ቃለ ምልልስ ከዳዊት [ዳኒ] ወልዴ ጋር

“በቀድሞ ዘመን የተዘመሩት መዝሙሮችና የድምጽ ውህደቶች የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት የሙዚቃ መሠረቶች ናቸው”

dannywoldeዳዊት የሙዚቃ ኪነ ጥበብ ሰው ነው። ቦስተን አሜሪካ ከሚገኘው ስመ-ጥር በርክሊ ኮሌጅ በአውሮጳዊ ሙዚቃ ሠልጥኗል። ቀደም ሲል በአዲስ አበባ መካነ ኢየሱስ እና በሙሉ ወንጌል ቤተክርስቲያኖች በዘማሪነት በኳየር መሪነት በመዝሙር ደራሲነት እና በዜማ አቀናባሪነት አገልግሏል። ዳዊት ብዙ ተሰጥዖ ያለው ወጣት ሲሆን የአገሬውን ባህልና ታሪክ ሳይጥል ከዘመናዊው ጋር ለማቀራረብ አንዱን በሌላው ለመተርጎም ከሚጥሩ ጥቂት የትውልዱ መሪዎች መካከል ነው። mezmur91.com የተሰኘ ድረ ገጽ ባለቤት ነው። Ethiopianchurch.org ዋነኛ በሆነ በዝማሬ ጉዳይ እና በክርስቲያናዊ አገልግሎት ዙሪያ አሳቡን እንዲያካፍለን በፈረንጆች 2009 አነጋግረነው ነበር። መጠይቁ እጅግ ጠቃሚ ሆኖ ስላገኘነው በድጋሚ አትመነዋል - 9/23/15።

ኢትዮፕያንቸርች። ወደ ሙዚቃ ዓለም እንዴት ልትገባ ቻልክ? የዘማሪነት ጥሪ ያለህ ይመስልሃል? ወይስ ጥሪህ ምንድነው ትላለህ?

ዳዊት። ከህጻንነቴ ጀምሮ በክርስቲያን ቤት ውስጥ ሰላደግኩና ታላላቆቼም ዘማሪዎችና ሙዚቃ ተጫዋቾች ሰለነበሩ ከዚያ የተነሳ ይመስለኛል። አዎን ይመስለኛል። 

የአንጋፋውን ዘማሪ የአዲሱ ወርቁን “እጄን ይዞ መራኝ ጌታዬ” የምትለዋን መዘመር እንዴትና ለምን አሰብክ? በተለይም የ “ድሮ” መዝሙሮችን መዘመር በቀነሰበት ወቅት? ሌሎች መዝሙሮችን እንደዚሁ መዘመር አስበሃል?

የቀድሞዉን እና የአሁኑን ትዉልድ የዝማሬ ስታይል ለማቀራረብ በማሰብ ነዉ። እኔ እንደማስበው በዚያ ጊዜ የተዘመሩት መዝሙሮች በተለይ የሙሉ ወንጌል ኳየር፣ የተስፋዬ ጋቢሶ፤ የደረጀ ከበደን የመሳሰሉት ዜማዎችና የድምጽ ዉህደቶች የኢትዮጵያ ወንጌላውያን ቤተክርስቲያን የሙዚቃ መሠረቶች ናቸው ብዬ በጣም አምናለሁ። በአብዛኛዉ በአምልኮ ጊዜ እና በምጋበዝበት የአገልግሎት ቦታዎች ሁሉ የድሮ መዝሙሮችን በብዛት እዘምራለሁ፤ 

አንድ ቅጽ መዝሙሮች አሳትመሃል። ዜማ፣ ድርሰትና ቅንብሩን ራስህ ነው የሠራኸው ወይስ የተባበሩህ አሉ?

አዎን። ታላቅ ወንድሜ ሳሚ በግጥም የረዳኝ መዝሙሮች አሉ። “ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፣ የለም የሚመስልህ” የሚለውንና ሌሎችም ብዙ የሚታወቁ መዝሙሮችን የጻፈ ስለሆነ በመዝሙር አጻጻፍ ብዙ ረድቶኛል።  ዜማዎቹን እኔ ነኝ የፃፍኩት፡ ቅንብሩንም ። በተጨማሪ ሲዲው ሽፋን ላይ በእያንዳንዱ መዝሙር ላይ ማንኛዉንም አይነት እገዛ ያደረጉ ሰዎች ስም በዝርዝር ተጽፏል።

መዝሙር ስትደርስ ከአሳቡ ጥንስስ ጀምሮ አድማጭ ጆሮ እስከሚደርስ ያለውን ውጣ ውረድ እስቲ ንገረን። ለምሳሌ፣ “መዝሙር 91” የምትለዋን፤ ወይም ሌላም ጨምረህ።

እኔ እስካሁን በአብዛኛዉ መዝሙሩን የምጽፈው ወረቀት ላይ ሳይሆን እዚህ አገር “ፍሪ ስታይል”  በሚባለዉ ስልት ነዉ። መዝሙር 91 ን በጊዜዉ እያጠናሁ ስለነበረ ለረዥም ጊዜ ቃሉን መዝሙር 91 ላይ እንዳለ በዜማ አነበዉ ነበር፡ ቀስ በቀስ ሌላዉን ቃልና ዜማ እየጨመርኩበት  ከጊዜ በኋላ ነዉ ሙሉ መዝሙር ሆኖ የወጣዉ። ሙዚቃዉን በማቀናበር የረዳኝ ዮሐንስ የሚባለዉ ጓደኛዬ ሲሆን የሳክስፎኑን ሶሎ የተጫወተዉ ፒተር የሚባል ሌላዉ ጓደኛችን ነዉ። 

በዚህ ባሳተምከው ቅጽ ውስጥ የተለያዩ ባሕላዊ ቅኝቶች ይደመጣሉ። ለምሳሌ፣ የአይሁድ፣ የጥቁር ፈረንጆች፣ ያሬዳዊ፣ ወዘተ። ይህን አቀራረብ የወጠንከው ምን ለማስረዳት ነው?

በተቻለ መጠን በሙዚቃ ጉዞዬ ከልጅነት ጀምሮ እስካሁን ድረስ የነበረዉን ጉዞና ለብዙ ጊዜያት  አብሬ ያገለገልኩበትን ሌሎችንም የሙዚቃ ቅኝት የሚያሳይ ነዉ። እሱም ከባህላዊ ቅኝታችን የአልበሙ መግቢያ ጀምሮ በዚህ አገር ቆይታዬ ረዘም ላሉ አመታት ያገለገልኩበትን የጥቁር አሜሪካውያንን ስታይልና ሌሎችንም ጨምሮ የአልበሙ መዝጊያ የሆነው የአፍሪካ ቅኝት ይህንን የሚያመለክት ነው። 

በዚህ ዘመን በቤተክርስቲያን ውስጥ ብዙ ዘማሪዎች ተነሥተዋል። ቅዱስ ዝማሬ ከዓለም ዘፈን አልተለየም የሚል ትችት አልፎ አልፎ ይሰማል። አንዳንድ ዘማሪያን እንዲያውም እዚህ ምዕራቡ ዓለም እንዳሉት “ሰሌብሪቲ” መሆን ይቃጣቸዋል፣ ይባላል። ምን አስተያየት አለህ?

በእርግጥ ዜማና የሙዚቃ ቤቶችን በተመለከተ በጣም መመሳስል እንዳለ አይካድም። ድሮ በመዝሙርና በዘፈን መሃል በጣም ግልጽ የሆነ የዜማና የሙዚቃ ስታይል ልዩነት ነበረ። አሁን ግን ልዩነቱ የደበዘዘ ይመስላል። 

ዘማሪ ደረጀ ከበደ በቅርቡ ያሳተመውን ቅጽ 9 መዝሙር ከሙዚቃ ቅንብሩ፣ ከቋንቋ ይዘቱና ከመልእክቱ አንጻር እንዴት አገኘኸው?

የተወሰኑትን መዝሙሮች ሰዉ መኪና ዉስጥ ሰምቼ ነበር፡፡ ሁሉንም በደንብ እስከምሰማ ድረስ አሁን አስተያየት መስጠት   ይከብደኛል። 

ባንሳሳት ከሃያ ዓመት ወዲህ ብዙ ዘማሪዎችና አገልጋዮች በአደባባይ በህግ ስማቸው ሳይሆን በ “ቤት” ወይም በ “ቁልምጫ” ስማቸው መጠራት ይመርጣሉ። ዳጊ፣ ላሊ፣ ዳኒ፣ ሚኪ፣ ቤቲ፣ ጆዚ፣ ጩኒ፣ ሊሊ፣ ጆኒ፣ ሮሲ፣ እንዲ፣ የሚ፣ ሳሚ፣ ወዘተ [ከጌታ ቤት ውጭ ያሉትም እንደዚሁ፦ ቴዲ፣ ጂጂ፣ ቻቺ፣ ጆኒ፣ ወዘተ]። እንዴት ወደዚህ ባህል ተሸጋገርን ትላለህ?

በጣም ፈገግ የሚያስብል ጥያቄ ነዉ። እንግዲህ እኔንም ጨምሮ እንደሚመስለኝ ብዙ ሰዉ ከህግ ስሙ የበለጠ በቤት ስሙ ስለሚያዉቁት ይሆናል። 

አሁን እየተማርክ ነው ወይስ እየሠራህ ነው? ምን ዓይነት ሥራ? የትኛውን የትምህርት ዘርፍ? እየደረስከው ያለ ሙዚቃ/መዝሙር አለ?

አሁን ባለሁበት [] [ቨርጂኒያ] የኢትዮጵያውያን ቤተክርስቲያን ዉስጥ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና በኮሌጅ እድሜ ያሉትን ወጣቶች በሙሉጊዜ መጋቢነት አገለግላለሁ። እንደዚሁም የቤተክርስቲያንዋ የሙዚቃና የአምልኮ አገለግሎቶች መሪ በመሆን ሙሉ ጊዜ አገለግላለሁ። ከሌላዉ ጊዜ የተለዩና ቀለል ያሉ ለግሩፕ የሚሆኑ የጻፍኳቸዉ የአምልኮ መዝሙሮችም አሉ። 

እስካሁን በሕይወትህ ጉዞ ውስጥ ወይም በሙዚቃ ዝንባሌህ ላይ ዓይነተኛና መልካም ተጽእኖ ያሳደረብህ ሰው አለ?

ብዙ ሰዎች አሉ። እናቴ፣ ታላቅ ወንድሜ ሳሚና እህቴ አበቢ ጀምሮ የተለያዩ ሰዎች አሉ። የሲዲዉን ሽፋን ብታየዉ እዚያ ላይ የተዘረዘሩት በጣም ብዙ ናቸዉ። 

አንድን ዜማ ወይም ሙዚቃ የ “ዓለም” የ “ቤተክርስቲያን” ብሎ መለየት ይቻላል? ካለ ልዩነቱ ምንድነው ትላለህ?

ይቻላል። በኛ አገር የቤተክርስቲያን ዜማ የሚባለው የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ዜማ ከዘፈን ዜማ የተለየ ነዉ። እንደዚሁም የወንጌላውያን ቤተክርስቲያን መዝሙር አጀማመር ከሚሲዮናውያን ትርጉም መዝሙር ስለነበረ ዜማዉም ሆነ ምቱ ከዘፈን በጣም የተለየ ነበረ። ለዳንስና ለጭፈራ ተብሎ የሚሠራ ቅንብር በመንፈሳዊ ዝማሬ ዉስጥ ቦታ ይኖረዋል ብዬ አላስብም፤ ነገር ግን መንፈሳዊ ሙዚቃ በየዘመኑ እያደገና አቀራረቡም እየተሻሻለ ከጊዜው ኪነጥበብ ጋር አብሮ መሄዱን በጣም እደግፋለሁ።

አንድ መዝሙር ሲታተም ብዙ ተደክሞበትና ወጪ ወጥቶበት ነው። ታትሞ ለአድማጭ በነጻ ማደል አይቻልም። ተሸጦ በማዘጋጀት ለደከሙ ድጎማ ማስገኘት ይኖርበታል። ዘማሪዎቹ በበዙ ቁጥር ደግሞ ፉክክር መፈጠሩ አይቀርም፤ የገበያ አንድ ባሕርዩ ውድድር መፍጠር ነውና። ውድድርና ገቢ ደግሞ የዘማሪውን ማንነት፣ የቤተክርስቲያንን ኃላፊነት፣ የዝማሬውን ሥነ መለኮታዊ ይዘትና ጥራት ወዘተ መንካቱ የማይቀር ነው፤ ይህን ክስተት በሚዛን መያዝ ይቻላል? እንዴት?

በአሜሪካ ያየህ እንደሆነ ሁሉም አይነት ሙዚቃ የራሱ የሆነ አድማጭና ዘርፍ አለዉ። እንደዚሁም የተለያዩ ሬዲዮ ጣቢያዎች በራሳቸው ዘርፍ ያጫዉታሉ። ስለዚህ አድማጮች በሚወዱት ዓይነት ውስጥ ያሉትን ዘማሪዎች በደንብ ያዉቃሉ። አዲስ መዝሙር ወይም ዘማሪ ሲወጣ በሬዲዮ ከሰሙ በኋላ ያንን ሲዲ ይገዛሉ። እጅግ ብዙ ዘማሪዎች ቢኖሩም እንደኛ አገር ሁሉም በአንድ ዘርፍ  አይመደቡም። ለዚህ ይመስለኛል በኛ አገር ብዙ ጊዜ በጉባኤ መሃል የሚዘመሩ መዝሙሮች ሆን ተብሎም ይሁን ሳይታሰብ ለዘማሪዉ እንደዚህ አገር የሬዲዮ መዝሙር ማስተዋወቂያ የሚሆኑት። ሁሉም ዘማሪ አድማጭ ለማግኘት ሲል ተመሳሳይነት ያላቸዉ በጉባኤ ዉስጥ ሊዘመሩ የሚችል ስታይል ያላቸዉ መዝሙሮች ያወጣል። ገበያዉን የሚቆጣጠረዉ የሚያሠራጨው መዝሙር ቤት ይሆናል። ከጉባኤ ውጭ በጥሞና ሆነህ የምትሰማቸዉ የተለያየ መልእክትና አቀራረብ ያላቸዉ መዝሙሮች የመደመጥ እድል አይኖራቸውም ማለት ነው። ድሮ መዝሙር ለማውጣት ዘማሪው ካለበት ቤተክርስቲያን ማስፈቀድ ነበረበት። አሁንም ቢቻል ቤተክርስቲያን ካልሆነም አንድ መንፈሳዊ ድርጅት የሚወጡትን መዝሙሮች በዜማ በሙዚቃ ቅንብሩና በመልእክቱ እየከፋፈሉ ቢያስቀምጡ ሻጩ መዝሙር ቤት ሳይሆን አድማጩ ሰዉ እነዚህን አንተ የጠየቅካቸዉን ነገሮች በሚዛን መያዝ ይችላል።

የቅዱስ ዝማሬ ተግባርና ዓላማ ምንድነው ትላለህ?

እኔ እንደሚመስለኝ አንደኛውና ዋነኛው እግዚአብሔርን ማክበር ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ 1 ቆሮንቶስ 14:26 ላይ እንደተጻፈው ቤተክርስቲያንን ወይም አማኞችን ማነጽ ነዉ። 

በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት የአምልኮና የዝማሬ ሁኔታ ላይ አንድ ዋነኛ ለውጥ ማድረግ ቢያስፈልግ የትኛውን ነው ትላለህ? ማበረታታስ ቢያስፈልግ?

እኔ እንደማስበዉ አምልኮአችን ክርስቶስን መሃከለኛ ያደረገ ቢሆንና በእግዚአብሔር አምላክነት ላይ ያተኮረ አምልኮ ቢሆን እላለሁ። መዝሙሮቻችን በአብዛኛው ዘማሪው በርሱ/በርሷ ህይወት እግዚአብሔር ያደረገላቸውን እያነሱ የሚያመሰግኑ ስለሆነ እግዚአብሔርን በምድራዊ ስጦታ ብቻ የምናመልከው ይመስላል። ለዘማሪው የሆኑለት ነገሮች ለሁሉም አማኝ ላይሆኑ ስለሚችሉ እንደዚህ አይነት አምልኮ ሁሉንም አማኝ በአንድነት ከማምለክ ያግዳሉ። የሚበረታታው የሚመስለኝ ደግሞ፤ ቤተክርስቲያናት ለዝማሬ አምልኮ የሚሰጡት ጊዜ የሚበረታታ ነዉ፤ መሥመር ሳይለቅና ከእግዚአብሔር ቃልና ከሌሎችም አምልኮ ጊዜ ሳይወስድ ከተደረገ (አምልኮ ማለት ዝማሬ ብቻ አይደለም ብዬ ስለማስብ ነው)

የያዝከው የኪነ ጥበብ ዘርፍ ስለ ውበትና ስለ እውነት ሳያሳስብህ አልቀረም። ክርስቲያን ኪነ ጥበብን እንዴት ሊገነዘባት ይገባል ትላለህ? ቤተክርስቲያን በዚህ ረገድ በቂ ትምህርት ሰጥታለች ትላለህ?

የእግዚአብሔር ቃል በመዝሙር 33 ላይ ሲናገር አዲስ ቅኔን ተቀኙለት ይላል። [በአዲሱ መደበኛ ትርጉም] “አዲስ መዝሙር ዘምሩለት፤ በገናውን ባማረ ቅኝት ደርድሩ፤ እልልም በሉ” የሚለው የሚያሳየዉ ቅኔን ለመቀኘት ቅኔ ማወቅ እንደሚያስፈልግ ነዉ። እግዚአብሔር ያማረና በቅኔ (“ባማረ ቅኝት”) የታጀበን አምልኮ እንደሚወድ ነው። ስለዚህ እኔ እንደማስበዉ ኪነ ጥበብ በእግዚአብሔር ቤት ትልቅ ቦታ አለዉ። ይህ እንግዲህ ሌሎቹን የኪነ ጥበብ ክፍሎችን ሳይጨመር ነው። ቤተክርስቲያን በዚህ ረገድ በቂ ትምህርት ሰጥታለች ወይ? ላልክኝ ጥያቄ፡- እኔ አይመስለኝም። 

ምን ዓይነት ሙዚቃ ነው ማዳመጥ የምትወደው?

በተለያየ ጊዜ የተለያዩ መዝሙሮችንና ሙዚቃዎችን አዳምጣለሁ። በአብዛኛው የጥቁር አሜሪካዊያን  [ጋስፕል] መዝሙር አዳምጣለሁ፤ እሱም በትምህርት ቤትና በነበርኩበት ቤተክርስቲያን ውስጥ [ጋስፕል] ኳየር ውስጥ እዘምር ስለነበረ በጣም ደስ ይለኛል። ሥራ ቦታ በአብዛኛው ጃዝ እና ክላሲካል ሙዚቃዎችን አዳምጣለሁ። [ዳዊት የሠለጠነው በጃዝ ሳክስፎንና በክላሲካል ክላሪኔት ነው፤ እነዚሁኑ መሣርያዎች ሲጫወት ከአሥራ ሁለት ዓመት በላይ ሆኖታል]  

ሌሎች ከዘመሩት ውስጥ የተዋጣለት ነው የምትለው፣ ጥሩ አጻጻፍ፣ ቅኝትና ቅንብር ነው የምትለው  መዝሙር የትኛው ነው?

ባለፉት አመታት ከሰማኋቸው ውስጥ፤ በኔ ጆሮ በቅርቡ “ዜማ ለክርስቶስ” የሚባሉ በህብረት ያወጡት፤ እንደዚሁም ወርቅነህ አላሮ የሚባል ዘማሪም የዘመረው መዝሙር፤ ሌላ ደግሞ ሶፊያ ሽባባዉ የምትባል ዘማሪ ያወጣችዉ መዝሙሮች በኔ ግምት በጣም ጥሩ ናቸው ብዬ አስባለሁ። 

“ድሮ” በተለያዩ የሙዚቃ መሣሪያዎች በቡድን መዘመር የተለመደ ነበር፤ በእነዚህ አሥራ ዓመታት ግን እየተለመደና እየበዛ የመጣው በግል ሆኖ በ”ኪቦርድ” መዘመር ነው። ለዚህ አስተዋጽዖ ያደረገው ምንድነው ትላለህ? እንዴትስ ሁለቱን ማቀራረብ ይቻላል ወይስ አያስፈልግም?

በጣም ያስፈልጋል እንጅ። የእግዚአብሔር ቃልም የሚደግፈው ነው። በ”ኪቦርድ” ስትጫወት አብረው የሚያጅቡ በቅድሚያ የተቀናበሩ ብዙ መሳሪዎች ስላሉ አንድን መሳሪያ ጥሩ አርጎ ለመጫወት ለመማር የሚወስደውን ጊዜ ያህል አይወስድም፤ ለዚህ ይመስለኛል ብዙውን ጊዜ በ”ኪቦርድ” የምንጠቀመዉ። ቤተክርስቲያን የተለያዩ የሙዚቃ መሣሪያዎች በመግዛትና ተጫዋቾችን በማሠልጠን ሁለቱን ማቀራረብ ይቻላል ብዬ አስባለሁ። አንድም ለዚህም ነው በመዝሙር 91 አልበም ዉስጥ ወደ 11 የሚጠጉ የተለያዩ የሙዚቃ መሣሪያዎች የተጠቀምኩት። 

ሙዚቃን በተመለከተ ከእግዚአብሔር ቃል ውስጥ መሠረታዊ የሆነ መመሪያ ማግኘት ይቻላል? አንተን የጠቀመህ ካለ።

እንደምታውቀዉ ሙዚቃ ስንል በድምጽ ብቻ ከሚዜሙ ጀምሮ በተለያዩ የሙዚቃ መሣሪያዎች የሚቀርቡትን ሁሉ ያጠቃልላል። መዝሙረ ዳዊትን ብትመለከት ስለሙዚቃ የተባለ ብዙ አለ። ለኔ እንደመመሪያ ሆኖ የጠቀመኝ 33:3 ላይ ያለው ቅድም የተናገርኩት ቃል ነው። በአለኝ እዉቀትና ችሎታ ሁሉ ጥበብ የተሞላበትን መልካም የሆነዉን ሙሉ መስዋእት ያለስንፍና ለእግዚአብሔር ማቅረብ ነው። 

ቅዱስ ዝማሬዎችን በተመለከተ፣ በቤተክርስቲያን ሥርና ውስጥ ሆኖ ስለማገልገል ወይም በአምልኮ አቀራረብ ረገድ ከሌሎች ጋር ተገናኝታችሁ የተነጋገራችሁባቸው ጊዜአት አሉ? ወይም አስባችሁበታል?

እስካሁን በግል እንጂ በህብረት አላደረግንም። እግዚአብሔር ቢፈቅድ በኔ በኩል ለወደፊት አስባለሁ።

12/5/2009