“የክርስቶስ ሕይወት” በክሬምሊን

[መዝሙረ ዳዊት 145:8]

[የስቬትላና እና የክርስቶፈር ታሪክ]

ስቬትላና የስታሊን ልጅ ነች። ስታሊን፣ ከ1921 – 1945 ዓ.ም. የሶቭየት ገዥ የነበረው ዮሴፍ ስታሊን ነው። “ዮሴፍ” ትርጓሜው “ያህዌ ይጨምር፣ ያህዌ ያብዛ” ማለት ነው። “ስታሊን” እራሱ ያወጣው የበረሓ ስሙ፣ ዐረብ ብረት ማለት ነው [ብረት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የጦርነት ተምሳሌት ነው፤ "ሁሉን እንደሚቀጠቅጥና እንደሚያደቅቅ ብረት ይበረታል፤ እነዚህንም ሁሉ እንደሚፈጭ ብረት ይቀጠቅጣል ይፈጭማል፣" ትንቢተ ዳንኤል 2:40-43]። ብረት ደግሞ የቅዱሱ ተጻራሪ ሆኖ፣ በቤተ መቅደስ ሥራ የተከለከለ ነው፣ "የድንጋይም መሠዊያ ብታደርግልኝ ብረት በነካው ድንጋይ አትሥራው፤ በመሣሪያ ብትነካው ታረክሰዋለህና" ዘጸአት 20:25፤ ኢያሱ 8:31፤ 1ኛ ሳሙኤል 17:45,47]። አይገርምም? ስታሊን ከ1880 – 1886 ዓ.ም. ድረስ የቤተክህነት ትምህርት ቤት ተማሪ ነበር። በትምህርቱ ጎበዝ ስለነበረ ቲፍሊስ ሴሚናሪ ገባ፤ ከዓመት በኋላ ግን አቋርጦ ዙፋን ለመገልበጥ የሚታገሉ አብዮተኞችን ተቀላቀለ። እናቱ እንደ ተመኙት የእግዚአብሔር አገልጋይ ሳይሆንላቸው ቀረ። አመራሩም ብዙ ጭከናና ደም ማፍሰስ የታየበት ነበር።

ስታሊን የሶቭዬት ገዥ በነበረበት ዘመን ባላገር የሚኖሩ እናቱን የጠየቀበት ቀን በጣት ይቆጠራል። በአንደኛው ወቅት አሮጊት እናቱ ጥያቄ ጠየቁት

“ሶሶ፣ ለመሆኑ በሥራህ አሁን ምን ላይ ደርሰሃል?”

“ንጉሡ ትዝ ይልሻል እማማ?”

“አዎን፣”

“እንደ ንጉሡ ነኛ” ይላቸዋል፤

ተከዝ ብለው ቆይተው፣ “ለኔስ የእግዚአብሔር አገልጋይ ብትሆን ይሻል ነበር” ይሉታል።

ስታሊን፣ ከልጆቹ ሁሉ ሴት ልጁን ስቬትላናን ያቀርባት ነበር። የአስራ አንድ የአስራ ሁለት ዓመቷ ስቬትላና አንድ ቀን በአባቷ ላይብረሪ ውስጥ “የክርስቶስ ሕይወት” የሚል መጽሐፍ ታገኝና ማንበብ ትጀምራለች። ታሪኩ ስለገረማት፣ መጽሐፉን ወደ አባቷ አምጥታ “ይኼ እኮ ውሸትና አፈ-ታሪክ ነው” ትለዋለች። ስታሊን ምን አለ? ስቬትላናን ጭኑ ላይ አርጓት ክርስቶስ በእውነት የኖረ ሰው እንጂ አፈ-ታሪክ እንዳይደለ አንድ ባንድ ያስረዳት ጀመር። እግዚአብሔር የለም በተባለበት ምድር፣ አማንያን በሚሠቃዩበትና በሚገደሉበት ምድር፣ ትውልዱ በክህደት በተጠመቀበት ምድር፣ የክህደት አባት ስታሊን፣ ለዚያውም ክሬምሊን ቤተመንግሥት ውስጥ፣ ሴት ልጁን ጭኑ ላይ አስቀምጦ፣ ስለ ክርስቶስ ታሪክ አስተካክሎ ያብራራላት ጀመር። የጌታ መንገዱ እውነትም አይመረመርም።

ሁለተኛው፣ ክርስቶፈር ሂችንስ ነው። ክርስቶፈር በ2003 ዓ.ም. በ62 ዓመቱ በአሜሪካን ምድር የሞተው የእንግሊዝ ተወላጅ፣ ታዋቂ ደራሲና ጋዜጠኛ ነው። ከጋዜጠኛነቱና ከዜግነቱም ይልቅ የሚታወቀው በ“እግዚአብሔር የለም” ዘመቻው ነው። “እግዚአብሔር ታላቅ አይደለም” የአንደኛው መጽሐፉ ርዕስ ነው። ታዲያ ይኸ ለምን ይገርማል? የሚገርመው በሦስት ምክንያት ነው። በመጀመሪያ፣ “ክርስቶፈር” ስሙ ግሪክ ሆኖ ትርጓሜው “ክርስቶስን የሚሸከም” ማለት ነው፤ ሳያስበው የክርስቶስን ስም ሲያስጠራና ሲያስታውስ ኖረ። የክህደት ዘመቻው ስንቶችን ወደ እምነት እንዳፈለሰ የሚያውቅ እግዚአብሔር ብቻ ነው። ሁለተኛ፣ ከአማኝ ወንድሙ ፒተር ጋር የማይታረቅ ቅራኔ በመሓላቸው በመኖሩ በአደባባይ ሳይቀር ይሟገቱ ነበር። ሦስተኛው፣ ክርስቶፈር የጉሮሮ ካንሰር ሊገድለው ሲያጣድፈው ያከመው እውቁ ዶ/ር ፍራንስስ ኮልንስ ነበር። ኮልንስ በክርስቶስ የሚያምንና ሐኪም ነው። ኮልንስ አማኝ መሆኑን ክርስቶፈር ያውቅ ነበር። ኮልንስ ለክርስቶፈር በክርስቶስ ስም ይጸልይ፣ ያስጸልይ ነበር። ለክርስቶፈር ግን የተያያዘው የህመም መንገድ የማይመልስ መንገድ ሆነበት። ያን ጊዜ ነበር ለወዳጆቹ፦ “እግዚአብሔር አይበልና፣ በጣእር ሰዓት አምልጦኝ ‘በእግዚአብሔር አምኛለሁ’ ብል፣ ስሜ እንዳይጎድፍ አደራችሁን፣ ‘የወሰደው መድኃኒት ራሱ ላይ ወጥቶበት ነው’ በሉልኝ ብሎ የተናዘዘው።

ስቬትላና በ85 ዓመቷ በ2003 ዓ.ም. በአሜሪካን ምድር ሞተች። ስቬትላና እና ክርስቶፈር ሂችንስ እስትንፋሳቸው ልትቆረጥ፣ ሊሻገሩ ጠርዙ ላይ ቆመው፣ ማዶው ሲታያቸው፣ የተናገሩትን የሚያውቅ፣ ሲከታተላቸውና ፊቱን ብቅ ሲያደርግላቸው የኖረው፣ ጻድቅና መሓሪ አምላክ እግዚአብሔር ብቻ ነው። እግዚአብሔር ማዳኑን ለማስታወቅ የማይፈነቅለው ድንጋይ፣ የማይንደው ግንብ፣ የማያቋርጠው ባህር፣ ቀድዶ የማይወርደው ሰማይ የለም። እግዚአብሔር በመንገዱ ሁሉ ጻድቅ ነው በሥራውም ሁሉ ቸር ነው” [መዝሙር 145:17]። edited 4/23/17

ምንጭ፦ NPR / December 16, 2011; Stalin's Daughter / Sullivan, 2015