ልብ በሰበብ ይገለጣል

MBC sanctuary

ግንቦት ሃያ ሰባት 2011 ዓ.ም. ከቀኑ ሰባት ሰዓት ላይ ፕሬዚደንት ትረምፕ መክሊን ባይብል ቸርች ቭርጂንያ ጎራ ሊሉ ነው የሚል ወሬ ለመጋቢው ደረሰው። መጋቢው በወቅቱ ሥጋ ወደሙን ለሕዝቡ ሊያከፋፍል እየተዘጋጀ ነበር። ዝግጅቱን ወደ ጎን ትቶ ትረምፕን መድረክ ላይ ማስተናገድ ተያያዘ። መጽሐፍ ገለጠ፣ “እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር፥ ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ…” የምትለዋን አነበበ (1ኛ ጢሞቴዎስ 2:1-6)። ለፕሬዚደንቱ ጸለየ። ነገሩ ድንገት ይምሰል እንጂ ያልታቀደ አልነበረም።

አልቆየም፣ አድራጎቱ በምዕመን መሓል ቊጣና ቅሬታን አስነሳ። ትረምፕን የማይደግፉ አያሌ ነበሩና፤ ትረምፕ “ዕዳሪ መጣያ ከመሰለ ኋላ ቀር አገር መጡ” ያሏቸው ምዕመንም በብዛት በዚያ ነበሩ።

ለመሪዎቻችሁ ጸልዩ ይላል፣ ያረግሁት ያንን ነው አለ ፓስተሩ። የማይገኝ ዕድል እንዳያመልጥ አስቤ ነው አለ። ቅር የተሰኛችሁ ይቅር በሉኝ አለ። መግለጫ ደብዳቤ እለቱን ጽፎ በተነ።

እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ለመሪዎቻችሁ ጸልዩ ይላል (ሮሜ 13)። ግን ለምድራዊ መሪ ለመጸለይ፣ የሰማይና የምድር ጌታ ያዘዘውን ሥጋ ወደሙን ወደ ጎን ማድረግ ይገባል? ፕሬዚደንቱን ማስጠበቅ አይቻልም? በሕያው እግዚአብሔር ፊት መቆም ከአሜሪካ ሹም ጋር ከመታየት ጋር ይወዳደራል? ያንሳል? እነዚህ ተገቢ ጥያቄዎች ናቸው!

ፓስተሩ በወቅቱ አሳብ አልመጣለት ይሆናል፤ ሥጋ ለባሽ ነውና ፕሬዚደንቱን ማስጠበቅ ከብዶት ወይም አሳስቦት ይሆናል። በጸሎትና በወንጌል ማሳበቡ ግን በልቡ የነገሠውን አሳብ አልሸሸገለትም! በእግዚአብሔር ጉባዔ መሓል ጎራ ለይቶ መዋቀስና ማመኻኘትን አስከተለ። መፍትሔው ንስሃ ገብቶ ለወደፊቱ ጸጋን መለመን ብቻ ነው።

ሌሎች ቤተክርስቲያኖች በቭርጂንያ አልነበሩም ማለት አይደለም። መክሊን ባይብል ቸርች የተመረጠው ከፓስተሩ ዝናና ከሕዝቡ ብዛት የተነሳ ነበር። "የዚህ ዓለም ልጆች ለትውልዳቸው ከብርሃን ልጆች ይልቅ ልባሞች ናቸው" (ሉቃስ 16:8)! የአሜሪካ ፖለቲካ ሁሌ የሕዝብ ቀልብና ቊጥር እንዳነፈነፈ ነው። የሕዝብ ቊጥር በንዋይ፣ በምድራዊ ሥልጣን እና በዝና ይመነዘራል! በዚህ ስሌት፣ ቤተክርስቲያንም ቤተመንግሥትም ይጠቀማሉ፤ ይደጋገፋሉ። ስሌቱ ቅን፣ የጽድቅ፣ የክብር ነው ማለት እንዳይመስለን። ልብ የሠወረውን መግለጫ ሰበብ ነው!