ርዕሰ አንቀጽ

የሚርያም ታሪክ ሌላ ገጽታ

MeriamIbrahimሚርያም ኢብራሂም፣ ክርስትናዬን አልክድም አለች ተብሎ አገር ሲታመሰ ከረመ። እስር ቤት ተገላግላ፣ ከመቶ ጅራፍና ስቅላት ተርፋ ትላንት ጣልያን ገብታለች። ለባሏና ለልጆችዋ ስላበቃት እግዚአብሔር ይመስገን። የሚርያም አባት ሱዳናዊ እስላም፤ እናቷ ኢትዮጵያዊት ኦርቶዶክስ ናቸው። ሚርያም ስድስት አመት ሲሆናት ወላጆቿ ተፋቱ፤ ዛሬ ሃያ ሰባት አመቷ ነው።። ሚርያም የሕክምና ዶክተር ነች። ከሕክምና ሙያ በተጨማሪ የፀጉር ቤት፣ የእርሻ መሬት፣ የገበያ አዳራሽ ሱቅና የመሳሰሉ የንግድ ሥራዎች አላት። ከሦስት አመት በፊት ያገባችው የሠላሳ ሦስት አመቱ ዳንኤል ዋኒ የአሜሪካን ዜጋና ተቀማጭነቱ ኑሃምሽር ግዛት፣ ትውልደ ደቡብ ሱዳናዊ ነው። ዳንኤል እግሩ ስለማይረግጥለት በተሽከርካሪ ወንበር ይጠቀማል። ግንቦት 23/2006 የተሰጣቸው የጋብቻ ወረቀት የካርቱም ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ታህሳስ 9/2004 እንዳጋባቻቸው ያመለክታል። የአንድ አመት ወንድ ልጅና የሁለት ወር ሴት ልጅ ወልደዋል። በሚርያም ላይ ክስ ያስነሱባት ከሌላ እናት የተወለዱ ወንድሟና እህቷ ናቸው። የጠቆሟት፣ ወደ አሜሪካ ስትሄድ ከንግዱ ምንም እንደማታጋራቸው ስለ ተረዱ ነው። የከሰሷት፣ አባታችን እስላም ስለሆነ እርሷም እስላም ነች፤ እስላም ሆና ክርስቲያን ማግባቷ ክሕደት ብቻ ሳይሆን ዝሙትም ነው ብለው ነው።

ከሦስት አመት በኋላ ለምን ነገር ተጫረ?ለሚለው ምላሽ አግኝተናል። ምቀኝነት። በሌላ አነጋገር፣ ሚርያም ለወንድሞቿ ንብረት ብታጋራ ኖሮ ይኸ ሁሉ ግርግር ባልታየ ነበር። የአንድ ቤተሰብ ጉዳይ ለምን የሃይማኖት፣ የፖለቲካና የዓለም መንግሥታት መከራከሪያ ነጥብ ሆነ? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል። በ1983 በተሻሻለው የሱዳን ሕገ መንግሥት፣ ሃይማኖት መቀየር በስቅላት የማያስቀጣ ሆኖ ሳለ፤ ሚርያም ከሁለቱም ወገን አያቶቿ ገሚሳቸው ክርስቲያኖች ሲሆኑ። የዜጎች ሰብአዊ መብት መከበርና አለመከበር ጥያቄ ውስጥ ሳይገባ እንኳ በሕገ መንግሥቱ የሠፈረው ብቻውን በቂ ሆኖ ሳለ። ለምን?

የሚርያም ኢብራሂም ታሪክ የዘመኑን ጥልፍልፍ ባህርይ የሚያስረዳ፣ ብዙ ተዋንያንን ያካተተ ትርዒት ነው። እያንዳንዱ ተዋናይ የራሱን ዓላማ ያካሄዳል። ሳናጣራ ማስተጋባት ከወንጀሉ ጋር ተባባሪ የሚያደርገን ለዚሁ ነው። በተለይ የክርስቶስ ተከታዮች፣ ለእውነት ልንመሰክር እንደ ተጠራን ላፍታም መዘንጋት የለብንም። የምሰማው እውነት ነው? ማነው ያወራው? ለምንድነው ያወራው? ለምን አሁን አወራው? ወሬው ሌላ ገጽታ ቢኖረውስ? የኔ ድርሻ ምን ሊሆን ይገባል? ብለን መጠየቅ በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት ከማድረስ ይጠብቃል።

የሚርያም ጉዳይ ሌላም ገጽታ አለው። ከሚያዝያ ጀምሮ ሱዳን ውጥረት ላይ ነች። የኑሮ ውድነት ሕዝቡን እያስመረረ ነው፤ ተማሪዎች እየተንቀሳቀሱ ነው፤ ዳርፉር አላረፈችም፤ የኑባ ተራሮች በቦምብ ተደብድበዋል። የሚርያም ጉዳይ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ መነሳቱን መንግሥት ፈልጎታል። ለምን ቢባል፣ ፕሬዚደንት አልበሺርን የእስልምና ሃይማኖት ጠባቂና አስከባሪ ያደርጋቸዋል፤ ለምዕራባውያን የማይንበረከኩ ጀግና ያደርጋቸዋል። ኑሮና ሙስና ያስመረረውን ሕዝብ ቀልብ ይሠርቃል፤ ሱዳን እስላማዊ ሕዝብና አስተዳደር ያላት በመሆኑ። በዚህ ወቅት ስለ ኑሮ ማማረር፣ እስልምናን እንደ መቃወም ስለሚቆጠር መንግሥት ፋታ ያገኛል።

ምዕራባውያን ከኒዮርክ ቦምብ ፍንዳታ ወዲህ ከአክራሪ እስልምና ጋር ፍልሚያ ይዘዋል። ያንን ሥጋታቸውን መቆስቆስ በጣም ቀላል ነው። ሚርያምና ባለቤቷ እውነት ክርስቲያን ናቸው? ብሎ የጠየቀ ቢኖር ድምጹ አልተሰማም። የጉዳዩ መነሻ የቤተሰብ ጠብ እንጂ ፖለቲካዊ ወይም ሃይማኖታዊ ጸብ እንዳልሆነ የሚያውቅ ጥቂት ሰው ነው። እንደ ባላ ሁሉም የየራሱን ነገር እያንጠለጠለበት ኮተቱ በዛ። አንዳንዶችም ከእውነት ይልቅ የተገኘውን ሁኔታ ተጠቅመው አወሳሰቡት። ኮተቱን አንድባንድ አውርዶ የማን የማን እንደ ሆነ መበርበር አማራጭ የለውም።

ይህም ማለት ሚርያምና ባለቤቷ ጭንቅ አላገኛቸውም ማለት አይደለም። በቂም በቀል ፍርዱ ሊፈጸምባት ይችል ነበር። አልበሺር ፍርዱ እንደማይገባ እያወቁና ምሕረት ሊያደርጉ ሲችሉ፣ የፖለቲካ ዕድሜአቸውን ለማራዘም ሲሉ አሳልፈው ሊሰጡአት ነበር። ለሚርያም ምሕረት መስጠት ማለት ውርደትና ለእስልምና አለመቆም ሊመስልባቸው ሆነ፤ በዚህ መካከል ሚርያም አሜሪካ ኤምባሲ ገብታ ተደበቀች ተባለ፤ በድብቅ በአውሮፕላን ተሳፍራ ጣልያን ገባች ተባለ። እውን ከሱዳን መንግሥት አምልጣ ነው? ወይስ አልበሺር ከኃፍረት እንዲያመልጡ ታስቦ ነው?

የአሜሪካ ሪፓብሊካን ፓርቲ ተሳትፎ ክርስትናን ለማስከበር በሚል ነው፤ ዴሞክራቲክ ፓርቲ የሴትነት፣ የስደተኛና የሰዶማውያንን መብት ለማጉላት ነው። የሕጻናት መብት ተከራካሪዎች አሉ። [ሚርያም ከኮቷ ሥር የለበሰችውን የሰዶማውያንን "ሬንቦ" ባንዲራ ይመልከቱ። ከባሏ ጋር ልትኖር የምታመራበት የአሜሪካ ግዛት ኑሃምሸር የታወቀ የሰዶማውያን መነኻርያ ነው።] ጣልያንና እንግሊዝ ሱዳንን ለመንቀፍ ሲሉ። የፖለቲካ ሰዎች በዚህ በጎ ዜና ተገን በጎነትን ለመቀዳጀት ቀዳሚ ቦታ ለመያዝ ሲሰባሩ ታይተዋል። ከነዚህ መሓል ለወትሮው ክርስትናን የሚያንቋሽሹ የእንግሊዝ ጋዜጦችና ታዋቂ ሰዎች አሉባቸው። ተመሳሳይ ችግር በናይጄሪያ በሶርያ በግብጽ በሳውዲ በኢራቅ ወዘተ ቢኖርም ፖለቲካዊ ጥቅሙ አናሳ ስለሆነ ጊዜና ጉልበት ይቆጥባሉ። እያማረጡ በጎ ይውላሉ፤ ቅድሚያ ለራሳቸው ነው፤ ከተረፋቸው ብቻ ለተጎዳው ወገን ይደርሳሉ።

አባት እስላም ቢሆን፣ እናት ክርስቲያን ብትሆንም፣ የተወለደው እስላም ይሆናል የሚለው በአገር ደረጃ ሊያሳስበን ይገባል። 1/ ሚርያም፣ ክርስቲያን እናቴ ያሳደገችኝ እንደ ክርስቲያን ነው፤ እስላም አይደለሁም፤ ዘመዶቿ ነን የሚሉትን አላውቃቸውም ብላለች። ከእስላም የተወለደ እስላም ነው፤ ክርስቲያን የሚኾነውስ እንዴት ነው? ወንጌላውያንና ኦርቶዶክሳውያን ሁለቱም ክርስቲያን ነን እያሉ ለምን ተራራቁ? ያለ ክርስቶስ ምን ዓይነት ክርስትና ሊኖር ይችላል? 2/ ስለ ሃይማኖታዊ አስተምህሮ መዛባትና መባዛት መንግሥትን በኃላፊነት መጠየቅ ተገቢ ነው? ሃይማኖትን ማጽናትና ማስከበር የአማንያኑ [የመሪዎቹ] ድርሻ አይደለም ወይ? 3/ እውነተኛ ቤተክርስቲያን ክርስቶስን ያመነችና በርሱ ወንጌል ላይ የቆመች ነች። በአሁኑ ወቅት በምድረ ዐረብ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ወገኖቻችን ኑሮአቸውን ለማሸነፍ እየተንገላቱ ይገኛሉ። ባለፈው ዓመት 150 ሺህ ያህሉ ከሳውዲ ሲባረሩ ከ8ሺህ በላይ ሕጻናት አቅፈው መገኘታቸው ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው። ከኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ደጋግሞ የሚደመጠው እስላሞች ወንድሞቻችን ናቸው የሚል ነው፤ የዜግነት ወንድምነትና እህትነት ከሆነ አባባሉ ትክክል ነው። ምዕመን የሃይማኖትን ልክ ካለማወቁ፣ መሪዎችም የማስተማር ኃላፊነታቸውን ከመዘንጋታቸው የተነሳ ከሆነ ግን እጅግ አሳሳቢ ነው። ከመንግሥት ጣልቃ ገብነትና ከምናየው በዘር የመከፋፈል አባዜ ላይ ተጨምሮ በሚቀጥለው ትውልድ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ኅልውና መመለሻ የሌለው አደጋ ተጋርጦባታል። ለእግዚአብሔር ግን የሚሳነው የለም።