bikila almaz selemon

ጎ በ ዝ  አ ት ሌ ት  ወ ይ ስ  ፕ ሮ ቴ ስ ታ ን ት?

ሰለሞን ባረጋ የዘንድሮውን በር ከፋች የኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳልያ በ10ሺህ ሜትር ሐምሌ ጊዮርጊስ እለት ቶኪዮ ጃፓን ላይ አሸንፎአል። የአገራችንን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አስደርጓል፤ ብሔራዊ መዝሙራችንን በመላው ዓለም አሰምቷል!

የዜግነት ክብር በኢትዮጵያችን ፀንቶ
ታየ ህዝባዊነት ዳር እስከዳር በርቶ
ለሰላም ለፍትህ ለህዝቦች ነፃነት
በእኩልነት በፍቅር ቆመናል ባንድነት
መሰረተ ፅኑ ሰብዕናን ያልሻርን
ህዝቦች ነን ለስራ በስራ የኖርን
ድንቅ የባህል መድረክ ያኩሪ ቅርስ ባለቤት
የተፈጥሮ ፀጋ የጀግና ህዝብ እናት
እንጠብቅሻለን አለብን አደራ
ኢትዮጵያችን ኑሪ እኛም ባንቺ እንኩራ።

አበበ ቢቂላ ከ57 ዓመት በፊት (ሰለሞን ባረጋ ከመወለዱ የትና የት ቀድሞ) የቶኪዮ ማራቶን ሲያሸንፍ ብሔራዊ መዝሙር እንዲህ ተዘምሮ ነበር፣

ኢትዮጵያ ሆይ ደስ ይበልሽ
በአምላክሽ ኃይል በንጉስሽ
ተባብረዋልና አርበኞችሽ
አይነካም ከቶ ነፃነትሽ
ብርቱ ናቸውና ተራሮችሽ
አትፈሪም ከጠላቶችሽ።
ድል አድራጊው ንጉሣችን
ይኑርልን ለክብራችን።

(የአበበ ቢቂላ ድል እስከ ዛሬ ድረስ ከእኛ ይልቅ በጃፓኖች የሚታወሰው፤ ጃፓን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ፣ በጦር ቆስቋሽነት ከተማዎቿ ወድመው ሕዝቧ ያለቀው አልቆ ሰላምተኛነቷን ለዓለም ማሕበረ ሰብ ለማስተዋወቅ እድል ያገኘችበት ዘመን ስለ ነበረ ነው።) አበበ ቢቂላ በድል ሲመለስ አዲሳባ ላይ እንዲህ ተዘፍኖ ነበር፣

"እቱ ይሻልሻል፤ ይሻልሻል፣
እቱ ይሻልሻል፤ ይሻልሻል፣
አበበ ቢቂላ ያገባሻል፣
ጥላሁን ገሠሠ ይድርሻል!"

ጋዜጠኛ አበበ ግደይ ለ10ሺህው ጀግና ለሰለሞን ባረጋ:- "ብዙ አትሌቶች ድል ካደረጉ በኋላ በዘፋኞች ተወድሰዋል። ድልህን አስመልክቶ (አበበ ቢቂላ በሮጠበትና ባሸነፈበት ከተማ) ማን ቢዘፍንልህ ትመርጣለህ?" የሚል ጥያቄ አቅርቦለት ነበር። የሰለሞን ምላሽ?፦ "እኔ እንኳን ስለ ዘፈን ብዙ አላውቅም። እኔ ፕሮቴስታንት ነኝ" የሚል ነበር። መልካም። ለመሆኑ "ፕሮቴስታንት" ምንድነው? ሰለሞን ምን ማለቱ እንደ ሆነ ይገባኛል፤ ያሸነፈው ግን "ፕሮቴስታንት" ስለ ሆነ ወይስ ጥሩ አትሌት ስለ ሆነ?

ኋላ በእስራኤል ላይ የነገሠው "ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ገድሎ በተመለሰ ጊዜ፥ እየዘመሩና እየዘፈኑ እልልም እያሉ ከበሮና አታሞ ይዘው ንጉሡን ሳኦልን ሊቀበሉ ሴቶች ከእስራኤል ከተሞች ሁሉ ወጡ። ሴቶችም። ሳኦል ሺህ፥ ዳዊትም እልፍ ገደለ እያሉ እየተቀባበሉ ይዘፍኑ ነበር" (1ኛ ሳሙኤል 18፡6)። ማሕበረ ሰብ ደስታውን በሚያውቀው መንገድ ይገልጻል፤ ይህን መካድ አንችልም!

ከሰለሞን ባረጋ ይልቅ የአልማዝ አያና ምላሽ ይገርማል። አልማዝ በ2008 ዓ.ም. ሪዮ ብራዚል ላይ በ10ሺህ ወርቅ ብቻ ሳይሆን የዓለም ክብረ ወሰን በ15 ሴኮንድ ሰብራ አሻሽላለች። አሯሯጧ ታይቶ የማይታወቅ ነበርና ከተፎካካሪዎቿ መሐል (12ኛ የወጣችው) የስዊድኗ ሴራ ላቲ፣ አልማዝ ንጹሕ አትመስለኝም፤ ዕፅ ሳትወስድ በዚህ ፍጥነት ልታሸንፍ አትችልም ብላ ችክ አለች። ጋዜጠኞች፣ ሴራ፣ አልማዝ ዕፅ ወስዳ ነው ትልሻለች፣ ምላሽሽ ምንድነው? ቢሏት፤ ምላሼ? ምላሼማ 1ኛ/ ለዚህ ብዬ ዝግጅት ሳደርግ ነበር 2ኛ/ ወደ ጌታ ጸልዬ ነበር፤ ጌታም ሁሉን አሳክቶልኛል 3ኛ/ ዕፄ ኢየሱስ ነው፤ ምክንያቶቹ እነዚህ ናቸው!

ከዚያ ወዲያ አልማዝ አያናን ጥያቄ የጠየቃት የለም!