በእውነት ላይ ተደራድሮ አንድነት? እውነት ምንድነው?

JesusPilate

ወንጌላውያንን በአንድ ጥላ ሥር ለማሰባሰብ መንግሥት ጥረት ማድረጉን ቀጥሏል። ወንጌላውያኑ የመንግሥት እጅ ሳይገባበት በራሳቸው መሰባሰብ አለመቻላቸው አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን ምን ያህል በመሠረታዊ አስተምህሮ ዙሪያ ስምምነት እንደ ጠፋ ያስረዳል። የሚያስማማ ግለሰብ ወይስ ሐዋርያዊ አስተምህሮ ይሁን? ተቋማዊ አንድነት ወይስ የመንፈስ/የአስተምህሮ ስምምነት ይቅደም? ይቅር መባባልና መታረም ወይስ በድፍኑ “አንድ” መሆን ይቅደም? ጌታ ማን ነው? ኢየሱስ? የተቀቡ ግለሰቦች? ወይስ መንግሥት?

የወንጌላውያን መሠነጣጠቅ ዓይነቱ ይገርማል። ሲጀመር “ዲኖሚኔሽን” የሚሲዮናውያን ታሪካዊ ድርሻ አለበት። የሚሲዮናውያኑ ትኲረቱ የመልክዐ ምድርና የቲኦሎጂ ድንበር ማበጀት ላይ ነበር፤ ደቡብ (ኤስ አይ ኤም)፣ ምዕራብ (ሉተራን)፣ ጥምቀት፣ መንፈስ ቅዱስ፣ ምጽኣት፣ ወዘተ። ሁለተኛው ዙር፣ የስድሳ ስድስቱ አብዮት ያስከተለው ስደት የፈጠረው አንድነት ነው፤ በእሳት የተፈተነ አንድነት፤ የዲኖሚኔሽንን አጥር ያፈራረሰ፣ ኢየሱስን ያገነነ አንድነት። በአንድ ትውልድ ተበተነ ይሆን?

“ዲኖሚኔሽን” ውጭ የኖሩ ኢትዮጵያውያን ድርሻም አለበት። ከአገር ውጭ ለሚኖረው ሕዝብ እየተመላለሱ አገልግሎት የሰጡ አገልጋዮች ድርሻም አለበት፤ ከእነዚህም የየራሳቸውን "ሚኒስትሪ" የጀመሩ አሉባቸው። ከእነዚህም “አገልግሎት” የሚያስገኘው ገቢ እንዳይቀርባቸው ለሰሚው ጆሮ የሚስማማ ትምህርት/ትንቢት ሲቀልቡና ሲያተራምሱ የኖሩ አሉባቸው። በልምምድና በትንቢት ነፋሳት የተበተነን መሰብሰብ ቀላል አይደለም፤ የዘራነውን እያጨድን ነዋ!

አገልግሎት ሲባል ባብዛኛው አሜሪካ እንዳለው ዓይነት ነው። ይኸ በራሱ ምንም ክፋት የለበትም። ሆኖም “ሚኒስትሪ” ከነባሩ ጋር ከመሥራት ይልቅ በየራስ መቋቋም እንደሚቻል መንገድ ከፋች ሆነ። አገልግሎት በክልል ፖለቲካ ቀለበት ውስጥ ገባ። የ "ፕሮፌቶች" አገልግሎት ባብዛኛው ከደቡብ መሆን ትርጓሜው ምን ይሆን? የኦሮሞ "ፕሮፌት" ከአማራውና ከትግሬው የሚለይበትን ያመሳከረ ይኖር ይሆን?

የሰው ብዛትና የገንዘብ ብዛት የተያያዘ መሆኑን የተመለከቱ የየራሳቸውን "ሚኒስትሪ" እያበጃጁ ተለይተው ወጡ። አብዛኛው ምዕመን ወጣት መሆኑ በትውልድ መሓል ክፍተትን ፈጠረ። ቴክኖሎጂ የአገልግሎትን መልክ (በተለይ አምልኮና ዝማሬን) ቀየረው። ቴክኖሎጂ ወንጌልን ለማዳረስ ብቻ ሳይሆን እውነቱን በማጋነን ወይም በማስቀረት ተመልካቹን ማባበልና ማታለል እንደሚቻልም መሰከረ። “ሚኒስትሪ፣ ሕዝብ ቊጥር፣ ገቢ” ዋነኛ ትኲረት ባገኘበት፣ ዶክትሪን፣ ቅድስና እና ደቀመዝሙርነት መላላቱ አይቀርም! የሆነውም ይኸው ነው! ቴክኖሎጂ ቤተክርስቲያንን አየር ባየር አረጋት! ከላይ እስከ ታች የተቀደደውን መጋረጃ እንደገና ሰፍቶ ቅድስናን ሠወረ!

ከዶ/ር ዐቢይ በፊት ህወሓት/ኢሕአዴግ በኦርቶዶክሱም፣ በጴንጤውም፣ በሙስሊሙም መሓል የራሱን ወኪሎች ተክሎ ሲንቀሳቀስ ነው የኖረው። ለህወሓት/ኢሕአዴግ ፖሊሲ ድጋፍ የሚሰጡ ነቢያት ነበሩ፤ ዛሬ ለ “ወንድም” ዐቢይ ማድላት ይዘዋል። ሕዝብ ሲገደል እግዚአብሔር ሽብርተኞችን ገለጣቸው ይሉ የነበሩ ናቸው። ረብሻ እና ረሓብ ሆኖ “ሰላም ነው፣ የከፍታ ዘመን ነው” ይሉ የነበሩ ናቸው። “የከፍታ ዘመን” ያልተባለ አዲስ ዘመን አልነበረም! መጽሐፍ ቅዱስ ት/ቤት ከገባው አንዳንዱ ዓላማው የመንግሥትን ዓላማ ማራመድ ነበር። የዚህን ስልት አጀማመር ዶ/ር አረጋዊ በርሀ በ “ኤ ፖለቲካል ሂስትሪ ኦፍ ዘ ትግራይ ፒፕልስ ሊበሬሽን ፍሮንት” መጽሐፋቸው (ከገጽ 300 ጀምሮ) አስፍረውታል።

ዶ/ር ዐቢይ በኦርቶዶክስ አማንያን መሓል የተከሰተው መሠንጠቅ ለመቆሙ ምክንያት ሆነዋል። የሚያስተራርቊ ብጹዓን ናቸው፤ እግዚአብሔር ይባርካቸው። በሙስሊሙም መሓል። አሁን ደግሞ በፕሮቴስታንቱ መሓል እየሞከሩ ነው። በህወሓት/ኢሕአዴግ ዘመን ዝም ብለው ተስማምተው የኖሩ ፕሮቴስታንት መሪዎች ዛሬ በአደባባይ የሚያሰሙትን እና የሚሆኑትን ማየት ይልቅ የሚያስተዛዝብ ነው።

ፕሮቴስታንቱን አንድ ማድረግ ኦሮቶዶክሱን እና ሙስሊሙን አንድ ከማድረግ ከብዷል። ኦርቶዶስክሱ ሲከፋፋ ቢውል አንዲት እናት የአበው ቤተክርስቲያን ወላዲት አምላክ አለችኝ ይላል። ሙስሊሙም ነቢዩ፣ ቊርዐንና መካ ይላል። ፕሮቴስታንቱ በነፍስ ወከፍ ነው፤ ለአንዱ “እንደ ተሰማው” ነው፤ ለሌላው “እንደ ሐዋርያ እከሌ፣ እንደ አሜሪካ፣ እንደ ነቢዪት እከሊት” ነው። ለሌላው “ማምለክ ብቻ፣ ፍቅር ብቻ፣ ስለ ሌላው ምን አገባኝ” ነው፤ ለተቀረው “እንደ ቃሉ፣ እንደ ተሃድሶ ንቅናቄ አስተምህሮ” ነው።

በዚህ ሁሉ የሚድኑ አሉ። የጌታ ፍቅር፣ ኃያልነቱ፣ ትእግስቱ፣ ጥበቡንና ቸርነቱ አስገራሚ ነው!

ሁለት ዓይነት፣ ሁለት እርከን መሪነት ይታያል። ነባሮቹ መሪዎች፣ እዚህ ያደረስን እኛ ነን የሚሉ፤ ሌላው ሁሉ እንዲታዘዛቸው የሚሹ፣ ቀጣዩ ትውልድ ኃላፊነት እንዲረከብ ሳያዘጋጁ የቀሩ። የአዲሱ ትውልድ መሪዎች ደግሞ አሉ፣ ነባሮቹን የሚቀናቀኗቸው፤ የተከታዮቻቸውን እና የገቢአቸውን ብዛት እያራገቡ ያለ እናንተም እንቆማለን የሚሉ፣ ከነባሮቹ መሓል ድጋፍ ያገኙ፤ የሚያዝዛቸው የሌለ በየሁኔታው፣ በየሄዱበት አቋማቸውን ማስተካከል የተቻላቸው፣ በእግዚአብሔር መንፈስ የሚያመካኙ ናቸው፤ እነርሱን መያዝ ንፋስ እንደ መያዝ ነው።

ዶ/ር ዐቢይ የሚያደርጉት ሙከራ አንዳንድ መሪዎችን፣ አብያተክርስቲያናትን፣ ሚኒስትሪዎችን ሳያገልል አይሳካም። ለአንድነት ሲባል ሥልጣን መልቀቃቸው የማይታያቸው አሉ። የካቲት 16/2012 ዓ.ም. በተጠራው ስብሰባ ላይ ለምሳሌ፣ መጋቢ ጻዲቊ እና ቄስ በልእና ለ “አዲስ ወንጌላውያን” ያላቸው አመለካከት የተራራቀ እንደ ሆነ በግልጥ ታይቷል። ሁለቱ ግለሰቦች ራሳቸውን ቢያገልሉ ስምምነቱ ይፋጠን ይሆን? መሪ ወይስ ዓላማ ይቅደም?

ለመሆኑ፣ ዶ/ር ዐቢይ ፕሮቴስታንቱን አንድ ለማድረግ ለምን ፈለጉ? ለምን አሁን? እግዚአብሔርስ የተወሳሰበውን የሚያጠራው እንዴትና መቸ ይሆን?

ምትኩ አዲሱ

የካቲት 25/2012 ዓ.ም.

Photo credit: Christ in Front of Pilate (1881), by Mihály Munkácsy (1844-1900) [public domain / Wikimedia Commons]