የጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ካቢኔ

"ተፎካካሪ" ፓርቲዎችን ማካተቱ፣ ብቃትና አገራዊ አንድነትን እንጂ ጎሣን አለማጣቀሱ አዲስ ምእራፍ ነው። ለቂመኛና ለአምባገነናዊ ፖለቲካ እርምት የሚሰጥ ነው። ይህ ባህል እንዲጎለብትና እንዲሠምር አብረን ከመሠለፍ ውጭ አማራጭ የለንም። ክብረ በዓሉ በሰላም ደምቆ ተጠናቅቋል። ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ተከትሎ የኢትዮጵያ ሕዝብ (አዲሱ ትውልድ) የሚበጀኝን እኔ አውቃለሁ አትንገሩኝ ብሏል። እንደ ቀደመው ትውልድ (ኢሕአፓ፣ መኢሶን፣ ኦነግ፣ ደርግ፣ ህወሓት) በትንሽ በትልቊ መቧቀስ፣ ያለ እኔ ላሣር ላይል ዝቶ የተነሳ ይመስላል። ይህን ቊርጠኝነት ያጽናልን!

የዶ/ር ዐቢይን መንግሥት ከተገዳደሩት ጒዳዮች መሓል፣ ከብረት ጦርነት ባልተናነሰ፣ የውጭ ኃይላት ከህወሓት ጋር ተባብረው አገራችን ላይ የከፈቱት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ነው። የወ/ት ፊልሳን አብዱላሂ ከሳምንት በፊት ሥልጣን ለቅቄአለሁ ማለት ከዚሁ ጋር የሚደመር ነው፤ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ እጩ ሚንስትሯ በትግራይ የሴቶች እህቶቻችንን መደፈር እያየሁ በኃላፊነቴ ላይ መቀጠል ለህሊናዬ ይከብዳል ብለው ራሳቸውን አግልለዋል። (በህወሓት ዘመነ መንግሥት ግለሰቦች እንዲህ ሊያደርጒ ቀርቶ አስባችኋል ተብለው የደረሰባቸውን ማስታወስ አያሻንም!) ለማንኛውም፣ ፊልሳን የተቃወሙትን አሳፋሪ ድርጊት መንግሥትም አጣርቶ እና አምኖ እርምጃ ወስዶበታል። ጥያቄው፣ 1/ ወ/ት ፊልሳን በሌሎች አካባቢዎች ተመሳሳይ ወንጀል ሲፈጸም የት ነበሩ? 2/ ያለፈውስ አለፈ፤ ስህተቱ እንዳይደገም የተሰጣቸውን እድል እምቢ ማለታቸው ይልቅ ቅንነት የጎደለው ስንፍና መስሎባቸዋል።

የአዲሱ ካቢኔ ሢሦው በሴቶች መሞላቱ ሌላኛው ተስፋ ሰጭ አሠራር ነው፤ ሴቶቹ ሚንስትሮች የተሾሙት በሴትነት "ኮታ" ሳይሆን በብቃት እንደ ሆነ አንርሳ!

በኢዜማ ሊቀመንበር በፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ላይ ላፍታ እናተኲር። ግለሰቡ በትምህርት ሚንስቴር ላይ መሾማቸው አገራችን ከወደቀችበትና ከተበታተነችበት ልታንሠራራ ይሆን? የተማረ ዜጋ መኖር ለአገር እድገት እና ለዲሞክራሲያዊ አሠራር መሠረት ነውና። ብርሃኑ ምሑር እና ኢኮኖሚስት መሆናቸው ሁለት ተፈላላጊ የእውቀት መስመሮችን በአንድነት በማስኬድ የተፈለገውን ግብ ለመተለም እና ለመተግበር ያስችላል እንበል። የጠ/ሚ ዐቢይ መንግሥት ይህን ሹመት ሲሰጣቸው የትምህርት ጒዳይ አሳስቦት ቢሆን ነው፤ ሙሉ መንግሥታዊ ድጋፍ ለመስጠት ቆርጦ ቢነሣ ነው እንበል።

ህወሓት ለትውልድ የሚተርፍ ጒዳት በአገር ላይ ካደረሰባቸው ዘርፎች መሓል የትምህርት ዘርፍ ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል (ምንም በጎ አልተሠራም ለማለት አይደለም)። 1/ ህወሓት አዲሳባን ሲቆጣጠር 40 ከፍተኛ ብቃት ያላቸውን ፕሮፌሰሮች አባረረ። ትውልድ እንዳይጠቀም በአገር ሃብት የዳበረን የሰው ኃይል በተነ። ዛሬ በማስትሬት ከሚመረቊት አብዛኞቹ የሚጽፏቸው የምረቃ ሰነዶች ጥራት እና ብቃት የማይታይባቸው ናቸው 2/ ትምህርት ሚንስቴርን እንዲመሩ ህወሓት የሾማቸው አድር ባዮችን ወይም ብቃት የሌላቸውን፣ ከበስተኋላ ሆኖ ዓላማውን የሚያስፈጽማቸውን ነበር። በዚሁ ወቅት የትግራይ ክልል ተማሪዎች ከእውነታ የራቀ መረጃ ሲሠጣቸው ኖረዋል (ስለ ትግራይ የበላይነት፣ ስለ ትግራይ የቆዳ ስፋት፣ ወዘተ)፤ በ2008 ዓ.ም. ትምህርት ሚንስቴር ስለዚሁ "ስህተት" ይቅርታ ለመጠየቅ ተገድዷል 3/ በተለይ የዩኒቨርስቲዎች ቋሚ ዓላማ የተለያዩ አስተሳሰቦችን ባህሎችን ማዳቀል፣ ማስተዋወቅ፣ ማቻቻል ሆኖ ሳለ፣ በቂ ዝግጅት ሳይደረግባቸው ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ በየክልሉ ወረዳዎች መገንባታቸው ያስከተለው ችግር ደግሞ አለ። ከጥራት አኳያ ብቃት የሌላቸው መምህራንን ማሠማራት፤ አስተሳሰብን እና አብሮ መኖርን ከመቅረጽ ይልቅ ጎሠኛነትን ማባባስ በብዛት ታይቷል። ጥራት ከጎደላቸው ከሠላሳ አምስት ዩኒቨርሲቲዎች ይልቅ ሃያውን በጥራት እና በበቂ ዝግጅት ማካሄድ ሲቻል። ለከፋፋይ ፖለቲካ ሲባል በመምህርና በተማሪ፣ በመምህራንና በተቋማት አስተዳደር መሓል የማያቋርጥ ግብግብ መፍጠር 4/ ትምህርት ተሟሙቶ ዲፕሎማ መጨበጥ እንጂ ስብእናን ማነጽ፣ ማኅበረሰብን መቅረጽ ግቡ አለመደረጉ።

የትምህርት ሚንስትሩ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ትልቅ ብልሃት የሚሻ ትልቅ ውጣ ውረድ ከፊታቸው ይጠብቃቸዋል። ፈር በማስያዝ ሂደት ውስጥ ከውጭም ከውስጥም የተጠላለፉ የተሠለፉ ብዙ ኃይላት አሉ። በዝግታና በስፋት አሠሣ ማድረግ፣ አብረዋቸው የሚሠሩትን ዓይነተኛ ግለሰቦችን ማደራጀት ግድ ነው። ውሳኔን ባፋጣኝ ተግባራዊ ለማድረግ መሞከር ተቃውሞ ሊያነሳሳ እንደሚችል አለመርሳት፤ ገንዘብ ከለመዱ ከግል የገበያ ትምህርት ቤቶች፣ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከክልል ጽ/ቤቶች፣ ከሙያ ነክ ትምህርት ተቋሞች፣ ከውጭ ትምህርት ሰጭ ድርጅቶች፣ ወዘተ። በብቃት ሳይሆን በጎሣ ኮታ ለፖለቲካ፣ ለስለላ የተሠማሩ፣ ጒቦ የለመዱ ሁሉ ከተሠገሠጉበት ሆነው በቀላሉ ይተባበራሉ ማለት ዘበት ነው!

የትምህርት ይሁን የልማት ፖሊሲዎች ቀዳሚ ችግር አዲስ አሠራር መቅረጽ አለመቅረጽ ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ተግባራዊ አለማድረግ ነው። ለክቡር የትምህርት ሚንስትሩ ምን ምክር አለን? 1/ በመደበኛ ከሪኲለም ያልታቀፉ አገር ገንቢ ትምህርቶችን በሚንስቴር መ/ቤቱ ራዲዮና ቲቪ አገልግሎቶች ማስተላለፍ። የፕሮግራሞችን ዝግጅትና ኃላፊነት ከፍተኛ ብቃት ላላቸው ግለሰቦች መስጠት፤ 2/ የታሪክ ትምህርት ከወደቀበት እንዲያንሠራራ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ። ከክልል ውጭ ያሉ አካባቢዎችን ኩታ ገጠምነት ማጤን። ከዚህ ባልተናነሰ መንገድ የውጭው ዓለም (አጎራባች አገሮችን ጨምሮ) እንዴት እንደ ተደራጀ ማጤን፤ 3/ በተለይ በ1964 ዓ.ም. የአፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት ቀርፆት የነበረውን "ኢጁኬሽን ሴክተር ሪቪው"ን በጥንቃቄ ማጥናት እና ማጣቀስ። ፋሺስት ኢጣልያ የአገራችንን ምሑራን በመጨፍጨፍ ከፈጸመብን በደል በላይ እኛው በኛው ላይ የፈጸምነው ብሷል። "ሴክተር ሪቪው" ተግባራዊ እንዳይሆን ደንቃራ የሆኑት በቅድሚያ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና የጊዜው አብዮተኞች ነበሩ። የኃይለሥላሴ መንግሥት የገበሬ ልጅ ገበሬ፣ የልብስ ሰፊ ልጅ ልብስ ሰፊ፣ የቀጥቃጭ ልጅ ቀጥቃጭ ወዘተ ሆነህ እንድትቀር እያሤረብህ ነው ብለው ሥልጣን ላይ ለመወጣጫ ሕዝብ አበጣብጠውበታል (ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን ጨምሮ)። ያኔ ቢተገበር የት በደረስን! ስንት ጥፋት እና ድንቊርና ባመለጥን! የህወሓት መሪዎችም ከዚሁ መሓል የተገኙ ናቸውና ተራ ሲደርሳቸው የራሳቸውን የባሰበት ስልት ፈጠሩ፤ ለአገር ግን ኪሣራ ሆነ።

"ሴክተር ሪቪው" ዓላማው ባጭሩ ሦስት ነበር፤ 1/ መደበኛን ትምህርት በቀላሉና በፍጥነት ማዳረስ 2/ በቊጥር ከ80 ፐርሰንት በላይ ለሆነው ለአርሶ እና ለአርብቶ አደር ሕዝብ የሚመጥን፣ አኗኗሩን የሚቀይርበትን እቅድ በመንደፍ የተሳትፎ እድሉን ማስፋት 3/ ፖሊሲው በአገር ልማት ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ እንዲኖረው ማመቻቸት፤

መልካም የአገልግሎት ዘመን!

መስከረም 2014 ዓ.ም.