የመጨረሻው ዘመን ስህተት አሠራሮችና ጥንቃቄ  - 2

በሰለሞን ከበደ 

መጻሕፍትንና የእግዚአብሔር ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ” (ማቴዎስ 2229)

የመንፈስ ቅዱስን መምጣት አስፈላጊነት፣ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ሲያስገነዝብ “እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፣ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ እርሱን እልክላችኋለሁ” አላቸው (ዮሐ16፡7)። ያለ መንፈስ ቅዱስ መሪነትና ኃይል ምንም ማድረግ አንችልም። “በእኔ ኑሩ፣ እኔም በእናንተ” የሚለው ጥሪ እውን የሚሆነው በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ነው። 

 1. ስለ ኃጢአታችን የሚወቅሰን ወደ መስቀሉም የሚያደርሰን መንፈስ ቅዱስ ነው (ዮሐንስ 16፡8-10)
 2. ወደ ክርስቶስ ኢየሱስ የሚያመጣንና በክርስቶስ ኢየሱስ አካል ውስጥ የሚያስገባን፣ ለቤዛ ቀን የሚያትመን መንፈስ ቅዱስ ነው (1ኛ ቆሮ12፡13፤ ኤፌ 4፡30)
 3. ጌታ ኢየሱስን እንድንከተል የተሰጠንንም ተልዕኮ እንድናሟላ ኃይል የሚሰጠን መንፈስ ቅዱስ ነው (የሐዋ ሥ 1፡8)
 4. መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ፍቅር በልባችን ያፈሳል፤ መንፈስ ቅዱስ ድካማችንን ያግዛል፤ በማይነገር መቃተት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይማልድልናል (ሮሜ5፡5፤ 8፡26-27)
 5. በውስጥ ሰውነታችን እንድንጠነክር፣ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች በሕይወታችን እንዲታዩ የሚያደርግ መንፈስ ቅዱስ ነው (ገላትያ 5፡22፤ ኤፌ 3፡16)
 6. ለቤተክርስቲያን መታነጽና ማደግ የጸጋ ስጦታን የሚያድለን፣ ከጨለማ ኃይላት ጋር ባለው ውጊያ በኢየሱስ ክርስቶስ ድል ለማግኘት የሚያበቃን መንፈስ ቅዱስ ነው (ኤፌ 6፡10-16፤1ኛ ቆሮ 12፡4-11)
 7. በጊዜና በሥፍራ፣ ከአሁንና ከዚህ ማዶ ያለውን ምሥጢር የሚገልጽልን ወደ እውነት ሁሉ የሚመራን የሚያጽናናንም መንፈስ ቅዱስ ነው (ዮሐንስ 14፡15-17)
 8. ጌታ ኢየሱስ በምድር በነበረበት ጊዜ አብን ያከብር እንደ ነበረ ሁሉ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በዚህ ዘመን ኢየሱስ ክርስቶስን ያከብራል፣ ከእርሱም ወስዶ ለእኛ ይነግረናል፣ ከራሱ አይናገርምና (ዮሐንስ 16፡12-15)
 9. መንፈስ ቅዱስ በሁለት በኩል የተሳለ ሰይፍ ይጠቀማል፣ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው። መንፈስ ቅዱስና ሰይፍ የሆነው ቃሉ አይለያዩም። የመጽሐፍ ቅዱስም ደራሲ መንፈስ ቅዱስ ነው (ኤፌ 6፡17፤ ዕብ 4፡12፤ 2ኛ ጴጥ 1፡21)። ስለሆነም ሁል ጊዜ ዕለት በዕለት በመንፈስ ቅዱስና በእግዚአብሔር ቃል ልንሞላ ይገባል፣ ታዘናልም (ኤፌ 5፡18፤ ቆላስይስ 3፡16) 

ኃይልን ማድረግ -- ምሥጢራዊ እውቀትን መግለጥ በክርስትና ጉዞ በመንፈሳዊ ሕይወታችን እንድንታነጽ ባለ ብዙ ፍሬዎች እንድንሆን ኃይል ያሻናል፤ የተሰወረውንም ማወቅ ይረዳናል፤ ሆኖም ኃይል ከፍቅር ጋር፣ እውቀትም ከትሕትና ጋር ካልተቀናጁ ጉዳት ያስከትሉብናል። በውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ከማስፋፋት ይልቅ፣ በራስ መከናወንን ስለምንፈልግ ብዙዎቻችን ደግሞ ይህን እንናፍቃለን፣ ኃይልን መፈልቀቅ የተሰወረውንም ማወቅ መሸልቀቅ እንሻለን፣ በከፍተኛም ጉጉት እንጠብቃለን። ከዚህም የተነሳ ኃይል ሲገለጥ ስናይ፣ የተሰወረው ሲፈለቀቅ ስንመለከት፣ ያለምንም ፍተሻ ልናቅፈውና የራሳችንም ለማድረግ እንጥራለን፤ እንዘረጋለን፣ እንወረወራለን።  

የመንፈስ ቅዱስን ኃይል መቀበል፣ መንፈስ ቅዱስ እንደ ወደደ በማከፋፈል የሚሰጠውን የጸጋ ስጦታዎች ሁሉ (ጥበብን መናገር፣ እውቀትን መናገር፣ እምነት፣ የመፈወስ ስጦታ ወዘተ) ለቤተ ክርስቲያን መታነጽ ያሻታል፤ ልምምዱም መታቀብ የለበትም። ዳሩ ግን ሁሉን መፈተን፣ መልካሙንም መያዝ ከማናቸውም ክፉ ነገር መራቅ፣ የተሰጠን የአዲስ ኪዳን ትዕዛዝ ስለሆነ፣ ሁሉን በአግባቡ፣ ሁሉም ለማነጽ መሆኑን እያረጋገጥን መጓዝ ይገባናል። ልብ ልንል ያስፈልገናል፤ በመልካሙ የመንፈስ ቅዱስ አሠራር ሁሉ በአጠገቡ አሳሳችና ተቀናቃኝ አሠራር አለ። ተቀናቃኝና አሳሳች አሠራሩ መንስኤው ልዩ ልዩ ሊሆን ይችላል፤ ይኸውም፦

 1. ከሰዎች፤ እግዚአብሔርን መምሰል ለማትረፊያነት ሆን ብለው ከሚያውሉ ከሚለማመዱ (1ኛ ጢሞ 6)
 2. ካላስተዋለ የአእምሮ ወይም ለመንፈስ ቅዱስ ካልተገዛ የልቡና አሠራር፣ 
 3. ከክፉ መናፍስት ይሆናል።

የኃይልና የምሥጢራዊ እውቀት ምንጭ በዚህ ባለንበት ዓለም ከእግዚአብሔር ወይም ከሰይጣን ሊሆን ስለሚችል ማንኛውንም መንፈሳዊ እንቅስቃሴ መመዘን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው። 

 1. “መንፈስን አታጥፉ፣ ትንቢትን አትናቁ፤ ሁሉን ፈትኑ መልካሙን ያዙ፣ ከማናቸውም ዓይነት ክፉ ነገር ራቁ (1ኛ ተሰሎንቄ 5፡19-22)
 2. ነቢያትም ሁለት ወይም ሶስት ሆነው ይናገሩ፤ ሌሎችም ይለዩአቸው (1ኛ ቆሮ 14፡22) 

ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። የሚመጣውም ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክ ወይም ያላገኛችሁትን ልዩ መንፈስ ወይም ያልተቀበላችሁትን ልዩ ወንጌል ብታገኙ በመልካም ትታገሱታላችሁ (2ኛ ቆሮ 11፡3-5)። “በመልካም ትታገሱታላችሁ” የሚለው ሐረግ አሳቡ የሐሰት አሠራር በመካከላችሁ ሲካሄድ ምንም ያህል ሳይገዳችሁ በቸልተኛነት ታስተናግዳላችሁ የሚል ሲሆን አገባቡም በነቀፌታ መልኩ ነው። 

እንደዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ፣ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኛ ሠራተኞች ናቸውና ይህም ድንቅ አይደለም፣ ሰይጣን ራሱ የብርሃን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና። እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል (2ኛ ቆሮ 11፡13-15)። 

መንፈሳዊ እንቅስቃሴን መመዘን ለምን? በምን ልብ?። ልብ መባል የሚገባው፣ በቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ እንቅስቃሴ መመዘን እንቅስቃሴውን ለማንኳሰስ ሳይሆን የጠራውን ለመያዝና በዚያም ለመገልገል ከሚፈልግ እውነተኛና ቅን ልብ የተነሳ መሆን አለበት። አንዳንዶች ክርስቲያኖች በጸጋ ስጦታዎች መገለጥ ስለማያምኑ፣ ለማጣጣል መቃወሚያ ምክንያቶችን ይፈልጋሉ፣ ለድንዛዜም ሰበብ ይሆናሉ። “መንፈሳዊ ስጦታን በብርቱ ፈልጉ” (1ኛ ቆሮ 14፡1) የሚለውን አሳብ ገሸሽ ያደርጉታል። ሌሎች ደግሞ መንፈሳዊ እንቅስቃሴን ስለሚናፍቁ ብቻ የኃይልን መገለጥ ለማድነቅ ስለሚጓጉ ብቻ ያለ ምንም ምርመራ ሁሉ እንዳይነካ ከጥያቄ ውስጥ እንዳይገባ ይከለክላሉ፣ ይጋርዳሉ። ለሰይጣን ስውር አሠራር ከለላ ተገን ይሆናሉ። ሁሉ ለማነጽ ይሁን፣ ሁሉ በአግባብና በሥርዓት ይሁን የሚለውን የጌታን ትዕዛዝ ሲረግጡ ነቢይ ወይም መንፈሳዊ የሆኑ ይመስላቸዋል (1ኛ ቆሮ 14፡37-40)። እኒህ ሁለቱም አካሄዶች ሊታረሙ የሚገባ ጐጂ አካሄዶች ናቸው። 

አንዳንዶች በቃሉ ከመኖር ይልቅ የቃሉ ጠበቆች፣ ወይም በመንፈስ ቅዱስ ከመመላለስ ይልቅ ለመንፈስ ቅዱስ የጸጋ ስጦታዎች ነገረ ፈጆች ተሟጋቾች ለመሆን ይታጠቃሉ። በአንደበት ጠበቃ ለመሆን ከመነሳት ይልቅ በቃልና በሕይወት ምስክር መሆኑ ዋናና ተፈላጊ ነገር ነው። “ከእናንተ ጥበበኛና አስተዋይ ማን ነው? በመልካም አኗኗሩ ሥራውን በጥበብ የዋህነት ያሳይ። ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አድመኝነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ አትመኩ፣ በእውነትም ላይ አትዋሹ። ይህ ጥበብ ከላይ የሚወርድ አይደለም፣ ነገር ግን የምድር ነው የሥጋም ነው የአጋንንት ነው፤ ቅንዓትና አድመኝነት ባሉበት ሥፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ሥራ ሁሉ አሉ። ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፤ በኋላም ታራቂ፣ ገር፣ እሺ ባይ ምሕረትና በጐ ፍሬ የሞላባት፣ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት። የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉ ሰዎች በሰላም ይዘራል (ያዕቆብ 3፡13-18)። 

ትክክለኛውን መንገድ አውቀው ከማድረግ በዚያም ከመመላለስ ይልቅ ምቹውን መንገድ የሚመርጡ አያሌዎች ናቸው። ይህ አባባል ትክክለኛውን ተረድተው በዚያው መመላለሱ የማያምኑትን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን አማኞችንም ይመለከታል። ለራሳቸው ምቾት ከመኖር ይልቅ ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሳው ለኢየሱስ ክርስቶስ ለመኖር የመረጡ ናቸው። በአንዳንድ ክርስቲያኖች አስተሳሰብ መንፈስ ቅዱስ ልምምድ ብቻ ነው ወይም ኃይል ብቻ ነው። አዎን ከመንፈስ ቅዱስ የሆነ ልምምድ አለ፤ ይሁን እንጂ መንፈስ ቅዱስ ከልምምዳችንም ከተቀበልነውም ኃይል በላይ የሆነ የራሱ ማንነት የራሱ ፈቃድ ያለው ከሥላሴ አንዱ የሆነ መለኮት ነው። አምላካዊ አክብሮት ሊኖረን ልናሳይም ይገባናል። በሌላ በኩል ደግሞ ያለ መንፈስ ቅዱስ ኃይል የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክሮች ልንሆን አንበቃም። ወንጌልን ለማዳረስ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በየጊዜው መሞላት ያሻናል። ታዘናልም። የመንፈስ ቅዱስ የጸጋ ስጦታዎችን መገለጥ አጥብቀን መፈለግ በአግባቡም መጠቀም ለቤተ ክርስቲያን መታነጽ እጅግ አስፈላጊአችን ነው። 

መንፈሳዊ ግርግር በአንዳንድ ሥፍራ በጸጋ ስጦታዎች ስም የሚታየው ውዥንብር ትኩረትን የሚጠይቅ ሆኖአል። መንፈሳዊ ልምምድ ከሚሰፈርና ከሚለካ ነባራዊ ሁኔታ ውጭ ስለሆነ አንዳንዶቻችን እንዳሻን ልንልበት፣ እንዳሻን ልናደርግበት፣ ፈር የወጣንበት፣ ተመልካች፣ መዛኝ የሌለበት፣ በማን አለብኝ አስተሳሰብ የምንለቀቅበት የምንቧልልበት ሜዳ መስሏል። ከመንፈስ ቅዱስ ሳይሆን ከገዛ መንፈሳችን እንደ ምኞታችን እንደ ስሜታችን “እንዲህ አለኝ” “እንዲህ ተናገረኝ” “እንዲህ ታየኝ” ስለዚህ “እንዲህ በሉ” “እንዲህ አድርጉ” ብለን ትእዛዝ የምንሰጥበት፣ በዙሪያችን ላሉ እንደየሁኔታቸው እንደየምኞቶቻቸው እያስተያየን የመከናወንን ተስፋ የምናርከፈክበትና በምላሹ ታላቅነትን ተቀባይነትን አጀብን የጥቅም ማጋበስን የምንጠብቅበት መስተጋብር፣ የሥነ ተረት ስንክሳር ሆኖአል። መቸም “ግርግር ለሌባ ያመቻል” አንዳንዶች መንፈሳዊ ግርግሩን ይወዱታል። የእግዚአብሔር ቃል “እግዚአብሔር የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አይደለምና በቅዱሳን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዲሁ ነው” ሲል ሁከት ከእግዚአብሔር እንዳልሆነ ያስገነዝበናል (1ኛ ቆሮ 14፡43)። ከእግዚአብሔር ካልሆነ ደግሞ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከአሳሳቹ ከሌባው ከሰይጣን መሆኑን ልናስተውል ይገባል። ብዙውን ጊዜ በኑሮአቸው ጽድቅና ቅድስና የማይንጸባረቅባቸው በየዕለት አካሄዳቸው ሃቀኛነት የማይታይባቸው በእንደዚህ ዓይነቱ መንፈሳዊ ግርግር ወቅት ዋናና አጋፋሪ ይሆናሉ። ታላቅና መንፈሳዊ መስለው ለመታየት ይሻሉ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ መናፍስትን የመለየት የጸጋ ስጦታ ያለው የእግዚአብሔር ሰው የከበረውን ከተዋረደው የሚለይ መልእክት ቢያመጣ በዙሪያው ያሉት “ሊወግሩት” ይጋበዛሉ። የጠራ ነገር አይፈለግምና።

“አንተም የሰው ልጅ ሆይ፣ ከገዛ ልባቸው ትንቢት በሚናገሩ በሕዝብህ ሴቶች ልጆች ላይ ፊትህን አድርግ ትንቢትንም ተናገርባቸው፣ እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ነፍስን ለማጥመድ ለእጅ ድጋፍ ሁሉ መከዳ ለሚሰፉ ለሰውም ሁሉ ራስ እንደየ ቁመቱ ሽፋን ለሚሰሩ ሴቶች ወዮላቸው፤ የሕዝቤንም ነፍስ ብታጠምዱ በውኑ ነፍሳችሁን ታድናላችሁን? ውሸታችሁን ለሚሰሙ ሕዝቤ እየዋሻችሁ …ስለ ጭብጥ ገብስና ስለ ቁራሽ እንጀራ በሕዝቤ ዘንድ አርክሳችሁኛል” (ሕዝ. 13፡17-19)።     

"አለምሁ እያሉ በስሜ ሐሰትን የሚናገሩትን የነቢያትን ነገር ሰምቻለሁ ትንቢትን በሐሰት በሚናገሩ የልባቸውንም ሽንገላ በሚናገሩ ነቢያት ልብ ይህ የሚሆነው እስከ መቸ ድረስ ነው? … እነሆ እያንዳንዱ ከባልንጀራው ዘንድ ቃሌን በሚሰርቁ ነቢያት ላይ ነኝ ይላል እግዚአብሔር። እነሆ ከምላሳቸው ትንቢትን አውጥተው እርሱ ይላል በሚሉ ነቢያት ላይ ነኝ ይላል እግዚአብሔር። እነሆ ሐሰትን በሚያልሙ በሚናገሩ በሐሰታቸውና በድፍረታቸውም ሕዝቤን በሚያስቱ ነቢያት ላይ ነኝ ይላል እግዚአብሔር እኔም አላልኋቸውም አላዘዝኋቸውምም ለእነዚህም ሕዝብ በማናቸውም አይረቡአቸውም ይላል እግዚአብሔር” (ኤርምያስ 23፡25-32)።  

አሳሳች ተቀናቃኝ አሠራር ሰይጣን የማሳቱን ሥራ ለማካሄድ ሽምጥጥ ያለ ገሃድ ውሸት ይዞ አይደለም ወደ እኛ የሚመጣው። የሚያስተን እውነትን ከሐሰት ጋር አደባልቆ ለእኛ የተቆረቆረ መስሎ በማባበል ነው። አዳምና ሔዋንን ሲያስት “ሞትን አትሞቱም ከእርሷ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካሙንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ” በሚለው አነጋገር ውስጥ እውነትና ሐስት ተደባልቀዋል (ዘፍጥረት 3፡4)። ከፍሬዋ በበሉ ጊዜ በእርግጥ ሞቱ፣ ከእግዚአብሔር ተለዩ። ይሁን እንጂ መልካሙንና ክፉውን ለማወቅ እንደ እግዚአብሔር ሆኑ። “እግዚአብሔር አምላክም አለ እነሆ አዳም መልካሙንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ…” (ዘፍ 3፡22)፤ ስለሆነም ሰይጣን ቅልጥጥ ባለ መንገድ ወደ እኛ እንደሚመጣ በማሰብ እንዳንታለል። አሳሳች አሠራር የማስመሰል ስልት አለው። በቀላሉ እንዳይነቃ እስከ ተቻለ ድረስ ይመሳሰላል። ለምሳሌ፦ አንድ የሩዝ ትል መጠኑና ቀለሙ አንድ የሩዝ ፍሬ ይመስላል። የፀጉር ቅማል እንደ ፀጉር ጥቁር ነው። አሳሳች ሰይጣን እንደ ብርሃን መልአክ ራሱን ይለውጣል።  

የመወያያ ጥያቄዎች፦ 

 1. አንድ ሰው ልኩን እያወቀ ለምን አያደርገውም?
 2. ጸሐፊው፣ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ስለታየ ብቻ እውነተኛ መንፈሳዊነት አለ ማለት አይደለም ይለናል፤ ስለዚህ ምን አድርጉ ይለናል?
 3. እውነተኛ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ምልክቶቹ ምንድናቸው?
 4. ሰይጣን የሚያስተው እንዴት ነው? የሚያስተውስ ምን ዓይነቶቹን ሰዎች ነው?
 5. የስሕተትን አሠራር የሚያራምዱትን አገልጋዮች እንዴት ይገልጻቸዋል?
 6. መንፈስ ቅዱስ ማነው? አሠራሩስ ምን ይመስላል?
 7. ከቤተ ክርስቲያን መልስ “እስቲ ዛሬ ምን ተማርኩ” እንላለን? መልእክቱ ግልጽ ነው ወይስ የተወሳሰበ ነው? ከሌሎች ጋር በሰማነው መልእክት ላይ እንወያያለን?