ብ     ቸ     ኝ     ነ     ት

lonelygate

ብቸኝነት እንደ ረሓብና እንደ ጥም። በሰዎች መሓል ግንኙነት ሲቋረጥ ይበረታል፣ ግንኙነት ሲበጅ ይታገሳል። ብቸኝነት ያልነካው ዘመንና ማኅበረሰብ የለም። በበለጸጉ አገሮች እንዲያውም አምርሯል፤ ከሃምሳና ከስድሳ ዓመት በፊት በእድሜ ከገፉና ባል ወይም ሚስት ከሞተባቸው ጋር ይዛመድ ነበር። ዛሬ ከሃምሳ ዓመት በታች ያሉ ሚሊዮኖችን እያንገላታ። ችግሩ ተባብሶ የሚዋጥ ማስታገሻ ኪኒን ወደ መቀመም ተሻግረዋል። ብቸኝነትን በኪኒን። ብቻውን ኪኒን ሊውጥ! ቀማሚዎችም የችግረኛን ብዛትና ትርፋቸውን እያሰቡ ...

ስንቱን በኪኒን አክሞ ይዘለቃል?

ኦፒዖይድ ኪኒን፣ አደንዝዞ የብቸኝነትን ግዝገዛ እንዲያስረሳ ዕፎይታን እንዲቸር ታስቦ ነበር፤ ሕይወት አወደመ እንጂ አልጠቀመም። ብዙ ፈገግታና ፍንደቃ በቴሌቪዝን መስኮት አየን፣ “አሜሪካን አይዶል” ሲል “ኢትዮፕያን አይዶል” አሰኝተን የደረሱበት የደስታ ደረጃ ላይ ለመድረስ ተሰባበርን። ከሥር የጎዘጎዘውን ሐዘን አላየን፤ የምእራባውያንን ባህል በምኞታችን ልክ አሰፋን። ጠበል የማያስለቅቀውን ዐመል መሓል አዲሳባ ቆሞ ተመለከትን። ዋጋ እየከፈልን አለን።

እነሆ፣ ብቸኝነት እንደ ካንሠርና ኤይድስ፣ እንደ ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደዌ ስም ተመዝግቧል። የአእምሮ ህመም ጓዝ ጭኗል። ከአንደኛው ሳንገላገል ሌላኛው በሩን በርግዶ ገብቶ። ቴክኖሎጂ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከደጅ የሚታሠር አጋሰስ ነበር፤ ዛሬ የመግቢያ ቊልፍ ተረክቦ ቤተኛ ሆኗል፣ ብዙዎችን እስረኛ ግዞተኛ አርጓቸዋል።

ፌስቡክ ከመሠረቱ ሲፈጠር ሱስ እንዲያስይዝ ታስቦ ነው፤ ዩቱብ ቅጭል ሲል አንዲት ሳንቲም ጠብ እያረገ ስንቱን ጀግና አንበርክኮ! ከነስሙ ሱስ። ሱስ መያዝ ቀላል፣ መላቀቁ ሕይወት አስከፍሎ! ከዘመድ አቆራርጦ! እንደ ቀንድ አውጣ ስብእናን ከሆድ ቀብሮ!

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰማንያ አምስት በመቶ ያህሉ፣ እድሜው ከአርባ ዓመት በታች ነው። አብዛኛው ሥራ አጥ ነው። ቴክኖሎጂ በአፅናኝ ተመስሎ ብቸኝነትና ግልፍተኛነትን ለቅቆበታል። የሚጠራጠሩ ድረገጾችና ኢንተርኔት ቲቪ ይዩ። ድሮ መቊጠሪያ ነበር በእጅ የሚያዝ፤ ወይም መስቀል(ተሰላጢን)፣ ነፍጥ፣ የውሃ ቅል፣ መሀረብ፣ ጃንጥላ፣ ሸንኮራ አገዳ፣ ሽንብራ እሸት፣ ዳማከሴ፣ ጥዋ፣ ወይም ወንጌል። ዛሬ ሴልፎን ኖክያ ሳምሶን(ግ) አይፎን ሞባይል ታብሌት ኋዌ ካልያዘ ደጅ አይወጣም! ባዶ እጅ እርቃን ይመስለዋል፤ (አብሮነት መሸርሸሩን እንጂ ቴክኖሎጂ አይጠቅምም አይደለም!)

ሰው ማኅበራዊ ፍጡር ነው፤ ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ ረዳት አስፈለገው (ዘፍጥረት 2፡18) ከፈጣሪው ጋር፣ ከአምሳያው ጋር እንዲኖር ተበጀ። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ይለናል፣ “ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ። ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፥ እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተክርስቲያን እላለሁ ... እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው ... ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን። ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን፤” (ወደ ገላትያ 2፡20፤ ኤፌሶን 5፡31፣32፤ ወደ ሮሜ 6፡4፣5) ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ያመኑት ናቸው።

ሰው ትዳር ስለያዘ ከብቸኝነት ይላቀቃል ማለት አይደለም። በአንጻሩ፣ ትዳር ስላልመሠረተ ከሕይወት ጎድሏል ማለት አይደለም። ከእግዚአብሔር ጋር ከታረቀ፣ በክርስቶስ ማኅበር ከታቀፈ፣ የክርስቶስ አካሉ ነውና ያ ሰው በክርስቶስ ሙላት ሙሉ ነው! እግዚአብሔር ትዳርን ሲመሠርት ይህን ታላቅ ምሥጢር ለመግለጽ ጭምር ነው!

የአማኞች ማኅበር (ኦርቶዶክስ ይሁኑ ወንጌላውያን) ፈጥነው የብቸኝነት ሰለባ እየሆኑ ነው! በጎሳ ብቸኝነት፤ በቋንቋ ብቸኝነት፤ በኃይማኖት ብቸኝነት፤ ግለኛ፤ ብቸኛ። መሪዎችና ምዕመን ሴልፎን ላይ በቀን ምን ያህል ጊዜ ከማን ጋር ምን እየሠሩ ያጠፋሉ? ምዕመን ሲታደም፣ በር ላይ ሴልፎኑ ተለቅሞ ቢፈተሽ የሰው ውሎው ምን ይመስል ይሆን? ያለ ቴክኖሎጂ ሽፋን ማምለክ ባዕድ ሆኖብን ይሆን? ቤተክርስቲያን የቴክኖሎጂን ጥቅም ብቻ ሳይሆን የማራቆት ኃይሉንም ሳትፈትሽ ምስክርነቷን ማጥራት አትችልም! በሴልፎን የፈረሰ ትዳር ቊጥሩ ምን ያህላል? ስንቱ መድረክ ባሜሪካኖች ቲቪ ትርዒት ተቀላልሟል? የማኅበር አምልኮ መልክ ያላቸው ብዙዎች፣ በብቸኝነት ይወዛወዛሉ፤ ኃይሉን ክደው፣ ግርግር ይፈጥራሉ። አእምሮአቸውን ለሚያባክን በራሪ መንፈስ ይከፍታሉ። “ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለ ሆነ፥ እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ። እውነትንም ከመስማት ጆሮቻቸውን ይመልሳሉ፥ ወደ ተረትም ፈቀቅ ይላሉ።” (2ኛ ጢሞ 4፡3፣4) በጸጋም ይራቆታሉ!

መንግሥት አልፎ አልፎ ኢንተርኔት መዝጋቱ መተዳደሪያ ለሆናቸውና ለመብታቸው ለሚቆረቆሩ ኪሳራና ራስ ምታት ሆኖባቸው ይሆናል። ምታቱ እንደ ቡና፣ ሱሱ ስለ ተቋረጠ ጭምር ይሆን? መቋረጡ የኖረ አብሮነታችንን በአክብሮት እንድንይዝ ይረዳ ይሆን? ያላየነውን ናፍቀን ብቸኛ ተንከራታች ከመሆን ያላቅቀን ይሆን? ቴክኖሎጂን በሚዛን መጠቀም እንማር ይሆን?

ምትኩ አዲሱ

ነሐሴ 22/2011 ዓ.ም.