ይህ ክፍል “ወንጌል ወይስ ሌላ ወንጌል? በሚል ርዕስ መጋቢ በለጠ ደሳለኝ ያዘጋጁት ሁለተኛውና የመጨረሻው ክፍል ነው። በዚህ ዘመን፣ ታሪካዊ መነሻን ያላገናዘቡና ሚዛን የሳቱ አተረጓጎሞች የወንጌልን ጥራት እየሸረሸሩ ይገኛሉ። ይህም በተራው፣ የአማንያንን ሕይወት ጥራት እየነሳ፣ ማኅበራት ከወንጌል ጋር ያልተገናዘበ አስተምህሮ እንዲያስተናግዱ አድርጓል። በእውነተኛዪቱ የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ወንጌል መተኪያ አይገኝለትም። እነዚህን ሁለት ክፍሎች ጊዜ ወስደው በጥሞና ያንብቡአቸው፤ ለወዳጆችዎ አባዝተው ወይም በኢሜይል ያስተላልፉ። ኢትዮፕያንቸርች አዘጋጅ

የክርስቶስን ወንጌል ክርስቶስ እንደኖረውና እንዳስተማረው፣ ሐዋርያቱ እንደኖሩት፣ እንዳስተማሩትና እንዳስተላለፉልን፣ በዘመናት ሁሉ አሁንም የእግዚአብሔር ቅሬታዎች በመኖርና በማስተማር እንደገሚገልጹት የወንጌልን ኃይል ለመረዳት ከወንጌሉ በፊት የነበሩትን ሁኔታዎች ማወቅ ይረዳል። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለሚገኙት ሲጽፍ፣ “በወንጌል አላፍርም፣ አስቀድሞ ለአይሁድ፣ ለግሪክም ሰዎች፣ ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነውና” ካለ በኋላ “ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኝ የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው” ይላል። እመኑና ዳኑ፤ ብሎ ቢቀጥል ኖሮ የክርስቶስ ወንጌል የማዳን ኃይሉ ባልጎላ ነበር (ሮሜ 1፡16፤ 3፡21-25)።

ሮሜ ምዕራፍ 1 ቁ.18 እስከ ምዕራፍ 3 ቁ.20፣ ወንጌል ለሰዎች ያስፈለገበትን ምክንያት በጥቂቱ ይዘረዝራል። የሰው ልጅ እውነትን በአመጻ በመከልከል፣ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ግልጽ ሆኖ ያለውን የዘላለም ኃይሉንና ባሕርዩን እያወቀ እግዚአብሔርን ባለማክበርና ባለማመስገን፣ ክብሩንና ምስጋናውን ለፍጡሮች በመስጠት ለርኩስነት፣ ለሚያስነውር ምኞት እና ለማይረባ አዕምሮ አልፎ ተሰጠ። ባሕርዩ በሮሜ 1፡24-32 እና በሮሜ 3፡11-18 የተዘረዘሩትን ሁኔታዎች አንጸባረቀ። ከእግዚአብሔርም ክብር ጎደለ። በበደሉና በኃጢአቱ የሞተ፣ በሰይጣን ሥር በባርነትና በመታዘዝ የኖረ፣ እንደ ሥጋው ምኞትና እንደ ልቦናው ፈቃድ የተመላለሰ፣ ከፍጥረቱ የቁጣ ልጅ፣ ደካማ፣ ኃጢአተኛ እና የእግዚአብሔር ጠላት ሰለነበረ በጥፋት ፍርድ ሥር ተዘጋ (ኤፌ 2፡1-3፤ ሮሜ 5፡6-7፣10)። ፍርዱም ይግባኝ የሌለው ነበረ። የእግዚአብሔርም ቁጣ ከሰማይ ሊገለጥበት ሆነ (ሮሜ 1፡18)፤ በእግዚአብሔር ፊት ቆመው ከዚህ ጥፋትና ቅጣት ለማምለጥ ሕጋዊ ምክንያት ሊያቀርቡ እንደማይችሉ ተረዳ። በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከመጣለት የምሥራች ወንጌል በፊት የሰው ሁሉ ሁኔታ እንዲህ ነበር። እግዚአብሔር ተመጣጣኝ ፍርድ ነው ብሎ ያስቀመጠውና ይቆየን የነበረው የዘላለም ቅጣት ሲዖል ነበር።

ከዚህ የዘላለም ፍርድ ለማምለጥ እንድንችል፣ አንዲያ ልጁን በመስቀል ላይ ሠዋልን። በምድር ካለህ(ሽ)ና ወደፊትም ከሚኖርህ(ሽ) ጊዜያዊ ንብረት፣ ዝና፣ ምኞት፣ ጤና፣ ትዳር፣ ድሎት፣ ፍላጎት እና አንተነትህን (አንቺነትሽን) ብትሰጠ(ጪ)ኝ በዚህ ምድር ሰላምን በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወትን እሰጥሃ(ሻ)ለሁ ቢል ይህንን ድርድር እንቀበል ነበር? ሁላችንም እንኳ ባንሆን አብዛኛዎቻችን ይህን ድርድር እምቢ የምንል አይመስለኝም። እግዚአብሔር በአሥር ጣቶቻችሁ ፈርሙ ብሎ ቢጠይቀን እንኳ ያለምንም ማቅማማት የምንፈርም ይመስለኛል። ይህንንም እውነት በተቀበልንበት መልኩ ለማስተላለፍ እና የክርስቶስ ታማኝና ታዛዥ ባሪያዎች ሆነን ለመኖር የልብ ቃል ኪዳን እንገባ ነበር።

እምነታችን፣ እግዚአብሔር ቃሉን እንደሚጠብቅ እርግጠኞች መሆናችን ሲሆን የእምነታችን ማስረጃ ደግሞ እኛም ቃላችንን መጠበቃችንን በመታዘዝ ማሳየታችን ነበር። እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ ካደረገልን ድንቅ ነገሮች አንጻር ሁለንተናችንን እርሱን ደስ የሚያሰኝ ሕያውና ቅዱስ መስዋዕት አድርገን ማቅረባችንና መስጠታችን፣ ለአዕምሮ የሚመች አገልግሎታችን ወይም መንፈሳዊ አምልኮአችን ነው (ሮሜ 12፡1-2)። ከዚህ ያነሰ መስጠት ከእምነት አይደለም፤ የክርስቶስ ወንጌልም አይደለም።

አንድ ወንድና ሴት ሲጋቡ በብዙ ሰዎችና በእግዚአብሔር ፊት ቆመው፣ “በኀዘን ሆነ በደስታ፣ በብልጽግና ሆነ በድኅነት፣ በሕመም ሆነ በጤንነት፣ ሊዋደዱና አንዱ ሌላውን ሊንከባከብና እስከ ሞትም ላይለያዩ ቃል ይገባባሉ። የዘመኑ የክርስቲያኖች የፍቺ ስታትስቲክስ እንደሚመሰክረው ባልም ሚስትም በተለያዩ ስሜታዊ፣ ቁሳቁሳዊ፣ ሞራላዊ፣ አንዳንዴም ምክንያት-የለሽ ምክንያቶች የገቡትን ቃል ኪዳን ሲያፈርሱ እናያለን። ክርስቲያኖችም በእግዚአብሔርና በፍጥረቱ ፊት “አምላኬ፣ አዳኜና ጌታዬ ነህ፣ ለዘላለም እከተለሃለሁ” ብለን የገባነውንና በውኃ ጥምቀትም የመሰከርነውን ሰማያዊ የዘላለም ቃል ኪዳን በተለያዩ ምድራዊ ምክንያቶች ስናጥፍ እንታያለን። በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፣ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች መሆናችንን እንዘነጋለን (1ኛ ቆሮ 15፡19) ።

የክርስቶስ ወንጌል፣ “በዋጋ ተገዝታችኋል፣ ለራሳችሁ አይደላችሁም” (1ኛ ቆሮ 6፡20) ይለናል። በዋጋ የተገዛና የራሱ ያልሆነ ሰው፣ ባሪያ ነው። ባሪያ የጌታው ነው፤ ባሪያ የሚኖረው ለጌታው ነው፤ የራሱ የሆነ ፈቃድ፣ የራሱ የሆነ ንብረት፤ የራሱ የሆነ መብት የለውም። ነገር ግን የልዑል እግዚአብሔር፣ የጌታ ኢየሱስ ባለሟል ነው፤ በዓለም አንደኛና ከፍተኛ የሆነ ሥራና ቦታ አለው። የክርስቶስ ወንጌል ይህ ነው። ነገር ግን ይህ ወንጌል ለብዙዎች አይጥምም።

በዘመናት ሁሉ እግዚአብሔር ሰዎችን ሕዝቡ የሚያደርጋቸው በጸጋው ነው። ሕዝቡ ለመሆን የሚከፍሉት ክፍያ አልነበረም፤ ነገር ግን ሕዝቡ ሆነው ለመቆየት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሳያስታውቃቸው አላለፈም። በብሉይ ኪዳን እሥራኤላውያንን (ግብፃውያንም ነበሩባቸው) ከግብፅ ካወጣቸው በኋላ በሲና ተራራ በሙሴ በኩል እንዲህ አላቸው፣

በግብፃውያን ያደረግሁትን፣ በንስርም ክንፍ እንደ ተሸከምኋችሁ፣ ወደ እኔም እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል። አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፣ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ መንግሥት ትሆኑልኛላችሁ፤ እናንተም የካህናት መንግሥት የተቀደሰም ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ…ሕዝቡ ሁሉ አንድ አፍ ሆነው፦እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን ብለው መለሱ (ዘጸ. 19፡4-6፤19፡8)።

በአዲስ ኪዳንም እንዲሁ ነው። ወደ መንግሥቱ ለመግባት ሰዎች የሚያደርጉት ነገር አይኖርም። ነገር ግን በመንግሥቱ ውስጥ ለመቆየትና የመንግሥቱን በረከቶች ለመቀበል በክርስቶስ ኢየሱስ ውስጥ ሆነው በመንግሥቱ ሕግና በቃል ኪዳኑ መኖር ግዴታቸው ነው። እኛንም በጌታ ኢየሱስ በኩል ከዓለም ካወጣን በኋላ ይህን በሚመስል ቃል ተናግሮናል፣

"ነውርና እድፍ እንደሌለው እንደ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም የተዋጃችሁት… በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር የተወለዳችሁ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ ለርስቱ የተለየ ወገን የሆናችሁት …ምሕረት ያገኛችሁ የእግዚአብሔር ወገን የሆናችሁት …ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ በእርሱ የተጠራችሁትና በክርስቶስ ኢየሱስ ዳግም የተወለዳችሁት የተፈጠራችሁት እግዚአብሔር አስቀድሞ በክርስቶስ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ በማድረግ ትመላለሱበት ዘንድ እና የእርሱን በጎነት እንድትነግሩ ነው" (1ኛ ጴጥ 1፡19, 23፣ 2፡9-10፣ ኤፌ 2፡10)።

በእምነት በመታዘዝ እንድንኖር ተጠርተናል። በተጠራንበት መጠራታችን እንደሚገባ እንድንመላለስ ይጠበቅብናል (ኤፈ 4፡1)። በዚህ እውነት መጽናትና ትምህርቱን ሳንበርዝ በትክክል ማስተላለፍ የግድ ነው። ዕብራውያን 10፡36 “የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ፣ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና። ገና በጣም ጥቂት ጊዜ ነው፣ ሊመጣ ያለው ይመጣል፤ አይዘገይምም፤ ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል፣ ወደ ኋላም ቢያፈገፍግ፣ ነፍሴ በእርሱ ደስ አይላትም” ይላል። እግዚአብሔር ቃሉን ሰምተው ቃል ኪዳንን ያልጠበቁትን ቀጥቷል። የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው ያስመረሩት፣ ከግብፅም ከወጡ በኋላ ኃጢአትን አድርገው ሬሳቸውም በምድረ በዳ የወደቀ፣ ባለማመናቸውና ባለመታዘዛቸው ወደ ዕረፍቱ አልገቡም (ዕብ 3፡16-19)። ማመንና መታዘዝ የአንድ ሳንቲም ፊትና ጀርባ ናቸው። የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፏል (ሮሜ 15፡4)። ይህም ሁሉ እንደ ምሳሌ ሆነባቸው፣ እኛን የዘመናት መጨረሻ የደረሰብንን ሊገሥጸን ተጻፈ (1ኛ ቆሮ10፡11)። ለዚህ እውነት ትኩረት ብንሰጥ መልካም ይሆንልናል።

ምዕመኖች ቤተ ክርስቲያንን ለቅቀው እንዳይሄዱ በሚያባብሉ ለብ ያሉ መልእክቶች የሕይወት ለውጥ አይገኝም፤ የክርስቶስ ወንጌልም አይሰበክም። የነገራቸውን እውነት መቀበል አቅቷቸው፣ ወደ ኋላቸው የተመለሱትን ምግብና ፈውስ ፈላጊ ተከታዮችን፣ ኢየሱስ አላባበላቸውም። ከጌታ የተመለሱትን አይተው፣ “ይህስ ከባድ ትምህርት ነው፤ ማን ሊቀበለው ይችላል?” ላሉት ለአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ እንኳ “እናንተስ ልትሄዱ ትወዳላችሁ?” በማለት አቋማቸውን አስለይቷቸዋል (ዮሐ 6፡67)።

ኢየሱስ ለድነት እና ለአገልግሎቱ ሲጠራን ትርፍና ኪሳራችንን ቆርጠን ውሳኔ እንድናደርግ ነው። እርሱን መከተል የሚያስከትለውን መከራ ነግሮን፣ የሚያስከፍለውን ዋጋ አስታውቆን ነው። ማንም ወደ እኔ የሚመጣ ቢኖር አባቱንና እናቱን ሚስቱንም ልጆቹንም ወንድሞቹንም እኅቶቹንም የራሱን ሕይወት ስንኳ ሳይቀር ባይጠላ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም፤ መስቀሉን ተሸክሞ በኋላዬ የማይመጣ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም (ሉቃስ 14፡25)፤ ማንም ከእናንተ ያለውን ሁሉ የማይተው ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም (ሉቃ 14።33) በማለት እውነቱን ነግሮን አስጠንቅቆናል። ጨምሮም “በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፣ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ዕለት ዕለት ተሸክሞ ይከተለኝ (ሉቃስ 9፡23)” ብሏል ። በእርሱ ታምኖ እስከ ፍጻሜው መጽናት የሚያስገኘውንም ሽልማት በሐዋርያቱ በኩል አስታውቆናል (ሮሜ 8፡18)። እያንዳንዱ ክርስቲያን የሚገጥመውን ጊዜያዊ መከራና የሚቆየውን ዘላለማዊ ሽልማት አመዛዝኖ ክርስቶስን የመከተል ወይም ያለመከተል ውሳኔ ማድረግ ምርጫው ነው (ዮሐ 6፡67፤ ሉቃስ 14፡26-35)።

የክርስቶስ ወንጌል በመጀመሪያ ዘመን አማኞች ሕይወት ዓይን መታየት አለበት። ክርስቶስ የኖረበትን ፈለግ መከተል ምርጫ የሌለው ግዴታ ነው። በዕብራውያን 11 የምናደንቃቸውና ምሳሌነታቸውን በየስብከቱ መድረክ የምናወሳላቸው የእምነት አርበኞች 1) እግዚአብሔር እንዳለና ለሚያምኑት ዋጋ እንደሚሰጥ በመረዳት፣ 2) እግዚአብሔር የሰጣቸውን ተስፋና በሩቅ ያለችን ከተማ ለማግኘት በተስፋ በመጽናት፣ እና 3) ያንን ተስፋ ለመቀበል በፊታቸው የገጠማቸውን መከራ ጸንተው በመቻል፣ 4) ሁኔታዎች ያቀረቡላቸውን ጊዜያዊ ድሎትና ምቾት በመናቅ የክርስቶስን ወንጌል ኖሩ፤ አስተላለፉ። ክርስቶስን የሚያውቅና የክርስቶስን ጥሪ የተቀበለ ሰው እንዴት መኖር እንዳለበት አሳዩ። በቀጭኑ መንገድ በመጓዝ በጠባቡ በር ለመግባት ረጅሙን መንገድ ተጓዙ። ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ በእነርሱ አያፍርም (ዕብ 11፡16)፤ ክርስቶስም ወንድሞቼ ብሎ ሊጠራቸው አላፈረባቸውም (ዕብ 2፡13)። የክርስቶስ ወንጌል አንዱ ክፍል ይህ ነው።

በመዳናችንና በክርስቶስ ምጻት መካከል በምድር ላይ የምንኖረውን ጊዜ ለክርስቶስ ጌትነት በመገዛትና በመታዘዝ ከመኖር ወዲያ አማራጭ የለንም። ጌታም የርሱ ከሆኑት ይህንኑ ይጠብቃል፣ እርሱን የመውደዳችንም ምልክት ነው። እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ካደረገልን መልካምነትና በጎነት አንጻር ሁለንተናችንን ቅዱስ፣ ሕያውና እግዚአብሔር የሚቀበለው መስዋዕት አድርገን ማቅረብ ለአዕምሮ የሚመች አገልግሎታችን እና መንፈሳዊ አምልኮአችን ነው (ሮሜ 12፡1-2)። በብሉይ ኪዳንም ሆነ በተለያዩ ሃይማኖቶች የሚቀርበው መስዋዕት ታርዶ ነው። በአዲስ ኪዳን የተጠየቅነው መስዋዕት ግን ሕያው ሆኖ እንዲቀርብ ነው። አንዳንድ ጊዜ የመስቀሉ ሥቃይ ሲበዛብን በመሰዊያው ላይ መቆየት ፈተና ይሆንብናል። ነገር ግን በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ (ብፁዕ) ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወት አክሊል ይቀበላሉና (ያዕቆብ 1፡12) የሚል የተስፋ ቃል ስላለን በታማኝነት መጽናታችን እግዚአብሔርን ያስደስተዋል። 

የእግዚአብሔርን ጸጋ ትርጉም በትክክል አንረዳም። የእግዚአብሔር ጸጋ፣ ያለ ሥራ፣ እንዲያው በእምነት ቢያድንም ባለመታዘዝ እንድንኖር አይፈቅድልንም። “ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጧል፣ ይህም ጸጋ ኃጢአተኛነትንና ዓለማዊ ምኞትን ክደን የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን አምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠብቅን፣ ራሳችንን በመግዛትና እግዚአብሔርንም በመምስል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል” (ቲቶ 2፡11-14)። እግዚአብሔርን እየመሰሉ የሚኖሩ ስደት ቢኖርባቸውም፣ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራን ጌታ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ሰጥቶናል (2ኛ ጢሞ 3፡12፤ 2ኛ ጴጥ 1፡2)።

በክርስቶስ ውስጥ የሚገኘው ሰላም የስሜታችን አለመጎዳት አይደለም፤ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረን ጥል አብቅቶ በመንግሥቱ ውስጥ መሆንን ማወቅ እንጂ (ሮሜ 8፡10)። ሰላሙ፣ በእቶኑ ውስጥ አብሮን መመላለሱን በእምነት ዓይን ማየት ነው። በሞት ጥላ ውስጥ ከእኛ ጋር እንዳለ በመገንዘብ ክፉውን አለመፍራት ነው። በስሙ ከሚመጣብን መከራ አለመሸሽ፣ ስለስሙ መከራን መቀበል ነው። ተዓምራቶችና ድንቆች በእጆቻችን ሲከናወኑ፣ ደስታችን በተዓምራቶቹ ሳይሆን ስሞቻችን በሕይወት መዝገቡ ላይ መጻፋቸውን እርግጠኞች በመሆን ሐሴት ማድረግን ይጨምራል። ወጀቡ ሲያይልብን በእኛ የጀመረውን መልካሙን ፈቃዱን ሳያከናውን እንደማይተወን ተረድቶ መቆም፣ በእርሱ ውስጥ የሚኖረንን ሰላም ያሳያል። “ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል” (ዕንባቆም 2፡4) ያለውን የዕንባቆም መዝሙር “በለስ እንኳ ባታፈራ፣ በወይን ሐረግ ፍሬ ባይገኝ …” እያልን በተመቻቸ የማምለኪያ አዳራሽ በተቀነባበረ ሙዚቃ ታጅበን እያጨበጨብንና ዕልልታውን እያቀለጥን ከመዘመር በላይ ነው። የዕንባቆምን መዝሙር መዘመር ብቻ ሳይሆን እንደ ዕንባቆ መኖር ያስፈልጋል።

በጸጋው እርሱን የሚያስደስት ሰዎችን የሚባርክ አገልግሎት ስናቀርብ የሰዎችን ምስጋና አለመጎምጀት መልካም ነው። የበረከቱ ምንጭና የአገልግሎቱ ጌታ ማን እንደ ሆነ እንደሚገባ መረዳት ይኖርብናል። ሰዎች በቃል ሆነ በ “ፍቅር ሥጦታ” ከፍ ሊያደርጉን ሲፈልጉ፣ “የማንጠቅም ባሪያዎች ነን፣ ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል (ሉቃ 17፡10)” የሚለውን የጌታን ቃል በመገንዘብ ክብሩን ለአገልግሎቱ ጌታ መስጠት ባህሪያችን መሆን አለበት።

በእንቅስቃሴ ብዛት እና በአገልግሎት እሽቅድምድም እግዚአብሔርን ያስደሰትን ይመስለናል፤ ባለመታዘዛችን ልቡን መስበራችን ግን አይታሰበንም፣ የልብ ኀዘንም አናሳይም። የተፈጠርነው በሰማይ ያለውን የእግዚአብሔርን ክብር በምድር ለማንጸባረቅና ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር የእግዚአብሔርን ክብር በማወቅ ትሞላለች የሚለውን የእግዚአብሔር ቃል ተግባራዊ ለማድረግ ነው (ዕን 2፡14)። ይህ ዕውነት ተግባራዊ የሚሆነው እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለመሥራት በክርስቶስ ኢየሱስ የዳንበትን ወንጌል በዕለት ኑሮአችን ተግባራዊ ስናደርግ እና ቃሉን በትክክል ስናስተላልፍ ነው (ኤፌ 2፡10)። ኢየሱስ፣ አባቱን “እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ” አለው (ዮሐ 17፡5)። እኛም እግዚአብሔርን በእውነት አከበርን ለማለት የምንደፍረው የሰጠንን ሥራ ፈጽመን ስንገኝ ብቻ ነው። ደቀ መዝሙር ከመምህሩ፣ ባሪያም ከጌታው አይበልጥም። ደቀ መዝሙር እንደ መምህሩ፣ ባሪያም እንደ ጌታው መሆኑ ይበቃዋል (ማቴ 10፡24-25)። የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ነህ? የክርስቶስ ባሪያ ነህ?

እንግዲህ፣ በእምነታችን፣ በአገልግሎታችንና በምስክርነታችን መካከል ፍጹም የሆነ ስምምነት መኖር አለበት። ኢየሱስ ክርስቶስን በአዳኝነቱ ብቻ ሳይሆን በጌትነቱም እንደ ተቀበልነው ትምህርታችንና ሕይወታችን ማንጸባረቅ አለበት። በዘፍጥረት 14፣ አብርሃም፣ እውነተኛ ጽድቅ በእምነት ብቻ እንደሚገኝ ሲያሳይ፣ ሐዋርያው ያዕቆብ ደግሞ የአብርሃም ይስሐቅን መሰዋት በመጥቀስ እምነት እውነተኛነቱ የሚረጋገጠው በተመጣጣኝ መታዘዝ ሲደገፍ ብቻ እንደ ሆነ ጽፏል (ዘፍጥረት 22፤ያዕ 2፡17)። በኑሮአችንም በአገልግሎታችንም ዘላለምን በጊዜያዊ፣ መንግሥተ ሰማይን በምድራዊ፣ እምነትን በምኞት፣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ በምድራዊ በረከት፣ የመስቀልን ጉዞ በድሎት ኑሮ እንዳንተካ ለእግዚአብሔር ቃልና ለነፍሳት መጠንቀቅ ብልህነት ነው። በቃሉ ላይ ለምንጨምር ወይም ከቃሉ ለምንቀንስ፣ ቃሉ የሚለውን እንዳይል ለምናደርግ፣ ቃሉ ያላለውን እንዳለ ለምናስመስል ወዮልን፤ “የባሰውን ፍርድ እንድንቀበል ታውቃላችሁና” (ያዕ 3፡1)።

በመጨረሻም፣ እግዚአብሔር ዕድልና ጸጋ ሰጥቶን የክርስቶስን ወንጌል የምንሰብክ/የምናስተምር እነዚህን እውነቶች ልብ እንድንል ያስፈልጋል፣1/ ድነት፣ በእግዚአብሔር ፍቅር በክርስቶስ ኢየሱስ ጽድቅ በእምነት ብቻ የሚገኝ የጸጋ ስጦታ ነው፤2/ እውነተኛ እምነት እውነተኛ ድነትን ያስገኛል፤3/ የእውነተኛ እምነት/ድነት ማስረጃ በቅድስና መመላለስና በእግዚአብሔር ቃል የተደገፈ መታዘዝ ነው፤4/ ሰሚዎች ለቃሉ ለመታዘዝ ዕድል እንዲያገኙ የእግዚአብሔርን ቃል በትክክል መስበክ/ማስተማር ነው፤5/ የእግዚአብሔር ስም በውሸት መገለጥ፣ በማይፈጸም ትንቢት፣ ባልተመጣጠነ ትምህርት እንዳይሰደብ መጠንቀቅ ነው፤6/ ለሚጠይቁንም ሆነ ለምናስተምራቸው ትክክለኛ መልስ ለመስጠት እንድንችል ቃሉን ማጥናት/መማር ነው፤7/ ምዕመንም የስሕተትን ትምህርት ለመለየት እንዲችል እንደ ቤሪያ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ዕለት ዕለት መመርመር ነው፣8/ በክርስቶስ ፊት ስንቆም ሰባኪ እገሌ፣ አስተማሪ እገሊት አስታኝ ነው በማለት ከፍርድ ልናመልጥ አንችልምና።