ድንኳናችንን ሌባ ይዞብን ሄደ እኮ!

ሁለት ጓደኛሞች ቀኑን ሙሉ ሲጓዙ ውለው ጭው ካለ በረሃ ላይ መሸባቸው። ድንኳናቸውን ተከሉና እራት ቀማምሰው ጋደም እንዳሉ እንቅልፍ ይዟቸው ጭልጥ አለ። ሌሊት ላይ አንደኛው ከእንቅልፉ ነቃ። ነቃና ሌላኛውን ቀሰቀሰው፣

የተቀሰቀሰው “ምነው ቀሰቀስከኝ?” አለው።

“ቀጥ ብለህ ሰማዩን እይ ልልህ ነው”

የተከናነበውን ገለጠና። “አየሁት … እና?” 

“እና ምን ይታይሃል? ምን ታስተውላለህ?”

“ምን ዓይነት ጥያቄ ነው? ከዋክብት ነዋ” 

“ታዲያ ምን አስተዋልክ?”

ለጥቂት ደቂቃዎች ዝም ብሎ አሰበና፣ “በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደማቅ ከዋክብት አያለሁ፣ … የከዋክብቱ አሠላለፍ በዚህ በግራ በኩል የማንቸስተር ሲቲ አሠላለፍ ይመስላል፤ የባሎቴሊ ጠጉር ቁርጥ ይታየኛል፤ … ጊዜው ዘጠኝ ሰዓት እንደሆነ እገምታለሁ፤ … በመንፈሳዊ ዐይን እንየው ካልክ ደግሞ፣ እግዚአብሔር በኃይሉ ታላቅ አምላክ እንደሆነ፣ ሰው ግን ትቢያ እንደሆነ እገነዘባለሁ” አለው።

ጓደኛውም ተቀብሎ፣ 

“አይ ወንድሜ፣ ተኝተን ድንኳናችንን ሌባ ይዞብን ሄደ እኮ!” አለው።