የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአል

goodShepherd

ኢየሱስም በይሁዳ ቤተ ልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰብአ ሰገል። የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና እያሉ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። ንጉሡ ሄሮድስም ሰምቶ ደነገጠ፥ ኢየሩሳሌምም ሁሉ ከእርሱ ጋር፤ የካህናትንም አለቆች የሕዝቡንም ጻፎች ሁሉ ሰብስቦ ክርስቶስ ወዴት እንዲወለድ ጠየቃቸው። እነርሱም። አንቺ ቤተ ልሔም፥ የይሁዳ ምድር፥ ከይሁዳ ገዢዎች ከቶ አታንሽም፤ ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ መስፍን ከአንቺ ይወጣልና ተብሎ በነቢይ እንዲህ ተጽፎአልና በይሁዳ ቤተ ልሔም ነው አሉት። ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገልን በስውር ጠርቶ ኮከቡ የታየበትን ዘመን ከእነርሱ በጥንቃቄ ተረዳ፥ ወደ ቤተ ልሔምም እነርሱን ሰድዶ። ሂዱ፥ ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔ ደግሞ መጥቼ እንድሰግድለት ንገሩኝ አላቸው። እነርሱም ንጉሡን ሰምተው ሄዱ፤ እነሆም፥ በምሥራቅ ያዩት ኮከብ ሕፃኑ ባለበት ላይ መጥቶ እስኪቆም ድረስ ይመራቸው ነበር። ኮከቡንም ባዩ ጊዜ በታላቅ ደስታ እጅግ ደስ አላቸው። ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፥ ወድቀውም ሰገዱለት፥ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት። ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ በሕልም ተረድተው በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ሄዱ [ማቴዎስ 2፡1-12]።

በዚያም ምድር መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ። እነሆም፥ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፥ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ። መልአኩም እንዲህ አላቸው። እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ። ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ። ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ። መላእክትም ከእነርሱ ተለይተው ወደ ሰማይ በወጡ ጊዜ፥ እረኞቹ እርስ በርሳቸው። እንግዲህ እስከ ቤተ ልሔም ድረስ እንሂድ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንይ ተባባሉ። ፈጥነውም መጡ ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ። አይተውም ስለዚህ ሕፃን የተነገረላቸውን ነገር ገለጡ። የሰሙትን ሁሉ እረኞቹ በነገሩአቸው ነገር አደነቁ፤ ማርያም ግን ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ እያሰበች ትጠብቀው ነበር። እረኞችም እንደ ተባለላቸው ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ ተመለሱ [ሉቃስ 2፡8-20]።

በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና። በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል። ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ ነው። ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፥ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደ ሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል [የዮሐንስ ወንጌል 3፡16-21]