ርዕሰ አንቀጽ
ነብ ለማሠልጠን

ትውልድ ታሪኩን በጥንቃቄ የመፈተሽ ኃላፊነት አለበት። አለዚያ ከታሪክ ሳይማር ይቀርና ብዙ ያባክናል። ታሪኩን ሲፈትሽ ግን በራሱ ምኞት ሚዛን ሳይሆን እውነቱን ለማወቅ የታመነ መረጃ በመያዝ መሆን አለበት። አንድ የተሳሳተ አስተሳሰብ አለ፤ ይኸውም ዘመናዊው የተሻለ እንደሆነና፤ ያለፈው ታሪክ እውነትነት የሚጸናው በዘመናዊው ተመዝኖ ካለፈ ብቻ ነው የሚል ነው። ሌላም የተሳሳተ አስተሳሰብ አለ፤ እውነት እንደ አመለካከት ነው የሚል። እውነትን እንደ አጠድ በመቀስ እየዞሩ የሚከረክሙ በዝተዋል። እዚህ አፈንግጧል፣ ይስተካከል ይላሉ። ወጣ ያለው ቅርንጫፍ ከፍጥረቱ መሆኑ አይገዳቸውም። ይኸ አፈጣጠሩ ነው ሲባሉ አክራሪነት ነው ይላሉ። እሳት ጎርሰው አክርረው ይራገማሉ። የዘመኑ ሙያ እውነትን ፍለጋ ሳይሆን የማይጋጠመውን ማዋሓድና ማደላደል ሆኗል። የተሳሳተ አስተሳሰብ ሦስተኛም አለው። ይቺን እንለፋት እንጂ ሌላውን ሌላ ጊዜ እንወጣዋለን ይላል። ያ የታሰበው “ሌላ ጊዜ” ሳይመጣ ይቀርና። ያልጠበቅነውን ይዞ ከች ይልና። ድብቁ ይፋ ይወጣና ጉድ እንዳይሠራን የሚል ሁሉ በጨለምተኛነት ይወነጀላል።

ሼኽ ሐሰን ላክብ የሞሮኮ ተወላጅ ነው። አክራሪ እስልምናን ለመወጋት መፍትሔው የነብዩ መሐመድን ማንነት ማወቅ ነው ብሎ የአሜሪካ ከተሞችን እያዳረሰ ይገኛል። ከኒውዮርኩ አደጋ በኋላ የእስላማውያን ሽብርተኞች መበራከትና መስፋፋት በእስልምና ተከታዮች ላይ ብዙ ጫና እያስከተለ ነው፤ ለአሜሪካ ፕሬዚደንትነት ከሚወዳደሩት መሓል ዶናልድ ትረምፕ ሙስሊሞች እዚህ አገር እንዳይደርሱ አደርጋለሁ ማለታቸው ነገሩን አባብሶታል። የሼኽ ሐሰን ትምህርት ይህን ሁሉ ለመቋቋም የታሰበ ይመስላል።

የአሜሪካ ወጣት በኃይማኖት ጉዳይ መሰላቸት ይታይበታል። ኃይማኖት እንደልቡ እንዳይደሰት መንገድ ላይ ተገትሮ የሚያስፈራራ ፖሊስ መስሎ ይታየዋል። ስለዚህ የሚፈልጋትን መርጦ የግሉን ኃይማኖት መቀመምን ተያይዞታል። የኃይማኖት አስተማሪዎችም ይህን ፍላጎቱን ስለሚያውቁ ትውልዱ በሚመቸው አኳኋን አነጋገርና አለባበሳቸውን አሰማምረው ይቀርቡታል። ትውልዱም የሚስማሙትን ይሻቸዋል፤ የማይስማሙትን ጥሎአቸው ይኮበልላል።

እንደ ሼኽ ሐሰን አባባል፣ የመሐመድን ስብእና መገንዘብ እርሱን ለመውደድና አርኣያነቱን ለመከተል ይጠቅማል። ነብዩን ዘመናዊ አሜሪካዊ አድርጎ እንደ አማራጭ ማቅረብ አዳዲስ ነገር መሞከር የማይሰለቸውን ወጣት ለመማረክና ጥላቻን ለመቅረፍ ታስቧል። አሜሪካኖች “ሲከር ፍሬንድሊ” የሚሉት ስልት መሆኑ ነው፦ አድማጭህ የሚገኝበትን ሁኔታ አጥና፤ መስማትና መቀበል በሚፈቅደው መጠንና መንገድ ስሜትና ምቾቹን ሳትነካበት መልእክትህን አቅርብ።

መልእክቱ ምንድነው? መልእክቱ፣ መሐመድ እንደ ዘመኑ ሰው ስልጡን ነበረ ነው። ለምሳሌ፣ ፀጒሩን ያስረዝም፣ ቀለምና የፀጉር ቅባት ይቀባ ነበር፤ ከአቧራ ብናኝ ለመከላከል [የዛሬ “ባንዳና”] ስካርፍ ፀጉሩ ላይ ያስር ነበር። ደልደል ያለ የስፖርተኛ ተክለ ሰውነት ነበረው። ከመተኛቱ በፊት ሁለት እጆቹ ላይ እፍ ይል ነበር፤ ተኝቶም እንኳ እጆቹ ላይ እፍ ይል ነበር፤ ማንኮራፋቱ ግን አይደለም። የሚተኛው በቀኝ ጎኑ ነበር። ከመካ ወደ መዲና ተጉዞ ብዙ አይሁድን ባገኘ ጊዜ አቀረባቸው፤ ፀጒሩን እንደ አይሁድ መሠራት ጀመረ፤ በዚህም ሰላም ፈላጊና አብሮ የመኖርን ጥቅም፤ የሌሎችን ባህል ማክበር አስፈላጊነት አስተማረ [ሙስሊሞች በአሜሪካ፣ እስራኤልና ዐረቦችም በያሉበት መቀራረብ ይችላሉ ማለት ነው]። መሐመድ የፈረንጅ ዱባ መብላት ይወድ ነበረ [የዛሬ “ቬጂቴርየን”]፤ የቴምር ጭማቂ በማርና በወተት ቀላቅሎ ይጠጣ ነበር [የዛሬ “ስሙዚ”]። ተከታዮቹ ከጓሮአቸው አትክልት ምግብ ያመጡለት ነበር ["ሎካሊዝም"]፤ እርሱም ስጦታ ሰጥቶ ይሸኛቸው ነበር። መሐመድ አይሳደብም [ዛሬ ወጣቶች እንደሚሳደቡት ዓይነት]፤ ሲስቅ የጥርሱ ንጣት ደስ ይል ነበር። ተከታዮቹ ፀጒራቸውን እንዲያበጥሩ፣ ጥፍራቸውን እንዲከረክሙና ጥርሳቸውን እንዲፍቁ ይነግራቸው ነበር [የዛሬ ታዳጊ ወጣቶች ችግር]። ስለ መሐመድ ጥቃቅኗን ነገር ማወቅ አስፈላጊ ነው፤ አካሄዱን፣ ቁመናውን በዐይነ ልቡና መቃኘት ጠቃሚ ነው። የሚስቶቹን ቁጥርና ዕድሜአቸውን ግን በዘመኑ በነበረው ባህል መሠረት መመዘን ያሻል ይለናል። በተጨማሪ፣ ሴቶች ጂንስ ሱሪ ተመችቶአቸው ስለለበሱ እስልምናቸው ያነሰ አይሆንም [ባጭሩ፣ እስልምና “ኩል” ነው፤ የግል ምቾትና ደስታን አይቃወምም]፣ ወዘተ።

የሼኽ ሐሰን ትምህርት በአሜሪካ ምን ውጤት ያመጣ ይሆን? እዚህ ላይ ቆም ብሎ የማልከም ኤክስን ታሪክ መከለሰ ይጠቅማል። ማልከም ኤክስ የሕግ ስሙ ማልከም ሊትል ነበር። ሊትል ነጭ የጫነብኝ ስም ነው ብሎ ኤክስ አረገው፤ ሠረዘው። ማልከም በትንሽነቱ ትምህርቱን አቋርጦ ዕፅ በመሸጥና በብዙ አልባሌ ሥራ ተጠመደ። በአውሮጳ አቆጣጠር ሃምሳዎቹና ስድሳዎቹ ጥቁር አሜሪካውያን ስለ መብታቸው የሚታገሉበት ዘመን ነበር። ጨቋኙ ወገን ነጭ ክርስቲያን ነበረ። ብዙ ጥቁሮች ኢየሱስ ክርስቶስ ነጭ እንደሆነ ይመስላቸው ነበር [ነጮቹም እንደዚሁ ነጭ ይመስላቸው ነበር]። ጥቁሮች ክርስትናን ከነጭ ጭቆና ጋር አዛመዱት። በጥቁር አሜሪካዊው ኤላይጃ ሙሐመድ መሪነት ጥቁሮች ክርስትናን ጥለው ወደ እስልምና መፍለስ ጀመሩ። የነጭ አሜሪካዊ ክርስቲያን ዘረኝነትን በጥቁር አሜሪካዊ እስልምና ዘረኝነት መዋጋት ጀመሩ።

ኤላይጃ ሙሐመድ “የመጨረሻው የአላህ መልእክተኛ” እኔ ነኝ ይል ነበር። ማልከምን እስር ቤት ሆኖ ሰበኩት። በዚህ ወቅት ነበር ነጮች ከፍጥረታቸው አጋንንት ናቸው፣ ጥቁሮች የበላይ ነን የሚለውን ትምህርት የተቀበለው። ከልቡ ሙስሊም ሆነ [ኤል ሃጅ ማሊክ ኤል ሻባዝ ተሰኘ]። በልጅነት ያጣውን ቤተሰብ አገኘ። በኤላይጃ ሙሐመድ አባትነት ከስድብ ከመጠጥ ከሌብነት ከዝሙት ርቆ ሕይወቱን በዲሲፕሊን ይመራ ጀመር። አበላሉ፣ አለባበሱና ንጽሕና አጠባበቁ ያማረ ሆነ። ብሩህ አእምሮ የተለገሰው ነበርና በማደራጀትና በመምራት የታመነና ጠቃሚ ሰው ሆነ። ብዙ ያነብብ፣ ብዙ ይጠይቅ ነበር። እውነቱን ማወቅ የማያቋርጥ ጥማቱ ሆነ። ለተረዳው እውነት ደግሞ ወደ ኋላ አይመለስም ነበር። የአስተሳሰቡና የንግግሩ ርቀት የብዙዎችን ትኩረት ሳበ፤ ይህም ለመንግሥትና በአመራር ላይ ለነበሩት ስጋት ፈጠረባቸው። ሁለት ሁኔታዎች ግን የነበረውን አስተሳሰብ ለአንዴም ለመጨረሻም እንዲለውጥ አስገደዱት። የመጀመሪያው በአውሮጳ አቆጣጠር በስድሳ አራት መካከለኛ ምሥራቅና አገራችንን ለሁለት ወር በጎበኘበት ወቅት ነበር። እስልምና የጥቁሮች ብቻ ሳይሆን ሁሉ አቀፍ መሆኑን ተመለከተ። ሁለተኛው፣ ኤላይጃ ሙሐመድ እንደሚሰብኩት ሳይሆን ወጣት ሴቶችን ያማግጡና ገንዘብ አለአግባብ ይጠቀሙ እንደነበር ተረዳ። ከእውነት ጋር ስምምነት ስለነበረው ይህን አይቶ ዝም ማለት አላስቻለውም። ማንም የማይደፍራቸውን ኤላይጃን ተናገረ። ተናግሮ ብዙ አልቆየም፤ በጥይት ተቀነጠሰ።    ... ይቀጥላል

ምንጭ፦ ናሽናል ፐብሊክ ሬዲዮ፤ በፈረንጆች፣ ማርች 10/2016፤ 5:38 ዋሽግተን ዲሲ። አቅራቢ ቶም ጀልተን ከሼኽ ሐሰንና ሌሎች ተሳታፊዎች ጋር።