rescue

ግ ን ዛ ቤ፣ ኢ ት ዮ ጵ ያ ች ን ን  ለ ማ ዳ ን  ቆ ር ጠ ን  ስ ን ነ ሳ

መዝ ኃይሌ

አሁን ለንዴት፥ ለቁጣም የሚሆን ምክንያት አግኝተናልና፤ በዚህ አጋጣሚ እንኳን ቢሆን፥ ስለ እውነት ስንል ኢትዮጵያችንንም ለማዳን ስንል እንነሳ። እስቲ እናንት በሳል ፖለቲከኞች፥ ተመራጭ መሪዎቻችንም ላንድ አፍታ ዝም ብላችሁ አዳምጡን፤ እስቲ እናንት የኢትዮጵያ ልጆች እስከ ዛሬ ያጠፋናቸውን እና የተሳሳትንባቸውንም ለማየት እንሞክር፣ ካለአንዳች ፍርሃት።

የፍልስፍና ጥቊረት

[በዚህ ጽሑፍ “የጠቆረ ፍልስፍና” የምንለው ሁሉ፥ አገር ጥርት ባለ ፍልስፍና ካልተመራች ብዥታን፥ አጉል መደናበርን የሚያስከትል ስለሆነ ነው]
ሀ) ከአገር ህልውና ብልጽግና ይቀድማል ብሎ ማሰብ ስህተት ነው። የአገር ብልጽግና ረጅም ጊዜ የሚፈጅ፥ የአገር ህልውና ግን ጊዜ የማይሰጥ ነው። መንግሥት ሁለቱን ጎን ለጎን በማድረግ የሠራቸው አያሌ በጎ ሥራዎች ቢኖሩም፥ ቅድሚያውን ለአገር ህልውና ባለመሥጠት (ወይም በቸልተኝነት) የተነሳ፥ በጠላት እጅ መውደቅን (ወይንም መቀደምን) አስከትሏል ባይባልም፥ እንደ አንድ ስህተት ሊቆጠር ይችላል።
ለ) ከመሠረታዊ ለውጥ ይልቅ ሪፎርም (ጥገና) ይሻላል ብሎ ማሰብ በጠቆረ ፍልስፍና ውስጥ መንከላወስ ነው። ምኑ ይጠገናል የተበላሸ ስርአት? የአንድን አገር መንግሥት በአንድነት፥ በሰላም፥ በእኩልነት እና በነጻነት፥ ጸንቶ እንዲቆይ የሚያደርግ የሶሻል፥ የፖለቲካና የኢኮኖሚ መመሪያ ሳይዝ የተነሳ መንግሥት ነው ጥገናን የሚወድ። “ይጠና፥ ይጠና፥ ..” እያሉ ጊዜ የማይሰጡ አቢይ የአገር ጉዳዮችን ወደ ጎን ዞር ማድረግ፥ የሕዝቡንም ትኩረት ወደ ሌሎች አናሳ ጉዳዮች ላይ እንዲሆን መገፋፋት ነው። በዚህ አንጻር ሲታይ፥ “ሪፎርም” የተባለው ቃል ካለቦታው ውሏል፤ የእውነተኛ ለውጥ ሽፋን እንዲሆን እንጂ፥ ወያኔ በዘር ላዋቀረው ፌዴራላዊ መንግሥት የተሻለ አማራጭ ለማምጣት የአገራችን ምሁራን በአመታት ሳይሆን በወራት የሚያጠናቅቁት የቤት ሥራ ይሆን ነበር (ይህንን ማከናወን ደግሞ መፈንቅለ መንግስተኝነት ወይንም ሪቮሉሺን አይደለም)።
ሐ) ከደርግ በኋላ ወያኔ (ኢሕአዲግ) ሥልጣን ሲይዝ አንግቦት የተነሳውን አላማ ካለመረዳት ወይንም የአላማው ደጋፊ በመሆን፥ ወይንም መሃል ሠፋሪ በመሆን በተሠሩ ተንኮሎች ላይ ግልጽ አቋም አለመውሰድ ብዥታን፥ አጉል መደናበርን አስከትሏል።

የሕዝቦችን ጩኸት አለመስማት

ሀ) የዚህ እና የዚያ አካባቢ የሕዝቦች ጩኸት፥ እሮሮ፥ ልቅሶ፥ ምንድነው ምክንያቱ ብሎ አለመጠየቅ እና ስሜታቸውን በመረዳት፥ በተግባር እንኳን ባይሆን በስሜት አብሮ ለመሆን አለመሞከር በሕዝቦች ዘንድ አመኔታን ያሳጣል፤ አመኔታ ሲጠፋ አብሮ መሥራት ያስቸግራል፤ የሚከተለውም አለመግባባት እስከ ጦርነት ሊያደርስ ይችላል።
ለ) የሕዝቦችን ጩኸት አለመስማት ወይንም ስሜታቸውን ከአለመረዳት ከሕዝቦች በበጎ መንፈስ ሊፈልቅ የሚችል፥ ለአገር አንድነት እና ጥቅም የሚውል ሃሳብ ይቀራል፤ እናንተ ዝም በሉ፤ እኔ ነኝ የማውቅላችሁ፤ እኔን ብቻ ስሙ ማለት ደግሞ የአምባ ገነኖች (ዲክቴተሮች) ጠባይ ነው። ይህ ስህተት በጊዜው ቢታረም ኖሮ፥ አሁን “ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ውይይት ይደረግ” የሚባለውም ባላስፈለገ፥ ወይንም ተፈላጊነቱ በቀነሰ ነበር፤ ምክንያቱም በዲሞክራሲ ምርጫ የተመረጠ መንግሥትም ቢሆን ራሱ ዲሞክራሲን የሚለማመደው የሕዝቦችን ጩኸት ሰምቶ፥ “ምን ላድርግላችሁ? ምን እናድርግ?...” እያለ ምክርን በየጊዜው ከሕዝቦች እየተቀበለ ሲሆን ነው።
ሐ) የሕዝቦችን ጩኸት እየሰማ የማይንቀሳቀስ መንግሥት በቶሎ ሊያድግ ያስቸግረዋል፤ ምክንያቱም እድገት (ብልጽግናም) የሚፋጠነው በህብረት ሲሆን ነውና።
መ) ሀብት ንብረት ሲዘረፍ፥ ሰው ሲገደል፥ ሲፈናቀል የቆየው (እስካሁንም የቀጠለው)፥ በአብዛኛው የሕዝቦችን ጩኸት ከአለመስማት የተነሳ ነው እንጂ፥ አላስፈላጊ ግጭቶችን (ጦርነቶችን) መከላከል ያን ያህል ከባድ ሆኖ አይደለም።

ግላዊ የሰው ልጅ ጠባይ

ሀ) እጅግ ሲበዛ ጥሩ ወይንም እጅግ ሲበዛ ቸልተኛ ሰው መሆን፥ የክፉዎችን ሴራ (ተንኮል) ለመረዳት እና ወቅታዊ እርምጃ ለመውሰድ አያበቃም፤ እጅግ ሲበዛ ብልጣብልጥ መሆን ደግሞ፥ ለግል ከማሰብ ጋር (ከሥልጣን ጥም) ጋር ከተያያዘ ታላቅ አደጋን ያስከትላል።
ለ) ኢትዮጵያ ብዙ ጥሩ ሰዎች አሏት፤ ግን የሁላችንም (ወይንም የአብዛኛዎቻችን ችግር) ሰውን (በተለይ የአገር መሪን) ስህተት በመንቀፍና በመተቸት ፋንታ ውዳሴ ከንቱ እናበዛበታለን። ያ ውዳሴ ከንቱ ለግለሰቡ ለአገርም (ለማንም) አይጠቅምም።
ሐ) በኢትዮጵያችን ውስጥ ጥሩውን ነገር በተግባር ከማሳየት ይልቅ ማንም (ለተማረም ላልተማረም) ገሃድ የሆነውን ነገር ሁሉ በመደጋገም ታላቅ ሥራ የተሠራ ማስመሰል ከእውነተኛ አገር ወዳድነት የሚመነጭ የሰው ልጅ ጠባይ አይደለም።
መ) ባሁኑ ወቅት ውሸት ከታክቲክ ደረጃ አልፎ እስትራተጂ ወደ መሆን የተቃረበ የፕሮፓጋንዳ መሳሪያ ሆኗል (መስሏል)፤ ለጊዜው እየመሰለን ነው እንጂ፥ እውነትን ብቻ ይዞ መጓዝ ነው የሚጠቅመው።
ሠ) ተመራጭ ፖለቲከኞቻችን ባለ ሁለት መላስ ሆነው (ዛሬ የተናገሩትን ነገ ሲያጥፉት) በሕዝቡ ዘንድ ታማኝነታቸው ይቀራል። የሚያስፈራው ግን ይህ ብቻ አይደለም፤ ሕዝቡም የነርሱን ሁለት መላስ ተከትሎ ለሁለት ይከፈላል፤ የሕዝቦች አንድነት ይሸረሸራል። በተለይ አገሪቷን የሚያጨናንቅና የሚፈትን ጊዜ ሲመጣ፥ የነርሱ ዝም ማለት ነው የሚሻለው።

በክፉው ስርአት ላይ አለመዝመት

ሀ) በክፉው ስርአት ላይ አለመዝመት፥ መድኃኒቱ እያለ ታሞ መማቀቅን መምረጥ ይመስላል።
ለ) የክፉውን ስርአት ክፋት ባለመገንዘብ፥ ወይንም “እርሱን ለኛ ተዉት” እያሉ በመቆየት በብዙዎቻችን ላይ የአይምሮ የጭንቀት በሽታ ያመጣ፥ ታማሚዎች ያደረገን፥ ሰሚ ያሳጣን የሃሳብ እስረኞች ያደረገን መሆኑን አለማወቅ ይመስላል።
ሐ) በክፉው ስርአት ላይ አለመዝመት ወይንም ዝም ብሎ ማየት ሊናደፍ ሰተት ብሎ የሚቀርብን እባብ እንደማይተናኮል ቆጥሮ እርሱን ለማስተናገድ እንደ መሞከር ይቆጠራል። በሰሜን ለተከሰተው ጦርነትም አንዱ ምክንያት እንደ ሆነ፥ ይህንን አለመረዳት ከምን የተነሳ ነው? ጦርነት ማለት በጠመንጃ (በአካል) መዋጋት ብቻ አይደለም፤ የሃሳብ ጦርነትም በማካሄድ አገራዊ እውነቶች በውሸቶች ላይ ድልን እንዲቀዳጁ ማድረግ ያስፈልጋል።
መ) በክፉው ስርአት ላይ አለመዝመት ወይንም ይህንን እንደ ቀላል ነገር ማየት፥ ከሁሉም የባሰ የፍልስፍና ጥቁረት መሆኑን እንመልከት፤

“ሰዎች (ብሄረሰቦች) በክልል በክልሉ እየሆኑ እራሳቸውን ቢያስተዳድሩ ምናለበት፥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሰላም አብሮ እንዲኖር የሚያደርገውን ሁኔታ እስከፈጠርንለት ድረስ...?” የሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው። ምክንያቱም፥ ገና ከጥንቱም ይህ እንዳይሆን ስለተፈለገ ነው ዘረኛነት ለ27 ኣመታት ሲሰበክ የቆየው (የወያኔ መንግሥት የሰውን ልጅ ዳግመኛ ፈጥሮታል! አማራውን ትግሬ እያደረገ፤ የኢትዮጵያችንንም ታሪክ እያጠለሸ....)።

የጋራ ታሪካችንን በማሳጣት፤

ትግሬዎች “የኢትዮጵያ ታሪክ ተብሎ የሚተረከው የኔን ቀምተው ወይንም የኔ ብቻ ነው..” እንዲሉ በማድረግ፤
ኦሮሞዎች “የኢትዮጵያ ታሪክ ተብሎ የሚተረከው የኔን ቀምተው ወይንም የኔ ብቻ ነው..” እንዲሉ በማድረግ፤
አማሮች ““የኢትዮጵያ ታሪክ ተብሎ የሚተረከው የኔን ቀምተው ወይንም የኔ ብቻ ነው..” እንዲሉ በማድረግ፤

መደምደሚያ

ከላይ የተዘረዘሩት ሁሉ በጥሞና አለመመልከት፥ ወይም ችላ ማለት የእውቀት ማነስ ብቻ ሳይሆን፥ ከክፉዎች ጋር መተባበርን ነው የሚያመለክተው። በአገራችን ውስጥ በየጊዜው ሲካሄድ ለነበረው ጦርነት እና መፈናቀል ዋናው ምክንያት ትህነግ በሕገ መንግሥቱ ያረቀቀው ሕዝቦችን በብሄር እና በክልል ባስቀመጠው፥ በዘር ላይ በተመሠረተ ፌዴራሊዝም ሳቢያ የመጣ መሆኑ እየታወቀ፥ ይህም አሁን እና ለወደፊትም የሚያስከትለውን መዘዝ በደንብ አለመረዳት፣ ወይም ችላ መባሉ፥ መንግሥት እጅግ በጠቆረ ፍልስፍና ውስጥ እንደሚዋዥቅ ያሳያል። ለምሳሌ፥ ለሕዝቦች እስከ መገንጠል መገንጠልንም ጨምሮ የሚያበቃውን ዲሞክራሲያዊ መብት በሕገ መንግሥት ማጽደቅ ምንም ክፋት ላይኖረው ይችላል፤ “ያ ብሔር ብሔረሰብ የተባለው ማነው በኢትዮጵያችን ምድር?” ብሎ ለማወቅ የፈለገ ግን በኢትዮጵያ ውስጥ ስንት ብሄር አለ? የትኛው ብሔር ነው ብቻውን የኖረ? የሚሉትን እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎችንም አብሮ በመጠየቅ ይህ በብሔሮች የተዋቀረ የፌደራል መንግሥት ትህነግ ለተንኮልን የቀየሰው ዘዴ መሆኑን ያሳውቀዋል።

“ያ ብሔር ብሔረሰብ የተባለው ማነው በኢትዮጵያችን ምድር?” ብሎ መጠየቅ ሲገባ በኢትዮጵያችን ላይ ከተሠራባት ተንኮል ጋር አብሮ መቆየት ነው ያቆሰለን። የክልሎቹም የጂኦግራፊ አቀማመጥ ኢትዮጵያችንን ለመከፋፈል (ለማፍረስ) ታስቦበት የተቀየሰ መሆኑን፥ ብሎም የትግራይ የመገንጠል ፍላጎት ለማሳካት፥ ኦሮሞንም ወዲያ ብሎ፥ አማራንም ወዲያ ብሎ.፥ ኢትዮጵያን አፍርሶ፥ ሌሎች ትናንሽ መንግሥታትን ሲመሠርቱ ትግራይ ከጎን ብድግ ብላ ኃያል መንግሥት እንድትሆን የታቀደ መሆኑን በቀላሉ መረዳት አያዳግትም።

ባጠቃላይ ኢትዮጵያን እና የሕዝቦቿን የጋራ ማንነት (የጋራ ታሪክ፥ የጋራ ባህል፥ የጋራ ቋንቋ...)፥ የጋራ የሆነ ሁሉ እንዲጠፋ በማድረግ እጅግ የከፋ ተንኮል ስላለ፥ ይህንን ተንኮል ለመስበር ሪፎርም (ጥገና) የሚሉት ፈሊጥ በቂ አይደለም፤ ስር ነቀል መንግሥታዊ መዋቅራዊ ለውጥ ያስፈልጋል። የጋራ ብልጽግና (የጋራ እድገት) የሚታሰበው (ዘላቂነትም የሚኖረው) ከዚያ በኋላ ነው።

ማስጠንቀቂያ

እኛ ኢትዮጵያኖች (ትግራይ፥ አምሃራይ፥ ኦሮማይ....) ደጎች ጥሩዎች ነን፤ ግን የተጠቀሱትን ሁሉ አይተን፥ ተገንዝበን ዝም የምንል ከሆነ፥ የኛ ደግነት እና ጥሩነት ለወደፊቱ ትውልድ ምንም ጠቀሜታ አይኖረውም፤ ይልቁንም፥ የእኛ ዝም ማለት ከተንኮለኞች ልፈፋ ጋር ተጣምሮ ለወደፊቱ ትውልድ (ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪቃም) አስጊ ሁኔታን ነው የሚፈጥረው። ስለዚህ እናስብበት።

© መዝ ኃይሌ፣ 2014 ዓ.ም. | 2022

ኢትዮፕያንቸርች የዚህን ጠቃሚ ጽሑፍ ሙሉ አሳብ አይጋራም። ጨዋነት በተመላ አገላለጽ፣ ለአገር ኅልውና በመቆርቆር የተፃፈ በመሆኑ ግን አትመነዋል። አራት ዓመት ያልሞላውን የጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድን አስተዳደር በአግባቡ መገምገም እጅግ አዳጋች ነው። ምክንያቱም፣ አገራችን ለሃያ ሰባት ዓመታት የተጓዘችበት ጎዳና ስውርና ውስብስብ በመሆኑ።