ያ ል ዘ ራ ነ ው ን አ ላ ጨ ድ ን ም

hacaalu2

ሃ ጫ ሉ  ሁ ን ዴ ሳ

[1976--2012 ዓ.ም.]

የሃጫሉ ሁንዴሳ መገደል ጥቅሙ ምንድነው? ለማንስ ነው? ያልተስማሙንን በኃይል ማስወገድ መፍትሔ እንደማይሆን መቸ ይሆን የምንማር? እንዲህ ዓይነት ግድያ ይልቅ የግለሰቦቹን ኅልውናና የቆሙለትን ዓላማ ቢያጎላ እንጂ እንደማያከስም እንዴት ታጣን? ሃጫሉስ ምን የሚያስገድል ጉድ ተገኘበት?

በሃጫሉ ሁንዴሳ ዐይን ውስጥ እንታያለን። ከሃጫሉ የተለየ ባህርይ የለንም። አንደኛችን ሲገደል፣ ሁላችንም እንደ ሕዝብ ተገድለናል። ይህንን እውነት አለመገንዘብ በአካል ባይሆን በስብእና ያሳንሰናል። አናሳ ሞራል ያለው ሕዝብ ለሌላው ክብር የለውም፤ የሌለውን መስጠት አይችልማ! ከሁሉ በፊት ግን የሰው ክቡርነት ከእግዚአብሔር የተሰጠ ሥጦታ እንደ ሆነ ማወቅ ያስፈልጋል። የሰው ደም ማፍሰስ በእግዚአብሔር ፊት አስጸያፊ ነው፤ “የሰውን ደም የሚያፈስስ ሁሉ ደሙ ይፈስሳል፤ ሰውን በእግዚአብሔር መልክ ፈጥሮታልና።” (ዘፍጥረት 9፡6)

የአንጃ ፖለቲካ አፈ ቀላጤዎች በየማኅበራዊ ሚድያ እየዞሩ የሚዘበዝቧቸው ቃላት እንደ ፈንጂ በስነ ልቦናና በአካል ላይ ጒዳት እንደሚያስከትሉ ይኸ ቋሚ ማስረጃ ነው። እነዚሁ ጎጂ ቃላትን ቀፍቅፈው የውጤቱን አሰቃቂነት ሲያዩ ወይ ለቀስተኛ መስለው ይቀላቀላሉ፤ ወይም አይመለከተንም ብለው ይክዳሉ። እንደ ሕዝብ የዘራነውን ነው የምንበላው። ጥላቻና ግድያ ዘርተን ፍቅርና ሰላማዊ ሕይወት አናጭድም።

ጥላቻና አሉባልታን በገንዘብ የሚቸበችቡ አሉ፤ የሰው ደም በእጃቸው ላይ አለ፤ በነፍስና በኑሮአቸው ገና ዋጋ ይከፍላሉ። ድረገጽ አታሚዎችና ታዳሚዎቻቸው በአሳብ ነጻነት ስም ጥላቻና ሽብር እንዳያራምዱ በህግ እንዴት ማገድ ይቻላል? ዜጎችስ መቸ ነው ከቀዬአችን ያለፈ ቊምነገር የሚታይብን?

ሁለት አሳሳቢ ጒዳዮች አሉ። አንደኛው፣ ቂም በቀል ነው። የገዳዩን ማንነት በመጠየቅ ይጀምራል። አንዳንዶችም በግርግር አጥፊ ዓላማቸውን ያራምዳሉ። ይህ አደገኛ አካሄድ ነው። ከንፈር መምጠጥ አማራጭ አይደለም። እንዳይዛመት ማገድ የእያንዳንዳችን ግዴታ ነው። ሃጫሉ የተገደለው ዞሮ ዞሮ በጥላቻ ነው። ጥላቻ ዘር የለውም። ጥላቻን በፍቅር እንጂ በጥላቻ ማምከን የተቻለበት ዘመን ወይም አገር የለም። ሁለተኛው፣ የዶ/ር ዐቢይ አስተዳደር ንዝህላልነት ነው። ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንዳየነው ሕዝብ መምራት ሕዝብን ከማረጋጋትና አመኔታን ከመፍጠር ተለይቶ አይታይም። የነገሮች በጊዜው እልባት አለማግኘት፤ የጒዳዮች መድበስበስ አሳዛኝና ቊጣን ቀስቃሽ ናቸው። ይባስ፣ ሕዝብ እንዳይተማመን፣ ፍትኅ አገኛለሁ ብሎ ተስፋ እንዳያደርግ ያግዳሉ። የሚመለከተው ክፍል በአፋጣኝ ግልጽ የሆነ መልስ ይስጥ!

እግዚአብሔር ያዘኑትን ያጽናና።

ሰኔ 22/2012 ዓ.ም.