ርዕሰ አንቀጽ
ዲያስጶራ ዲያስፖራ ዳያስፖራ

ከሃያ ዓመት በፊት። “ዲያስጶራ” ን ከእነ ፕሮፌሰር መስፍን ሌላ ብዙ ሰው ሰምቶ አያውቅም ቢባል ማጋነን አይሆንም። የሀገራችን የተቃርኖ ፖለቲካ ከመደብ ትግል ወደ ጎሣ ክልል ተሸጋግሮ “ዲያስጶራ”ን የአደባባይ መነጋገርያ አድርጎታል። ዛሬ ከአንድ ሚሊዮን በላይ እህቶቻችን በህጋዊና በህገወጥ መንገድ በግርድና ዐረብ ምድር ፈስሰዋል። ወደ አፍሪቃና ወደ አውሮጳ የጎረፈውና የሚጎርፈው ብዛቱ በውል አይታወቅም። በተገኘ አጋጣሚ ለመፍለስ ያኮበኮበው፣ ቅርሱን ካገር ውጭ ካሸሸው ጋር ተደማምሮ “ዲያስጶራ ያልሆነ የለም” ያሰኛል። አንድ እጁ፣ ዐይኑና እግሩ ደጅ ያልወጣ የአገር መሪ የለም። ቪዛ ይታደላል ቢባል የማይሰለፍ ለምልክት እንኳ ይገኝ ይሆን?

ሳይቆይ አውሮጳና ሰሜን አሜሪካ የሠፈረው ወገን፣ አገር የሚመራውን መቃወም ጀመረ። የተካረረ ፖለቲካ በተራው ሦስት ዓይነተኛ አፍራሽ ውጤት አመጣ፦ 1/ መረጃ የማይሻ ጅምላ አስተሳሰብን አራባ፤ በዚህ ስሌት፣ “ዲያስጶራ” ተቃዋሚ ነው። “እኔ ያልኩት ብቻ” በዝቶ የመገናኛ መስመሩን አጣበበ፤ 2/ በጅምላ ማውገዝና የራስን ማወደስ እንጂ ከውጭ ሆነ ከውስጥ ቅን ወቀሳ ማሰማት በጠላትነት የሚያስፈርጅ ሆነ፤ የብዙዎችም አንደበት በፍርኃት ተሸበበ፤ 3/ ውጭ ይሁን አገር ውስጥ ሁሉም “ኢትዮጵያዊ” ይባል እንዳልነበረ፣ “ዲያስጶራ” ባዕድ [አገር-ከዳ] የሚል ትርጓሜን ተቀዳጀ። የሚገርመው፣ [ባዕድ] የውጭውን ብቻ ሳይሆን የአገር ውስጡን መጨመሩ ነው! ከዚያ “ኦሮሞ ዲያስጶራ፣” “ተጋሩ ዲያስጶራ” እያለ በየክልሉ ይሸነሽን ገባ።

አሁን የሚገዛው መንግሥት የ “ዲያስጶራ ጉዳይ" መምሪያ ጽ/ቤትና “የዲያስጶራ ቀን” አቋቁሟል። ይህ በአንድ መልኩ ሊበረታታ ይገባል። ሆኖም ብዙዎች የሚሉት የመምሪያው ተቀዳሚ ዓላማ ውጭ ያሉት ቅርሳቸውን አገር ውስጥ “ኢንቬስት” እንዲያደርጉ እንጂ በዜግነት መብታቸው ሙሉ ተሳትፎ እንዲኖራቸው አይደለም፤ እንዲያውም በ “ዲያስጶራነት” አሳብቦ ስለሚከፋፍል ብዙኃኑን አይወክልም የሚል ነው።

ይህ መጤ ባሕል በፖለቲካው ክልል ብቻ ሳይወሰን በክርስቲያን ማኅበራትም ውስጥ ዘልቆ ገብቷል። እርግጥ በኦርቶዶክሳውያን መሓል ከርሮ ሥር ሰድዶ ይሆናል። በወንጌል አማንያንም ዘንድ በአደረጃጀትና በአመራር ያልታሰበ ልዩነት እየታየ ነው። ውጭ ያሉ ወንጌል አማንያን አገር ውስጥ ካሉት ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት ይኑራቸው? የበላይና የበታች ወይስ የእኩልነትና የአብሮነት አገልግሎት? ምን ያህሉን በጋራ፣ ምን ያህሉን በተናጠል በምን ቅደም-ተከተል ያገለግሉ? “ዲያስጶራ” ወገኖቻችን ከሚሲዮናዉያን በምን ተለዩ? የሚል ነው። ገንዘብ የችግሩ መንስኤም መፍትሔም ሆኗል። ገንዘብ ከውጭ አሰባስበው ለሚመጡ በአፋጣኝ ውጤት ማስገኘት የፈጠረው ጫና የገበሬን ትእግሥት በነጋዴ ቅልጥፍና ከልሶታል። ይህም ቅራኔና አለመተማመን ፈጥሯል። ውጭ ኗሪ ሳይሆኑ የሚዘዋወሩ አገልጋዮችና፣ ተቀማጭነታቸውን ውጭ አድርገው የተሠማሩ፣ የአገልግሎቱን መስክና መልክ ለውጠውታል፤ ማን ለማን ተጠሪ ይሁን ለሚለው ምላሹ ዛሬም ተድበስብሶአል።

“ዲያስፖራ” መሠረተ ቃሉ ግሪክ ሆኖ፣ የሕዝበ እሥራኤል በአሶራዉያን፣ በባቢሎናዉያንና በሮማዉያን ተፈናቅሎ መበተንን ያመለክታል፤ “እግዚአብሔርም በአሕዛብ መካከል ይበትናችኋል፣” [ዘዳግም 4፡25-28]። ኋላ ቃሉ በባሪያ ንግድ፣ በቅኝ ገዢዎችና በጦርነት ለተፈናቀሉ፣ አገር ውስጥ ለተሰደዱ፣ ድንበር ተሻግረው ሥራ ለሚፈልጉ ሁሉ ጠቀሜታ ዋለ። “ዲያስጶራ” ስደተኛ ማለት ነው። ታዲያ ከስደተኛ ይልቅ “ዲያስጶራ” ለምን ተመረጠ? ምክንያቱ “ዲያስጶራ” ሰወር ስለሚል፤ “ስደተኛ” ግን ለሰው ሁሉ ግልጽ ስለሆነ ነው። ስደተኛ “በረኀብ ወይንም በአንድ ችግር ምክንያት ከሀገሩ ወጥቶ ወደ ባዕድ አገር የተሰደደ አገሩን ያጣ” ማለት ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ በአገሩም ውስጥ በረሃብ በጦርነት በወረርሺኝ በሃይማኖት በሠፈራ ተሰድዶ ያውቃል። “ስደተኛ” ሆድ የባሰውን ሁሉ ስለሚጨምር፤ ቃሉ የስደትን መንስኤና የክፋቱን መጠን ስለሚያስረዳ። ሰው ባገር አልቀረም ወደሚለው ስለሚተረጎም። ያም አገር ለሚመሩ ጥሩ ግምት ስለማያሰጥ። የ “ዲያስጶራ” ቃል ጠቀሜታ እንግዲህ እዚህ ላይ ነው። “ዲያስጶራ” ባዕድ ነው፤ የባዕድ ስለሆነ ከአገሬው እንደሚሻል ይታሰባል። ቃሉ ጅምላ ስለሆነ አጎበር ሆኖ የሚሸሽገው ነገር አለ [ለውጥ ላለማለት "ትራንስፎርሜሽን"፤ መነሻ አሳብ የሚያዘናጉ አሕጽሮተ ቃላትን ይታዘቡ - ኢሠፓኮ፣ ኢሕአዴግ]። በሽሽግነቱ የጋዳፊ ቤተሰብ ያጎሳቆላት ሸዋዬ ሞላ አትታሰብም፤ ለቅሶዋም አይሰማም፤ በፈላ ውኃ ፊቷ መላላጡ አይታይም። በጭፍኑ “ዲያስጶራ”።

የአገርና የቤተክርስቲያን መሪዎች በአማርኛ ንግግር ሲያደርጉ እንግሊዝኛ የሚቀላቅሉት ለምን ይሆን? የቋንቋ ልቀታቸውን ለማስመስከር ነው? አሳቡ በእንግሊዝኛ ቢነገር የተሻለ ጥራትና ክብደት የሚቀዳጅ ስለሚመስላቸው ነው? ሰሚው ቢገባው ባይገባው ኃላፊነት ስለማይሰማቸው ነው? የሚገርመው፣ በየትኛውም ማኅበረሰብ፣ ፊደልና ሥልጣን የቆነጠሩ ጥቂቶች፣ በብዙኃን ላይ የሚሠለጥኑበት ዘዴአቸው ተመሳሳይ መሆኑ ነው። ብዙኃኑም የሰማውን ሲያስተጋባ ከገዢዎቹ ጋር የተተካከለ እየመሰለው ተገቢ ጥያቄ ላያነሳ ራሱን ይደልላል።

ሕዝበ እስራኤል ቤተመቅደስ ከመፍረሱ በፊት ከምድር ዙሪያ ወደ ኢየሩሳሌም ቢያንስ አንድ ጊዜ በዓመት ይሰባሰቡ ነበር [ለቀዳሚው ትእዛዝ ዘጸአት 23፡17፤ ዘዳግም16፡16 ይመልከቱ]። ከግሪክ ግዛቶች፣ ከሮም ግዛቶች፣ ከእስክንድርያ ግብጽ፣ ከሊቢያ፣ ከምድረ ዐረብ፣ ከእስያ፣ ከኢትዮጵያ፣ ከምድር ዙሪያ ይሰባሰቡ ነበር። በበዓለ ሃምሳ [የጴንጤቆስጤ ቀን] የሆነው ይህ ነው [የሐዋርያት ሥራ 2]። “በዚህም ወራት ደቀ መዛሙርት እየበዙ ሲሄዱ ከግሪክ አገር መጥተው የነበሩት አይሁድ በይሁዳ ኖረው በነበሩት አይሁድ አንጐራጐሩባቸው፥ በየቀኑ በተሠራው አገልግሎት መበለቶቻቸውን ችላ ይሉባቸው ነበርና፤” [የሐዋ. ሥራ 6፡1-2]።

በኢየሩሳሌም የኖሩ አይሁድ ከውጭ የተሰባሰበውን “ዲያስጶራ” እንደሚገባ አላስተናገዱም። ያለምክንያት አይደለም። “ዲያስጶራው”ን የውጭ አገር ኑሮ በብዙ መልኩ ቀይሮታልና ነው፤ ውጭ ተዋልዷል፣ ዕብራይስጥ ሲናገር ያዝ ያደርገዋል። እንግሊዝኛ ይቀላቅላል። ከውጭ ያመጣውን ገንዘብ ይመነዝራል፤ መንዛሪም ጸሎት ቤት ደጃፍ ቆሞ ትርፉን ያቃጭላል። ከዚያ ስመ-ጥር ሆቴል ገብቶ “ወፍራም ቲፕ” ይሰጣል። ድሮ በናቀው ተነፋነፍ፣ ቁንጮና ጥብቆ ተሽሞንሙኗል። በቅል ፈንታ በፕላስቲክ ውኃ አንጠልጥሎ መንገድለመንገድ ይጎነጫል [ለነገሩ የአገር ቤቱም እንግሊዝኛ ይቀላቅላል፣ ጠርሙስ ውኃ ከአጠገቡ አያጣም]። አዲስ አበቤዎች ይኸ “ያገር ልጅ” ይኸ “ክልስ” እያሉ ተቧድነው ይወቃቀሳሉ ይሞጋገሳሉ። ውጤቱ ማንጎራጎር ሆነ።

መንፈስ ቅዱስ አዋቂ ነው፤ “እንደ ወደደ ብልቶችን … በአካል አድርጎ” አንዲትን የክርስቶስን ማኅበር ፈጠረ፤ [1ኛቆሮንቶስ 12፡18]። ለተከሰተው ችግር ሐዋርያት የሰጡት ምላሽ ዛሬም ለክርስቲያን ማኅበራት ቋሚ መመሪያ ሊሆን ይገባል። “ዲያስጶራ” የለ “ያገር ልጅ” “ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥” ነው [ኤፌሶን 2፡14-15]። እርሱ አንድ ያረገው ሲበተን፣ በእሾህ አጥር ሲካለል ዝም ብሎ አያይም፤ ያስቆማል፣ ያፈርሰዋል፣

“አሥራ ሁለቱም ደቀመዛሙርት ሁሉን ጠርተው እንዲህ አሉአቸው፦ የእግዚአብሔር ቃል ትተን ማዕድን እናገለግል ዘንድ የሚገባ ነገር አይደለም። ወንድሞች ሆይ፥ በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብም የሞላባቸውን ሰባት ሰዎች ከእናንተ ምረጡ፥ ለዚህም ጉዳይ እንሾማቸዋለን፤ እኛ ግን ለጸሎትና ቃሉን ለማገልገል እንተጋለን፤”[የሐዋ.ሥራ6፡1-4]፤

እናስተውል። ሐዋርያት የችግሩን መኖር አልካዱም፤ አላመካኙም። የማዕድ አገልግሎት “መንፈሳዊ” አይደለም ብለው አላንኳሰሱም፤ ለጌታና በስሙ የተደረገ የሚጣል የለምና። የጸሎትና የቃሉን ሥፍራ መሻማት የለበትም ብለው ደመደሙ። እያንዳንዱ በጸጋ ክፍሉ ቢቆም ሁሉ በሥርዓት ይሆናል፤ ሁሉ ለማነጽና ለጌታ ክብር ይሆናል አሉ። እግዚአብሔርን እንጂ ሰዎችን አልፈሩም። ጠቅልለው ሥልጣን መያዝ እንዳለባቸው አልገመቱም። ችግሩ በራሱ ይወገድ አላሉም። ጸሎትና ቃሉ መካከለኛውን ሥፍራ ሲይዙ ሁሉም ይስተካከላል ብለዋልና። እንዳሰቡትም አደረጉ፤ “ይህም ቃል ሕዝቡን ሁሉ ደስ አሰኛቸው …የእግዚአብሔርም ቃል እየሰፋ ሄደ፥ በኢየሩሳሌምም የደቀ መዛሙርት ቍጥር እጅግ እየበዛ ሄደ፤ ከካህናትም ብዙ ሰዎች ለሃይማኖት የታዘዙ ሆኑ፤” [ቁ.5፣7]።

ኢትዮጵያውያን ለምን አገራቸውን ጥለው ይሰደዳሉ? ምክንያቶቹ እንደየግለሰቡ ቢለያዩም ዞሮ ዞሮ የተቃርኖ ፖለቲካና የኑሮ መጥበብ ካመጣው ጠንቅና ከገንዘብ ፍቅር አያልፉም። በሚስት በባል በልጆች ትምህርት በ“ዲቪ” ይመኻኛል። ማመኻኘት ማመኻኘት። ስለ ኃጢአት ማመኻኘት የኖረ ልማድ ነው። [ጽድቅ ግን የራሱ ምክንያት ነውና ምክንያት አይሻም!] ቀስ በቀስ ክርስቲያኖች የግዢና ጋብቻ “ዲቪ” ሎተሪም እንኳ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሳይሆን አይቀርም አሉ።

ቀጣዩ ትውልድ ፍልሰትን ልኩ እንደሆነ ቢቀበል አይድነቀን! የገዛ ታሪክን አለማወቅና አለማገናዘብ፣ የግል ምቾትን ከማኅበራዊ ግዴታ፣ ግለኛ አመለካከትን ከእውነታው መነጣጠል የራሱ የሆነ አሳር እየቀሰቀሰ ይገኛል። ለምሳሌ፣ ገጣሚና ጋዜጠኛ ነቢይ መኮንን በ2000 ዓ.ም. ኒውዮርክን በጎበኘበት ወቅት ስለ “ዲያስጶራ” የታዘበውን እንዲህ ገልጾታል፣

“ወደ ኒውዮርክ ልንሄድ በዋዜማው እንደለመድኩት ከአንድ አራት የዲሲ ነዋሪ አበሾች ጋር ለማምሸት ቀጠሮ ይዤ ነበር። እነሱም የአገር ቤት ወሬ ናፍቀዋል። እኔም የነሱን አንዋንዋርና ህይወት ለማወቅ ጉዋጉቻለሁ። ከቅርብ አመታት ወዲህ በዲቪ ወደ አሜሪካ ስለሚወጣ የአገራችን ሰው ጨዋታ ተጀመረ። በነባሩ አበሻና በዲቪ በሄደው መካከል ልዩነቱን ያወቅኩት ያኔ ነው። ‘የሚገርመው’ አለ አንደኛው። አነጋገሩ ምሬት-ቅልቅል ነው፤ ‘ይህ በዲቪ የመጣው መንጋኮ የአሜሪካን መንግስት እዚህ አምጥቶ ቤት ሰጥቶ ስራ አስይዞ አንቀባሮ የሚያኖረው ይመስለዋል፤ ጅል ሁሉ!’ አለ።”

ትዝብቱ ሚዛናዊ ያልሆነ ልሙጥ ትዝብት ነው ብለን እንለፈው። ሌሎች በአንጻሩ ስደተኛው በሃይማኖትና በፖለቲካ መካለሉንና መማዘዙን ሲያጎሉ ይደመጣሉ። ወቀሳቸው አንዳንዴ ቅናት ይታይበታል። አብዛኛው “ዲያስጶራ” ጎራ ሳይለይ ራሱንና ዘመዶቹን ለማገዝ የሚያደርገውን መፍጨርጨር እነዚሁ ዘንግተው ያዘናጋሉ።

ሕዝበ እስራኤል ተሰድደው እንኳ ኢየሩሳሌምን ከማሰብ አርፈው አያውቁም። “መጪውን ዓመት ኢየሩሳሌም እንገናኝ” ማለት ዛሬም እንኳ ሰላምታቸው ነው። “ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ብረሳሽ፥ ቀኜ ትርሳኝ። ባላስብሽ፥ ምላሴ በጕሮሮዬ ይጣበቅ፤ ከደስታዬ ሁሉ በላይ ኢየሩሳሌምን ባልወድድ፣” [መዝሙር 137፡5-6]። የወጡበትን ምድር ማሰብ ደግሞ የሕዝቦች ሁሉ ልማድ ነው። እግዚአብሔር ከጧቱ “ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደ ሆነ፥ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ፥ የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው” ብሏልና፤ [የሐዋርያት ሥራ 17፡26]። ለዘመን መለወጫ፣ ለመስቀል፣ ለጥምቀት፣ ለጾም ፍቺ፣ ለሠርግና ለቀብር አገር ቤት ማሰብና መመላለስ ትርጉሙ አንዱም ይኸ ነው። በስደት አገር፣ መተሳሰብና መቀራረብ ያገር ልጅነትን ስሜት ማጎልበቻ መንገዱ ነው።

“ምድርና ሞላዋ ለእግዚአብሔር ናት፥ ዓለምም በእርስዋም የሚኖሩ ሁሉ፤” [መዝሙር 24፡1]። ከደምና ከሥጋ ሳይሆን ከእግዚአብሔር መንፈስ ዳግም የተወለዱ ሁሉ ኢየሱስ የሚገዛባት መንግሥት ዜጎች ናቸው [ዮሐንስ 1፡12-13]። በምድራዊ ዜግነት ብቻ የተወሰኑ አይደሉም ማለት ነው። ምድራዊ ዜግነት በደምና በሥጋ በመወለድ ነው። የተሰደዱበትን አገር ዜግነት ለወሰዱ፣ ኢትዮጵያዊነታቸው ይቀንሳል ማለት ግን አይደለም። መንግሥት “ትውልደ ኢትዮጵያዉያን” ማለቱ ጥሩና ተገቢ ስያሜ ነው። “ዲያስጶራ” እና “ትውልደ ኢትዮጵያዉያን አሜሪካዉያን፣ ጀርመናዉያን፣ ወዘተ” አባባሉ ሕጋዊ ቢሆንም ላለመተማመንና ማንም የሻውን ትርጓሜ እንዲለጥፍ መንገድ ከፍቷል። ይህ መታረም ይኖርበታል።

ለክርስቲያኖች ሌላ ተጨማሪ ቁምነገር በዚህ ውስጥ አለ። ለክርስቲያኖች፣ መኖር እግዚአብሔርን ማምለክና ኅልውናውን ማገልገል ነው። ይኸ ዓይነቱ ሕይወት በቦታና በዘመን ብቻ አይወሰንም። ክርስትና፣ ዓለም አቀፋዊም ቀበሌያዊም ነው። “ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ … በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ፤” [ማርቆስ 16፡15፤ የሐዋርያት ሥራ 1፡8]። ክርስትና ሰብዓዊነትን ከዜግነት ያስቀድማል። ሰው [ሁሉ] በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥሯል ይላል [ዘፍጥረት 1፡27]!! ክርስቲያን ሥራና ሥፍራ ቢለቅ እግዚአብሔር የመራው ጉዞ ይሁን አይሁን አበክሮ ለማወቅ ይገደዳል። ክርስቲያን በምድር ላይ መጻተኛነቱን ላፍታ አይዘነጋም፤ ምድር መተላለፊያ እንጂ ቋሚ ቤቱ አይደለችም፤ “በዚህ የምትኖር ከተማ የለችንምና፥ ነገር ግን ትመጣ ዘንድ ያላትን እንፈልጋለን … እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤” [ዕብራዉያን 13፡14 ፊልጵስዩስ 3፡20]። ይህ አገርን አለመውደድ ወይም የብሔራዊ ስሜት ማነስ አይደለም። ይልቅ ከዘላለሙ አንጻር፤ ሁሉን የፈጠረውን አምላክ ኅልውና መገንዘብ ነው። ለኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነትና ጌትነት መገዛት ነው። ሁሉም መንገዱን ይመርምር።

ለክርስቲያን፦ ትሰደዳለህ ተብሎለታል፤ በዓለም እንጂ ከዓለም አይደለህም ተብሎለታል [ዮሐንስ 17፡15-16]። “በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ … በአንዲቱ ከተማም መከራ ቢያሳዩአችሁ ወደ ሌላይቱ ሽሹ፤ እውነት እላችኋለሁና፥ የሰው ልጅ እስኪመጣ ድረስ የእስራኤልን ከተማዎች አትዘልቁም …፤” [ማቴዎስ 10፡21፣23]። አስተማማኙን ይዞ አስተማማኝ ባልሆነ ዓለም ውስጥ መኖር ይህንን ይመስላል። ስደት ከቤት ይጀምራል፤ እስከ ምድር ዳርቻ ይዘልቃል። “በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” [የሐዋርያት ሥራ 1፡8]። ክርስቲያን በቻይና በምድረ ዐረብ በቡልጋሪያ በአውስትራልያ በአንታርክቲካ በጃፓን በሳይቤሪያ በምድር ሁሉ፣ ኢየሱስ መጥቶ እስኪሰበስበው እንደ ጨው እንደ ብርሃን ተበትኗል። በተበተነበት እግዚአብሔር ለፍጥረቱ ያዘጋጀውን የዘላለም መንግሥት ዜና ማብሠር ይጠበቅበታል። ክርስቲያን ደግሞ እልፍ አእላፍ ምስክሮች እንደ ደመና ከበውታል [ዕብራውያን12፡1]። ከዲያስጶራም ዳያስፖራ ክርስቲያን ነው አያሰኝም? Revised 1/23/16