የድመት መለኲሴ

bishop cat2

አንድ የከተማ ድመት ዐይጥ ስላደመበት ወፍና እንሽላሊት አድኜ እበላለሁ ብሎ ገጠር ወረደ። ደርሶ ሲያየው እንዳሰበው አልሆነለትም። አንድ ብልሃት መጣለት። እመለኲሳለሁ አለ። የመለኲሴ መቊጠሪያ ከሸረሪት ድርና ከእሾህ ፍሬ አበጃጅቶ አንገቱ ላይ አሠረና መቋሚያ ይዞ ወደ ሠፈር ተመለሰ። ተመልሶ፣ የለመደው አንድ የዐይጥ ጉድጓድ አጠገብ፣ እንደ ተኛ መስሎ በጮኽታ ኲርር ኲርርር ኲርርርር ይል ጀመር። የዐይጥ ኮረዳ ሰምታ ብቅ ስትል፣ ያ ድመት ነው። ዘልላ ከጉድጓዷ። ትንሽ ቆይታ፣ ዐይኔ ነው ምንድነው ብላ በበሩ መስታወት በኲል እያየች። ትልቅ እህቷን ተጣራች፤ ነገረ ሥራው ገርሟቸው ትክ ብለው ያዩታል።

መለኲሴው ለካንስ በአንድ ዐይኑ አጮልቆ ያያቸው ኖሯል። ዐይጢት! አለ። እህቷ ላይ ልጥፍ አለች። ምነው ሸሸሺኝ? ከስግደት የተመለሰን ወዳጅ፣ እንኳን ደህና ገባህ እንደማለት መሸሺሽ አሁን ተገቢ ነው? ቅረቢኝ እንጂ አትፍሪኝ አላት፣

አነጋገሩ ስላስገረማት ዐይጢት በሩን ገርገብ አርጋ አጥብቃ ይዛ፦ አጫውቺ  ኝ? አንተስ አይደለህ ጠላቴ? ዘመዶቼን የጨረስክ? ጠጋ ብል እኮ ዘልለህ ነው የምትውጠኝ አለችው፣

እውነትሽን ነው፣ ወቀሳሽ ተገቢ ነው። አልበደልኩም አልልም፤ በድያለሁ። አንደኛው ጥፋቴ ጩሉሌ ስሜን ስታጠፋ እግዚሐር ላይ ከስሻት ብቻ ዝም ማለቴ ነው። እኔ እንደሆንኩ ከንግዲህ እየጸለይኩ፣ ዳዊቴን  እየደገምኩ ዘመኔን ልጨርስ ቆርጫለሁ። ለመሆኑ አንገቴ ላይ ያሠርኩት መቊጠሪያ ከዚያ ርቀት ይታይሻል? ቀረብ ብለሽ እዪው፣ ከፈለግሽ ፊቴን ላዙርልሽና ንኪው። ቅድም እኮ ዳዊት ስደግም ነበር ያየሺኝ። ይቅር ባይ መሆንሽን ስለማውቅ እንጂ እኔ እንኳ ተፈጥሮ ሆኖብኝ ሰው ማስቸገር አልወድ።

ዐይጢት የምትለው ጠፋት፤ ዝም ብለሽ ከምታዪኝ፣ ሂጂና ዘመዶችሽን፣ ድሮ የምታውቁኝ አይደለሁም፤ ዛሬ ለነፍሴ ያደርኩ ነኝ፤ ስላለፈው በደሌ ከወሰናችሁብኝ መቀጮም እከፍላለሁ ብሎአል በይልኝ። እኔም እስክትመለሺ ውዳሴ ላድርስ ብሏት ኲር ኲርርር ማለቱን ቀጠለ።

እህትማማቾቹ ሄደው ወሬውን ለጎረቤት ሁሉ አዳረሱ። ጎረቤት በዐይናችን እንይ ብለው ከጉድጓዱ አፍ ሳይርቁ ተጠጋግተው አኳኋኑን ተመለከቱ። እውነትም ለነፍሱ አድሯል። የጢሙን ርዝመትና አንገቱ ላይ ያሠረውን መቊጠሪያ ተመለከቱ፤ የሚደግመውን ጸሎት ሰሙ፤ እንዴት ይጠራጠሩ?

ይኸን ነገር እናጣራ ተባባሉ። ከመሓላቸው ረጂም ጠጒር አፍንጫው ላይ ያለበትን መርጠው ላኩ። የተላከው ከርቀት እጅ እየነሳ፣ አያ መለኲሴ፣ እንዴት ከርመዋል? አለ። መለኲሴው እንዳልሰማ እንዳላየ ማነብነቡን ቀጠለ። መልእክተኛው ጠጒሩን ሲያስተካክል ሲንጎራደድ ለረጅም ሰዓት ዝም ብሎት አቆየው። ሌሎቹ የሚሆነውን ይጠባበቃሉ። መለኲሴው ጸሎት አብዝቶ ኖሮ ሞረመረው፤ ነቅነቅ ከማለቱ ዐይጦ ዘሎ ከጉድጓዱ።

መለኲሴው ከት ብሎ ሳቀ፤ አይ ያንተ ነገር፤ ምን አጣደፈክ? አለው። የምደግመው አሰለቸህ ወይስ በትክክል አልደገምክም ብለህ ነው ብሎ ተቆጣ፣

ኧረ አይደለም! አለ ዐይጥ፤ ከጉድጓዱ ተመቻችቶ ገብቶ። መድገሙንስ ድንቅ አድርገህ ደግመሃል፤ ስታየን የምትሆናት ግን አለቀቀችህም አለው ይባላል።

© ምትኩ አዲሱ | ግንቦት 2012 ዓ.ም. | "አፈ ታሪክ ከእንደገና"