ርዕሰ አንቀጽ

ዝም ብሎ ማየት ነው

የሚሆነውን ዝም ብሎ ማየት ነው። ፈጥኖ አለመናገር ነው። ጆሮ አለመቀሰር፣ ጉልበት አለመጨረስ ነው። አንደበት ለማንቀሳቀስ አሁን ጊዜው አይደለም። ጆሮ ለመቀሰር ጊዜና ዕድሉ አልፎአል። ላስቻለው መድኃኒቱ ራስን ቆጥቦ፣ ወዶ-ገባ እስረኛ መሆን ነው።

"በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ [አልሁ] / ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ / በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ አልሁ፤ / ከዝምታ የተነሣ / እንደ ዲዳ ሆንሁ / ለበጎ እንኳ / ዝም አልሁ /  ቁስሌም ታደሰብኝ / ልቤም በውስጤ ሞቀብኝ / ከማሰቤም የተነሣ / እሳት ነደደ፤" [መዝሙር 39፡2-3]።

ለሁሉም ጊዜ አለው። ለመናገር ጊዜ አለው፤ ዝም ለማለት ጊዜ አለው። በንግግር የማይሞከር አለ፤ በዝምታ የሚታለፍ አለ። ንግግር ማብዛት ውጤቱ ድንዛዜና ቂም መፍጠር ነው። “ይህ ወገን በጸሎትና በጦም ካልሆነ” አይሞከርም እንዳለው፣ ነገሩ ተወሳስቧል። ጸሎት በቅድሚያ ለራስ ነው፤ ከመንፈሰ መራራነት ራስን ለማዳን። ጸሎትና ጦም ደግሞ ለሁሉም ወገን ምሕረት እንዲወርድ ነው። በስተፍጻሜ። እንዳለ የሚቀጥል የለም። ስለዚህ አለመቸኮል ነው፤ መቸኮል ከሚያበላሽና ከሚያዘገይ በቀር ፋይዳ የለውም፤ መቸኮል አንዳንዴም ጥዝጣዜ እንደማቀበል ነው።

ከማሰቤ የተነሣ እሳት ነደደ፤ ሳልፈነዳ ብዬ አውጥቼ ተናገርሁ። ባወጣ ያውጣው ብዬ ተናገርሁ። የተናገርሁት ለራሴና ለእግዚአብሔር ነው፦

"አቤቱ፥ ፍጻሜዬን አስታውቀኝ፥ [ብዬ] / [አካሄዳቸውን ይለዩ ዘንድ ብርሃንህን አብራላቸው ብዬ] / የዘመኔ ቍጥሮች ምን ያህል እንደ ሆኑ፥ / እኔ ምን ያህል ወደ ኋላ እንደምቀር፤ አውቅ ዘንድ [ብዬ]። / እነሆ፥ ዘመኖቼን አስረጀሃቸው፤ / አካሌም በፊትህ እንደ ኢምንት ነው። / ሕያው የሆነ ሰው ሁሉ / በእውነት ከንቱ ብቻ ነው። / በከንቱ ይታወካል እንጂ / በእውነት ሰው እንደ ጥላ ይመላለሳል፤ / ያከማቻል የሚሰበስብለትንም አያውቅም፤" [መዝሙር 39፡4-6]።

ሁላችንም በየፊናችን የሚታየንን ብቻ እያየን ተጓዝን፤ እግዚአብሔርም በፊናው ሁሉን እያየ ኖረ። ብርሃኑን እስኪለግሠን በያለንበት ዝም ብለን ማየት፣ አድፍጦ መተያየት ሆነ። እኔም ለእግዚአብሔር ተናግሬአለሁና ጊዜው ሲደርስ ለሰው እናገራለሁ ብያለሁ። ያንጊዜ ስለ እግዚአብሔር በእግዚአብሔርና በሰው ፊት እናገራለሁ፤ ስለ ሰው በእግዚአብሔርና በሰው ፊት እናገራለሁ። ቀን የሠወረውን ቀን ይገልጠዋል። ሣምንት አስሮ ያዘገየውን ዓመት ይፈታዋል። ለእግዚአብሔር ከተነገረ፣ እግዚአብሔር አዋቂ ነው። እግዚአብሔር ካወቀ በቂ ነው። ተስፋ ማድረግ ይህንን ነው። እስከዚያ ዝም ብሎ ማየት ነው።

"አሁንስ ተስፋዬ ማን ነው? / እግዚአብሔር አይደለምን? / ትዕግሥቴም ከአንተ ዘንድ ነው፤" [መዝሙር 39፡7]። / "እግዚአብሔር በተስፋ ለሚጠብቁት ለምትሻውም ነፍስ መልካም ነው። / ሰው ዝም ብሎ የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ ቢያደርግ መልካም ነው። / እርሱ አሸክሞታልና ዝም ብሎ ለብቻው ይቀመጥ። / ተስፋ የሆነው እንደ ሆነ አፉን በአፈር ውስጥ ያኑር። / ጕንጩን ለሚመታው ይስጥ፥ ስድብንም ይጥገብ፤" [ሰቆቃው ኤርምያስ 3፡25-30]። / "ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና። / ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፤ [ታማኝነቱ] ብዙ ነው፤" [ሰቆቃው ኤርምያስ 3፡22-23]።