ምርጫ ቦርድ2

ብ ሔ ራ ዊ  ም ር ጫ  ቦ ር ድ  እና  ሌ ሎ ች  ቊ ም ነ ገ ሮ ች

ባለ አምስት አባላት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ሁለት ሴቶች ሦስት ወንዶች፣ ሴት ሊቀ መንበር። ገለልተኛ ቦርድ። ተሰምቶም ታይቶም አያውቅም። እህቶቻችን የገነኑበት። ታሪክ ሠርተው ያስመሰከሩበት። ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የዲሞክራሲያዊ አሠራር መሠረት "ሀ" ተብሎ የተጣለበት ዕለት ነው። በልዩ አዋጅ "የዲሞክራሲ ቀን" በዓል በያመቱ መከበር አለበት። በትምህርት ቤቶች መማሪያ መጽሐፍ ውስጥ መጨመር አለበት! የዶ/ር ዐቢይ አሕመድ አመራር ጠንካራ ጎን የታየበት ነው። ብርቱካን ሚዴቅሳ--ምርጫ ቦርድ። ማርያም የሰፋችው እስኪመስል እጅና ጓንቲ ነው።

ክብርት ዳኛ ብርቱካን ሚዴቅሳ መለስ ዜናዊን በዲሞክራሲ አደባባይ ልትፋለም!? ሴት ልጅነቷን፣ ጀማሪነቷን። በወንድ ዓለም ደፋርነቷን አይተው ምናልባት ቢራሩ (እርሳቸውም የሴት ልጅ አባት ናቸውና)። አልራሩም። የአቶ መለስ ፖለቲካ ስልት እንኳን ለጀማሪ ለእግዚአብሔርም አዳግቶ ነበር!

እስር ቤት፤ ፈተና፤ ማመንታት፤ ብዙ ማመንታት፤ ብስለት፤ መጠንከር፤ ስደት፤ ዘመን፤ ክብር እና ጠባሳ፤ ለታሪክ ማህደር። የሕይወትን ጥሪ እና ሂደት ማወቅ አስቸጋሪ ነው፤ ባዲሳባ ነቢያት አኳኋን አይወሰድብኝና ክብርት ዳኛ ብርቱካን ሚዴቅሳ ተንግዲህ ለፓርቲ ፖለቲካ አትሆንም! ያንስባታል። ጥሪዋ በምድራችን ዲሞክራሲ እንዲያብብ ማስተማር፣ ትውልድ ማሠልጠን፤ የሴቶችን ተሳትፎ በየትምህርት ቤቶች፣ በማህበራዊ ሚድያ ማወያየት፣ ማበረታታት፤ መጽሐፍ መጻፍ፣ ዶክዩሜንተሪ መቅረጽ፤ ወዘተ። ይኸ እቅድ በሁለት የሕይወት ዘመን የሚያልቅ አይደለም። የሚቻለውን ለማድረግ ግን አልዘገየም!

እግዚአብሔር ምድራችንን እና ሕዝባችንን ይባርክ።

ምትኩ አዲሱ

photo credit: nebe.org