ቃጭል ለ ማ ሠ ር

bellingcat

ዐይጦች ከድመት የሚደርስባቸው ጥቃት ስላስመረራቸው ብልሃት ለመፈለግ ዝግ ስብሰባ አደረጉ። አንዱ እንዲህ እናድርግ ሲል፤ ሌላው፣ የለም እንዲህ ይሻላል ሲሉ ዋሉ። በመጨረሻ አንደኛው ተነሥቶ፦ “እስቲ አንድ ጊዜ ስሙኝ!” አለ፣ “ይህ ነገር እንዳከበዳችሁት ሳይሆን በጣም ቀላል ነው። እንደምታውቁት ጥቃት የሚደርስብን የጠላታችንን አመጣጥ ማወቅ ስላልተቻለን ነው። አመጣጡን ብናውቅ ሳይደርስብን ሮጠን ባመለጥን። ለዚህ መድኃኒቱ በመጀመሪያ ትንሽ ቃጭል ፈልገን መግዛት ነው፤ ከዚያ ጠላታችን አንገት ላይ በሲባጎ ማሠር ነው። ጎብለል ጎብለል እያለ ገና ከሩቅ ወደ ሠፈራችን ሲያቀና ቃጭሉ ቀድሞ ምልክት ይሰጠንና ሮጠን በየጒድጓዳችን እንገባለን” እንዳለ፣ የተሰበሰቡበት አዳራሽ ድመት በሚያስበረግግ ጭብጨባ ደመቀ።

ጭብጨባው ሲበርድ፣ ከዚህ ቀደም ድመት ጅራቱን ቀርጥፎት ያመለጠ ኮሳሳ ዐይጥ ተራውን ሊናገር ተነሣ። እያሳለው፦ “አሁን የሰማነው እርግጥ ግሩም ብልሃት ነው። ጓዱም እንደ ተናገረው ቃጭሉ ሊያስመልጥ ይችላል። ኧረ እንዲያው ለመሆኑ፣ ከመካከላችን ቃጭሉን ጠላት አንገት ላይ በሲባጎ የሚያስርልን ማን ነው?” አለ።

ሕጻናቱ ብቻ እየፈሩ መሣቅ ጀመሩ ...

ከ “ዘንድሮስ አልዋሽም” | © ምትኩ አዲሱ፣ 2002 ዓ.ም. | ገጽ 148 | "አፈታሪክ ከእንደገና" | Art credit: mythfolklore.net