ርዕሰ አንቀጽ

እግዚአብሔር ። እና ቻይና

እንጀራ አምስት፣ በላተኛ መቶ አምስት ቢሆን። አማራጩ፣ እንጀራ መጨመር። ወይም በላተኛ መቀነስ ነው። ማን ይቀነስ? በምን ሚዛን? ሚዛኑ ቋንቋ ነው እንበል። በቋንቋ ይካለልና ቁጥሩ ከበዛበት ላይ በላተኛ ይቀነሳል ማለት ነው። በሚልዮኖች ሕይወት የተከፈለው የቻይና “አንድ ልጅ” ፖሊሲ ይህን ይመስላል።

የቻይና መንግሥት ከአንድ በላይ ልጅ መውለድ አልፈቅድም ሲል ከርሞ በ37 ዓመቱ ዘንድሮ ሁለት ይቻላል ብሏል። መካሪ አጥቶ ነው? እንጀራ ከመጨመር ይልቅ በላተኛ መቀነስ ተሽሎ ነው? ሕዝብ ኑሮው ሲሻሻል፣ የመንግሥት እጅ ሳይገባበት በራሱ ብዙ ልጆችን ላለመውለድ ይወስን አልነበረም? አዲስ አበቤዎች እንደ ወላጆቻቸው ብዙ ልጆች የማይወልዱት ለዚህ አይደል?

ከ37 ዓመት በኋላ የቻይና ሕዝብ በ400 ሚሊዮን መቀነሱ ታውቋል [ለዚያውም መንግሥት ከታመነ ነው]። ከዚህ መሓል 300 ሚሊዮኑ በ“ወሊድ ቁጥጥር”፣ በአስገድዶ ውርጃና ዘር በማምከን ያለቀ ነው። ቅነሳው በቁጥር ከበዙ ጎሣዎች ላይ ነው። ሦስት መቶ ሚሊዮን ሕዝብ። የኢትዮጵያ፣ የሱዳን፣ የደቡብ ሱዳን፣ የሶማልያ፣ የኤርትራ፣ የኬንያ እና የግብጽ ሕዝብ አልቆ ማለት ነው።

የቻይናውያንን ሰቆቃ እግዚአብሔር እና ቤት ይቁጠረው። ቁጭትና ተስፋ መቁረጥ። ተወልደው የተጣሉ ሴቶች። ያልተፈቀዱ ሁለተኞች። ለጉዲፈቻ የተሰጡ መዝገብ ያላወቃቸውና የትምህርትና የሥራ ዕድል ያጡት ቁጥር፣ የጂቡቲን የኤርትራና የሶማልያን ሕዝብ ብዛት ያህላሉ። የወንዱ ቁጥር ከሴቱ በ40 ሚሊዮን በመብለጡና ትዳር መመሥረት ስላልቻሉ ከአፍሪካ ማግባት ጀምረዋል። ያልነበሩ [የጤና፣ የዘረኛነት፣ ወዘተ] ማህበራዊ ቀውሶች እየታዩ ነው። አዛውንት ያለጧሪ ቀርቷል። መንግሥት በዘፈቀደ ያወጣው ህግ ውጤት ይህን ይመስላል። ፈርኃ እግዚአብሔር ያልገዛው መንግሥትና ርኅራኄ ቢስ አመራር ለሰው ሕይወት ዋጋ የለውም። ብልሹ አስተዳደር በአገራችን ያስከተለው ረሓብ፣ ስደት፣ ጦርነትና ድህነት፤ ከዕድሉ ያጓደለበት ትውልድ በ45 ዓመታት ውስጥ ብዛቱን ማን ይገምት? ማን ይጠየቅ? እንዴት ይካስ? በፈጣን ልማት ስም ብዙኃኑ ከዳር ቆሞ ተመልካች ተስፈኛ ስደተኛና ተመጽዋች የሚሆነው እስከ መቸ ነው? አንድ ነገር ግልጽ ነው። መንግሥት-ብቻ መራሽ የአንድን ሕዝብ ኑሮ ከፍ ሊያደርገው አይችልም።

በ1968 ዓ.ም. የሞቱት የቻይና መሪ ማዖ ጼቱንግ ‘የሕዝብ ብዛት ኃይል ነው’ ይሉ ስለነበር የወሊድ ቁጥጥሩ ዕቅድ እርሳቸው እስኪሞቱ መቆየት ነበረበት። ማዖ በርኅራኄ የሚታወሱ መሪ አልነበሩም። የሚታወሱት ዓለም አቀፋዊ አብዮት ለማጧጧፍ “እስከ ሦስት መቶ ሚሊዮን ሕዝብ እንማግዳለን …” በማለታቸው ነበር። “ሞት ለማዳበሪያነት ጠቀሜታ አለው … የሚበላ ሲጠፋ … ገሚሱ ጠግቦ እንዲበላ ገሚሱ ማለቅ አለበት” ይሉ ነበር። ከ1942 እስከ 1945 በተካሄደው የኮሪያ ጦርነት ለምሳሌ፣ አሜሪካኖች ከደቡብ ኮሪያ፣ ቻይና ከሰሜን ኮሪያ ወግነው ነበር። ማዖ የአሜሪካኖችን ምሽግ ያስለቀቁት ግማሽ ሚሊዮን ሕዝብ ማግደው የአሜሪካኖችን ቦምብና ባሩድ በማስጨረስ ነው።

ሰው ለሰው አክብሮት የሚኖረው እንዴት ነው? ሰው ለራሱና ለሌላው አክሮት የሚኖረው እግዚአብሔር ሰውን በአምሳሉ መፍጠሩን ሲገነዘብ እና ፈርኃ እግዚአብሔር ሲገዛው ብቻ ነው። የእግዚአብሔር ፍርኃት ሲጠፋስ? መፍትሔው ማስተማር ነው፤ “ልጆቼ ኑ፥ ስሙኝ፤ እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችኋለሁ…አምላክህን እግዚአብሔርን ፍራ፤ እርሱንም አምልክ፤ በስሙም ማል” [መዝሙር 34:11፤ ዘዳግም 6:13]። መፍትሔው በኢየሱስ ክርስቶስ የተገለጸውን የፍቅርና የፍርድን የምሥራች መስበክ ነው።

ባለፉት 200 ዓመታት ቻይናን በወንጌል ለማዳረስ ጥረት ተደርጓል። እንግሊዛዊው ሐድሰን ቴይለር [በ1897 ዓ.ም. ሞተ] አንደኛው የወንጌል መልእክተኛ ነበር። ቻይናዉያኑ ጆን ሱንግ [በ1936 ዓ.ም. ሞተ]፤ ዋችማን ኒ [በ1964 ዓ.ም. ሞተ]፤ እና ሚንግዳዖ [በ1983 ዓ.ም. ሞተ]፤ ሁላቸውም ወንጌልን አገልግለው አልፈዋል፤ ፍሬአቸውም ዘልቆአል።

ማዖ የመሩት የኮሚዩኒስት ግንባር በ1941 ዓ.ም. ሥልጣን እንደያዘ ወዲያው ክርስትናን ለማስወገድ መንቀሳቀስ ጀመረ። እነ ዋችማን ኒን አሰረ፤ አማንያንን አሳደደ። የነበረውን ታሪክ ክዶ፣ ፍቆና ቀይሮ አዲስ ታሪክ ይኸውላችሁ አለ። ቤተክርስቲያንን ከፓርቲው የሃይማኖት ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ቁጥጥር ሥር አዋለ። “የራሳችንን በራሳችን” ብሎ ብሔረተኛ መመሪያ ወጣ። ክህደትን እያስተማረ፣ ከ57 ሺህ የሚበልጡ ቤተ እምነቶችን አደራጀ። ለሰባኪያን ሥልጠና፣ መታወቂያና ሥራ ሰጠ። ቀጥሎ፣ ይህ ይሰበክ፣ ይህ አይሰበክ አለ። የጌታ ምጽዓት አይሰበክ። የውኃ ጥምቀት በኮታ ይሁን። ለፓርቲና ለጦር ሠራዊቱ አባላት አይሰበክ። ከውጭ አገር መጽሐፍ ቅዱስና እርዳታ አይግባ። የመንግሥትን ፖሊሲ ከመደገፍ ውጭ ጥያቄ ማንሳት “ፖለቲካ” ነው፤ ወዘተ። ቤተክርስቲያን በጥልፍልፍ የጆሮ ጠቢ እርከን ታጠረች። ፍርኃት ነገሠ፤ መተማመን አልተቻለም። ወንድም ወንድሙን አሳልፎ ሰጠ።

ወንጌል ግን እንደ ሰደድ እሳት ተቀጣጠለ። ከሰባ አምስት ዓመት በኋላ፣ "አማኝ ነኝ" ማለት ያስፈራቸውን ሳይጨምር፣ የቻይና አማንያን ቁጥር የኢትዮጵያና የኤርትራን ሕዝብ ብዛት በልጧል። “ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም” [ማቴዎስ 16፡18]! የአማንያን ቁጥር ከ15 ዓመት በኋላ የኢትዮጵያን፣ የኤርትራን፣ የሱዳንን፣ የደቡብ ሱዳንን፣ የሶማልያን፣ የሯንዳን፣ የቡሩንዲን፣ የኬንያን፣ የኡጋንዳን ሕዝብ ያክላል ይባላል። ቻይና የሚመላለስ አርኪቴክት ወዳጄ እንደ ነገረኝ፣ በየቤቱ በውድቅት ሌሊት የሚካሄደው የወንጌል ሥራ ለጉድ ነው። ያመኑትን ከማጥመቁ በፊት መጋቢው በጉባኤ ፊት እንዲህ ይጠይቃቸዋል፦ “በኢየሱስ ታምናለህ?" አዎ፣ "በኢየሱስ ስላመንህ ነቀፋ፣ እስር፣ ሞት ሊደርስብህ እንደሚችል ተረድተሃል?” “አዎ!” ይህን ሲሉ ብቻ ያጠምቃቸዋል ብሎኛል። ዋጋቸውን ተምነዋልና መስዋእት ይከፍላሉ። ስንቶች ነን በእውነት ላይ የምንደራደር?

አገር መምራት ከሩቅ እንደሚያዩት ቀላል አይደለም። ለመሪዎች እንጸልይ። መሪዎች ሥጋ ለባሽ እንጂ አማልክት አይደሉም። አገር የሚመሩ፣ ፈርኃ እግዚአብሔር ሊገዛቸው፣ እንደ ቱሪኩ ከማል አታቱርክ እንደ ታንዛንያው ጁልየስ ኔሬሬ እንደ ማህትማ ጋንዲ ለሰው አክብሮት ሊኖራቸው፤ ቅንነት፣ ርኅራኄና አርቆ አስተዋይነት ሊገኝባቸው ይገባል። ከመሪዎቻችን በአርቆ አስተዋይታቸው የሚጠቀሱ ስንት አሉ? መሪዎች የሚደነግጓቸው ሕጎችና አፈጻጸማቸው የዛሬን ብቻ ሳይሆን የረጅሙን መተለም ይኖርበታል። በአመራር ላይ የሚሰየሙ በብቃታቸውና በቀናነታቸው እንጂ የሕዝቡን ሕይወት መለማመጃ እንዳያደርጉት መጠንቀቅ ያሻል። ሰሞኑን የታየው ሕዝባዊ ውዝግብ የመጥፎ አስተዳደር ውጤት ነው። ከእንግዲህ ኢትዮጵያውያን የመንግሥት እጅ አይጠብቁ፤ ያለ ዜጋ መንግሥት የለምና፣ ከባሰ ኪሳራ ለማዳን፣ ዜጎች ሁሉ ስለ አገራቸው ጉዳይ ያለ ፍርኃት ይጠይቁ፣ በቅንነት ይወያዩ፣ በሰላምና በትጋት ይሳተፉ። እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሁሉ ትልቅ ሥራ ይጠብቃቸዋል። 10/18/2016