ፊደላት

ሁ ለ ት  ወ ዶ

~ እንቢልታ ነፋንላችሁ ዘፈንም አልዘፈናችሁም፤ ሙሾ አወጣንላችሁ ዋይ ዋይም አላላችሁም፤ ማቴዎስ 11፡17

ከኢትዮጵያ ሁሌ እንግዳ ነገር አይታጣም! ከላይ በስተግራ የሚታየውን፣ መከረኛ ኢንተርኔት ላይ ተለጥፎ ሳይ፣ ፊደል ተረሳኝ ወይስ አዲስ ፈጥረው? አልኩኝ። ባለጒትያ “ጎ” እና ባለቀለበት “ጐ” ሁለቱም የ “ገ” ሰባተኛ፤ ለየብቻ መቆም የተገባቸው፣ ሳያስፈልግ ተጣምረው ድምፃቸውን ተቀሙ። ማ አጣመራቸው? መልአክ? ኮምፒዩተር? ኮምፒዩተሩን ማ መራው? የጠላት ሤራ ይሆን?

ከሁለት ልክ የትኛውም ቢመረጥ ስሕተት አይሆንም። ከላይ የምናየው ግን፣ ሁለት ባንዴ ወዶ ሁለት ያጣን ታሪክ ያስታውሰናል። አገሩን ይወድዳል፤ ብሔሩን ከሁሉ አስበልጦ ይወድዳል። ሰላም እንዲወርድ፣ ይዝታል የስድብ ናዳ ያወርዳል። ጎራ ለይቶ፣ አንድነት! አንድነት! ይላል። በሌላው ላይ የጠላውን በርሱ ላይ እንዲወዱለት ይመኛል። እንቊልልጬ! የኔ ስውር ጥላቻ ካንተ ካንቺ ስውር ጥላቻ የተሻለ ነው! የኔ አንዲት ውሸት ያንተን አስር እውነት ያስንቃል ይላል!

ከኢትዮጵያ እንግዳ ነገር አይታጣም። የደርግ መሥራች አባል፣ ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ ዛሬ በኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ተጥሷል ብለዋል። መፍትሔውስ? ሲባሉ፣ ጠ/ሚ ዐቢይ ሥልጣን ያስረክቡ! ለማን ያስረክቡ? በደፈናው ለ “ሽግግር መንግሥት”፤ ሽግግር፣ ክርክር፤ ግርግር። በዘመነ ደርግ ሽግግር ያሉ መጨረሻቸው ምን ነበር?

ኤርትራዊው ረዘነ ሃብቴ፣ ከኢትዮጵያ ‘ቅኝ አገዛዝ’ ነጻ አውጪው ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ኢትዮጵያዊ ማንነቱን ክዶ አያውቅም ... የፖለቲካ ስልጣን ባለቤት ከነበሩት ቤተሰቦች በመወለዱ ... ከጥንታዊቱ ኤርትራ ጋር በተያያዘ እንደ ሃገርም እንደ ማንነትም ሌሎች እንደሚመኩት ኢሳያስ አፈወርቂ ሲመካ አልተሰማም ...” ይለናል! ጒድ እኮ ነው! ከሃያ ዘጠኝ ዓመት በኋላ! “ነጻነት” መስሎን! ለካ “ባርነት” ኖሯል! ይለናል (“ደም የተከፈለበት ባርነት”፣ 2011 ዓ.ም.)። ተ.መ.ድ. እንዳይሰማ ብቻ!

ጅማሬው እንግዳ፤ ፍጻሜው እንግዳ፤ ሁሌ እንግዳ። “ደም የተከፈለበት ባርነት” (2011 ዓም) የ “መደመር” (2012 ዓም) የመልስ ምት ነው ወይስ ጥንስሱ?

**

ከላይ፣ በስተቀኝ በኲል የሚታየው “ት” ነው “ች”? ሲታይ፣ የምናውቀውን ፊደል ይመስላል፤ ስንቀርበው ግን ባእድ ነው። ከአገባቡ ብቻ “ች” ነው እንላለን። ፊደላቱ ስለ “ኢትዮጵያዊ አእምሮ” ምን ያስረዱናል? ኢትዮጵያዊ አእምሮ ብሎ አለ? የሚል አይጠፋም። የቀረጽናቸው የቀረጹን “ምሑራዊ” ትርክቶቻችን ለዚህ ፍንጭ ይሰጡናል፦ ኢትዮጵያዊ አእምሮ መቸውንም ቢሆን የፍርሓት እና የሐዘን ጒዝጓዝ አያጣውም!

ባህልና እውቀት መዋዋስ ያለ ነገር ቢሆንም፤ ከሌላ ተውሶ የተዋሰበትን ምንጭ ደብዛውን አጥፍቶ የግል ንብረት ማድረግ ግን ኢትዮጵያዊ አእምሮ ነው። በሌላ አነጋገር፣ አታላይነት (አራዳነት፣ ግትርነት፣ አድመኛነት፣ ሥርዓተ አልበኝነት፣ እልኸኝነት)። ክርስትና ኢትዮጵያዊ ነው? (መልሱ፣ አይደለም ነው።) ይህን ጥያቄ መጠየቅ ለምን የስድብ ናዳ እንደሚጋብዝ ግልጽ አይደለም። በትርክቶቻችን እና በትውፊቶቻችን ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ኢትዮጵያዊነታቸው ለምን ጥርጥር ውስጥ እንደሚገባ ግልጽ አይደለም። ስድብ ተፈርቶ ሳይጠየቅ ይታደር? ወሮበላ ወሮበላው ብቻ ኢትዮጵያዊ አይደለም? ኢትዮጵያ የንጹሓን የቅዱሳን አገር የተባለች ‘ለት ያኔ ኢትዮጵያነቷ ከሰመ!

ኢትዮጵያዊ አእምሮ ቄንጠኛ ወገንተኛ ተሳላሚም ነው። ቀላልና ግልጹን ቀጣጥሎ አምልኮ የማስመሰል ልክፍት አለበት። በማወሳሰብ ሌላውን ማንበርከክ ይሻል። ቆም ብሎ ራሱን አይመረምርም፣ ያለአክብሮት ያለፋታ ሌላውን ይበረብራል። ሰውን በሰውነቱ እንዳያዩ ዐይኖቹ በብሔር ተቀላልመዋል፤ ይህ ህወሓት ያመጣው ሳይሆን የኖረ ባህርዩ ነው! ፈርሃ እግዚአብሔር ካልገዛውና ሆዱ ካልሞላ ሳይቀረፍ ይኖራል!

እንግሊዝኛና አማርኛን፣ እንግሊዝኛና ኦሮምኛን፣ እንግሊዝኛና ትግርኛን ይቀላቅላል። ሲናገር የገዛ ድምጹን መስማት ያስደስተዋል፤ ስለሚናገረው ጒዳይ አድማጭ ባይገባው ደንታው አይደለም። ቀጥታ መናገር ሲችል፣ ለምን ይቀላቅላል? አዋቂነቱ እንዲታወቅለት? የአድማጭን ድንቊርና ለማጋለጥ? አላዋቂነቱን ለመሸሸግ? የሚገርመው ግን፣ ዘወር ብሎ፣ ባእድ አልገዛኝም፣ ባእድ አይገዛኝም ይላል! በአስተሳሰብ እንደ ገዛው አላወቀ! እንደ ፈረንጅ እያረገው ቊቤን ይተቻል። ለአገር ከእኔ እኲል የሚቆረቆር የለም ይላል!

እንደ ኢትዮጵያ ቅድስት፣ እንደ ኢትዮጵያዊ (ኦሮሞ፣ ወላይታ፣ ትግራይ፣ አማራ) ታላቅ (ወርቅ) ዘር የለም ይላል። ይኸ ከናትዚ ጀርመን ትርክት በምን ይለያል? ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሳይሾም ሹም የሆነ ይመስለዋል። ቀጭን ትእዛዝ መስጠት ያዘወትራል፤ ሌላው እንዲያደምጠው እንጂ ሌላውን አያደምጥ! ሌላው ሲናገር የሚያጣጥልበትን ምላሽ ይዶልታል እንጂ ከቶውንም የሚባለውን ከልቡ አይሰማም። ፈንጠር ብሎ ቆሞ፣ አንተም አንቺም “ዲያስፖራ” ናችሁ ይላል (ባእድ ናችሁ ለማለት)፤ ወዲያው ደግሞ ለእናት አገራችን እንረባረብ!!

ኢትዮጵያዊ አእምሮ በአድማና በድግግሞሽ፣ ከሌለ እውነት እውነትን ይፈጥራል። ሻሸመኔ ስትቃጠል፣ የተጎዳው አንድ ወገን ብቻ ነው? ሦስት ተከታታይ ሰኔዎችን አገር ያመሰ ሤራ ያቀናጀች እጅ የማን ናት? ዳቦና ሽቶ በመጥፋቱ የተጠቀመው ማን ነው? የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ ለምን ተባለ? በኢትዮጵያ ብቻ ነው ድሃና ሥራ አጥ የዘረፈውና ንብረት ያወደመው? ድህነት ሥራ አጥነት ጭካኔ ስስት በኢትዮጵያ ብቻ ነው ዘር የለየው?

ፍቅር፣ ፍትህ፣ ሰላም፣ ለሰው ሁሉ! ይላል። ተመልሶ፣ ያልተስማማውን ወገን ቄሮ፣ መንጋ፣ ሽብርተኛ፣ ትምክሕተኛ፣ ጽንፈኛ ይላል። ንግግሩ በጅምላ ስለሆነ ስለ እነማን እንደሚያወራ ራሱም አያውቅም (ራሱን እንደሚጨምር አያውቅም)፤ ደስታው ከማሸበር ነዋ! ቀጥሎ፣ ቄሮ፣ መንጋ፣ ሽብርተኛ፣ ትምክሕተኛ፣ ጽንፈኛ ከሰው አልተፈጠረም ይላል፤ ከእንስሳ ያነሰ፣ የሠይጣን ቊራጭ ነው ይላል። ቃል ድርጊትን እንደሚጋብዝ ማየት ተስኖታል። በአምሳለ እግዚአብሔር የተፈጠረን ሰው ካራዊት ፈርጆ፣ ካሠየጠነ በኋላ፣ ሠይጣንን መጥላት ኃይማኖትም የሚደግፈው ነውና፤ ይጠላል፤ ያጣላል፤ ያጥላላል፤ ገድሎ ይጥላል። እግዚአብሔርን እንዳገለገለ፣ አገርን እንደ ታደገ እንደ ጽድቅ ጀግነቱን ያስወራል። ወገንተኛ ሆኖ ሲያጸድቅና ሲኮንን፣ የራሱን ስብእና ያጣል። ፍቅር፣ ፍትህ፣ ሰላም፣ ለሰው ሁሉ! ይላል። ንግግሩ አያታልልህ። ፍቅር፣ ፍትህ፣ ሰላም፣ ለኔና የኔ ለሆኑት ብቻ! ማለቱ ነው! ሌላውን ሲነፍግ እርቃኑን እንደ ቀረ አላወቀ! ይህም የኢትዮጵያዊ አእምሮ ውጤት ነው።

በኢትዮጵያ ቤተኛ ያልሆነ መጤ የኦሮሞ ሕዝብ ብቻ ነው? ቤተኛ ስላልሆንክ የተደረገልህን ውለታ እየቆጠርክ አመስግነህ ኑር ነው? ይኸማ ቢሸፋፍኑት የማይደበቅ ዘረኛነት ነው! ግጦሽ ፍለጋ ታች ላይ የተመላለሰበትን ዘመን ተከታትሎ የመዘገበ አለ? ሌላው ከየት መጣ? እኔ ብቻ መጤ አይደለሁም የሚል ሕዝብ የት አገርና አህጒር ይሆን የሚገኝ? አለማወቃችንን በሌሎች አለመኖር መተርጎም ተገቢ ነው? ከአዳም ጀምሮ ከተጠፈጠፈበት አፈር ላይ ተወልዶ አድጎ ተዋልዶ የኖረ ሕዝብ አለ? አዳምና ሄዋን እንኳ የተዋለዱት ከዔድን ገነት ተባርረው ወደ ምሥራቅ (ወደ ዛሬዪቱ ኢራቅ አካባቢ) ከተሰደዱ በኋላ ነው (ዘፍጥረት 1፣2፣3)። አዳም እውነት ግእዝ/አማርኛ ተናጋሪ ነበር? መጽሐፉስ ኢትዮጵያን ነው የዔድን ገነት ያለው? (ዘፍጥረት 2፡13) መረጃ ሲባሉ፣ መረጃውማ ትውፊታችን ነው ይላሉ፤ አምርረው ይቀየማሉ! ኢትዮጵያዊ አእምሮ መረጃ ሲያጥረው፤ የራሱን መረጃ ይፈጥራል፤ አድማ ይመታል፤ በዘመን ርቀት ያሳብባል፤ ዐይንባይን ይክዳል፣ ይራገማል።

የአዳምና ሄዋን ዝርያዎች ሲጓዙ በሰናዖር አንድ ሰፊ ሜዳ አገኙ (ዘፍጥረት 11)። አንድ ቋንቋ ነበሩ፤ አንድ ሕዝብ ነበሩ፤ ከተማችንን በሰናዖር እንመሥርት ተባባሉ። የዛሬዪቱን ኢትዮጵያን ያስታውሳሉ፤ ዛሬም አንድ ቋንቋ፣ አንዲት አገር፣ አንድ ኃይማኖት ይኑረን የሚሉ አሉ (ታዲያ ቋንቋውም፣ ኃይማኖቱም የራሳቸው ከሆነ ብቻ ነው!)። የሰናዖር አንድነት ሲታሰብ መልካም ይመስላል፤ አንድነቱ ግን የተፈለገው ለአንድነት ሳይሆን ለአድማ ነው፤ አድማውም ዞሮ ዞሮ በእግዚአብሔር ላይ ነው! ምክራቸው አልጸናችም! በምድር ላይ በተናቸው፤ ቋንቋቸውን ደበላለቀው። በእግዚአብሔር ላይ ያደመ ልብ ለሰውም አይተኛ! በሰው ላይ ሲያድም ካገኘኸው፣ ልቡ ቀድሞውን በእግዚአብሔር ላይ አድሟል! አድማና አንድነት አብረው አይሄዱም! ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ! የሚል ሁሉ፣ ሁሉን አቀፍ ኢትዮጵያን ማለቱ ላይሆን ይችላል!

ኦሮምኛ መናገር የምናየውን የሰለቸ ትርምስ አስወግዶ ለሁላችን የሚብቃቃና የሚተርፍ ሰላምና ልማት የሚያመጣ ቢሆን ስንቶች ኦሮምኛ መናገርን እንመርጣለን? አማርኛ መናገር የምናየውን የሰለቸ ትርምስ አስወግዶ ለሁላችን የሚብቃቃና የሚተርፍ ሰላምና ልማት የሚያመጣ ቢሆን ስንቶች አማርኛ ብቻ መናገርን እንመርጣለን? ለዚህ የምንሰጠው ምላሽ የልባችንን መነሻ አሳብ ይገልጣል!

እውነትን መፍራት፣ ጭለማን መምረጥ ነው። አንድከም፤ እውነት ሳይነጋገር አንድነት አይኖርም፤ ሰላም አይኖርም። ብርሃንን ጠልቶ ለምን ጨለመ ይላል፤ ቂል ነው። በውሸትና በደባ እየተገበያየ ሰላም ለምን ጠፋ ይላል። ሁለት ወዶ አይሆንም! መሲሕ! መሲሕ! ብሎ ያነገሠውን በነጋታው አርዮስ! አርዮስ! ብሎ ይራገማል፤ ከእውነት ጋር ቊርኝት ስለሌለው ኅሊናና ሰው ይታዘቡኛልን አያውቅም! የዘመኑ “ምሑር” “አክቲቪስት” ኢትዮጵያዊ አእምሮ ልብ የማይጣልበት ልበ ከዳ ነው!

ኢትዮጵያዊ አእምሮ ያጋንናል፤ እልኸኛ ነው፤ ከማን አንሼ ይላል። ገዳ እውን ለሁሉ የሚብቃቃ “ዲሞክራሲ” ነው? ወይስ በ ከማን አንሼ ስሜት የተጋነነ ዲሞክራሲ? “ዲሞክራሲ” የወንዱን የሴቱን የሕጻኑን የአዋቂውን የባእዱን የሰውን ሁሉ እኲል ተሳትፎና መብት ያስከብራል ካልን፣ በጥንት ግሪኮችም ዘንድ እንኳ ያልነበረ ነው!

ኢትዮጵያዊ አእምሮ የራሱን ስሕተት አይቶ ይኸማ ቀላል ስህተት ነው ይላል። ስህተትን አጣጥሎ እውነት እንዲሆንለት ይሻል። እልኸኛ ስለሆነ ዐይንባይን ይክዳል። እውነትና ሃሰትን አንድነት ካልወደድኩ ይላል። ከተጠያቂነት ለመሸሽ ያመኻኛል። ድሃና ኋላ ቀርነቱን ላለመቀበል፣ ጥንት ታላቅ ነበርን! ይላል።

ነቢዩ እንዲህ ብሏል፦ በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጕርጕርነቱን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን? (ኤርምያስ 13፡223)። መልሱ፣ ኢትዮጵያዊ መልኩን፣ ነብር ዝንጕርጕርነቱን ይለውጥ ዘንድ አይችልም ነው። የኢትዮጵያዊስ አእምሮና ልብ ሊለወጥ ይችላል? መልሱ፣ አዎን ይችላል! ነው።

ምሥጢሩ፣ ቅን መሆን ነው። ቅን የሚኾነው እንዴት ነው?

ምትኩ አዲሱ

ጳጐሜን ፫፣፪፻፩፪ ዓ.ም.

፪፻፩፪ ዓ.ም. በድረገጾች፣ በዩቱብ፣ በፌስቡክ፣ በቲቪ ዐይን ሲቃኝ።

 

እንኳን ለ ፪፻፩፫ ዓመተ ምሕረት አደረሰን! ቅንነት የሚንሠራፋበት ዘመን ይሁንልን!