እውነት ጋር እንዳንጋጭ

diogenes

ለእውነት ታማኝ አለመሆን በሐሰት መገበያየት ነው። በአሳብ የሚገበያዩ አጥብቀው እውነትን የሚሹ መሆን አለባቸው፤ በአሳብ ዙሪያ የሚወያዩ ከእውነት ጋር ከመስማማት ውጭ አማራጭ የላቸውም። አለዚያ በጨለማ ይንከራተታሉ።

አንደኛችን ያፈለቀውን አሳብ ሌላው ይዋሳል፣ በመረጃ ይሞግተዋል፣ ያጸናዋል፣ አክሎበት ያፋፋዋል፣ ወይም አዲስ ፈር ያስይዘዋል። ይህን በማድረጋችን፣ ለተጋረጡብን ፈተናዎችና የኅልውና ጥያቄዎች መፍትሔ እናገኛለን። በዚህ ሂደት ውስጥ ከኛ የላቀ እይታ ያላቸው እንዳሉ አንዘነጋም።

የኢትዮጵያን ታሪክ በተመለከተ ባህሩ ዘውዴን ወይም ሪቻርድ ፓንክኸርስትን አለመጥቀስ አይቻልም። በቲያትርና በቅኔ ጸጋዬ ገብረመድኅንን። በኪነ ጥበብ አፈወርቅ ተክሌን። በጥንታዊ የኃይማኖት ታሪክ ጌታቸው ኃይሌን፤ ወዘተ። ግለሰቦቹ ረጅም ዘመን ሠውተው ጥናት ሲያካሄዱ ኖረዋልና በክፍላቸው ባለ ሥልጣናት ናቸው።

የተመሠረተውን መነሻ አለማድረግ የታሪክን ሂደት ማናጋትና መዘንጋት ነው። ሁሌ አዲስ መሠረት ማነፅ፣ ኋላ መቅረትና ማባከን ነው። የባለ ሥልጣናቱን ሥራዎች ሌሎች ከጻፉት ጋር አናነጻጽርም ማለት አይደለም፤ ወይም በአዲስ መረጃ ብርሃን አንዳኝም ማለት አይደለም።

የተጀመረውን መሠረት ክደን ወይ አፍርሰን አዲስ የመገንባት ባህል የወላድ መኻን አድርጎናል። የቅርብ ጊዜ ታሪካችን፣ ተጀምረው ባላለቁ በደበዘዙ አሻራዎች ተዝረክርኳል። የአገራችን ቋሚ ችግር በአንድ መልኩ ሲታይ፣ አዲስ ግኝት ወይም ራእይ ማጣት ሳይሆን፣ የተዝረከረኩትን አሰባስቦ ፈር አለማስያዝ ነው! ባለፉት መቶ ዓመታት፣ በኃይማኖት መስክ ስንት ሁሉ የሚጋራው ሰማእት መጥቀስ እንችላለን? በብሔራዊ ስፖርትስ? በሴቶች መብትና አገራዊ ድርሻስ? በሙዚቃ? በአገር አስተዳደር? በንግድ ሥራ? በዘመናዊ ትምህርት? በምህንድስና? በምርምር? በባህላዊ መድኃኒት? ወዘተ። የእሴት ኮሮጆአችን ቀዳዳ በመሆኑ፣ መሠረት ያልያዙ፣ ራእይ የማይፈነጥቁ፣ ጧት ተገንብተው ምሽት ላይ የሚፈርሱ ጅማሬዎች በዝተዋል! ከቅርብ ዘመን መረጃ ስላጣን፣ ብዙዎቻችን በማናውቀው በረሳነው ባላጣራነው አንዳንዴም በተጨማመረ ደብዛዛ “ጥንታዊ” (አፈ) ታሪክ እንወዛገባለን። አጥርቶ እስካላወቀ፣ የሼኽ ኾጀሌ ታሪክ ለአዲስ አበቤ ምኑ ነው? ሕዝቡን ሳናስተምር፣ በድንቊርና አጥረን፣ ጥያቄ እናበዛለን፤ የእውቀት ተቋማት ተንኮታኲተው እያየን የማይመጣ መልስ እንጠብቃለን! በጥቂቶች ውዝግብ ሕዝቡን እናምሳለን!

እውነቱ በእኛና በወዳጆቻችን እጅ እንዳለ መስሎናል። እውነትን ለመጋራት፣ ካስፈለገም የያዝነውን ጥለን የሌሎችን ለማስተናገድ የሚበቃ ትእግስትና ትሕትና ይታይብናል? ያለ ትሕትናማ ቀድሞውንም እውነትን ማወቅ አይቻል!

አሁን የቸገረው፣ ማ ባለሥልጣን፣ ማ ጀማሪ፣ ማ አስመሳይ እንደ ሆነ ግራ ማጋባቱ ነው። ኢንተርኔት የማጭበርበሪያም መድረክ እንደ ሆነ ያልተያዘላቸው ብዙዎች አሉ። ከኢንተርኔት ቀፍፈው ባልተገባቸው ማእረግ፣ ባልተፈተሸ እውቀት፣ በዩቱብ አደባባይ ይንፈላሰሳሉ። በአጀብ ዕፅ እንጂ አይንቀሳቀሱም። የተዋሱበትን ምንጩን ይሸሽጋሉ። እውቀታቸው ቅንጥብጣቢ፣ እንደ ሙዝ ልጣጭ የዋሃንን አዳልጦ የሚጥል ነው!

በመቶዎች የሚቆጠሩ የአገር መሪዎች በአመራር ትምህርት ዲፕሎማ እንዳላቸው እንሰማለን፤ አገራችን ግን በብልሹ አስተዳደር (ወይም እንደ መንግሥት አባባል በ “መልካም አስተዳደር” እጦት) ትታመሳለች። ለዚህ ምክንያቱ ሦስት ነው፦ አንደኛ፣ ጥራትን መዝኖ የሚዳኝ፣ ብቊና የሚታመን አካል አለመኖሩ፤ ሁለተኛ፣ መመዘኛዎቹ ሁሉ አቀፍ ሳይሆኑ፣ በክልል የታገቱ መሆናቸው፤ ሦስተኛ፣ ብቃት የሌላቸው፣ ለአገር በማይመጥን፣ በክልል ኮታ ተገን ያልተገባቸውን ሥፍራ ስለያዙ ነው። በክልል የሚሸነሸን፣ ክልል የማይሻገር እውነት ምንጊዜም እውነት ሊሆን አይችልም።

እንደዚሁም፣ ከእንግሊዞችና ከመጻሕፍቶቻቸው ላይ እንዳለ የሚቀዱ እውነት ይፈታተናቸዋል። በወዳጆቻቸው አስተያየት የሚሞካሹ ደራሲያንም እውነት ይፈታተናቸዋል። የመጽሐፉን ይዘት ሳያጤኑ የሚያሞግሱ፣ አንባቢውን ለድንቊርና አሳልፈው በመስጠታቸው እውነት ይፈታተናቸዋል።

ከእውነት ጋር እንዳንጋጭ፣ እውነቱን ለይተን እንወቅ፤ ያወቅነውን እውነት ያለድንበር ያለፍርኃት እናክብር፣ እናስከብር። ከኛ የቀደሙ እንዳሉ አንርሳ። በማፍረስ ከመሠማራት ይልቅ የተጀመረውን እናጽና። እውነቱ መስዋእት የተከፈለበት ነውና፣ ከእኛም ይኸው ይጠበቅብናል! ይህን በማድረጋችን ወደ ብርሃን፣ ወደ ስምምነት እንቃረባለን!

photo credit: googleimages | ፎቶ፡ ዲዮጋን ግሪኩ