በሽታው እውነት ነው!

ፌዴራል መንግሥት ሰኔ 21/2013 ዓ.ም. በራሱ ተነሳሽነት በትግራይ ተኲስ አቊም አድርጌአለሁ ብሎናል። የአዝመራ ጊዜ እንዳያልፍ፣ ፀጥታ ማስከበር ያስከተለው ወጪ እና የውጭ መንግሥታት ጫና ለውሳኔው ምክንያት ተደርገው ቀርበዋል። ፌዴራል መንግሥት እውነቱን ሁሉ ይንገረን አይንገረን ማወቅ አይቻልም። በተለያዩ ጊዜአት ወቅታዊ መረጃ ለሕዝብ አለማቅረቡ ያሰለቸ ጒዳይ ነው። ለምሳሌ፣ "ህወሓት ማለት በንፋስ ላይ እንደ ተበተነ ዱቄት ነው" እንዳልተባልን፣ ህወሓት እዚህ ታየ፣ እዚያ ገባ ወሬ እየተናፈሰ ፌዴራል መንግሥት ጭጭ ማለቱ ትርጒም የለውም። እርግጥ ነው፣ ህወሓት የሚታወቀው አሳች ወሬ በመንዛት ነው። ሕዝብ አመኔታ እንዲኖረው ካስፈለገ ግን፣ ለህወሓት ተስፋፊ ወሬ፣ በተለይ በውጭው ዓለም ዜና አውታሮች ለሚሠራጩ መረጃ አልባ ወሬዎች፣ አፀፋ መስጠት ግድ ነው።

የአገራችን በሽታ እውነት ነው! እውነት አለመነጋገር ነው። ውሸቱን የሚለይ መረጃ ማጣት ወይም አለመፈለግ ነው። ኤስ ቢ ኤስ አውስትራልያ አማርኛ ራዲዮ ሦስት ኢትዮጵያውያንን ስለ ተኲስ አቊሙ አነጋግሯል። ያቀረበላቸው ጥያቄ፦ "የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጠል ተኲስ ማቆም ዕወጃ ፋይዳ ምንድነው?" የሚል ሲሆን፣ ምላሻቸውን ቆንጽሎ እንዲህ ለጥፎታል፦

“የረጅም ጊዜ አዎንታዊ ተፅዕኖው ወደፊት የሚታይ ሆኖ፤ መንግሥት የወሰደውን የአንድ ወገን ተኩስ አቁም የምመለከተው በአዎንታዊ ጎኑ ነው። የመንግሥትን ሆደ ሰፊነትና ቻይነት የሚያሳይ መልካም ራዕይ ያለው ውሳኔ ነው።” አቶ አዳሙ ተፈራ

“የፌዴራል መንግሥቱ ተኩስ አቁሜያለሁ ብሎ ቢያውጅም፤ የእርዳታ ክልከላው፣ የቴሌኮም ክልከላው፣ ድልድይ መስበሩና ባንክ እንዳይንቀሳቀስ ማድረጉ አልቆመም። ጦርነቱ መልኩን ቀየረ እንጂ የፌዴራል መንግሥቱ ጦርነቱን አስቁሞታል የሚል ዕምነት የለኝም።” ዶ/ር ፍሳሃ ኃይለ ተስፋይ

“የተወሰደው የተኩስ ማቆም ሰከን ብለን ከዚህ ቀውስ ውስጥ እንዴት እንወጣለን ብሎ ለማሰብና ወደ ፖለቲካዊ መፍትሔ ለመሔድ ዕድል ይሰጣል ብዬ አስባለሁ።” አቶ አያሌው ሁንዴሳ

ይታያችሁ። ሦስቱም ለሕዝብ የሚሆን እውነት የላቸውም፤ ወይም ሆን ብለው ሊሸሽጒ ወስነዋል። የአቶ አዳሙ ተፈራ አተያይ፣ ፌዴራል መንግሥት የወሰደውን እርምጃ የሚደግፍ ነው። የዶ/ር ፍሳሃ ኃይለ ተስፋይ ፌዴራል አተያይ፣ መንግሥትን ኮንኖ ከህወሓት የሚወግን ነው። የአቶ አያሌው ሁንዴሳ መካከለኛና ሚዛናዊ አተያይን ለማሳየት የታለመ ነው። አንድ ከአማራ፣ አንድ ከትግሬ፣ አንድ ከኦሮሞ ይመስላል። ኤስ ቢ ኤስ ራዲዮ አዘጋጆች በአቀራረባቸው ገለልተኛ መሆናቸው ነው፤ የተለያዩ የተቃረኑ አሳቦችን አጠናቅሮ አድማጭ አድምጦ የራሱን ውሳኔ ወይም ምርጫ ያድርግ ነው! ይኸ አቋም ከማንም ጋር አያጣላም። ይኸ ነው እንግዲህ የዘመኑ እውነት! እውነቱን መዘገብ ብዙ ድካም ብዙ ነቀፌታ፣ አድማጭ ማጣት ሊያስከትል ነው!

አድማጭ በበኲሉ ከቀረቡለት ሦስት አማራጮች አንዱን መርጦ ይወስድና ያስተጋባዋል። ባብዛኛው ኦሮሞው የኦሮሞውን አተያይ፣ አማራ የአማራውን አተያይ፣ ትግሬው የትግሬውን አተያይ ይወስዳል ማለት ነው! መተያየት የለም! ሁሉ በየክልሉ በየጎሬው ድቤ ይደልቃል፤ እውነቱን ግን አላገኘም ወይም ባያገኝ ደንታው አይደለም!

ይታያችኋል ምን ዓይነት አዙሪት ውስጥ እንደ ገባን? ምን ጊዜም ከገባንበት ማጥ ውስጥ አንወጣትም። ነፃ ለመውጣት ከፈለግን እውነቱን መያዝ እንጂ አማራጭ የለንም። "እውነትንም ታውቃላችሁ፣ እውነትም አርነት ያወጣችኋል" ብሏል። መስዋእት ሊያስከፍል ይችላል፤ ወዳጆቻችንን ልናጣ እንችላለን፤ ስድብና ነቀፌታ ሊገጥመን ይችላል። እውነቱ ግን ብቻውን ያኖረናል፤ እውነት ያያይዘናል። እውነት ሰላም ይሆነናል፤ እውነት ያለ ፍርሓት ያኖረናል። እውነተኞች እንዲበዙልን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

ለመሆኑ የፌዴራል መንግሥት ተኲስ አቊም፣ የህወሓት ነገር እውነቱ ምንድነው? ሳንፈራ፣ ለቀኝ ለግራ ሳንል እንነጋገር። እውነቱ ካሰብነው ሌላ ከሆነ የያዝነውን ለቅቀን እውነቱን ለመያዝ ፈቃደኞች ነን? ፈቃደኞች ካልሆንን ከሰማይ መልአክ እንኳ ቢላክልን አንሰማም። ለእንዲህ ዓይነቶቹ የምለው የለኝም።

ምትኩ አዲሱ