አ ይ  ው በ ት፣  አ ይ  ው በ ት

alemay

አለማየሁ እሸቴ በ80* ዓመቱ አርፏል። የሕይወቱ ምእራፍ ሲነበብ ምን ይላል?

ወደድንም ጠላን ከአንድ ማህበረ ሰብ ተገኝተናል፤ ተጎራብተናል፣ ከቅርብ ከሩቅ ተያይተናል፤ ደጃችንን ከፍተን አካም ጅርታ ተባብለናል። በአለማየሁ ውስጥ እኛ አለን፤ እርሱም በእኛ ውስጥ ይኖራል። እኛን ይዞ ነጒዷል።

ከስድሳ በላይ ዓመታት ባንጎደጎዳቸው ቅኔዎቹ፣ ቅላፄዎቹ፣ የማይደገሙ ርክርኮቹ፣ አለባበሶቹ፣ በፀጒር አበጣጠሮቹ፣ በፈገግታ አኳኋኖቹ ተጽእኖ አድርጎብናል። በፈጠራዎቹ ተውበናል። የተመኘናት ውበት እንደ ህልም ሆናብን ተጎሳቊለናል። አይ ውበት፣ አይ ውበት፣ አሟልቶ ሠርቶሻል | እንኳን ሕይወት ያለው አፈር ይመኝሻል ...

እሴቶቻችንን ከባህር ማዶዎቹ ጋር አዳቅሎ አፋፍቶ መልሶ ክሶናል። በቊልምጫችን እና በአክብሮታችን እርሱም ተበራትቷል። በሥራዎቹ ተዝናንተናል። ከአካባቢአችን ወጣ ብለን ሩቅ አልመናል፤ ነፃ ለመውጣት ተጣጥረናል። እንደ አሞራ ሆ፣ እንደ አሞራ ክንፍ አውጥቼ ልብረራ ክንፍ አውጥቼ ልብረራ ...

ደግሞ ስነ ምግባር አስተምሮናል፤ ወላጅን ማክበር፤ ፍትህን መጠማት፤ እጅ አጣምሮ ከማየት መሳተፍን። መማር መማር መመራመር ትርጒሙ ምንድነው? | ሰዎች ሰዎች ተዛዘኑ በዙሪያው ፍጡር ነው | ባንድ ዐይኑ ያለቅሳል ትርጒሙ ጠፍቶት | የቆመበት መሬት ጨለማ መስሎት | ከንፈር መጥጦ ማዘን ጽድቅ አይሆን እርዳታ | ተው እንተዛዘን ጨርሶ አናመንታ።

ባጭሩ፣ አብረን ኖረናል። ዛሬ ለትውልድ የሚብቃቃ የታሪክና እና የባህል ማስታወሻ ትቶልን በአካል ተለይቶናል። የሚገርመው፣ ሦስት ትውልድ ጥያቄው ፍትህ እውቀት እና አብሮነት ነበር፤ ዛሬም ገና ጥያቄው አልተመለሰም፤ ይባስ ተወሳስቧል። ፍትህን በጠመንጃ አፈሙዝ ፈላለግናት፤ ተሠወረችብን! ሽጉጥ መትረየሱን አንግቶታል | ያ ጥቊር ግስላ ደም ሸቶታል አልን። የዛሬ እውቀት አገር ማዳን ቀርቶ የግል እና የጎሳ ግለትን የሚያስቀድም የታነፀነውን የሚያፈርስ ሆኗል። እውነቱ ግን ይህ ነው፦ በእግዚአብሔር ፍርሓት ተግተን ታግሠን ተሳስበን ተከባብረን ካልሆነ እንደ ተቅበዘበዝን እንቀራታለን።

የአለማየሁ እሸቴ በሞት መለየት እንደ አንድ ሕዝብ ያለንበትን ሁኔታ እንድንመረምር ያስገድደናል። ዛሬ ከሞላ ጎደል የቅኔ ኪሳራ ውስጥ ገብተናል። በአብዛኛው ራሳችንን መሆን አቅቶናል። በኢትዮጵያዊነታችን መኲራት ተስኖናል። በፍቅር ንፍገት ደዌ ተመትተናል። ያልተገባቸው ሰዎች በትንሹ ሲካቡ ሲሿሿሙ እያየን ነው፤ ገንዘብ/ብልጽግና የሰውም የእውነትም ልክ እና መመዘኛ ተደርጓል።

ከዚህ ሁሉ በኋላ ልብ ገዝተን ከስህተታችን እንማር ይሆን? የተመደበልን ዕድሜ ሰባ ዓመት ነው፥ ቢበረታ ሰማንያ፤ ቢበዛ ድካምና መከራ ነው፤ ለዚያውም ቶሎ ያልፋል!

እግዚአብሔር ያዘኑትን ያጽናና።

* ምንጫችን እድሜውን 79 ብሎ ነበር፤ ኋላ በ 80 ተክቷል። የአገራችንን ዜና ዘጋቢዎች መተማመን ጨርሶ አይቻልም።

ምትኩ አዲሱ