ርዕሰ አንቀጽ

ተዋናዩን ትተን ተመልካቹን ብናይ

የአሜሪካ ራዲዮ ቪኦኤ ጥር 25/2007 አንዲት ባለትዳር ምእመን ከአንድ ባለትዳር [ዘማሪ] ጋር ስለፈጸሙት ተግባር"ልዩ" ዘገባ አቅርቦ ነበር። ዘገባው በዋነኛነት ሁለቱን ባለትዳሮች የሚመለከት ቢሆንም ወሬው በአድማጩም ዘንድ ብዙ ክርክር ጭሯል። የሚገርመው አድማጩ በአብዛኛው እቅጩን ከመናገር ይልቅ ጎራ ለይቶና ሰበብ ፈጥሮ መቆራቆሱ ነው። ባለትዳሮቹን ለጊዜው ወደ ጎን አድርገን በወሬ አቅራቢውና በአድማጩ አስተያየት ላይ ብናተኩር ምን ግንዛቤ ይሰጠን ይሆን? ተዋናዩን ትተን ተመልካቹን ብናይ።

የአብዛኛው አድማጭ አስተያየት፦ ሴቷ [ኤልዛቤል] አሳተችው። ማንም ይስታል። የግል ጉዳይ ስለሆነ አያገባንም። ክርስትናን የሚጠሉ የግራ አክራሪዎች ደባ ነው። ድርጊቱ ጨርሶ አልሆነም። ፓስተሮችን በገንዘብ አለመታመን የወነጀሉ የነዙት ውሸት ነው። ለፍርድ የምትቸኩሉ ተጠንቀቁ። ማካበድ አይገባም። እንጸልይ። የዘማሪው አገልግሎት እንዳይደናቀፍ ወሬውን ባናንዛዛ። አስቀድመህ የራስህን ጉድፍ እይ። ንስሃ እስከገባ ድረስ ምንም አይደለም። ጌታ ይቅር ብሎታል፣ ማን ሆንክና ነው የምትቃወም? ስንት ቁም ነገር እያለ በዚህ ጊዜ ማጥፋት አይገባም። ወዘተ፣ እና ለዘማሪው፦ ማገልገልህን አታቁም፤ የሚል ነው።

ሁለት ትዝብቶች። ጥንት በአዳምና በሔዋን እንደሆነው ሁላችንም ማመኻኘት እናበዛለን [ዘፍጥረት 312-14]። ሁለተኛ፣ እቅጩን መናገር ነውርና አክራሪነት እየመሰለ መጥቷል፤ አንድን ድርጊት ልክም ስሕተትም ነው ማለት እየተለመደ ነው። አንድ ማሳሰቢያ። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ በወቅቱና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለማወያየት እንጂ በጎ ነገሮች የሉም ለማለት አይደለም።

የቪኦኤ ጋዜጠኞች አዲሱና አሉላ "ነገሩ ገፍቶ ስለመጣ … ላለማቅረብ አልተቻለም" ብለውናል። ሁለቱ ባለትዳሮች የተገናኙት ከአራት ወር በፊት መስከረም 29 እና 30/2007 እንደሆነና ሽማግሌዎች ጉዳዩን እንደያዙት እየታወቀ "ልዩ" ዜና ሆኖ ጥር 25/2007 ለሕዝብ ቀረበ። "ገፍቶ የመጣው" የሴትዮዋ የሕግ ባል ስልክ ደውለው በራዲዮ ይተላለፍልኝ ስላሉ ነው። ጋዜጠኛ አዲሱ፣ ዘማሪውን ለሦስተኛ ጊዜ በስልክ ለማግኘት ሞክሮ ነበር፤ "ከወዳጆቻቸው ስሰማ" በራዲዮ ለመመላለስ ፈቃደኛ "እንዳልሆኑ" ተረድቻለሁ ብሏል። ሸምጋዮችም በራዲዮ መተላለፉን እንደማይስማሙበት አስታውቀዋል። ይኸን ዓይነት ችግር መሸምገል [ያውም ከርቀት] በአራት ወር ያበቃል ማለት ውስብስብነቱን አለመረዳት ነው። ይኸ ሳይገታቸው ጋዜጠኞቹ "በዚህ አንጻር ወሳኞቹ እኛ ነን" ብለዋል። "ጥቃት" ደርሶብኛል ለሚል ሁሉ ከንግዲህ ጋዜጠኞቹ ምላሻቸው ምን ሊሆን ነው? ይኸስ ከቪኦኤ ዋነኛ ተልእኮ ጋር አይጣረስም?

ዘገባው ከተላለፈ ከጥቂት ቀናት በኋላ ጋዜጠኛ አዲሱ ወንጌል አማኞችን ለመዝለፊያ ምክንያት ፈልጎ ነው የሚል ወሬ ተነዛ [ዲሬቱብ ዶትኮም፣ በፈረንጆች 2/12/2015 ታየ]። ወሬው በየድረገጾች ተራብቶ ወንጌል አማንያንን በየአስባቡ በጅምላ ለመወረፍ ላኮበኮቡ የመፈንጫ ሁኔታን ፈጠረ። በነገራችን ላይ፣ በጅምላ "እነዚህ ጴንጤዎች/እነዚህ ጥቁሮች/ነጮች/ሴቶች/ኦርቶዶክሶች" ብለው የሚወነጅሉ ለማጣራት የሰነፉ ወይም ያልፈቀዱ ናቸው። ሳይቆይ ሌላ ቀጣይ ፕሮግራም በቪኦኤ ቀረበ። ጋዜጠኞቹ ችግር ፈጣሪ ሳንሆን መፍትሔ አፈላላጊዎች ነን ለማለት ያሰቡ ይመስላል። በፕሮግራሙ ላይ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ እንደ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታይነታቸው፣ ዶ/ር ቶሎሳ እንደ ፕሮቴስታንት አማኝነታቸው አስተያየት እንዲሰጡ ተደረገ። ሁለቱም ተገቢ ማብራሪያና መልካም አስተያየት ሰጥተዋል። መጀመሪያ የተጠየቁት ዶ/ር ቶሎሳ ናቸው [229ደቂቃ እስከ 346 ደቂቃ ባለው ጊዜ፣ በጠቅላላው 117 ደቂቃ። ፕሮፌሰር ጌታቸው ከ354 ደቂቃ እስከ 807 ደቂቃ ባለው ጊዜ፣ በጠቅላላው 413 ደቂቃ]ለፕሮፌሰር ጌታቸው የተፈቀደው ጊዜ ለዶ/ር ቶሎሳ ከተፈቀደው በሦስት ተኩል እጅ መብለጡ ያስተዛዝባል ብለን እንተወው፤ "ክፍል አንድ" የተቋረጠው ከጋዜጠኛው አስተያየት በኋላ ፕሮፌሰር ጌታቸውን ቀጥለው እንዲናገሩ በመጋበዝ ነው። ማጣራት የሚሹ የዝግጅቱን ኦሪጅናል ከቪኦኤ ጠይቀው ማግኘት ይችላሉ [ወዲያውም ከ3:41 እስከ 3:55 ደቂቃ የ"ጨዋታ" ድምጸቱን በጥሞና ያደምጣሉ]። ለማንኛውም ተመሳሳይ ድርጊት በዋሽንግተን ዲሲ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ተከስቶ ያሁኑን እንዲህ ማጉላት ለምን አስፈለገ የሚል ጥያቄ ተነስቶ ነበር። ጋዜጠኛነት ጥሪ በመጠባበቅ ብቻ ነው ወይንስ ጭምጭምታ አነፍንፎ ከቦታው በመሄድም ጭምር ነው? ስልክ ደውለው ጠየቁን የተባሉት ግለሰብስ ያን እንዲያደርጉ ተመክረው ነው? የቪኦኤ መመሪያ እንደሚያትተው ሚዛናዊነትን ማዛባትና ስብዕናን መጉዳት ያስጠይቃል። በሌላ አነጋገር፣ ሚዛናዊነትን ለመጠበቅ የታሰበው ዜናው ከተላለፈ በኋላ ይመስላል፤ "ተኩስ!” ከዚያ "አነጣጥር!” እንደሚባለው ማለት ነው።

ጋዜጠኛ አዲሱ ይህን "ልዩ" ዘገባ ለማቅረብ ከባለትዳሮቹ በተጨማሪ ከታች ስማቸው የተመለከተውን ፓስተሮች በየተራ ማነጋገሩ ጥያቄ የፈጠረባቸው አሉ። ፓስተር ስለሺ፣ ፓስተር እንድርያስ፣ ፓስተር ሙሉጌታ፣ ፓስተር ግዛው ደርሰህ፣ ፓስተር መስፍን፣ አቶ ምስጋና፣ ፓስተር ታዬ። ፓስተሮቹ በሽምግልና ይዘነዋልና በራዲዮ ማስተላለፍ ተገቢ አይደለም ማለታቸው ጋዜጠኛውን አልገታውም፤ ባል፣ ሚስቴ "ጥቃት" ደርሶባታል ማለታቸው በቂ ምክንያት ነው ብሎናል። ዘማሪው ተጎትጉቶ እምቢ ቢልም ሁለት ጊዜ በስልክ [ስሕተቱን አምኖ ንስሃ መግባቱንና ይቅርታ መጠየቁን] "በትክክል መዝግቤአለሁ"ማለቱ ጋዜጠኛ አዲሱ ለምናልባት ችግር ቢፈጠር መከላከያ ማዘጋጀቱ ይሆን? ዘገባው ቅር ያሰኛቸው ወገኖች ለአሜሪካ ራዲዮ "እንባ ጠባቂ" ቅሬታቸውን በጽሑፍ ማቅረብ ይችላሉ።

በግንባር ሳይሆን በቴሌኮንፈረንስ መሸምገል ችግር ፈጥሮ ይሆን? ባል፣ ሰሚ አጣሁ፣ ዓለም ይወቅልኝ ማለታቸው ለዚህ ይሆን? ወይስ በሽምግልና የተሰየሙት አንዴ ከሆነ በኋላ በሚል አድበስብሰው ሊያልፉ ስለሆነ ነው? ምን ያህል ቢራቀቅ ቴክኖሎጂ በግንባር እንደመገናኘት አይሆንም። በፓልቶክ፣ በቻትሩም በስልክ በኢንተርኔት ቲቪ የሚካሄዱ መንፈሳዊ ስብሰባዎች በቤትና በቤተክርስቲያን የሚካሄዱትን ሊተኩ እንደሚችሉ መታሰብ የለበትም [ዕብራውያን 1024-252ኛ ዮሐንስ 12፤ ፊልጵስዩስ 228]

የተከሰተው ችግር ቤተክርስቲያን የምትገኝበትን፣ እያባበለች የምትጓዝበትን ሰባራና ሰፊ ጎዳና ገላልጦታል። ጥያቄው:- የቤተክርስቲያን መሪዎች እርምጃቸውን ለማረም ፈቃደኛ ናቸው ወይ? በዋነኛ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም ለመውሰድ ዝግጁ ናቸው? ለምሳሌ ምስክርነታቸው ያልታመነ አገልጋዮችን መድረክ መንሳት፣ እንዳስፈላጊነቱ ለአብያተክርስቲያናት ማስታወቅ። ፈቃደኛነት ከሌለ ግን መልአክም እንኳ ከሰማይ ቢላክ ለውጥ አይመጣም። በቪኦኤ የሰማነው "ልዩ" ዜና የከረመ ያስቸገረ የለመደ እንጂ ድንገት ዱብ ያለ አይደለም። ካልንስ፣ የፎቶ ቴክስት ማስረጃ ባይኖር ድርጊቱ"ጥቃት" ነው ባልተባለ፣ በቪኦኤ ባልቀረበ። ስንቶች ይሆኑ በፎቶ ወጥመድ ተጠልፈው በዝምታ ቁም እስር የሚኖሩት?

እግዚአብሔርስ የወደቀን አያነሳም? ያነሳል እንጂ። ሰውስ ከስሕተት ፈጽሞ ሊጠራ ይችላል? አይችልም። ጸጋ ግን አይሰጥም ማለት አይደለም። የጸጋን ኃይል መዘንጋት፣ ከሩሲያዊው ራስፒዩትን ጋራ፣ ጸጋ እንዲበዛ ኃጢአት እንለማመድ ወደማለትና የጌታን ቃል ወደማጣመም ይመራል [ሮሜ 61]። ተጠያቂነት በሌለበት ግራ መጋባት ይኖራል፣ እርምት መውሰድ ያዳግታል። በቃሉ እውቀት አለማደግ ጉዳት ያስከትላል። ጉዳቱ የሥልጣን አያያዝና አጠቃቀምን ይጨምራል። የጸሎት ሕይወትና እርስበርስ የመጠባበቅ ልምድ ምን ይመስላል? ለመሆኑ ከቃሉ እውቀት ውጭ ሥልጣንና ኃይል ሊኖር ይችላል? ["መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ስለዚህ የምትስቱ አይደለምን? ማርቆስ 1224”]። ቃሉን አጥርቶ አለማወቅ ውጤቱ አለመገዛት፣ ያልተለወጠ ሕይወትና መረን መውጣት ነው ["ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሳ ጠፍቶአል፣ ሆሴዕ 4"]

ባጭሩ፣ የምናምነውን ለይቶ ማወቅ ወይም አለማወቅ በአስተሳሰብ በአነጋገር በአኗኗር በአበላል በአለባበስ ላይ ሳይቀር ትልቅ ተጽእኖ ያመጣል። ዛሬ የቸገረው የተያያዘ፣ የተሟላ ትምህርት ለማስተማር የበቁ ቁጥራቸው ማነሱና የተዘባረቀ ትምህርት መብዛቱ፤ ዓለማዊነትና ንግድ በቤተ መቅደስ ውስጥ ገብቶ መንሠራፋቱ ነው [ስለጌታ ምጽዓት ከሰሙ ምን ያህል ጊዜ ሆነዎ? ስለ"በረከት" ስለብልጽግናና ስለመከናወንስ?]

የእግዚአብሔርን ቃል መጽሐፍ በመጽሐፍ እያጠኑ ሕዝቡን ለማነጽ የሚተጉ አብያተክርስቲያናት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው [ዳላስና ሂውስተን አብያተክርስቲያናት ለምሳሌ]። እግዚአብሔር ፍቅር ብቻ እንጂ ቅዱስና ፈራጅ መሆኑ ተዘንግቷል። ኃጢአትን ኃጢአት ላለማለት ዙሪያ ጥምጥም መሄድ የመጣው ከዚህ የተነሳ ነው። ብዙ አሳር ያለበት እረፍት-የለሽ የምድረበዳ ጉዞ ነው። ተጠያቂነትስ? ከቦታ ቦታ የሚዘዋወሩ አገልጋዮች ለመሆኑ ተጠሪነታቸው ለማን ነው? ለእግዚአብሔር ብቻ ነው ማለት "መንፈሳዊ" ቢመስልም ማታለልና ለውድቀት ራስን ማጋለጥ ነው። ምዕመን ተመልካች የሆነበት ዘመን ላይ ነን። ፓስተሮች ምዕመኑ ሊሰማ የሚሻውን ማዝናኛ ብርዝ እያስተናገዱ ይሆን? በአመራር ላይ የተሰየሙ ተምረው ለማስተማር ሳይሆን በጌታ ሕዝብና ንብረት ላይ ለመሠልጠን ይሆን? አንዳንዶችም ያልዋሉበትን ያልተሞከሩበትን ማእረግ ለቃቅመው መድረኩን ይዘውታል። ለመሆኑ"ፓስተር" እንጂ እረኛ መባል ለምን አይመረጥም? "ፓስተር" መጠሪያው ዘመናዊና ፕሮፌሽናል ስለሚያስመስል ይሆን? "ሴሌብሪቲ" ባህልና ዓለም-ቀመስ ውዝዋዜ እንዴት እንዲህ ፈጥኖ ሊንሠራፋ ቻለ?

የጌታ ኃይል አልተለቀቀምና ኃጢአትን የሚቋቋም ጉልበት ጠፍቷል። የጌታ ቤት ወተት ብቻ በሚጋቱ ሕጻናት ተሞልቶ እንዳይሆን እንስጋ። ከዚህ ቀደም በዚሁ ድረገጽ እንዳመለከትነው፣ ተዘዋዋሪ ዘማሪዎችና ሰባኪዎችን በየደረሱበት የሚያቀርቡትን አገልግሎት መከታተል ከመቸውም ይልቅ አስፈላጊ ነው። ይኸ ቁጥጥር ሳይሆን አንዱ አንዱን መጠበቂያ ይልቁንም የወንጌልን ንጽሕናና የጌታን ስም ማስከበሪያ ብልሃት ነው። በሌላ አነጋገር፣ በቪኦኤ የተዘገበው ዜና በአንድ ቀን ተነስቶ የሆነ አይደለም ለማለት ነው።

አብያተክርስቲያናት ለሁለት ዓመት ዘማሪና ሰባኪ ከውጭ መጋበዝ ቢያቆሙስ? አገልጋዮች በሰዎች አሳብ እንዳይጠመዱ፣ ጸጋን በቪዛ እንዳይሸጡ ምን ጥንቃቄ ሊወሰድ ይገባል? ለመሆኑ የቤተክርስቲያን መሪዎች ሥልጣናቸው እስከምን ድረስ ነው? ምዕመንና አገልጋይስ ለመጠባበቅና ለቤተክርስቲያን ለመገዛት ፈቃደኛ ናቸው? ስለክርስቶስ ቤተክርስቲያን መሠረታዊ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውቀት አለ? ከሃያ ሦስት ዓመት በፊት በራሱ አነሳሽነት ማንም "የራሱን" ቤተክርስቲያን አይመሠርትም። ቤተክርስቲያን ምዕመኑንና በአገልግሎት የተሠማሩትን በጥብቅ ትከታተላለች፤ ትመክራለች፣ ትገስጻለች፣ ሲያስፈልግ ታገልላለች። ዛሬ ከዚህ ወጥቶ እዚያ መዛወር ችግር የለበትም። ሲያሰኝ ፓስተር መባል፣ በወዳጅ መሾምና መሿሿም ተለምዷል። የደረጃ መዳቢዎች መ/ቤት ይመስል የአገልግሎት እርከን እየተራዘመ ሰማይ ጠቅሷል። ተቀዳሚ ዓላማው የርስበርስ ፉክክር፣ ኑሮን ማደራጀትና በሌላው ላይ ለመሠልጠን የሚደረግ ሩጫ መስሏል። ዘማሪ መባል አልበቃም፤ የፓስተር ካባ ደርቦም አልሞቀም። ወንጌላዊ መባል አንሷል። እንደ ክዋክብት ከሩቅ የሚታዩ አዲስ ነገድ በገንዘብ ተገዝተው ሠርግ የሚያደምቁ መድረክ የሚያሞቁ ተነስተዋል። ሌላው ሐዋርያ ነው፣ አባት ነው፤ ነቢይ እከሌ ነው። ቅርብ ጊዜ ዶ/ር ሐዋርያ ተጨምሯል [ወንጌል ዶትኮም 2006]። በጥልቅ ለመወያየትና ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድ መቸ ይሆን ሰዓቱ? እግዚአብሔር አብ ሆይ፣ ስለ ስምህ ስትል ማረን። የቤተክርስቲያንህ ጌታና እረኛ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፣ ሕዝብህን እርዳ። መንፈስ ቅዱስ ሆይ፣ ለሕዝብህ ብርታትና ማስተዋልን ስጥ።

ይኸ ነገር ኃጢአት ነው ማለት ራስን ማጽደቅ ወይም ሌላውን መኮነን ሳይሆን፤ ልኩን መናገር ነው። እግዚአብሔር አለ፤ ልክና ስሕተትም አለ። ራሳችንን አንመለከትም፣ የሚያስመካ ጽድቅ የለብንምና። እኛንና ዓለምን ወደሚዳኝ ጌታና ውስጣችን ወዳኖረው መንፈሱ እንመለከታለን፤ ቅዱስ ቃሉን እንመረምራለን፣ ራሳችንም እንመረመራለን። ለመፍረድ አንቸኩልም። አንዳኝም አናጣራም አንመረምርም ማለት ግን አይደለም [ገላትያ 61-51ኛቆሮንቶስ 1127-32፤ ዘዳግም 1618-20፣ ዮሐንስ 7241ኛቆሮንቶስ 512-1361-62ኛ ተሰሎንቄ 314-15]። ባልተረዳነው ጉዳይ፣ ሳያስፈልግ፣ ላያንጽ አንዳኝም። እያንዳንዱ የራሱ ኃጢአት አያጣም ማለት ቁምነገሩን ማዛባት ነው፤ የክርስቶስን ደም የማንጻት ኃይል ማቃለልና ላመኑ የሚሰጠውን የጸጋ ልብስ ማሳሳት ነው። ጸጋና ምሪት የሚሰጠው በትሕትና ለሚራመዱ እንጂ ራሳቸውን ላገለሉ፣ ለሚያመነቱና ለሚመኩ አይደለም። ልክና ስህተቱን መመዘኛ በቅድሚያ የእግዚአብሔር ቃል ነው፣ ኅሊናም አለ፣ መንፈስ ቅዱስ ያስተሳሰረው የቅዱሳን ማኅበርና ማኅበራዊ ሚዛኖችም አሉ። በተለይ ወንጌል አማንያን ልኩን ከስህተቱ መለየት ካልቻሉና፣ ስለተረዱት እውነት ለመናገር ካመነቱ ከዘመኑ መንፈስ ጋር ተጋብተዋል፤ ድፍረታቸውን ተነጥቀዋል ማለት ነው።

 

በልበ ሙሉነት ልኩን የሚናገርና የሚደመጥ ጠፍቷል። በሽታው አፍጥጦ የማያድን መድኃኒት ይፈለጋል። የድርድር ጉዞ ነው፤ የድርድር ቤት ደግሞ አጥር የለውም። ኃጢአት የሌለበት የመጀመሪያውን ድንጋይ ይወርውርን ሲጠቅሱ "ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ" ብሎ ማስጠንቀቁን ግን ችላ ይላሉ[ዮሐንስ 811]"አትፍረዱ፣ እንዳይፈረድባችሁ...” ሲል ንጹሑን ከእርኩሱ አትለዩ ማለት አይደለም። ራሳችሁም ድካም እንዳለባችሁ በመዘንጋት "በፍርድ ወንበር" ላይ ቁጢጥ አትበሉ ማለት እንጂ። በሁሉ ላይ ዳኛ የሆነው፣ ሁሉን የሚያውቅ፣ በቅንነትና በጽድቅ እናንተን ሳይቀር የሚዳኝ ጌታ መሆኑን በፍርኃት አስቡ ለማለት ነው [ዮሐንስ 522-27]። መዳኘታችሁ በሌላው ውድቀት ደስ በመሰኘት ሳይሆን፣ የወደቀውን ወንድም/እህት ለማንሳት፣ የተናጋውንና የታመመውን ማኅበር ለማነጽና ለመፈወስ በመሻት ይሁን ለማለት ነው። ሁሉ በፍቅር ይሁን፣ ሁሉ በሥርዓትና በማስተዋል ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን ለማለት ነው።