ፍቅር ባስተርጓሚ አይሆንም
ከአራት ዓመት በፊት “ቋንቋን በቋንቋ፦ ቋንቋህ ያስጠላል፤ ቋንቋዬ ይበልጣል” በሚል ርእስ በዚህ ድረገጽ ላይ መለጠፋችን ይታወሳል። የጒዳዩ መነሻ፣ ትህነግ ያካሄደው የነበረው አፍራሽ የቋንቋ ፖሊሲ ነው። ፖሊሲው ግራ አጋቢ ከመሆኑም በላይ፣ ለአክራሪ ፖለቲከኞች መፈንጫነት ውሎ ነበር። ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ከያዙም በኋላ ጒዳዩ አልረገበም፤ እንዲያውም ተባብሷል። ባለፈው ወር፣ የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ጽሑፍ መነሻ በማድረግ፣ ኦሮምኛ በቊቤ (ላቲን) ሳይሆን በፊደል መፃፍ አለበት የሚል አሳብ፣ ኢሳት ቲቪ ቀስቅሶ ነበር። ከሚሠዘነሩት አስተያየቶች አንፃር፣ የብዙዎች ፍላጎት የአገርን አንድነት ማስከበር ነው። በጎ አሳብ ነው። በጎ መመኘት ግን በእውቀት ካልተደገፈ በቀር፣ ለአንዳንዶች የሥጋት ምንጭ መሆኑ አልቀረም። ውይይቱን በደም ፍላት ሳይሆን በመረዳት ላይ መመሥረት ያስፈለገው ለዚህ ነው። 1/ ኦሮምኛ በላቲን ይሁን ውሳኔው፣ የፖለቲካ ውሳኔ ነው 2/ ወዲያው፣ በፊደል እንጂ በላቲን መሆን የለበትም የሚል ከፍተኛ ተቃውሞ አስነሳ፤ ጒዳዩ በአክብሮትና በማስተዋል ባለመያዙ ተባባሰ፤ አሁን ያለንበት ደረጃ ላይ ደረሰ፤ 3/ ኦሮምኛ በላቲን ዛሬ የአንድ ትውልድ መገበያያ ሆኗል፤ መቀልበስ ቀላል አይሆንም። ውይይቶች በምክክርና በጋራ ጥቅም ላይ ሳይመሠረቱ ከድጡ ወደ ማጡ ናቸው 4/ ከአንድ በላይ ፌዴራል ቋንቋ መጠቀም እንደ ተፈራው አፍራሽ እንዳይደለ ከአገራት ታሪክ ማየት ይቻላል። “ቋንቋን በቋንቋ” ከጠቆማቸው መፍትሔዎች አንደኛው፣ ኦሮምኛ ተናጋሪ አማርኛን፣ አማርኛ ተናጋሪ ኦሮምኛን በትምህርት ቤት እንዲማር የሚል ነው። ከታች የተመለከተው ጽሑፍ ምንጩ ቢቢሲ አማርኛ ነው፤ ቅንነት እና ትጋት ካለ ብዙ የምንናቆርባቸውን መፍታት እንችላለን የሚል አሳብ ያዘለ ነው። ~ ኢትዮፕያንቸርች አዘጋጅ፣ 12/21/22
በሦስት ዓመት ኦሮምኛ ተምሮ የቋንቋውን መማሪያ መጽሐፍ ያዘጋጀው የህክምና ዶክተር
ትውልድ እና እድገቱ ሰሜን ኢትዮጵያ ጎንደር ከተማ ነው። ኦሮምኛ ሲናገር ለሰማው ግን ዕድገቱ በኦሮሞ ማኅብረሰብ ውስጥ ሊመስለው ይችላል። የ30 ዓመቱ ዶ/ር ሃብታሙ ገበየሁ ኦሮምኛ ቋንቋ አንድ ብሎ መማር የጀመረው ግን ከሦስት ዓመታት በፊት ነበር። አሁን ላይ ቋንቋውን አቀላጥፎ ከመናገሩ ባሻገር ቋንቋውን ለመማር የሚያግዝ የኦሮምኛ ቋንቋ ሰዋሰው መጽሐፍ ማዘጋጀት ችሏል።
በአዲስ አበባ ከተማ በአንድ የጤና ተቋም ውስጥ በጤና ባለሙያነት እያገለገለ የሚገኘው ዶ/ር ሃብታሙ፤ ቋንቋ ለማወቅ ያለው ጥልቅ ፍላጎት የጥረቱ አንዱ ስኬት መሆኑን ይናገራል። “ከድሮ ጀምሮ የኦሮምኛ ቋንቋን የመማር ፍላጎት ነበረኝ። በአገራችን ብዙ ቋንቋዎች ይነገራሉ፤ ከእነዚህ ቋንቋዎች እኔ የማውቀው የአፍ መፍቻ ቋንቋዬ የሆነውን አማርኛ ብቻ ነበር። ቢያንስ አንድ ተጨማሪ ቋንቋ መልመድ አለብኝ የሚል ፍላጎት ነበረኝ” ይላል። ዶ/ር ሃብታሙ በሥራ ገበታው ላይ በተለይ ከአዲስ አበባ ዙሪያ ከሚመጡ እና ኦሮምኛ ቋንቋ ብቻ ከሚናገሩ ታካሚዎቹ ጋር መግባባት እጅጉን አዳጋች ሆኖበት እንደነበረ ያስታውሳል።
ዶ/ር ሃብታሙ ከታካሚዎቹ ጋር በአስተርጓሚ አማካይነት መግባባትን ባለመምረጡ በሥራው ላይ ያጋጠመው ፈተና እና ቋንቋ የመማር ፍላጎቱ ተደማምሮ ኦሮምኛ መማር እንዲጀምር እንዳስቻለው ገልጿል።
የመጀመሪያዎቹ 500 ቃላት
“ባለቤቴ ብዙም ባይሆን የተወሰነ የኦሮምኛ ቋንቋ ችሎታ አላት። መማር የጀመርኩት እርሷ የምታቃቸውን ቃላት ነው” ይላል የጤና ባለሙያው። “ቋንቋውን የሚያውቁትን በመጠየቅ፣ ከኢንተርኔት እንዲሁም መዝገበ ቃላት በማጥነት... እስከ 500 ቃላት ተማርኩ” ይላል። ዶ/ር ሃብታሙ ቃላቶቹን ይወቅ እንጂ ቃላቶቹን ሰካክቶ በትክክለኛ ሰዋሰው ዓረፍተ ነገር መስራት ቀላል እንዳልነበረ ያስረዳል።
“ቃላቶቹን በመደርደር ዓረፍተ ነገር በመስራት ቋንቋውን መጠቀም አልቻልኩም። ስለዚህ የኦሮምኛ ቋንቋ አጠቃቀም ሥርዓት (ሰዋሰው) የሚያስተምር መጽሐፍ ካለ ብዬ ፍለጋ ተነሳሁ።” ነገር ግን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባሉ ቤተ-መጽሐፍት ቢያፈላልግም ሊያገኝ አልቻለም። ማግኘት የቻለው በኦሮምኛ የተጻፉ መዝገበ ቃላት እና ንግግር የሚያስተምሩትን ብቻ ነበር።
ዶ/ር ሃብታሙ በዚህ ተስፋ ባለመቁረጥ ሌላ መፍትሄ ማፈላለግን ያዘ። “በዚህ ተስፋ አልቆረጥኩም፤ ወደ ቋንቋ ትምህርት ቤት ሄድኩ። እነሱም የቋንቋ ሰዋሰው የሚያስተምሩት በግል እንጂ በቡድን እንዳልሆነ ነገሩኝ። ማወቅ የፈለኩት የቋንቋውን አጠቃቀም ሥርዓት ስለሆነ ወጪ አውጥቼ ተማርኩኝ።” በመቀጠል በኦሮምኛ የተጻፉ መጽሐፍን በማንበብ የማንበብ ችሎታውን ማዳበሩን ቀጥሎ፣ በኦሮምኛ መናገር እና መጻፍን በደንብ አድርጎ ለመቻል በቃ። በዚህም እንደ እሱ ቋንቋውን በራሳቸው ለመማር ፍላጎት ያላቸው ሰዎችን የሚያግዝና ኦሮምኛ ቋንቋ ለመማር የሚያስችል መጽሐፍ አዘጋጀ። ሪቂቻ - የኦሮምኛ ሰዋሰው [ሪቂቻ - ሴርሉጋ አፋን ኦሮሞ] የሚል መጽሐፍ ለጀማሪዎች ማዘጋጀት ችሏል። “ቋንቋውን ስማር የቋንቋውን ሥርዓት በአፍ መፍቻ ቋንቋዬ የሚያስተምር መጽሐፍ ባለማግኘቴ ይህን ክፍተት ለመሙላት ነው ይህን መጸሐፍ የጻፍኩት” ይላል ይህ የጤና ባለሙያ። በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ጤና እንጂ ቋንቋ ወይም ሥነ-ጽሑፍ አልተማርኩም የሚለው ዶ/ር ሃብታሙ፤ የቋንቋውን ሰዋሰው የማዘጋጀት ትክክለኛው ሰው ባይሆንም፣ ያጋጠመውን ክፍተት ለመሙላት መጽሐፉን እንዳዘጋጀ ይናገራል። ዶ/ር ሃብታሙ ከታካሚዎቹ ጋር በቋንቋቸው መግባባት መቻሉ ትልቅ ስኬት ነው ይላል።
ኦሮምኛ መማር ምን ያህል ከባድ ነው?
አማርኛ ተናጋሪዎች ኦሮምኛ ቋንቋ መልመድ ይቸግራቸዋል የሚል እምነት ነበረኝ የሚለው ዶ/ር ሃብታሙ፤ ቋንቋውን ለማወቅ ጥረት ማድረግ ከጀመረ በኋላ “አማርኛ የሚናገር ሰው በቀላሉ ኦሮምኛ መማር እንደሚችል እኔ ምስክር ነኝ” ይላል።አሁን ላይ ኦሮምኛ ተናገሪ የሆኑ ታካሚዎቹን በቋንቋቸው ‘ህመም የሚሰማዎ የቱጋር ነው?’ ብሎ በመጠየቅ በቀጥታ መግባባት መቻሉ “ለእኔ ትልቅ ስኬት ነው” ይላል የ30 ዓመቱ ወጣት። “አሁንም ቋንቋውን ተምሬ አልጨረስኩም፤ እስካሁን በደረስኩበት ደረጃ ታካሚዎች ጋር በቀላሉ ተግባብቼ ሳስተናግዳቸው ፊታቸው ላይ የማየው ደስታ እና አመስግነውኝ ሲሄዱ ለእኔ ትልቅ ደስታ ነው” ይላል። “የመጽሐፌ ርዕስ ‘ሪቂቻ’ ይላል። ሪቂቻ በአንድ ወንዝ ላይ የሚገነባ በተለያዩ ሁለት ቦታ ላይ የሉ ሰዎች የሚያገናኝ ድልድይ ማለት ነው።
“ከዚህ በተጨማሪም በእኛ ማኅብረሰብ ውስጥ ‘ቋንቋ ወንዝ ያሻግራል’ ይባላል። ለዚህ እሳቤ እውቅና ለመስጠት በማሰብ ጭምር ነው መጽሐፌን ‘ሪቂቻ’ ስል የሰየምኩት” ይላል ዶ/ር ሃብታሙ። የጤና ባለሙያው ቋንቋውን መማር ለሚፈልጉ መጽሐፍ ብቻ አዘጋጅቶ ቁጭ አላለም። በማኅበራዊ ሚዲያ መተግበሪያ የቴሌግራም ቡድን ፈጥሮ ፍላጎት ያላቸውን እያስተማረ ይገኛል።
ዘጋቢ፦ ኤልያስ ሙሉጌታ ሆርዶፋ (ቢቢሲ አማርኛ) https://www.bbc.com/amharic/articles/c0379e6vmllo
ቋንቋን በቋንቋ ያንብቡ