ጥሪዬን እንዴት አውቃለሁ?

በዮሐንስ ባሰና

ስለዚህ ወንድሞች ሆይ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ (2ኛጴጥ 1፡10)

ጥንትም ሆነ ዛሬ ጌታ ሰዎችን ለፈለገው ሥራ ጠርቶ እንደሚልክ ለሁላችንም ግልጽ ነው። ሆኖም በዚሁ ሂደት ውስጥ በርካታ ጥያቄዎች መነሣታቸው አልቀረም። የእግዚአብሔርን የጥሪ ድምጽ እንዴት ለይቼ ማወቅ እችላለሁ? የእግዚአብሔርን ድምጽ ከሌላው ለይቶ ማወቅ የሚቻለው እንዴት ነው? አገልጋይ ጥሪውን እንዴት ይቀበላል? ከተቀበለስ በኋላ በወገኖቹና በቤተ ክርስቲያን በኩል ችግር ቢገጥመው ምን ማድረግ አለበት?

እግዚአብሔር የዓለምን ሕዝብ ሁሉ ወደ ራሱ ይጠራል፤ ሁሉም ፈቃደኞች ሆነው ባይመጡም ከተጠሩት መካከል ለራሱ ሥራ የሚሆኑትን ይመርጣቸዋል። የጥሪውና የምርጫው መከናወን ከብዙ አንጻር ቢታይም እግዚአብሔር ለምን ሰውን ይጠራል? ለሚለው ጥያቄ ከሚጠቀሱ በርካታ ምክንያቶች መካከል ሁለቱ የሚከተሉት ናቸው። አንደኛ፣ እግዚአብሔር ሰውን ከፍርድ፣ ከሲኦል፣ ከገሃነመ እሳትና ከሁለተኛ ሞት ለማዳንና ልጆቹና የመንግሥቱ ዜጐች ለማድረግ ይጠራል። ሁለተኛ፣ እግዚአብሔር አሳቡን፣ ዕቅዱንና ዓላማውን ተግባራዊ ለማድረግ ሲል ሰውን ለአገልግሎት ይጠራል። እግዚአብሔር የራሱን ዓላማ ለመፈጸም ከነዓናዊውን፣ አማሌቃዊውን፣ ፍልስጤማዊውን፣ ግብጻዊውንና አረባዊውን … ይጠራል። ከተጠቀሱትም ሆነ ካልተጠቀሱት ኅብረተሰብ ውስጥ በፈቃደኝነት ወደ እርሱ የሚመጡትን ይጠቀማል። ኢትዮጵያውያንን፣ ናይጄርያውያንን፣ ሴቶችንና ወንዶችን፣ የተማሩትንና ያልተማሩትን፣ ሐብታሞችንና ድሆችን … ይጠራል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በብዙ ቦታዎች እግዚአብሔር ሰውን ‘ፈለግሁ’፤ እንዲሁም ‘አገኘሁ’ ሲል እናያለን። ይህ የሚያሳየን ሰው ተፈልጐ የሚገኝ መሆኑንና እግዚአብሔርም እስኪያገኝ ድረስ የሚፈልግ መሆኑን ነው (ዘፍ.38፡9፤ ሕዝ.22፡30፤ የሐዋ. ሥራ 13፡22)

እግዚአብሔር ፈልጐ ያገኘውን ያዘጋጀዋል፣ ይቀርጸዋል፣ ያበጀዋል፣ በቅባቱና በዘይቱ ይቀባዋል፣ ብቃትንም ይሰጠዋል። የማይጠቅመውን ሰው ጠቃሚ ያደርገዋል (1ኛ ጢሞ. 112)። እግዚአብሔር የጠራውና ጥሪውን ለይቶ ያወቀ ሰው በተራው ሌላውን ይጠራል። በአገልግሎቱም በአምላኩ ቤት እንዲቆም ይረዳዋል፣ ይተክለዋል፣ ይኰተኩተዋል፣ ያሳድገዋል፣ ለፍሬ ያበቃዋል። የቅዱሳንን ልብ በአገልግሎቱ ያሳርፋል። ከአምላኩና ከሰዎችም ጋር የመኖርን ዘዴ ይማራል። ትክክለኛ ጥሪ ለዚህ ሁሉ መሠረት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የእግዚአብሔርን ድምጽ ለይተው በመስማት የተጠሩ በርካታ ሰዎችን መጥቀስ ይቻላል። አብርሃም በግልጽ ለአገልግሎት ተለይቷል (ዘፍጥረት 12፡1-4)። የእሥራኤል ልጆች ለአገልግሎት ተጠርተው ከግብጽ ወጥተዋል (ዘፀአት 7፡17፤ 8፡1፣20፤ 9፡1፣13፤ 10፡3፣7-8)። እግዚአብሔር በመደጋገም “ያገለግሉኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ” እያለ ከግብጽ ንጉሥ ከፈርኦን ግዛት አውጥቷቸዋል። ተራ ሰዎችን ጠርቶ ዓለምን በወንጌል እሳት እንዲያጥለቀልቁ አድርጐአቸዋል።

እኛንም ከዛሬይቱ “ግብጽና ባቢሎን” አውጥቶ የራሱ ሕዝቦች አድርጐናል። ለአገልግሎቱ ሾሞናል፤ ታማኝ አድርጐ ቆጥሮናል፤ ኃይልንም ሰጥቶናል። የእግዚአብሔር ሥራ አስፈጻሚ አባላት፣ የክብሩ መግለጫዎችና የፈቃዱ መተላለፊያ መሣርያዎች አድርጐናል። እግዚአብሔር ሰውን ለማዳን መጥራቱ በሚከተሉት ጥቅሶች ውስጥ ተጠቅሰዋል (ኢሳይያስ 55፡1-5፤ ኤርምያስ 51፡45-50፤ ማቴዎስ 11፡28-30፤ ዮሐንስ 7፡37-38፣ 6፡35-37)። ለአገልግሎት መጥራቱን ደግሞ እነዚህ ጥቅሶች ያረጋግጡልናል (2ኛ ዜና መዋዕል 29፡11፤ ኢሳይያስ 49፡2-7፤ ኤፌሶን 2፡10፤ ቲቶ 2፡14)። እግዚአብሔር ሰውን ለአገልግሎት ሲፈልገው ለመስማት፣ ለመረዳትና ለመታዘዝ በሚችልበት ሁኔታና መጠን ነው። ሙሴን በእሳት ነበልባል ውስጥ ሆኖ ጠራው፤ ሳሙኤልን በለሰለሰ ድምጽ፤ ኢሳይያስን በሚያስፈራ ግርማ፤ ኤርምያስን በለውዝ በትርና በሚፈላ ማሰሮ ምሳሌ፤ ኢያሱን ግልጽና በሚያበረታታ ድምጽ።

የእግዚአብሔርን ጥሪ እንዴት ለይቼ ማወቅ እችላለሁ? እግዚአብሔር ሰውን ሲጠራው ድምጹ አያውክም፤ አያስጨንቅም፤ ሰላም አይነሳም። ከሰዎች ጋር በተለይም ከመንፈሳውያን ወገኖች ጋር አያጣላም። ግጭትን፣ መለያየትን፣ አለመታዘዝን አይፈጥርም። ይህ ማለት ግን የተጠራ ሰው ምንም ችግር አይገጥመውም ማለት አይደለም። ይህንን አሳብ ኋላ እንመለስበታለን። በሮሜ 12፡2 ላይ እንደ ተመለከተው “የእግዚአብሔር ፈቃድ፣ እርሱም በጐና ደስ የሚያሰኝ፣ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ” ይላል። በዚህ ቃል መሠረት የእግዚአብሔር ድምጽ በጐ ነው፤ ደስ ያሰኛል፤ ፍጹም ነው። እግዚአብሔር በጥሪውና በምርጫው አይሳሳትም። ድምጹ ሙሉ ለሙሉ መንፈሳዊ ነው፤ አያሻማም፣ አያጣድፍም፣ ለአእምሮ አይከብድም። በብዙ ማስረጃዎችና ምስክሮች የተደገፈ ነው። ለግለ ሰቡ ብቻ ተገልጾለት ለሌላው ምሥጢር አይሆንም፤ ጥያቄም አይፈጥርም።

አይሁዶችና አሕዛብ እንደ እሳትና ውሃ የማይገናኙ ሕዝቦች ሆነው በነበረበት ጊዜ አይሁዳዊው ጴጥሮስ ከአሕዛብ ወገን ወደ ሆነው ወደ ቆርኔሌዎስ ቤት ሄዶ ቃሉን እንዲሰብክ የእግዚአብሔር ጥሪ መጣለት። ጥሪውም በማስረጃ የተደገፈ ነበር። ለጴጥሮስ ለራሱ ራእይ መጣለት። እግዚአብሔር ያሰበውን ለቆርኔሌዎስም ነግሮት ነበር። ጴጥሮስ መጥቶ ገና መናገር ሲጀምር በሁሉም ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው፤ የጸጋ ስጦታዎችን ተቀበሉ (የሐዋ.ሥራ 10 እና 11)። የእግዚአብሔር ጥሪ ለጌታ ልጆች በሁሉም አንጻር ይስማማቸዋልና በዚህ ለይተን ማወቅ እንችላለን። የእግዚአብሔርን የጥሪ ድምጽ አብራሩ ለሚሉ በጥቂቱ የምለው አለኝ። እግዚአብሔር ለማዳንና ለመላክ ወደ እኔ ኑ ብሎ የጥሪ ድምጹን ያሰማል። ሰምተው ለሚመጡ አድርጉና አታድርጉ የሚለውን በግልጽ ይናገራል፤ ይህንንም በቃሉና በተለያዩ መንገዶች ያሰማል። አገልጋዩ ጥሪውን የሚቀበለው ግን እንዴት ነው? ይህ ዋነኛው ጥያቄ ነው።

ጥሪው አንድ ጊዜ ብቻ እርሱ በሚፈልገውና በሚጠብቀው መንገድ ሊመጣ ላይመጣ ይችላል። ለራሱ በቀጥታ ሊመጣ ይችላል፤ ይህም በቃሉ፣ በራእይና በሌላም በተለማመደበት መንገድ ሊሆን ይችላል። ለሙሴ፣ ለኤልያስ፣ ለሳሙኤልና ለጳውሎስ በየግል ጥሪ መጥቶላቸዋል። ጥሪው በሌሎች ክርስቲያን ወገኖች በኩል ሊመጣ ይችላል። ለአሮን በሙሴ በኩል፣ ለኤልሣዕ በኤልያስ፣ ለሳውልና ለበርናባስ በሌሎች በኩል መጥቶላቸዋል። ለእኔ የደህንነትና የአገልግሎት ጥሪ የመጣልኝ ገና ልጅ ሳለሁ አማኝ በነበረ አጐቴ በኩል ነበረ። ከዚያ ቀደም ሲል ደግሞ በተወለድኩበት ቀን እናቴ ከምታመልክበት ቤተ ክርስቲያን የነበረ ወንጌላዊ መጥቶ፦ “ይህ የተወለደው ልጅ የእግዚአብሔርን ቤት የሚያገለግል ትልቅ ሰው ይሆናል፤ ስሙም ዮሐንስ ነው” ብሎ እንደ ሰየመኝ ነግረውኛል። እናቴ ከሞተች በኋላ አባቴ ስለ እምነት እጅግም ግድ ስላልነበራቸው ከቤተ ክርስቲያን ራቅሁ። እንደ አካባቢው ልማድ 17 ሲሞላኝ ትዳር ያዝሁ። ከትዳር በኋላ ነው ከጌታ ጋር መንገዴን ያስተካከልሁት።

ታዲያ አጐቴ አስጠርቶ ጌታ ለቤቱ አገልግሎት እንደሚፈልገኝ በነገረኝ ጊዜ ተናድጄና ንቄ የማይባርክ ቃል ተናግሬው ከፊቱ ወጣሁ። ስወጣ፦ “እንድነግርህ የታዘዝኩትን ሳልነግርህ ከሚቀር ሰምተኸው ብትቃወም ይሻላል፤ ጌታ የተናገረውን ይፈጽማል” ብሎኝ ተለያየን።

ከዓመታት በኋላ በከባድ በሽታ ተይዤ ሞቷል በተባልኩበት ምሽት አንድ ራእይ አየሁ። በሰማይ ይመስለኛል ጌታ እንደማገለግለው፣ ባላምነውና ባላገለግለው ግን በምድር ላይ እንደማልቆይ ነገሮ አሰናበተኝ። ዕለቱ ዐርብ ከምሽቱ አንድ ሰዓት 1960ዓ.ም. ነበረ። ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ስለ እርሱ እየመሰከርኩኝና እያገለገልኩት እስከ ዛሬ ድረስ በርሱ ጸጋ ውስጥ በቤቱ አለሁኝ። ጥሪው የሚመጣበትና አገልግሎቱ የሚጀምርበት ወቅት ሊለያዩና ሊራራቁ ይችላሉ ማለት ነው። አንዳንድ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በኩል በጥቆማ፣ በምርጫ፣ በዕጣና በሌላም መንገድ ጥሪው ሊመጣ ይችላል። ለምሳሌ፣ ሳኦል፣ ሰባው የእስራኤል ሽማግሌዎች፣ ማትያስ፣ ሰባቱ ዲያቆናት እንደ ተጠሩበት ማለት ነው (1ኛሳሙ.10፡20-24፤ዘኁ.ቁ11፡16-17፤የሐዋ.ሥራ1፡26፣6፡3-6)

አንድ አገልጋይ ጥሪውን ከተቀበለ በኋላ የጠራው እግዚአብሔር ሁኔታዎችን ሁሉ እስኪያመቻችለት ድረስ እየተዘጋጀ ጊዜውን መጠበቅ ይኖርበታል። እግዚአብሔር ጊዜው አሁን ነው ብሎ ሙሉ ትጥቅ አስታጥቆ፣ ዘሩን አስጨብጦ ሜዳውንና እርሻውን አሣምሮ ሳይሰጥ ቸኩሎ በራሱ ጊዜ ቢወጣ ችግር ይገጥመዋል። ሙሴ ሕዝበ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት ነጻ እንዲያወጣ የተጠራ ቢሆንም በራሱ ጊዜና ብልሃት በመነሳቱ አገልግሎቱን ግብጻዊ በመግደል ጀመረ። ከዚህም የተነሣ ሥፍራውን ትቶና ፈርጥጦ ወደ ምድረ በዳ መሸሽና መደበቅ ነበረበት። አቤሴሎም በራሱ ጊዜ የእስራኤላውያንን ልብ በመስረቅ ተከታዮቹን አስከትሎ ወጣ። ውጤቱ በዛፍ ባላ መካከል ተንጠልጥሎ መሞት ሆነ። ዛሬም በብዙ ቤተ ክርስቲያኖች በራሳቸው ጊዜ የሚነሱ ሰዎች፣ ለጊዜው ተቀባይነት ያገኙና፣ ተከታዮችን ይዘው ይሄዳሉ፤ ጌታን ማገልገልና መመስከር ትተው ነፍሳትን ሽባ እያደረጉ የሚያወድሷቸውን ይሰበስባሉ፣ በሕይወታቸውም እንዲሞቱ ምክንያት ይሆናሉ። ፍጻሜአቸውም የታሪክ ኃፍረት፣ ውርደትና ሞት ይሆናል።

ጳውሎስ በእናቱ ማሕጸን ሳለ የተጠራና የተለየ ቢሆንም በደማስቆ መንገድ ላይ ጌታ እስከ ተገለጠለት ድረስ አገልግሎቱን አልጀመረም። ሰለሞን ቤተ መቅደስ ለመሥራት የተጠራ ቢሆንም ለመሥሪያ የሚያስፈልገው ሁሉ ተሟልቶም እንኳ የእግዚአብሔርን ሰዓት መጠበቅ ነበረበት። ሳሙኤል የተጠራ ቢሆንም የቤተ መቅደሱን ኃላፊነት እግዚአብሔር ከዔሊ ወስዶ እስኪሰጠው መቆየት ነበረበት። ዳዊት ሳዖል እያሳደደው የጌታን ጊዜ ይጠብቅ ነበር።

አገልጋይ ጥሪውን ከተቀበለ በኋላ ከቤተ ክርስቲያንም ሆነ ከሌሎች ዘመዶቹ ችግር ሊገጥመው ይችላል። እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ስለሆነ እርሱ አንድን ነገር ለማድረግ ማንንም አይፈራም፣ አይሠጋም፣ በሚያደርገው ነገር ሁሉ እርሱ ልክ ነው። በኛ ላይ የፈቀደውን ማድረግና የምንፈልግውን አለማድረግ መግደልም እንኳን ቢሆን እርሱ ልክ ነው። የሚያደርገውን ግን ሳይናገር አያደርግም። ለማንም መንገደኛ ሳይሆን ለባሪያዎቹ ይናገራል፤ የተናገረውን ተከታትሎ ይፈጽማል። “እፈጽመው ዘንድ በቃሌ እተጋለሁ” ይላል። የእግዚአብሔር ጥሪ ሲመጣ ችግርና ተቃውሞም ይሠለፋል። በግል ሕይወት፣ ከሰይጣን፣ ከአማኞች፣ ከማያምኑ፣ ከቤተ ሰብና ከቅርብ ጓደኛ መፈራረቅ ይጀምራል። ችግሩም ሊያንገላታው፣ ሊያቆስለው፣ ሊጎዳው ይችላል። እረፍት የሚያገኘው በእግዚአብሔር ትከሻ ላይ ብቻ ይሆናል። ሁሉም ሲሸሸው የእግዚአብሔር ቅርበት ግን ይበዛለታል። ሙሴን ወንድሙ አሮንና እህቱ ማርያም ተቃወሙት። በአሞጽ ላይ ካህኑ አሜስያስ ተነሣበት። በኤልያስ ላይ ንጉሡ፣ ንግስቲቱና 450 የበኣል ነቢያት። ቄሱ ዘካሪያስ የሞት ጽዋ ደረሰው። ማርቲን ሉተር ተሰደደ። ይህም ሁሉ ቢደርስ “የሚጠራችሁ የታመነ ነው፤ እርሱም ደግሞ ያደርገዋል” የሚለውን ቃል በመታመንና በጸሎት በመጽናት ጌታን በሚከፍተው በር ማገልገል ያሻል።

የእግዚአብሔርን ድምጽ የሚመስሉ ድምጾችን እንዴት ለይቶ ማወቅ ይቻላል? የሚለው በዘመናት ሁሉ ዋነኛና አስቸጋሪ ጥያቄ ነው። ቢሆንም እግዚአብሔርን አያስቸግርምና የእርሱን ድምጽ የምንለይባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ። በተጻፈው ቃሉ ላይ የተመሠረተ ድምጽ ከሆነ የእግዚአብሔር ድምጽ ነው። በውስጣችን ያለው መንፈስ ቅዱስ የማይቃወመው፣ የሚመሰክረውና የሚደግፈው ከሆነ ይህ መለኰታዊ ድምጽ ነው። የተናጋሪው ሕይወት በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ነውርና እንከን የሌለበት ከሆነ ሌላ ድምጽ አይደለም፤ ከጌታ ነው። ተናጋሪው ለእግዚአብሔር ቃል ሥልጣንና የበላይነት የሚቀበልና የሚታዘዝ፣ ለቤተ ክርስቲያን ታዛዥና ታማኝ ከሆነ በዚህ መለየት ይቻላል። የተነገረው መልእክት አስቀድሞ በቃሉ የተፈተነና ተፈጻሚነትን ያገኘ ከሆነ የመለየት ስጦታ ያለው ሰው እውነተኛ መሆኑን ካረጋገጠ፣ ይህም ከእግዚአብሔር ነው። ይህ ስጦታ ያለው ሰው ባይኖር ክርስቲያኖች ሁሉ “ሁሉን ፈትኑ፣ መልካሙን ያዙ፣ ከማናቸውም ዓይነት ክፉ ነገር ራቁ” በሚለው ቃል መሠረት መርምረው ማወቅ ይችላሉ። ሊያድነንና ለአገልግሎቱ ሊሾመን የጠራን የእግዚአብሔር ስም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይባረክ።

የውይይት ጥያቄዎች፦

  1. ከአገልግሎት በፊት መቅደም የሚገባው ምንድነው?
  2. የጥሪን እውነተኛነት ለማስረገጥ ሦስት የማይነጣጠሉ ምስክሮች ምንና ምንድናቸው?
  3. እግዚአብሔር ያልጠራቸውን እንዴት መለየት ይቻላል?
  4. ጥሪ አስከትሎ የሚመጣው ሁለት ሁኔታዎች ምንድናቸው?
  5. ጸሐፊው እግዚአብሔርን እንዴት ይገልጸዋል?
  6. የአማኝን ለአገልግሎት መጠራት በተመለከተ የቤተክርስቲያን ሥልጣንና ኃላፊነት ምንድነው?

መጋቢ ዮሐንስ ባሰና በኢትዮጵያና በወላይታ ቃለ ሕይወት አብያተክርስቲያናት ውስጥ ከአርባ አምስት ዓመታት በላይ እያገለገሉ የሚገኙ የእግዚአብሔር ሰው ናቸው። ይህ ጽሑፍ ከ”ሕይወት መጽሔት”፣ መስከረም 1987፣ገጽ 8-9 ላይ ተወስዶ በድጋሚ የታተመ ነው።