አ  ስ  ር   ዓ  መ  ት 

tenthAnniversary

በኢትዮፕያንቸርች አገልግሎት ከጀመርን ሚያዝያ ወር አስር ዓመት ሞላን። ስንጀምር ይህን ያህል እንጓዛለን ብለን አልገመትንም። ዛሬን አድርሶናል ይመስገን፤ ለሚመጣው ሕያው እግዚአብሔር ያውቃል። በኢንተርኔት ማገልገል በአብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ገና ባልተለመደበት ወቅት ፓስተር ፀሐይ ዓለሙ ይህን ራእይ አካፈለችን። በቴክኖሎጂው ማን ይርዳን ስንል፣ ወንድም በትረ ቀንዓ አውሮፕላን ተሳፍሮ መጥቶ ዓርብ ከሰዓትና ቅዳሜን ውሎበት አጠናቅቆ አስረከበን። ስለ ትጋቱና ስለ በጎ ፈቃዱ ጌታ ይክፈለው። የመጻፍ ፀጋ የተሰጣቸው በተለያዩ ርዕሶች ላይ ጽፈው ልከውልን፣ እነሆ ለብዙዎች አዳርሰናል። ለእነርሱም ጌታ በረከቱን ያብዛላቸው። የለጠፍናቸው ጽሑፎች ወጪና ጉልበት የጠየቁ ቢሆንም ያለዋጋ አሠራጭተናል። ዕድሜና ጤና ሰጥቶ ከሚያስፈልገው አንዳች ያላጓደለብን አምላክ ይባረክ። በኢትዮፕያንቸርች የምንለጥፋቸው ጽሑፎች ከርዕሰ አንቀጽ አንስቶ፣ ሐተታ፣ ግጥሞችና የመጽሐፍት ግምገማን ያካትታሉ። የመጽሔታችን ትኲረት በአሳብ ዙሪያ፣ በዐበይት ስነ መለኮታዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የመነጋገርን ባህል ማዳበር ነው። መንፈሳዊና ማኅበራዊ ጉዳዮችን በሚዛናዊነትና በጥራት ያለፍርኃት በወንጌል ብርሃን መመርመርና እውነቱን መግለጥ ነው። ይኸ ዓላማችን ምን ያህል ተሳክቶልናል? እርግጠኞች አይደለንም። ሥራን የሚመዝን እግዚአብሔር ነውና ስለ ራሳችን አንመሰክርም። 

“ሰው ማነው?” ለሚለው ጥያቄ ሁሉም የየራሱ መልስ አለው፤ ከዚያ በመነሳት ሁሉም አመለካከቱንና አካሄዱን ይቀይሳል። የኢትዮፕያንቸርች አቋም ግልጽ ነው፤ ሰው በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥሯል፤ ኅልውናውና ማንነቱ ከማኅበራዊና ከታሪካዊ ሂደቶች ባለፈ፣ በክርስቶስ በተገለጠ አምላክ ማንነትና ሚዛን ይተመናል፤ “ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለ ሁላችን አሳልፎ የሰጠው” [ሮሜ 8፡32] ይላል። ወንጌል መገለጥ ነው፣ ወንጌል መገለጥ ብቻ አይደለም፣ ታሪክም ነው። በእግዚአብሔር አምሳል ስለተፈጠረ፣ ሰው ክቡር ነው። እግዚአብሔር እግዚአብሔር እንጂ ሰው አይደለም፤ ሰው ሰው እንጂ አምላክ አይደለም። የሰውን ክቡርነት የሚቀናቀን የኃያሉን የእግዚአብሔርን ሥልጣን ይቀናቀናል። ኃጢአት የሰውን ክቡርነት ይቀናቀናል። ኃጢአት በመሠረቱ እግዚአብሔርን ‘አታስፈልገኝም፣ በራሴ ብቁ ነኝ’ ማለት ነው። ኃጢአት በማኅበራዊ አደረጃጀቶች፣ ውስጥ ለውስጥ፣ የሰውን ክቡርነት ያዋርዳል። ኃጢአት ውጤት አለው። የኃጢአት ውጤት ሞት ነው። ሞት በድህነት፣ በፍትህ መጓደል፣ በሙስና፣ በሰዶማዊነት፣ በጦርነት፣ ወዘተ፣ ይመነዘራል። ሞት ከእግዚአብሔር፣ ከራስ፣ ከርስበርስና ከፍጥረት ጋር መቆራረጥ ነው። ሞት መድኃኒት የለውም ማለት ግን አይደለም። ለሞት መድኃኒት ተገኝቷል። መድኃኒቱ እንዲያውም ከበሽታው ቀድሞ የታወቀ ነው። ኢየሱስ። ኢየሱስ ሞትና ትንሣኤው የመድኃኒቱ ብሥራት ነው። የምሕረትና የይቅርታ አዋጅ ታውጇል። ላልሰሙ ማሰማት፣ ለዘነጉ ማሳሰብ ተልዕኮአችን ነው።

በሐዋርያት ዘመን፣ ሮም በዓለም ላይ የመገናኛ መስመሮች እንደ ዘረጋጋና ያም ለወንጌል ሥርጭት እንደ ጠቀመ ሁሉ፣ ዛሬም ኢንተርኔት የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ተሸክሞ ወደ ዓለም ዳርቻ ይፈጥናል። “እግዚአብሔር ቃሉን ሰጠ፤ የሚያወሩት ብዙ ሠራዊት ናቸው” [መዝሙር 68፡11]። ብዙዎች ወገኖቻችን ከሰሜን አሜሪካ፣ ከአረብ ምድር፣ ከህንድ፣ ከአህጉራችን፣ ከምድራችን፣ ከአውሮጳ፣ ከቻይና፣ ከአውስትራልያ ተመላልሰው ገጻችንን ተመልክተዋል። በብዛት የተነበቡ ጽሑፎች አሉ። ከርዕሰ አንቀጽ “የሺህ ጋብቻ ወይስ ቅዱስ ጋብቻ” [3507 ጊዜ]፤ “የስነምግባር እሴቶች [3503 ጊዜ]። ከሐተታዎች “ስኳር በሽታ” በዶ/ር ወርቁ አበበ [4418 ጊዜ]፤ "ውጤታማ ፀሎት" በተድላ ሲማ [3484 ጊዜ]። ከግጥሞች “እብዷ” በዘውዱ ሳህሉ [2889 ጊዜ]፣ "መስቀሉ ማማሩ" በጎዳና [2779 ጊዜ]። ከመጽሐፍት ግምገማ “የተስፋዬ ጋቢሶ መዝሙሮች” [5149 ጊዜ]፤ "በመሪዬ እጅ" [3000 ጊዜ] ተነብበዋል። የአምላካችን ጥበብ ወሰን የለውም፤ የዓለም መንግሥታትና ፍጥረት ክብሩን ያወራሉ። እኛም እናወራለን፤ “መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው [ሮሜ 10፡15]።” 

“ይኸማ ፖለቲካ ነው!” ያሰኙ ጽሑፎች ደግሞ አሉ። የሚገርመው፣ እንደዚያ የሚሉ ቡድናቸውን አለመደገፍ እንጂ መደገፍ “ፖለቲካ ነው” አለማለታቸው ነው። ለማንኛውም፣ ቁምነገሩ ሁሉም በደረሰበት መጓዙ ነው። በቀራንዮ መስቀል ትይዩ መቆሙ ነው። ቁምነገሩ አንዱ ሌላውን ማነጹ ነው፤ እውነቱን መሻቱ ነው፤ ሁሉም ለጌታ ክብር መዋሉ ነው። ወንጌል ሁሉን መመርመሪያ ብርሃን ነው፤ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራመብራትን ከዕንቅብ ወይስ ከአልጋ በታች ሊያኖሩት ያመጡታልን? በመቅረዝ ላይ ሊያኖሩት አይደለምን? ማቴዎስ 5:16ማርቆስ 4:21አደባባይ መውጣት የለበትም የሚባል ወንጌል የለም። ለአደባባይ የማይበቃ መብራት፣ መብራት ሊባል አይችልም።

ፀልዩልን። ይህን አገልግሎት ለሌሎች በማስተዋወቅ የጌታን ሥራ ያግዙ። እናንብብ። እናስነብብ። እንመካከር፣ እንጸልይ። ጠቃሚ መጻሕፍት ወይም የራስዎን ግምገማ ይላኩልን። አድራሻችንን በ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ይጠይቁ። ያሳተምናቸውን መጻሕፍት ይግዙ። መጽሐፍ ለመጻፍ ካሰቡ እንርዳዎ። 2/5/2008 [5/2/2016]