ርዕሰ አንቀጽ

እንዴት እዚህ ላይ ደረስን?

ተማሪ ባዶ የሬሳ ሣጥን ተሸክሞ “ዋይ! ዋይ! ንጉሡ” እያለ ከስድስት ኪሎ አራት ኪሎ አመራ። በዓመቱ ነሐሴ 21/1967 ንጉሡ በግፍ ተገደሉ፤ የወደዳቸውም ያልወደዳቸውም ፍርሃትና ሐዘን በተቀላቀለ ዝምታ ተዋጠ። ጥቂት ቆይቶ የቤተክርስቲያን አባት ብፁእ አቡነ ቴዎፍሎስ ተገደሉ። ያወቃቸውም ያላወቃቸውም በያለበት አዘነ። በሰላሣ ሰባት አመቱ ታሪክ ዞሮ ገጠመ። የያኔ ተማሪ ዛሬ የአገር መሪና የቤተክርስቲያን ተጠሪ ሆነ። በነሐሴ ወር 2004 ሁለት መሪዎቻችን ተከታትለው ሞቱ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፊሉ ጮቤ ረገጠ፤ ከፊሉም እንባ ተራጨ፤ አንዱ ባንዱ ላይ አሾፈ። ሐዘኑን ተጋርቶ አብሮ የኖረ ሕዝብ እንደዚህ ሆነና ተለያየ። እንዴት እዚህ ላይ ደረስን?

ንጉሥ ሰለሞንን ሮብዓም የተሰኘ ልጁ ተካው [1ኛ ነገሥት 12]። ቀንበር ከብዶብናልና እባክህ አቅልልልን እንገዛልሃለን ብሎ ሕዝቡ ለመነው። ሮብዓምም ሦስት ቀን ስጡኝ አለ። ልምድ ካካበቱ ሽማግሌዎች ጋር ተማከረ። ሽማግሌዎቹም፣ ሕዝቡን እሽ ብትላቸው፣ በገርነት ብትናገራቸው በሰላም ይገዙልሃል አሉት። ሮብዓምም ሊሰማ የፈለገውን ስላልነገሩት፣ የሽማግሌዎቹን ምክር ወደ ጎን ትቶ “ከእርሱ ጋር ካደጉትና በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ብላቴኖች ጋር ተማከረ።” አብሮ አደጎቹም፣ ገና ምኑን አይታችሁ፤ አሁን ከብዶብናል ካላችሁ፣ የባሰ ቀንበር ስጭንባችሁ ምን ልትሉ ነው? በላቸው አሉት። በቀጠሮ ሲመለሱ፣ ይህንኑ ለሕዝቡ መለሰላቸው። ሮብዓም ሕዝቡን አልሰማም፤ ቅን ምክር የለገሱትን አልሰማም። እግዚአብሔርንም አልሰማም። ያም የውሳኔ ምርጫ እርሱን፣ ቤተሰቡንና አገሩን ሁሉ ለማያልቅ አሣር ዳረገ።

እንዴት አሁን የምንገኝበት ሁኔታ ላይ ደረስን? በምርጫችን። ቀስ በቀስ። ከእግዚአብሔር ፍርሃት ወደ ሰው ፍርሃት … ቀስ በቀስ ከሰው ፍርሃት ወደ ሰው አድናቆት … ከሰው አድናቆት ወደ እግዚአብሔር ንቀት ተሸጋግረን እዚህ ላይ ደረስን። እውን አሁን እግዚአብሔርን የሚንቅ አለና ነው ወይ? እንል ይሆናል። አዎን፤ ሰውን የናቀ እኰ በአምሳሉ የፈጠረውን እግዚአብሔርን ንቆአል።

እንዴት እዚህ ላይ ደረስን? ቀናው ስለተሠወረብን ነው? አይደለም። ዐይናችን እያየ የእግዚአብሔር ፍርሃትና የሰው አክብሮት የሌለበትን ጎዳና ስለመረጥን ነው፤ የሚያዋጣን የማያስጠይቀን መስሎን ስለተጓዝንበት ነው። ወደ ቀናው ለመመለስ ትሕትና ስለጎደለን ነው። የአገር መሪና የቤተክርስቲያን አባት ተከታትለው ሲሞቱ፣ የአገር መሪዎች ቃል የማይታመን ሆኖ ሲገኝ፣ የሕዝብ ኑሮ እንዲህ ሲጎሳቆል፣ አደጋና ሞት ፊትለፊት ተጋርጦ እንኳ የገዛን ምድር ለቆ መሄድ ሲያጓጓ፣ የገንዘብ አቅም ሲዳከም፣ ቆም ብሎ ፈጣሪ ምን ምልክት እየሰጠ ነው ማለት ማስተዋል ነው። ወቅቱ የሚጠይቀው ምክንያት መደርደርን ሳይሆን፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረት መለመንን ነው። ሞት ለማንም እንደማይቀር አውቆ ጊዜው ሳያልፍ ወደ አምላክ ፊትን ማዞርን ነው። ከሚጸጽት ተግባር መታቀብን ነው። የጸናና የማያሳፍር መታሰቢያ ለማትረፍ መጣርን ነው። 

ሁለቱ የተወሰዱብን መሪዎቻችን፣ እኛም፣ ይኸ ይሆናል ብለን አልጠበቅንም። ግን ሆነ። ሳይታሰብ ሳይዘጋጅ ድንገት ሆነ። “ሩቅ አሳቢ፣ ቅርብ አዳሪ” ነና። እናቅዳለን፣ እንመኛለን። እቅዳችንና ምኞታችን ይሥመር አይሥመር ልናውቅ አንችልም። ለዚህ ነው በእግዚአብሔር ፍርሃትና እርስበርስ አክብሮት እያሳየን ልንኖር የሚገባን። አክብሮቱ ላይ እንዴት ነው ልንደርስ የምንችለው? በቶሎ በአፋጣኝ መሆን አለበት። በንስሃ መሆን አለበት።

እግዚአብሔር ያዘኑትን ያጽናና። ለምድራችን እግዚአብሔርን የሚፈሩ፣ አርቀው የሚያስቡ፣ ለሕዝብ የሚራሩ፣ በቅንነትና በጽድቅ የሚዳኙ፣ ታማኝ መሪዎችን ይስጥ። አዲሱ ዘመን ያለፈውን መራራነት የሚያስወግድ አዲስ ተስፋ ይዞ ይድረስ።