ትላንት ዛሬ ቢሆን፣ ዛሬ ደግሞ ትላንት

በፀሐይ ዓለሙ

ትላንት ከሆነው ነገር ጋር አልፏል፤ የቀደሙት ጊዜአትና ድርጊቶች ሁሉ ዕድሎቹም ሁሉ ሄደዋል። ሰው ሁሉ አሁን ያወቅሁትንና የተረዳሁትን ያህል ያኔ ባስተውል ኖሮ ይህንና ያንን አደርግ ነበር ይላል። የዛሬው ዕድልና ሁኔታ ያኔ ቢኖር የታሰበውን ሁሉ ለመሥራት ይቀል ነበር እንላለን።

ማስተዋል ከዕድሜ ጋር እየተደጋገፈ ይመጣል፣የመረዳታችን ሁኔታ በጨቅላነትና በወጣትነት እንዲሁም በጎልማሳነት ወራት የተለያየ ነው፣ ሁሉም ደረጃውን ጠብቆ የሚሄድ የሕይወት ሂደት ነው።

እርግጥ በዝግታ አስተውለን ልናደርግ የተገባውን ነገር በጊዜው ሳንረዳ ቀርተን ብናልፈው ዕድሉን ለአንዴም ለመጨረሻም ልናጣው እንችላለን። ለምሳሌ ትዳር የመመሥረቻው ዘመን ክልል፣ ልጆችን ወልዶ የማሳደጊያው ዕድሜ ገደብ ዳርቻው እየታወቀ ችላ ቢባል ወደ ኋላ ተመልሶ ማስተካከል የማይሆን ነገር ነው። የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላል፦

እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ይደክሙበት ዘንድ የሰጣቸውን ጥረት አይቻለሁ።

ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ [መክብብ 3፡10-11]

ሁሉ በጊዜውና በሰዓቱ ሲደረግ እጅግ ያምራል። ሆኖም በቆይታም ውስጥ ተዘግተን ኖረን ዘመኑ እኛን እንዲያየንና እንዲጎበኘን ሆኖ የተመደበልንን ያህል ጊዜው ረድቶን ያልጠበቅናቸው ነገሮች እየተከታተሉ መጥተው ሲሆኑልን ስናይ የሕይወታችን ዘመን ክልል ከእግዚአብሔር በታቀደልን እቅድ ተከፋፍሎ የተፈጠረ፣ የተወሰነለትን እንዲቀበል ሆኖ የተሠራ መሆኑን እንገነዘባለን።

የኛ ማስተዋልና ጥረት ሳይታከልበት ራሱን ችሎ የሚሆን እግዚአብሔር ብቻውን የሚያደርገው ልዩ ልዩ ነገር አለ። ያም የኛን ብቃት ወይንም ማንነት ሳይጠይቅ እንዲሁ እርሱ እንደ ወሰነልን የሚሆን ነው። ሕይወት ራሱ ስፋቱ እንደ ውቅያኖስ የሚመስል፣ እንደ ባሕር ጥልቀት የሆነ የረቀቀ ምሥጢር ያለው ውስብስብ ነው። ይህን ጥልቅ ሕይወት በዝርዝር የሚያውቀውና ሊያነብበው የሚችል ሠሪው እግዚአብሔር ብቻ ነው። የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላል፦

ሁለንተናዬን የፈጠርህ አንተ ነህ

በእናቴ ማሕፀን አገጣጥመህ የሠራኸኝ አንተ ነህ

ክብር የሚገባህ ስለሆነም አመሰግንሃለሁ።

ሥራህ ሁሉ ግሩምና ድንቅ ነው፤ ጠንቅቄም አውቀዋለሁ።

አጥንቶቼ በመሠራት ላይ እንዳሉ በእናቴም ማሕፀን በጥንቃቄ

በመገጣጠም እንዳሉ፣ እዚያም በስውር በማድግበት ጊዜ

በዚያ መሆኔን አንተ ታውቅ ነበር።

ከመወለዴ በፊት አየኸኝ ለእኔ የተወሰኑልኝ ቀኖቼ ገና

ከመጀመራቸው በፊት በመዝገብህ ሰፍረዋል

አምላክ ሆይ! አሳብህ እጅግ የከበረና የሰፋ ስለሆነ

እኔ ልረዳው አልችልም። [መዝሙረ ዳዊት 139፡13-17። 1980 ትርጉም]

ዝርዝር አድርጎ የሚያውቀን እግዚአብሔር ብቻ ነው። የአካላችንም ክፍሎች በእርሱ ዘንድ የታወቁና የተመዘገቡ ናቸው። እኛ ግን ራሳችንን በከፊል እንጂ በሙላት አናውቀውም። ሁኔታዎችንና ጊዜአትንም አጠናቅቀን አንረዳም። ስለዚህም የሰው ሁሉ ሕይወት ብዙ ጥያቄ አለው። ሆኖም ሠሪውን አምላክ ካወቅነው፣ መሪያችንም ካደረግነው እርሱ ራሱ ለነፍሳችንና ለመንፈሳችን እረፍትን በመስጠት መልስ ይሆነናል። ቢገባን ባይገባንም ስለ ሕይወት ያለን አመለካከት የረጋና የተደላደለ ሊሆን የሚችለው ለፈጠረን አምላክ አክብሮትና ፍርሃት ሲኖረን ነው።

ትላንት ወይም ያለፈው ዘመን፣ አሁን ያለሁበትም ጊዜ ቢሆን እያልን ወደ ኋላ ተመልሰን እናስባለን? እንፀፀትስ ይሆን? የእግዚአብሔር ቃል ግን እንዲህ ይላል፦ በዙፋንም የተቀመጠው። እነሆ፥ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ አለ [ዮሐንስ ራእይ 21፡5]። እንዴት ነው ሁሉን አዲስ የሚያደርገው? ከሁሉም በላይ የኛን የውስጥ አመለካከትና አስተሳሰብ በመለወጥና አዲስ በማድረግ ነው። አምላክ እንደሚያየው እንድናይ፣ እርሱ የሚያስበውን እንድናስብ በማድረግ ያሳርፈናል።

እርሱ ተቀማጭነቱ ዙፋን ላይ ነው። በሥልጣንና በኃይል የሚሠራ ጌታ ስለሆነ የእርሱ ሃሳብና መንገድ የጸና ነው፤ ተፈጻሚነትም አለው። ስለ ብዙ እንጨነቃለን፤ የሚያስፈልገው ግን ብዙ ነገር አይደለም፤

ማርታ፥ ማርታ፥ በብዙ ነገር ትጨነቂአለሽ፣ ትታወኪማለሽ፥

የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው፣

ማርያምም መልካም ዕድልን መርጣለች

ከእርስዋም አይወሰድባትም አላት። [ሉቃስ 10፡41-42]

ያሁኑንም ያለፈውንም ለዚህ ታላቅ ጌታ አስረክቦ ሰጥቶ በእርሱ ፈቃድና ሃሳብ ለመመራት መወሰናችን ብቻ ያሳርፈናል። ከዚህ ውጭ ላለው ነገር ሁሉ ውስጣችን ከተከፈተ ግን ማብቂያ የሌለው መዋለል ይሠለጥንብናል።

በሕይወት ሩጫ ውስጥ ማንም አሸናፊ የለም፤ ለምን ቢባል ሁሉም የራሱን ድርሻ ለራሱ ነው የሚሮጠውና። ተሸናፊም የለም፤ ሁሉም የራሱን የሕይወት ትግል ነው የሚጋፈጠውና። እግዚአብሔርም ሕይወታችንን ለውድድር አልሠራትም። ከድካማችን ግን ሊያሳርፈን ተስፋ ስጥቶ ከጥረት ጋር ፈጥሮናል።

ስለዚህ በክርስቶስ የምናርፈው ከብዙ ጥያቄአችን ጋር ሆነን ነው። ይኼ ጌታ ምንጊዜም ልክ እንደ ሆነ እየተረዳን የምንጓዘው የሰላም መንገድ ነው። ስለ ብዙ ነገር እንዳንገረም አድርጎ በጸጥታና በሰላሙ በመሙላት ይመራናል። የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላል፦

አላዋቂዎችን ከጥበብ መራቅ ይገድላቸዋልና፥ ሰነፎችንም ቸልተኛ መሆን ያጠፋቸዋልና።

የሚሰማኝ ግን በእርጋታ ይቀመጣል፥ ከመከራም ሥጋት ያርፋል። [ምሳሌ 1፡32-33]

በአንተ ታምናለችና በአንተ ለምትደገፍ ነፍስ ፈጽመህ በሰላም ትጠብቃታለህ።

ጌታ እግዚአብሔር የዘላለም አምባ ነውና ለዘላለም በእግዚአብሔር ታመኑ። [ኢሳይያስ 26፡ 3-4]

ያለፉት ቅዱሳን እንዲሁ እንደ እኛው ሰዎች ነበሩ። እንዲሁ እንደ እኛው የሚመስል ሕይወት ነበራቸው። እጅግ ብዙ ጥያቄም ነበራቸው። ነገር ግን በእግዚአብሔር ማመናቸውና መደገፋቸው ጠቀማቸው። አእምሮንም የሚያልፈው የእግዚአብሔር ሰላም ሁለንተናቸውን በክርስቶስ ኢየሱስ ገዛላቸው።

የፍጥረት ሁሉ ሁኔታ ለእግዚአብሔር አይደንቀውም። እኛም የኛ ሁኔታ ሊያስደንቀን አይገባም። እንደ ሰው ማሰብና መኖር ስላለ እንደዚያ ሆነናል። በጌታ ሰላም ግን እረፍታችን የተጠበቀ ነው።           5/16/09