደቀየረ፣ ዛሬም እንኳ “ኢየሱስ ያድናል!” እያለ እንደሚሰብክ ገልጿል [ገጽ 288]።

ስብሐትስ? ዘነበ እንዲህ ይላል፦ “ስብሐት ለኢየሱስ ክርስቶስ ጥልቅ ፍቅር አለው። በአንድ ወቅት ኢየሱስ ርዕሳችን ሆኖ እንዲህ አለኝ፦ የእኔን እምነት ልንገርህ። ኢየሱስን እስከ መስቀሉ ድረስ አምነዋለሁ። እከተለዋለሁ። ከዛ ከሞት ተነሣ ሲሉኝ ማመን ያቅተኛል። ምክንያቱም እስካሁን አላወቅኸኝም እንዴ? እኔ እኮ ቶማስ ነኝ … ሰዎቹ ወደ ኢየሱስ እየተንጫጩ መጡ። ሴትዮዋ ሸሽታ መጥታ እግሩ ላይ ወድቃ የሙጥኝ አለች። ዋናው ግባቸው እርሱን ማጥመዳቸው ነው። ‘ሙሴ ሴት ስታመነዝር ከተያዘች ትወገር ብሏል። አንተስ ምን ትላለህ?’ አሉት። ከእናንተ መሐል ሐጢአት የሌለበት የመጀመሪያዋን ድንጋይ ይወርውር፣ ብሎ ኢየሱስ መሬቱን በስንጥር ይጭራል። በአንዲት ጥያቄ ሁሉንም በጥርጣሬ ውስጥ ከተታቸው። ተለያዩ፤ ጥለዋቸው ሄዱ። አለኝና ጋሼ ስብሐት አተኩሮ ያየኝ ጀመረ። እንባዎቹ ከዓይኖቹ ውስጥ ፍልቅ ብለው በጉንጩ ላይ ተሽኳለሉ። ለስላሳ አፍ ማበሻ ወረቀት ከኪሱ አወጣና እንባውን እየጠረገ፦ አይዞህ አትጨነቅ። ልክ የዛገ ጣራ እንደሚያፈስ አድርገህ እየው። አለኝ … በዝምታ ለረጂም ደቂቃዎች ያህል ቆየና፣ አንቺ ሴት ከሳሾችሽ የታሉ? ሲል ጠየቃት፣ አንድ ስንኳ አለች። በይ ድጋሚ እንዲህ ዓይነት ነውር አይልመድሽ ብሎ አሠናበታት። [ስብሐት]… እንባውን ጠራረገ” [ገጽ.22]

ስብሐትን ያስለቀሰው የራሱ ሕይወት እየታሰበው ይሆን? የኢየሱስ ርኅራኄና ምሕረት ይሆን? ኢየሱስን መከተል ወዶ “የመጽናት ጉልበት” በማጣቱ ይሆን [ገጽ 76]? በመጨረሻው እስትንፋሱስ ምን ብሎ፣ ምን አስቦ ይሆን? የተቀረነውን የሕይወቱን ምዕራፍ እንድናነብ ያሳስበናል። ኢየሱስ፣ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፣ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፣ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም” ማለቱ ምን ማለቱ ነው? ለነዚህ ጥያቄዎች እያንዳንዱ ሰው ቀጠሮው ሳይደርስ ምላሽ መስጠት ይኖርበታል። እግዚአብሔር ቤተሰቡንና ወዳጆቹን ሁሉ ያጽናና። አሜን።                    2/20/12