mengemelesabiy

የኢትዮጵያ ወይስ የግለ ሰብ ክብር ይቅደም?

ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በአንደኛው የፓርላማ ውሎ ላይ የተናገሩትን፣ ከቀጣይ የአገር ህልውና አንፃር በጥሞና ልናሥብበት ይገባል። "በኢትዮጵያ ክብርና ጥቅም ከመጣችሁ አንገቴን ይቀላል እንጂ አይደረግም። አይደረግም እሱ። በመጠምዘዝ የሚሆን ነገር የለም። ተላላኪ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ አይፈጠርም" ብለዋል። አባባላቸው ለአገር ያላቸውን ፍቅር እና ቊርጠኝነት ያሳያል እንበል። አማካሪአቸው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ለጋዜጠኛ ደረጀ ኃይሌ በሰጠው ቃለምልልስ ላይ ጠ/ሚ ዐቢይ ስለ ኢትዮጵያ ሲያነሡ እንባ ሁሉ እንደሚተናነቃቸው አመልክቷል። መልካም። የሁለቱ አባባሎች አሳሳቢነት ግን ሊዘነጋ አይገባም።

1/ የኢትዮጵያ ህልውና በግለ ሰብ መኖር አለመኖር ላይ ከተመሠረተ አወዳደቋ እጅግ ከባድ ይሆናል። ከኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም እንማር! (እግረ መንገድ፣ ዐቢይም ኮሎኔል እንደ ሆኑ አንርሳ!) መንግሥቱ እንደ ቴዎድሮስ የሞት ፅዋ ሊጠጡ ነበር፣ ሳይሆን ቀረና በጭለማ ከአገር ወጡ። እርግጥ ከአገር የወጡበት ሁኔታ የአሜሪካና የካናዳ መንግሥታት እጅ አለበት፤ ህወሓትና ሻብያ ሎንዶን ላይ አዲስ አበባ እንዲገቡ አሜሪካኖች ከበየኑልን በኋላ የመንግሥቱ መኖር የሚያስከተለውን እልቂት ለማስቀረት ያቀናበሩት ሤራ ጭምር ነው። መንግሥቱ ሥልጣናቸውን "ታሪክ የጣለባቸው አደራ" እንደ ሆነ ስላሰቡ፣ ተተኪ የማፍራት ነገር አልታሰባቸውም፤ ተተኪን እንደ ተቀናቃኝ እንደ ጠላት ቆጠሩ፤ አራቊ፣ አስወገዱ።

2/ ዶ/ር ዐቢይ በተለይ በፓርላማ ተገኝተው ከሚያደርጓቸው ንግግሮች ምን ያህሉ በአማካሪዎቻቸው ታይቶና ታርሞ ይሰጣቸው አይሰጣቸው አላውቅም (አማካሪ ይኑራቸው አይኑራቸው ወይም ይስሙ አይስሙ አላውቅም። አንድ ነገር ግን በግልጽ ይታያል፣ ይኸውም የከበቧቸው ባብዛኛው የሚያወድሷቸው ናቸው)። በስሜት ግለት የሚወረውሯቸው ቃላት እያደር ትልቅ ችግር ማስከተላቸው አይቀርም። ይልቊን በዲፕሎማቲኩ ዓለም። "ተላላኪ መንግሥት በኢትዮጵያ ውስጥ አይፈጠርም" አባባል በአገር ፍቅርና ወኔ የተነገረ እንጂ የውጭውን ዓለም ኃይል አሠላለፍ ያገናዘበ አይደለም። የመንግሥቱም የግለት አቋም ቢበልጥ እንጂ ከዐቢይ አይተናነስም! የዶ/ር ዐቢይ አንገት መቀላት የእርሳቸውን ቊርጠኝነት እንጂ የኢትዮጵያን ህልውና አያስጠብቅም። እርሳቸው ከሌሉ የአገራችን ዕጣ ምን ይሆናል? አሁን በምንገኝበት ሁኔታ ውስጥ ይህን ማስረገጥ አንችልም። ጠ/ሚ ዐቢይ እውነተኛ ፍቅር እንዳላቸው፣ ያለ እረፍት ትልቅ ሥራ እየሠሩ እንደ ሆነ ምንም ጥርጥር የለኝም። የኢትዮጵያ የነፃነትና አንድነት መሠረት ግን በእርሳቸው ህልውና ላይ ሳይሆን ቀጣይነትና ፅናት ባላቸው ተቋማትና ተተኪ መሪዎች ላይ እስካልሆነ ድካማቸው "ንፋስ እንደ በተነው ዱቄት" ነው! ኮሎኔል መንግሥቱ ከአገር ከወጡ በኋላ "ታላቊ፣ ውዱ" ብቸኛ መሪነታቸው ገበናችንን የማንሸፍንበትን ሁኔታ ፈጠረ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ጨዋነት እና በተለይም የአምላኩ ረድዔት ባይሆን ኖሮ ትልቅ እልቂት ይሆን ነበር። ኢትዮጵያን በሎንዶን ላይ የሚወክላት ጠንካራ መንግሥት ጠፋ። ህወሓት እና ሻብያ አዲስ አበባ ሲገቡ ከእነርሱ ጋር የሚደራደር ጠንካራ አካል ባለመኖሩ የአገሪቷን ተቋማት እና ሕዝቡን ብትንትኑን አውጥተው በራሳቸው ልክ ሰፉት! የያኔ ታሪካችን የአሜሪካኖች መጫወቻ ሆነ፤ ዛሬስ እንደማይደገም ምን ማስተማመኛ አለን?

ሌላው ቢቀር ከመለስ ዜናዊ እንማር። ከዚህ ቀደም ደጋግሜ እንዳልኩት ህወሓትን ያፈረሱት "አቻ የለሹ ታላቁ መሪ፣ " መለስ ዜናዊ ናቸው። እንዴት? ብርቱ ብቊ መሪዎችን ባለማስጠጋት፤ በመከፋፈልና አድር ባዮችና ብቃት የለሾችን በማሠማራት! እርሳቸው በሞት ተወገዱ፤ ሁሉ ተበተነ። ዐቢይ በሌሉበት የአገራችን ዕጣ እንዴት ይሆናል? ብልፅግና ፓርቲ አሸነፈን ትተን ይህን ጒዳይ በአጽንዖት እናስብበት!!!

ምትኩ አዲሱ