ጥቃቅን ናቸው ጥቃቅን አይደሉም

የእግዚአብሔር ቃል እንደ መሆኑ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ግድፈት ይገኝበታል ተብሎ አይታሰብም። ከሞራል ስሕተትና ከቋንቋ ወለምታ የምንታረምበት ስለሆነ ከግድፈት ነጻ መሆኑ ግድ ነው። የሆሄያት ግድፈት ሲገኝ የሌለ ትርጒም ይጨምራል፣ የታሰበውን ትርጒም ያጨናግፋል። አታሚዎች አርታኢዎች ፊደል ለቃሚዎች ተያቢዎች አንባቢዎች ሰባኪዎች ብዙ ጥንቃቄ ማድረግ የሚኖርባቸው፣ የእግዚአብሔር ቃል ከሌሎች መጽሐፍት ይልቅ በሕይወት ጒዳይ ሙሉ ሥልጣን ስላለው ነው። ተኣማኒ ስለሆነ ለሚሰሙትና ለሚያነብቡት ተኣማኒነትን ያጎናጽፋል። ባለሙሉ ሥልጣን ስለሆነ በሚታዘዙትና በማይታዘዙት ላይ ዳኝነቱ ፍጹም ነው።

ስለ “ቃል” ጥቂት እንበል። 1/ እግዚአብሔር “ይሁን!” አለ (ዘፍጥረት 1፤ መዝሙር 19። 147:15)፤ ቃሉም ዓለማትን ካለመኖር ወደ መኖር አመጣቸው። 2/ ሰዎች ማንበብ መጻፍ ቢችሉ ባይችሉ ቃሉ በጉባኤ (በግልም) በጮኽታ መነበቡ የሚሠራው ሥራ አለው፦ “በየስፍራቸውም ቆመው የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን የሕግ መጽሐፍ የቀን ሩብ ያህል አነበቡ፤ ሦስት የቀን ሩብም ያህል ተናዘዙ፥ ለአምላካቸው ለእግዚአብሔርም ሰገዱ(ነህምያ 9፡3። ዘዳግም 31:11። ነህምያ 8:1-18፤ 9:3። 1ኛ ጢሞ 4:13። የሐዋርያት ሥራ 15:21። ቆላስይስ 4:16። 1ኛ ተሰሎንቄ 5:27)። ኢየሱስ አገልግሎቱን ሲጀምር በምኲራብ ቆሞ ከኢሳይያስ መጽሐፍ አነበበ (ሉቃስ 4:16-21)። “ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ? … ካልተላኩ እንዴት ይሰብካሉ? እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው” (ሮሜ 10: 15-17)። 3/ የእግዚአብሔር ቃል የኃይል ቃል ነው (1ኛ ተሰሎንቄ 2:13። መዝሙር 19። ማርቆስ 4:39። መዝሙር 107:20)፤ የጸጋ ቃል ነው፤ የሕይወት ቃል ነው (ዮሐንስ 1:1፤ 6:63። ማቴዎስ 4:4)፣ ፍጹም፣ ንጹሕ ጥልቅ የዘላለም ቃል ነው (መዝሙር 12:6። 1ኛ ጴጥሮስ 1:25፤ 2ኛ ጴጥሮስ 3:16)፤ ቅዱስና የሚቀድስ፣ እውነት ነው (ዮሐንስ 17:17። 2ኛ ጢሞቴዎስ 2:15)፤ የራስ ቊር፣ የመንፈስ ሰይፍ ነው (ኤፌሶን 6:17። ዕብራውያን 4:12)፤ የትንቢት፣ የምስክር ቃል ነው (ዮሐንስ 5:39። ራእይ 1:2፤ 22:19)፤ መመርመሪያ መመዘኛ ነው፤ እንደ መስተዋት ነው (ያዕቆብ 1:22-23። የሐዋርያት ሥራ 17:11)፤ የጽድቅና የተግሳጽ ቃል ነው (2ኛ ጢሞቴዎስ 3:15-17)፤ የጥበብ የእውቀት ቃል ነው (ቆላስይስ 3:16)

ዛሬ በራሪ ጥቅሶች ተበራክተዋል፤ ያለ ዐውዳቸው የሚጠቀሱ፤ የታሪክ መሠረት ያልተከተሉ። የቃሉን ስፋት ያላገናዘቡ፣ ለሰሚውና ለዓላማቸው በሚስማማ መንገድ ቃሉን መከለስ የሚያበዙ አስተማሪዎች ተበራክተዋል። የእግዚአብሔርን ቃል፣ ምእራፍ በምእራፍ፣ መጽሐፍ በመጽሐፍ በጒባኤ በተከታታይ ማንበብ በስንቶች አብያተክርስቲያናት ዘንድ ተለምዶ ይሆን? የእግዚአብሔር ቃል በራሱ ሙሉ እንደሆነ ተዘነጋን ይሆን? አስተማሪዎች አያስፈልጉም ማለት አይደለም። ቀድሞውንም አስተማሪዎች ያስፈለጉት ብዙዎቻችን የማንረዳቸው ክፍሎች ስላሉና መንፈስ ቅዱስ የአስተማሪነትን ጸጋ ስለ ሰጣቸው፤ ቃሉን ማጥናት የሚያስከፍለውን ዋጋ ለመክፈል ስለ ቆረጡ ነው።

ቃሉ ሲነበብ ግን በግልጽና ያለግድፈት መሆን አለበት። እርግጥ ጥቂቶች ግድፈቱን አቃንተው ማንበብና መስማት ይችላሉ እንበል። ብዙዎች ግን የሌለ ሆኄ ጨምረው ወይም ቀንሰው የሚያነብቡ ናቸው! የሆኄ ግድፈት እስከ መኖሩ ልብ የማይሉ፤ ትርጒሙን እንዳዛነፉ የማያስተውሉ አሉ። ትርጒሙ እንዳይዛነፍ ጥንቃቄ ማድረግ ያሻል። “ከእናንተ ብዙዎቹ አስተማሪዎች አይሁኑ ... የባሰ ፍርድ” ይጠብቃቸዋል ሲል፣ የሚያስተምሩትን እራሳቸው ካልኖሩበት ማለቱ ብቻ ሳይሆን፣ ቃሉን ቢያሰናክሉ ማለቱ ጭምር ነው (ሮሜ 2:21-22። ያዕቆብ 3:1)

termitehill

 

መጽሐፍ ቅዱሴን በአማርኛ ጮኽ ብዬ ሳነብና በሲዲ የተቀዳውን ሳደምጥ፣ የሆኄያት ግድፈቶች መደጋገም ስላሳሰበኝ ይህን ማስታወሻ ለመጻፍ ተገድጃለሁ። ግድፈቶቹ አማርኛ ሁለተኛና ሦስተኛ ቋንቋቸው ለሆነ፤ የትምህርት ጥራት በወደቀበት ዘመን ላደጉ፤ “መንፈሳዊነት” በአእምሮ አለማደግ በሚመስላቸው ላይ እና ተደማምሮ በቤተክርስቲያን ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ውጤቶችን በማሰብ ነው።

ግድፈቶች የሚያጸኑት ወይም የሚያስተላልፉት ዋነኛ መልእክት አለ፦ የመጀመሪያው ለስህተት ኃላፊነትን አለመቀበልን፣ በሌሎች ማላከክን ነው። “አስተካክላችሁ አንብቡልኝ፤ ከሰው ስህተት አይጠፋም፤ የማይሠራ ብቻ ነው የማይሳሳት፤ እከሊት ነች ታይፕ ያደረገችልኝ፤ በችኮላ ነው፤ ወዘተ።” ሁሉም ከተጻፈው ውጭ ለየራሱ ትርጒም ቢሰጥ ምንም አይደለም የሚል ይመስላል። በሌላ አነጋገር፣ ባለሥልጣን የለም ነው። ሁሉም ባለሥልጣን ነው ነው! ይኸ አስተሳሰብ በአገር ደረጃ ሲመነዘር ኪሳራው ጎልቶ ይወጣል። በአገራችን ታሪክ ላይ ለምሳሌ፣ የታሪክ ምሑራንን ሳይሆን የየመንደራችንን ትርክት አግንነው፣ የሌላውን አቃልለው የሚነግሩንን ያለ ጥያቄ መቀበላችን ያስከተለውን ውጤት እያየን ነው። በቤተክርስቲያን ውስጥ የምናየው ትርምስ፣ የተጻፈውን ከምንጩ ለራስ ከማንበብ ይልቅ አነበብን ከሚሉትና በሶሻል ሚዲያ ከሚሠራጨው ከማዳመጥ የመጣ ነው። በተለይም የተለያዩ አንባቢዎች መጽሐፍ ቅዱስን በኦዲዮ ቀርጸው ለማሠራጨት መቻላቸው የግድፈቶችን አሳር አባዝቷቸዋል።

ግድፈት አእምሮአቸው ለጋ ለሆነ ለእርምት የሚያስቸግር ቅጭት ነው። በአሁኑ ወቅት ግድፈት መደበኛ ባህል ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ ወረርሺኝ ነው። መረጃ የሚሹ የዩኒቨርሲቲዎችን ድረገጽ፣ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንን የመመረቂያ ጽሑፎችን፣ የህወሓት/ኢሕአዴግን ድረገጽ፣ አዲስ ዘመን እና ኢትዮፕያን ሄራልድ ጋዜጦችን፣ ወዘተ ይመልከቱ። ፓርቲ ምዝገባ ከግድፈት ነጻ በመሆን ቢሆን፣ ተቃዋሚ የሚባል አንድ ስንኳ በምድራችን አይገኝም! ዋነኛ የሃገር ተቋማት፣ መሪዎችና ምሑራን በዚህ ጉዳይ ካልተጠየቁ ሌላው ዜጋ በአምሳያቸው መብቀሉ ምን ይደንቃል? ይኸ ስለ ትምህርት ቤቶች አደረጃጀት፣ መሓላችን ስለ ተንሠራፋው አለመተማመን ምን ይጠቁመናል?

የሚገርመው በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን (በ1954 ዓ.ም.) ከታተመው ከመጀመሪያው ቅጂ እስካሁን ግድፈት አላገኘሁበትም! ይኸ ስለ ዘመኑና ስለ ትውልዱ ምን ይነግረናል? ስሕተቶችን ማጒላት እንዳይሆንብን፣ ለናሙና ብቻ እነዚህን እንመልከታቸው፤

ከአዲሱ መደበኛ መጽሐፍ ቅዱስ - 1993 ዓ.ም. የታተመ

ገጽ 643። መኃልይ 1፡ 8(ሐ) “በእረኞቹ ድንኳን አጠገብ አሳማሪ።” = በእረኞቹ ድንኳን አጠገብ አሰማሪ | መኃልይ 13(ለ) “በምቋጠሪያ” | ገጽ 18። ዘፍጥረት 21:3 ይስሐቅ | ገጽ 1065። ሮሜ 9:7 ይሥሐቅ | ገጽ 937። “ማቴዎስ 4፡21” = ማቴዎስ 28:20 | ገጽ 1045። የሐዋርያት ሥራ 19:14 | ገጽ 1046። የሐዋርያት ሥራ 15:15 | ገጽ 1121። 1ኛ ጢሞቴዎስ 4:8 | ገጽ 1140። ያዕቆብ 1:10 “በመውርደቱ” = በውርደቱ

Word Project ድረገጽ

121:1። ዓይኖቼ ወደ ተራሮች አነሣሁ = ዓይኖቼ ወደ ተራሮች አነሣሁ። | 39:6። በእውነት ሰው እንደ ላ ይመላለሳል = በእውነት ሰው እንደ ላ ይመላለሳል።

[የተለያዩ አንባቢዎች በድምጽ የቀዱትን ክፍሎች አለፍ አለፍ ብሎ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ማስተያየት ያነሳነውን ችግር ያጎላዋል]

መፍትሔው ምንድነው?

1/ ግድፈት የተገኘበትን መጽሐፍ ቅዱስ ላመጣ የታረመው ይሰጥ?

2/ በእግዚአብሔር ቃል ሥርጭት ለሚሳተፉ ሁሉ ጥሪ ይላክ? በጥሪው እለት ተሳታፊዎች ግድፈቶችን ለቅመው እንዲያቀርቡ፣ ግድፈት የሚያስከትለውን ችግር ተወያይቶ ሁሉም ሊከተለው የተገባ መመሪያ ይዘጋጅ? በዚሁ ወቅት ስለፈጸምናቸው ግድፈቶች፣ ቸል ስላልንባቸው ዘመኖች ምሕረት የምንጠይቅበትና፣ ላለመድገም ቆርጠን የምንነሳበት ዕለት ይሁንልን?

3/ የመጽሐፍ ቅዱስ ማህበር ኃላፊነትና ድርሻ እስከ ምን ድረስ ነው? አብያተክርስቲያናትና የመጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጆች ለምን ዝም አሉ?

ለመሆኑ መዝገበ ቃላት ለምን አስፈለገ? ፍርድ ቤቶችስ? እነዚህ ባይኖሩ ወይም ስሕተትና ትክክሉን ለማስተማር ባይበቁ የሚከተለውን ውጤት በሚገባ አጢነናል? መጽሐፍ ቅዱስ ግን እንደ እነዚህ ተቋማትና ሥልጣናት አይሻሻልምና እጅግ ይለያል፤ የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነ ፍጹም ባለሥልጣን ነው። የሚሠራና የሚታመን ተቋማዊና ምሑራዊ ባለሥልጣን በሌለበት የግለሰቦችና የሕዝቦች ሕይወት ይመሰቃቀላል። መፍትሔው ጥቃቅን ግድፈቶችን በማጥራት ይጀምር!

ምትኩ አዲሱ

መጋቢት 29/2012 ዓ.ም.