ርዕሰ አንቀጽ

ስደተኛው ምን ታረገዋለህ? እራስህ ስደተኛ ነህ

migrantsEth 

በአንድ ጉዳይ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች ሊሰጡ ይችላሉ። ሁሉም አስተያየቶች እኩል ሚዛን ይኖራቸዋል ማለት ግን አይደለም፤ እንደ አስተያየት ሰጭው ዓላማ ሚዛኑም ያጋደለ ይሆናልና። ሰሞኑን በሳውዲ ያየነውን የወገኖቻችንን እንግልት ከተሠነዘሩት አስተያየቶች አኳያ እንመለከትና ሁለት ተያያዥ ጥያቄዎችን እንጠይቃለን። ጥያቄዎቹ፦ ለመሆኑ ከሰማነው ምን ያህሉ እውነት ነው? ለሰማነውስ ዜና አስተማማኝ መረጃ አለ? የሚል ሲሆን፣ የወንጌል አማንያንን ሁናቴ በዚያው እንመለከታለን።

ሰብዓዊነት ያልገዛው ፖለቲካ ግፍን ያባብሳል። በሚገዛው መንግሥትና ደጋፊዎቹ እና በተቃዋሚ ኃይሎች መካከል የምናየውን የመከፋፈልና የመቆራቆስ ፖለቲካ ወደ ጎን ትተን የተሠራጩትን አስተያየቶች ብቻ እንዘርዝር፦

1/ ክርስቲያን ስለሆንን እስላማዊው የሳውዲ መንግሥት ይጠላናል። እውነት ነው? ታዲያ የየመናዉያን፣ ኢትዮጵያውያንና ግብጻውያን እስላሞች መባረር እንዴት ይተረጎማል?

2/ መንግሥት ዜጎቹን በከፍተኛ እንክብካቤና በፍጥነት ወደ አገራቸው እያጓጓዘ ነው፤ ለዚህ ሊመሰገን ይገባል። ይህን አባባል እውነት ውሸት ከማለታችን በፊት የሚከተሉትን ነጥቦች እንመዝን፣ ሀ/ የሳውዲ መንግሥት የወጣት ዜጎቹ ሥራ አጥነት አሳስቦታል፤ ለ/ በግብጽና በሊቢያ የተከሰተው አብዮት በምድሩ እንዳይከሰት ሥጋት አድሮበታል፤ በራዲዮ “ሕገ ወጦች” ብሎ ለማጥላላቱ አንዱ ምክንያት ይኸው ነው፤ መ/ ዜጋ ላልሆኑና ሕጋዊ ፈቃድ ለሌላቸው ከሰባት ወር በፊት አማራጭ ሰጥቶ ነበር፣ ወይ ሕጋዊ መታወቂያ እንዲያወጡ ወይም ወደ መጡበት እንዲመለሱ። የሳውዲ ሕዝብ ብዛት 27 ሚሊዮን ሲሆን ሲሦ ያህሉ ከ14 አገሮች ለሥራ የመጣ እንደ ሆነ አንዘንጋ። እንዲወጡ ተወስኖባቸው ከቀሩት 130 ሺህ መካከል ከ80 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ናቸው። 500ሺህ የሚደርሱ የሌሎች አገሮች ዜጎች መንግሥታቸው በሰጣቸው መመሪያ መሠረት የኛዎቹ ያዩትን ውርደት ሳይቀምሱ ቀድመው አምልጠዋል። የሳውዲ መንግሥት የኛንም መሪዎች አስታውቆ ነበር። የሳውዲን መንግሥት አጥብቆ ማውገዝ ያቃተና የቸገረው አንዱም ለዚህ ነው፤ ዜጎች ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ እንዳይወጡ የተከለከለውም ለዚሁ ነው። ነገር ከገፋ ደግሞ የንግድ ትስስር ማቋረጥ ሊመጣ ነው። ጥያቄው ይህ ነው፦ የኛ መንግሥት እንደ ሌሎች መንግሥታት ለምን በሰዓቱ እርምጃ አልወሰደም? ቆንስላ ተወካዮች የዜጎችን መብት ለማስከበር አስፈላጊ ድጋፍ የማይሰጡት ለምንድነው? መንግሥት በጊዜው እርምጃ ቢወስድ ኖሮ በአገሪቱ ላይ የደረሰውን የገንዘብ ወጪና በዓለም አደባባይ ውርደት ባስቀረ አልነበር?

3/ በሳውዲ ብቻ 180ሺህ ያህል ኢትዮጵያውያን ሕጋዊ ፈቃድ ተሰጥቶአቸው እየሠሩ ይገኛሉ። በዚህ ዓመት በየወሩ 10ሺህ የቤት ሠራተኞች ወደ ሳውዲ ለማጓጓዝ በመንግሥታቱ መካከል ውል ተደርጎ በተባባሱ ችግሮች ምክንያት ለጊዜው ቆሟል። በዚያው ሰሞን መንግሥት ዜጎችን በማህበር ለማደራጀት የራሱን ሰው መርጦ ልኮአል። ማህበር ሲቋቋም ሹማምት ይኖሩታል፤ መተዳደርያ ደንብ ይኖሩታል፤ አባላት የሚያዋጡት ወርሃዊ መዋጮ ይኖራል። ከዚያ ባለፈ ማህበሩ በተመራጮቹ በኩል የሠራተኛውን መብት ለማስከበር መብትና ዕውቅና ይኖረዋል ማለት ግን አይደለም። በማህበር የማደራጀቱ ዓላማ ተጨማሪ ይሆን እንደ ሆነ እንጂ በመንግሥታቱ መካከል ሊደረግ የሚገባውን ዓለም አቀፋዊ ውል ሊተካ አይችልም፣ አይገባም። ባለፈው ዓመት ብቻ ወደ ዐረብ ምድር 200 ሺህ ወጣት ሴቶች ተልከዋል። በየመን ከ80 ሺህ ያላነሱ ኢትዮጵያውን በብዙ በመከራ ይገኛሉ። በሊባኖስ፣ ከታር፣ ዱባይ፣ ደቡብ አፍሪካ ወዘተ ያሉትን ብንጨምር ወጣቱ በአገር የቀረ አይመስልም። በሳውዲ የደረሰው ጉስቁልና ይልቅ ተከድኖ የቆየውን ደራሽ ያጣ ጉዳይ አደባባይ አወጣው። ይህ ሳይበግራቸው አሁንም እንኳ ወደዚያው ወይም ወደ ሌላ በእግር ይሁን ባይሮፕላን ለመሄድና በመሄድ ላይ ያሉ ሺህዎች ናቸው። እንግዲህ ሐቁ ይህ ነው። ወጣቱ የገዛ አገሩን ጥሎ ለመሄድ ያስገደደው ምንድነው? አገሩስ ውስጥ እንዲቆይ መንግሥት ያልወሰዳቸው እርምጃዎች ምንና ምንድናቸው? ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች ቅድሚያ ተሰጥቶአቸዋል? ይህን መመለስ አስፈላጊ ነው። እርግጥ አገራችን በኢኮኖሚ [በሞራል ባይሆንም] ዕድገት እያሳየች ነው። “በሞራል” ያልነው፣ ለሕዝብ ሊውል ሲገባ በሥልጣን ላይ ያሉ አገሪቷን እየዘረፉ መሆኑንና ለፍርድ ይቀርባሉ ብሎ መንግሥት ካሠራጨው ዜና በመነሳት ነው። የሕዝቡ ኑሮ እጅግ ተጎሳቁሏል። ያደገው ኢኮኖሚ እንዴት የሕዝቡን ኑሮ ሊያሻሽል አልቻለም? መንግሥት ተሻሽሏል ነው የሚለው፤ እውነታው ግን መረጃ ለሚሹና ውስጡ ላሉ ከዚያ የተለየ ነው። ሰሞኑን የወጣው ዘገባ አገራችን ባለፉት ስድስት ዓመታት ከአፍሪካ [2700] ሚሊዬነሮችን በማፍራት አንደኛነትን ይዛለች መባሉ እውን የጤና ነው? ለመሆኑ እነማናቸው? እንዴትስ ነው ግለሰቦቹ በዚህ ባጭር ጊዜ ውስጥ ይህን ደረጃ ሊይዙ የቻሉት? የብልጽግናው ተጠቃሚዎችና ተካፋዮች ጥያቄ እንዲነሳ አይፈቅዱ ይሆናል፤ ከሕዝቡ ኑሮ አንጻር ግን ይህን መጠየቅ ግድ ነው። ከላይ እንዳመለከትነው አንድን ሁኔታ ሚዛን ባለው መንገድ ለመገምገም ከግል ምቾትና ምኞት መላቀቅና ትክክለኛ መረጃ መሰብሰብ ያሻል። ሕዝቡስ በቤተሰቡ በጤናው በልጆቹ መስዋእት የሚከፍለው እስከ መቸ ነው?

4/ መንግሥት የመዘዋወር ነጻነት መስጠቱ ሊያስመሰግነው ይገባል። ወገኖቻችን ቀድሞውን ለምን ያለ ፈቃድ ሳውዲ ውስጥ ተገኙ? የሳውዲን ሕግ ከጣሱ ሳውዲ እርምጃ መውሰዷ ተገቢ ነው የሚሉ አሉ። ይኸስ እውነት ነው? በመጀመሪያ፣ መንግሥት ፈቀደ አልፈቀደ ወጣቱ አማራጭ ያለው አይመስልም። ከፍተኛ ሥራ አጥነት፣ መጎሳቆልና ተስፋ መቁረጥ ምድሪቱ ላይ ሰፍኗል። ሳውዲ ዐረቢያን በተመለከተ የተባበሩት መንግሥታት አባል ሆና ዓለም አቀፍ ሕግ የሚጻረር ድርጊት መፈጸሟ ትልቅ ወንጀል ነው። ሕጋዊ ፈቃድ ባይኖራቸውም ሰብዓዊነታቸው እንደዚህ ሊደፈር አይገባም። በራሳቸው የማይተማመኑ መንግሥታት ከራሳቸው ዜጎች የሚሠነዘርባቸውን ተቃውሞ ለማብረድ ማመካኛ መፈለጋቸው የተለመደ ነው።

5/ ጠላታችን ሳውዲ ነች፤ ለመቃወም ተባብረን እንነሳ። የመሐመድን ተከታዮች ተሰደው ሲመጡ ያስተናገድን ስንት የታሪክ ውለታ ለዋልነው ለኛ አጸፋው እንዴት ይኸ ይሆናል? የሚሉ አሉ። ስለዚህስ መረጃው ምን ይላል? ጊዜ ላላቸው የባርያ ፈንጋዮችንና የግራኝ አህመድን ታሪክ ማንበብ ጉዳዩ የውለታ ጉዳይ ሳይሆን የወቅቱን ጥቅም ማራመድ እንደ ሆነ ሊያስረዳቸው ይችላል።

6/ መንግሥት የሚችለውን እያደረገ ነው። ስንት መልካም ውጤቶችን እያስመዘገበ ልንተቸው አይገባም። የሚተቹና ጥያቄ የሚያነሱ ውጭ የተበተኑት ጯሂ ተቃዋሚዎች ብቻ ናቸው፤ እነዚህ ምንም አያረካቸውም ጨለማ ጨለማው ብቻ የሚታያቸው ናቸው፤ ሽብር መፍጠር ዓላማቸው ነው። ይኸስ እውነት ነው? እስቲ ሳናንዛዛ ከመሠረቱ ከአገር ውጭ በቤት ሠራተኛነት ተቀጥረው ስለሚጓዙት መንግሥት የዘገበውን መረጃ እንመልከት።

ትውልድ፣ አገሩን ጥሎ ለመሰደድ የተገደደበት ጊዜ እንደዚህ ዘመን በታሪካችን ታይቶ አያውቅም። ለመሰደዱ ዋነኛ ምክንያት ሥራ ለመሥራትና ቤተሰብ ለመመስረት ልጆች ለማሳደግና ለማስተማር ዕድሉ እጅግ ስለ ጠበበ ሲሆን ከመንግሥት ፖለቲካ ጋር አለመስማማትም አስተዋጽዖ አድርጓል። በመካከለኛው ምሥራቅ በትንሹ 1 ሚሊዮን ዜጎች አሉ። እርግጠኛውን ቁጥር የሚያውቅ የለም። ትክክለኛው ቁጥር አለመታወቁ ሕግና መዝገብ የማያውቀው ሕገወጥ ሥራ እየተሠራ ለመሆኑ ጠቋሚ ነው። በአሁኑ ወቅት የቤት ሠራተኛ ምልመላ የጎጆ ኢንዱስትሪ ሆኗል። እያንዳንዱ የአገር ውስጥ መልማይ/አስቀጣሪ ከተመልማዩ በነፍስ ወከፍ እስከ 800 የአሜሪካን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ይቀበላል [በመቶ ሺህ ተመልማይ ሲሰላ 80 ሚሊዮን ዶላር ማለት ነው፤ ይህን የሚቀራመቱት እነማን ይሆኑ?] ይህን ያህል ገንዘብ የሚያስገኝ ንግድ ምን ያህል ግፍ ቢታይበት ማስቆሙ ተጠቃሚውን [ባንኮችንና የመንግሥት ባለ ሥልጣናትን ጨምሮ] የሚያስቀርባቸውን ጥቅም መገመት አያዳግትም። ተመልማይ በወር ከ100 እስከ 200 ዶላር በሚሆን ደመወዝ ይቀጠራል [ከፊሊፒንስ አገር ለሚመጡት ከሚከፈለው ግማሽ ያህል ማለት ነው]። የሳውዲ አስቀጣሪ ምን ያህል እንደሚቀርጥ አይታወቅም። ሕጻናትን ለማደጎ፣ ወጣት ሴቶችን ለቤት ሠራተኛነት ወደ ውጭ መላክ በቂ ዝግጅትና ክትትል ስላልተደረገበት በወገኖቻችን ላይ [በአገሪቷ ላይ] ያልተተመነ የአጭርና የረጅም ጊዜ ጉዳት እያደረሰ ነው። እርግጥ ጥቂቶች በግርግር ሃብት አካብተዋል። ትኩረቱ የውጭ ምንዛሪ ማሰባሰብ ላይ እንጂ የዜጎችን ሕይወት መንከባከብ ላይ እንዳልሆነ እየታየ ነው። ትኩረቱ ከውጭ በሚገባ ምንዛሪ ላይ እንጂ አገር ውስጥከሚገኘው ላይ እንዳልሆነ ግልጽ እየሆነ ነው። 

አንድ የሳውዲ ነጋዴ ሲገልጸው “እኔ የጋማ ከብት አጓጉዛለሁ፤ ሚስቴ ደግሞ የቤት ሠራተኞችን። የተንዛዛ ስለሆነ ከቤት ሠራተኛ ይልቅ ከብት ማጓጓዝ ይቀላል” ብሏል። ተቀጣሪዋ የቤት ሠራተኛ በቀን ከ10 እስከ 20 ሰዓት ድረስ ትሠራለች። ቋንቋ አታውቅ፣ መብቷን የሚያስከብርላት የለ። ደከመኝ ማለት ወይም ሲያስፈልግ የባልየውን ፍትወት አለማርካት፣ ክርስቲያን ለሆኑ መጸለይና በእስላም ሥርዓት አለመገኘት አሰቃቂ ድብደባን ሊያስከትል ይችላል፤ ምርጫዋ ወይ ራሷን ማጥፋት ወይም ችሎ መኖር ነው። አለዚያ ወደ አገሯ ትላካለች። ስትሞት ሬሳዋ የትም ይቀራል። በሁለቱም መንገድ በወር ታገኘው የነበረው 100 ዶላር ይቀራል፤ አገር ቤት ገንዘብ ልኮ ቤተሰብ ማስተዳደር ይቀራል። የምንሰማው አሳዛኝ ዜና የባሰበትን ብቻ እንደ ሆነና ብዙዎች ለኑሮ ሲሉ በድብቅ እንደሚሠቃዩ አንዘንጋ። አጣብቂኝ ማለት ይኸ ነው። ቀጣሪና አስቀጣሪ ተባብረዋል፤ ተቀጣሪ ፍዳ ይከፍላል። የዜጎችን ሕጋዊ መብት ማስከበር ውሉን ካጠበቃችሁ ከሌላ አገር እንቀጥራለን ስለሚሉ ውሉ ለመላላቱ ምክንያት ሆኗል። የሳውዲ መንግሥት በዚህ ዓመት በየወሩ 10 ሺህ ወጣት ሴቶች ላኩልኝ ያለው ለዚህ ነው። በቂ ዝግጅትና ቁጥጥር ስለሌለም ነው ለማደጎ ሕጻናት የሚከፈለው ዋጋና የመረከቢያ ጊዜ በዓለም አጭሩና ርካሹ [$30 ሺህ በአንድ ሕጻን] የሆነው። በነገራችን ላይ፣ የተዘረዘረው በደል የደረሰው በጥቂቶች ላይ ብቻ ነው ማለት የበደሉን መጠን ሆነ ዓይነት አይለውጠውም።

በአንድ ጉዳይ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች ሊሰጡ ይችላሉ። ሁሉም አስተያየቶች እኩል ሚዛን ይኖራቸዋል ማለት ግን አይደለም፤ እንደ አስተያየት ሰጭው ዓላማ ሚዛኑም ያጋደለ ይሆናልና። በዜጎች ሥቃይ ተቃዋሚ ኃይሎችና የአገር መሪዎች ሲቆራቆሱና አንዱ ሌላውን ለማስዋሸት፣ ለማጥላላት እውነቱን የሚክድ ዜና ሲያሠራጭ ማየት አሳዛኝ ነው። ተቃዋሚ ኃይሎች አንዳች በጎ እንደሌለ እስኪመስል ድረስ በየሰበብ አስባቡ መንቀፍ ሱስ የሆነባቸው ይመስላል። ሦስት አማራጮች ለሁላችንም ይቀርባሉ። ተመሳስሎ መኖር፣ አጣርቶ ልኩን ማወቅና አቋም መውሰድ፣ ወይም ራስን ማግለል። ብዙዎች አማንያን ለከንቱ ረብ ሲሉ ወይ ተመሳሎ መኖር ወይም ራሳቸውን ማግለል መርጠዋል። በውጭ ያለች የኦርቶዶክስ ማኅበር አገር ውስጥ ያለችዋንና መንግሥትን የሚወቅስ መግለጫ አውጥታለች። ጥቂቶች ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት በበኩላቸው ጾምና ጸሎት እንዲደረግ ለየማኅበራቸው ማስታወቂያ ለጥፈዋል። ጥቂቶችም በ“ፓልቶክ” ሹክሹክታ እያሰሙ ነው። የጋራ አቋም መግለጫ ለማውጣት ያሰቡ ግን አይመስልም። ምክንያቱ ምን ይሆን?

1/ የሚካሄደውን አለማወቅ፤ ለማወቅ ጥረት አለማድረግ። ተግቶ እውነቱ ጋ ለመድረስ አማራጭ ከሌለ የተዛባውን ለማቃናት ተሳትፎ ሳያደርግ ይቀራል።

2/ ወንጌላውያን በተናጠል ራሳቸውን በማንቀሳቀስና በማኖር ላይ ስላተኮሩ።

3/ ወንጌልን በቁንጽሉ ከመረዳትና ራስ-ተኮር ከማድረግ። ዓለም ጠፊ ነች፤ ድርሻችን እግዚአብሔርን ማምለክና ነፍሳትን ማዳን ነው፤ ለተቸገሩ መጸለይና መርዳት ነው። የችግሩን መንስዔ አጥብቆ መመርመርና ጥያቄ መጠየቅ ከፖለቲካ ጋር እንዳያነካካ መጠንቀቅ ነው የሚል አስተሳሰብ።

4/ መንግሥት ስለ ለገሠን ነጻነት ውለታ አለብን። የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ታምራት ላይኔ እንዲያውም ሰሞኑን በ“ኤስ ቢ ኤስ” ራዲዮ ላይ ባሰሙን ቃለ ምልልስ በርሳቸው ፊርማ ፕሮቴስታንት አማኞች ይህን ነጻነት ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ ተቀዳጁ አስታውቀዋል። እርሳቸው ባይፈርሙ ኖሮ ቤተክርስቲያን መሰብሰቧን ታቆም ነበር? ደርግ ሊያስቆማት ያልቻለውን? የክርስቶስን ቤተክርስቲያን የሲዖል ደጆችም እንኳ ሊቋቋሟት አይችሉም!

5/ ጉስቁልና ሰውን ወደ አምላኩ እንዲያስብ ያደርገዋል። እግዚአብሔር ዓላማ አለው። ይልቅ ዜጎች ከአገር ወጣ ብለው መሥራት ስለ ቻሉ ተመስገን ማለት ይገባል።

6/ አገራችን እየለማች ነው፤ ወደ ፊትም የበለጠ ትለማለች። እስከዚያ መታገስ መልካም ነው።

7/ በጥበብ መጓዝ ያሻል፤ ግልጽ አቋም መውሰድ ገቢና ኑሮን ሊያናጋ ይችላል፣

8/ አንዳንዶችንም የስነ ምግባር ጉድለት አቋም እንዳይወስዱ ሥልጣን ነስቶአቸዋል፤ ወዘተ። 

ሦስት ሰዎች። አንዱ ካህን አንዱ ሌዋዊ እግዚአብሔርን እናውቃለን የሚሉ መንፈሳውያን ጻድቃን የተጎዳ መንገደኛ ወድቆ አገኙ [ሉቃስ 10፡25-37]። ሁለቱ መስዋእት ሊያስከፍላቸው ስለሆነ መንገድ አሳብረው ጉዳተኛውን ከወደቀበት ትተውት አለፉ። ከሕግ እየጠቀሱ “መንፈሳዊ” ምክንያት ደረደሩ። ሦስተኛው ያልታሰበ ሳምራዊ ግን ቸርነት በማድረግ ካህኑንና ሌዋዊውን በጽድቅ ቀደመ። ለባልንጀራው በመድረሱ ለእግዚአብሔር ያለውን ፍቅር ገለጠ። ሦስቱም ተመሳሳይ ሁኔታ ገጠማቸው። ስለ ሁኔታው የሰጡት ምላሽ ግን የሞትና የሽረት ያክል ልዩነት አመጣ፤ ሁለቱ ራሳቸውን አዳኑ፤ ሦስተኛው መስዋእት ከፈለ። አንዱ የዓለም መንገድ፣ ሌላኛው የክርስቶስና የመስቀሉ መንገድ ናቸው። ይህ ዕለት ዕለት የሚቀርብልን ምርጫ ነው። የትኛውን ትተን የትኛውን መረጥን? ጉዳዩ ይኸው ነው።

የአገር መሪዎችና ተቃዋሚዎች ተከፋፍለው ሕዝቡን በጎሣና በሃይማኖት ከፋፍለው እየተፋለሙ ይገኛሉ። በዚህ መካከል ሕዝብ በውሸት ናዳ ግራ እየተጋባና እየተጎዳ ነው። ቤተክርስቲያን በመስቀሉ ትይዩ መቆምና የወንጌልን እውነት ማብሠር እንጂ የየትኛውም አንጃ ደጋፊ ልትሆን አይገባም። ግዴታዋ እውነቱን ለይታ ማወቅና ማሳወቅ ነው። እውነቱን ለመናገር ዓለምን ፈቃድ መጠየቅ አያሻትም። ዝምታ ግን አቋም እንደ ሆነ አንዘንጋ። አማንያን የተሳትፎአቸውን ጠርዝ ማስፋት ይኖርባቸዋል። ብርሃንና ጨው ናቸውና። በሌላ አነጋገር፣ የአገር ጉዳይ ሁሉን የሚያሳትፍ እንጂ ጥቂቶች እናውቅልሃለን የሚሉበት አይደለም። ወንጌል ጉዳዩ በአምላክ አምሳል ከተፈጠረው ሰው ጋር ነው። የሰው ቀለሙ፣ ዜግነቱ፣ ሃይማኖቱ ከክርስቶስ ፍቅር አንጻር ማመካኛ ሊሆን አይችልም። ማንኛችንም በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠርን ሰዎች ነን፤ በዜግነት  ኢትዮጵያውያን ነን። ልዩ ልዩ መሆናችን በምርጫ ባይሆንም ልናከብረው የተገባ ውበት ነው፤ እስኪከፋፍለን ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ግን አይገባም። ሊከፋፍሉን ልዩ ልዩ መሆናችንን ለሚያጎሉብን ጆሮ መስጠት፣ ሳናጣራ ማስተጋባትና ዝምታ መቆም አለበት። የክርስቶስ ተከታዮች ራሳቸውን ከማህበራዊ ጉዳዮች አግልለው ሊገኙ አይገባም። እውነትን አውቀናል እያልን ለእውነት ካልቆምን ውሸት እያየለ እውነት መባል ይጀምራል። የአገራችን መሪዎች ለሕዝቡ ርህራሄ ሊያሳዩ ይገባል። አገራቸውን በዕውቀታቸው ሊያገለግሉ ሲችሉ በአሳብ ስለ ተለዩ ብቻ በውንጀላ ፍርሃት ራሳቸውን ያገለሉትን በቅን ልብ ማሰባሰብ መጀመር አማራጭ የለውም።

ለመሆኑ ይህ ትውልድ ከተበተነበት አገር ሲሰባሰብ ያልታሰቡ ምን ማህበራዊ ለውጦች ሊከተሉ ይችላሉ? በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ያገቡና ያላገቡ ወጣት ሴቶች ሲዋለዱ በጤና፣ በስነ ልቦና፣ በቤተሰብ ምሥረታ፣ በባሕል፣ በግልና በማህበራዊ ግንኙነቶች ላይ ምን ተጽእኖ ያስከትላል? በአሁኑ ወቅት እየተመለሱ ካሉት መካከል 8 ሺዎቹ ሕጻናት አዝለው መገኘታቸው ምን ይጠቁመናል? ስንቶቹ ከሳውዲ አባት ተወለዱ? ስንቶቹ ሳይፈልጉ ተገድደው ወለዱ? ሕጻናት ለማደጎ የሚሰጡበት አንዱ ምክንያት “ያልተፈለገ” ወሊድ ነው ተብሎ አይደለም ወይ? ወሊድ በሳውዲዎች ዐይን እስልምናን የማስፋፊያ ዘዴ ሆኖስ እንደሆን? ባጭሩ፣ ከዝግጅት ጉድለትና አርቆ ካለማሰብ የተነሳ ከደርግ ዘመን ይዘን እንደ ተሻገርነው ዓይነት አሣር ወደ ፊት ማጨዳችን አይቀርም። “ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና።”

ለመሪዎች እንጸልይላቸው፤ ጸሎታችን ትርጉም እንዲኖረው እውነቱን እናጣራ። ውሸት ስናስተጋባ እንዳንገኝ እንጠንቀቅ፤ የምናመልከው አምላክ እውነተኛ አምላክ ነውና። አለዚያ መዋሸት፣ ወንጌልንም ማስዋሸት እንጀምራለን። እግዚአብሔርን መውደድ ሰውን መውደድ ነው፤ ለተበደለውና ለተቸገረው መቆም ነው። የክርስቶስ ተከታዮች ለግራና ለቀኝ የማይል እውነት ይዘው  ሰውን በመፍራት ራሳቸውን ለማዳን  ዝምታ መምረጣቸው ግን አሳፋሪ ነው።  “ስለ ራሳቸው መናገር ለማይችሉት፣ ለችግረኞችም ሁሉ መብት ተሟገት። ተናገር፣ በቅንነትም ፍረድ፤ የምስኪኖችንና የድኾችን መብት አስከብር” ብሏልና [ምሳሌ 31፡8-9/አመ]። እግዚአብሔር ልጆቹን በማስተዋል ይሙላ፤ አርቀው የሚያስቡ ርህራሄ የሚያሳዩ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሕዝቡን የሚያሳርፉ መሪዎችን ለምድራችን ይስጥ።

pic credit: aljazeera.com