"ለ መ ቶ  ሚሊዮን የአገሬ ሕዝብ"

ethflags

ፎቶው መስከረም 21/2012 ዓ.ም. ዶሓ ካታር በተካሄደው ዓለም አቀፍ ስፖርት ውድድር ላይ ሦስት ዓይነት ባንዲራ ይዞ የወጣው ደጋፊ ፎቶ ነው። (ልሙጡ ባንዲራ፣ ባለ ኮከብ የህወሓት/ኢሕአዴ ባንዲራ፣ እና የኦነግ ባንዲራ።) የደጋፊው አኳኋን በእለቱ የስታዲዮሙን ታዳሚ ቀልብ ስቦ ነበር። ፎቶውን ያነሳው የ ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጠኛ ነው። አትሌቶቹ አንድ፣ ደጋፊዎቹ የኢትዮጵያውያንን መከፋፈል አደባባይ አወጡት፣ በሚል ርእስ ዘግቧል። ዘገባውን እንዲያጠናክርለት ከደጋፊዎች መሓል የአንዳንዶችን አስተያየት አያይዟል።

አብዛኛዎቹ ሯጮች ኦሮሞ መሆናቸው አዲስ ነገር አይደለም። አበበ ቢቂላ፣ ማሞ ወልዴ፣ ቶሎሳ ቆቱ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ደራርቱ ቱሉ፤ ወዘተ። የኦነግን ባንዲራ ያነገቡት ይህንኑ ለማጒላት ሞክረዋል። የ10 ሺህ ወርቅ ተሸላሚ ሲፋን ሃሰን ዜግነት ደች (ሆላንድ) ቢሆንም የአገራችንን ብሔራዊ ባንዲራ አለማንገቧ አንዳንዶችን ቅር አሰኝቷል (የሆላንድ ዜግነት ወስዳ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ማንሳት መታሰቡ?! መረጃ የማይቀበል ጭፍን ወኔ ይኸውላችሁ!)። የ5 ሺህ ሜትሩ ጀግና ሙክታር ኢድሪስ ያቀበሉትን የኦነግን ባንዲራ ጋዜጠኛ ጋ ሲቀርብ ጥሎ ባለ ኮከቡን አንስቷል። (በአንጻሩ፣ ሌሊሳ ደሲሳ ከሁለት ቀን በኋላ ማራቶን ሲያሸንፍ “ይኸ ድል ለመቶ ሚሊዮን የአገሬ ሕዝብ ነው!” ብሎ አውጇል።) ተባባሪ ጋዜጠኛ ኤልያስ መሠረት (ኒዮርክ ዴይሊ ንዩስ) ስፖርቱን ከጎሳ ፖለቲካ ጋር በማያያዝ ባለፈው ሳምንት ብቻ ከአንድ ሺህ አንድ መቶ በላይ ሰው መገደሉን ጨምሮ አትቷል። ይህ ለምን እንዳስፈለገ ግልጽ አይደለም!

ሦስት ጒዳዮችን እናስምርባቸው። ማንም አሳቡን እንዳይገልጽ መከልከል የለበትም፤ ለራሳችን የምንሰጠውን ነጻነት ለሌላው መንፈግ ተገቢ አይደለም። ሁለተኛ፣ በጅምላ ማውገዝ መቆም አለበት፤ ኦሮሞ ወይም አማራ ወይም ሲዳማ ሁሉ አንድ ወጥ እንደሆነ መታሰቡ አግባብ አይደለም፤ በስሜት ብቻ መነዳት እውነቱን ያዛባል። ሦስተኛ፣ አገራዊ ቊምነገሮችን ለይቶ አለማወቅ፣ ዛሬ የምንወስዳቸው እርምጃዎች በዛሬና በነገ ትውልድ ላይ የሚያሳድሩትን ተጽእኖ መዘንጋት ነው። በጥቃቅኑ ጊዜና ጒልበት ማባከን ነው።

ዋሽንግተን ፖስትና ሌሎች ጋዜጦች ከላይ የሚታየውን እንደ ጒድ መዘገባቸው ሊገርመን አይገባም። ጋዜጦች (ሰዎች ሁሉ) ከጦርና ከጦር ወሬ፣ ከጎርፍና ከምድር መናወጥ፣ ከገንዘብ፣ ከዝሙትና ከወንጀል የተሻለ ለጆሮ የሚጥም ቀልብ የሚስብ ትርፍ የሚያስገኝ እንደሌለ ካወቁ ሰነባብቷል! ይኸም በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በምድር ዙሪያ የሚታይ እውነት ነው። በኢትዮጵያ፦ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ እያልን ነው። በአሜሪካ፦ ነጭ፣ ጥቊር፣ ስደተኛ። በእንግሊዝ፦ እስልምና፣ ነጭ እንግሊዝ፣ የአውሮጳ ኅብረት። በቻይና፦ እስልምና፣ ክርስትና፣ አሜሪካ፣ ሆንግ ኮንግ፣ የአየር ጤና መበከል፣ ሙስና። በግብጽ፦ እስልምና፣ ሙስና፣ ዲሞክራሲ። በህንድ፦ ሂንዱ፣ እስላም፣ ፓኪስታን፣ ዳሊት። በየአገራቱ የሚታየውን ማስተዋል የኢትዮጵያን ሁኔታ ያለ ቅጥ ከማጋነን ያድነናል! የማጋነናችን ብዛት፣ ከኛ የተሻለ ድሃ የለም ማለት ይቃጣናል! ባጭሩ፣ ትክክለኛ መረጃ አለማግኘት ለተንጋደደ አመለካከት ዳርጎናል!

ከላይ ፎቶውን ይመልከቱ። ምን ይታዘባሉ? ሀ/ ሦስቱን ዓይነት ባንዲራ ያነገቡት አንድ ላይ ተቀምጠዋል፣ ለ/ በመልክ ይመሳሰላሉ፣ ሐ/ በቋንቋ ይግባባሉ፣ መ/ በአበላል ይመሳሰላሉ (ክትፎ ይቅረብላቸው? ጠላ? ቆሎ? እንጀራ? ገንፎ? ሠ/ በአለባበስ ይመሳሰላሉ (ጋቢ ይደርቡ? አጎዛ ይነጠፍላቸው? እንግዳ ያስተናግዱ?)፣ ረ/ ሁላቸውም ተሰድደው ወይም በሥራ ባዕድ ምድር ተሰባስበዋል! ወዘተ። ተመልካች እስከማይለያቸው ድረስ ይመሳሰላሉ፤ መመሳሰላቸው ግን አንድ ወጥ አያደርጋቸውም!

ፎቶውን አንዴ ይመልከቱ። የሦስቱም ባንዲራዎች ንጣፍ፣ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ነው። የኦነግም አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ነው፣ የህወሓት/ኢሕአዴግም፣ ልሙጡም! በሌላ አነጋገር ሦስት ይምሰል እንጂ ባንዲራው አንድ ነው። ችግሩ የመነጨው ከአመለካከት ነው፤ እኔ ያልኩት ካልሆነ ከማለት ነው። ከአመለካከት መዛባት ነው። አንዱ ሌላውን ለማንበርከክ ቆርጦ መነሳቱ ነው። ውጤቱ ሥራ መፍታት፣ በከንቱ ዘመንን መፍጀት ነው።

የሚያየው፣ ማየት የሚፈልገውን ነው! አንድነትን ሳይሆን ልዩነትን እንከንን ማየት ይቀናናል። ቅድም እንዳልነው፣ ሽብር፣ ዘረፋ፣ ዝሙት እና የመሳሰለው ከሰላምና ከአብሮነት ይልቅ ቀልብ ሳቢ ነው። በሌላ አነጋገር፣ አንዲት ሐረግ ተመዝዛ ሁሉን እንድታቀልም መደረጉ የተጋነነና የተንጋደደ አተያይ እንደ ፈጠረ እንመለከታለን። ብርሃን እያለልን ጭለማ ጭለማውን ማለት መታወር ነው። በቂ መረጃ በሌለበት ልብ በጥላቻ ይታሠራል። ባለቅኔው እንዲህ ብሎናል፣

ድንግል ጽጌ-ረዳ ፈልቃ | ፍልቅልቂት ድምብል ቦቃ …
ተንሠራፍታ የአበባ ጮርቃ | ታድያን ብሌኑ የጠጠረ
ባሕረ-ሃሳቡ የከረረ | የውበት ዓይኑን የታወረ
ልበ-ሕሊናው የሰለለ | አይ፥ አበባ አደለም አለ፤
አይ፥ እሳት አደለም አለ | ያልታደለ። …
ሰማይ ጨለማ ነው እንጂ፥ እሳት አደል ብሎ ካደ
እቶን ባይኑ እየነደደ። [ጸገመ | “እሳት ወይ አበባ” 1999 ዓ.ም.፣ ገጽ 139-140]

+ + + +

ባንዲራ በዝቷል የሚሉ አሉ። በኔ አስተያይ ባንዲራ አንሷል። ሁሉ የሚጋራው ልሙጡ ባንዲራ የሁሉም መሠረትና በዓለም ፊት መታያችን ነው፤ ከኛ አልፎ ሌሎች አገሮች የኮረጁት ነው። በልሙጡ ላይ የአክሱም ሐውልት፣ የፋሲል ግንብ፣ የአባይ ድልድይ፣ ሊማሊሞ፣ ዳሎል ተለጥፎ ለሰሜን ቢውል ችግሩ ምኑ ላይ ነው? በልሙጡ ላይ ባሮ ወንዝ፣ ህዳሴ ግድብ፣ አባይ ወንዝ ተለጥፎ ለምዕራብ። ለደቡብ፣ አዋሽ ወንዝ፣ እንሰት፣ ሽመና። ለምሥራቅ፣ ስፌት፣ የሐረር ግንብ፣ ጥንድ ጎራዴ። ለመሓል አገር አበበ ቢቂላ፣ ጥማድ በሬ፣ ቡና፣ ወዘተ፣ ወይም ሌላ ሌላ የተስማማ ምልክት ቢደረግ?

በግልጽ የሚታየውን አለማየት፣ ዐይኔን ግንባር ያርገው ማለት ልማድ ሆኖብናል። ልብ በጥላቻና በእልኽ ሲያዝ ዐይንና ሕሊናን ያሳውራል። ሰማይ ብርሃን ተሞልቶ ጨለማ ነው ይላል! የማጋነን መፍትሔው አለማጋነን ነው፣ የታመነ መረጃ ይዞ መወያየት ነው። እውነቱ ካልታየን ደግሞ፣ ግልጽ እስኪሆንልን ደጋግመን ማየት ነው። ደጋግመን የምናስበውና የምናደርገው ያ ሱስ ይሆንብናል። ብዙዎቻችን በጥላቻና በእልኽ ሱስ ተጠምደናል። መውጫ ከመሻት ይልቅ ተበክለን ሌሎችን እንበክላለን!! ለመሆኑ፣ ዋነኛ አድርገን ከምንጋደልባቸው አንዳንዶቹን ጉዳዮች ችላ ብንላቸው አሁን ከምናየው የባሰ ምን ይመጣል?!

ዋሽንግተን ፖስት እና ኤልያስ መሠረት የዘገቡት ዜና የተጋነነ፣ እነርሱው የፈጠሩልን ማንነት ስለሆነ እውነቱን አይወክልም! ለአገራችን ደህንነት ለሰላማችን ለአብሮነታችን ስንል እምቢ ማለት መብትና ግዴታችን ነው!

ምትኩ አዲሱ

መስከረም 27/2012 ዓ.ም.

ቀላሉን መንገድ | የማለዳ ድባብ | ከየት ተገኘሽ ሳልል | ቋንቋን በቋንቋ | ስደተኛውና አምላኩ | ሞት እና ፕሮፌሰር