በሞት ጥላ ከታለፈ በኋላ

ጸሎቴን ያልከለከለኝ ምሕረቱንም ከእኔ ያላራቀ እግዚአብሔር ይመስገን። መዝሙረ ዳዊት 6620

ስሜ ጽጌ ብሩ በንቲ፣ የባለቤቴ ደግሞ ጌታቸው ዘርጋው ይባላል። ነዋሪነታችን ለንደን ከተማ ሲሆን  ጌታን የምናመልከውና የምናገለግለው ለንደን ባለችው የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ህብረት ቤተክርስቲያን ነው።

በጥር ወር  2002 ዓ.ም  ህመም  ስለተሰማኝ  ወደ  ሀኪም  ቤት  ሄድኩ።  የህክምና ባለሞያዎች ህመሜ ምን እንደሆነ ለማወቅ እና ምን  ዓይነት  ህክምና መስጠት እንዳለባቸው ለመወሰን  ብዙ ምርመራና ጥናት  ካደረጉ በኋላ የካንሰር (Diffuse Large B-cell Lymphoma cancer, grade 2) ህመምተኛ መሆኔን ነገሩኝ። ከዚህ ህመም ለመዳን የሚረዳኝ ህክምና፣ ስድስት ዙር “ኪሞቴራፒ” እና ሁለት ዙር “ሪተክሲማብ” የተሰኘ እንደሚሆን፣  ይህም መድሃኒት በየሦስት ሳምንቱ እንደሚሰጠኝ ተነገረኝ።  ይህን አስደንጋጭ ዜና ከሰማን በኋላ እኔና ባለቤቴ ቤታችን ገብተን በራችንን በመዝጋት ከብዶ አቅም ያሳጣንን ነገር አቅም ላለው ሁሉን ለሚችል ለእግዚአብሔር አስረከብነው ።  ለቤተሰብ እና ለወዳጆቻችን ሁሉ ያለንበትን ሁኔታ በስልክና በኢሜይል በመግለፅ እንዲፀልዩልን ጠየቅን። 

tsigeእግዚአብሔር ረድቶን ፀጋውም በዝቶልን በፕሮግራሙ መሠረት በሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ ህክምናዬን  ጨርሼ አሁን በሙሉ ጤንነት ላይ እገኛለሁ። ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን። ህክምናዬን ጀምሬ ሁለተኛውን  ዙር “ኪሞ” ከወሰድሁ በኋላ አንድ ምሽት እንዲህ ሆነ። ባለቤቴ እየተደረገልኝ ያለው ህክምና በጤናዬ ላይ እያመጣ ያለውን ለውጥ፣ የሰጠኝን እረፍት ማየቱ በምናቡ እንዲነጉድና ጆሮዎቹ የሰቆቃ ድምፃቸውን ዓይኑም መከራቸውን እንዲያይ እረድቶት ብዙ እንዲተክዝና እንዲቆዝም ከሆነበት መለስ ብሎ፣ “እኛ እኮ ዕድለኞች ነን” አለ፤ “ሁሉ ነገር በተሟላበት አገር በመኖራችን ይኸው እየታከምሽ ነው። ግን የሀገራችን ሕዝብ በተለይም ድሀው ገጠሬ፣ እንደ ካንሰር ዓይነት ላለው በሽታ ብዙም ዕውቀት በሌለበት፣ እንዴት ይሆን የሚሆነው? እንዴት መከራው ይበዛ?” አለና፤ አስከትሎ፣ “ስትድኚ ባለን አቅም በሀገራችን የካንሰር ህመምተኞችን እንረዳለን” አለኝ።

ህክምናዬን ጨርሼ አቅሜ ጠንከር ሲል፣  በታህሳስ ወር 2003 ዓ.ም እኔና ባለቤቴ ቤተሰቦቻችንን እና ጓደኞቻችንን ለማየት ወደ ኢትዮጵያ ሄድን። በዚያው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላሉት የነፃ ህክምና ወደሚሰጠው ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የካንሰር ማዕከል አመራን። የካንሰር ህክምና ሃላፊ የሆኑትን ዶክተር ቦጋለ ሰለሞንን አግኝተን አነጋገርን። እሳቸውም ያለውን ሁኔታ በማብራራት የካንሰር ማከሚያ ክፍሉ ያለውንና የሚጎድለውን አዙረው አሳዩን። ወገኖቼ ሁኔታው በጣም ያሳዝናል። በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን በኢትዮጵያ ውስጥ በኤችአይቪ፣ በወባና በሳንባ ነቀርሳ ህመም ምክንያት ከሚሞተው ይልቅ በካንሰር በሽታ የሚሞተው ሰው ቁጥር እጅግ እየበዛ እንደሆነ ከካንሰር ማዕከሉ ተረዳን። ለመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ካንሰር ማከሚያ ያለው አንድ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ ነው። በዚህ ሆስፒታል ሥር ስድስት ሺህ የሚሆኑ የካንሰር ታካሚዎች ያሉ ሲሆን  በየዓመቱ  ቢያንስ ሁለት ሺህ አዲስ የካንሰር ህሙማን ይመዘገባሉ። ከዚያ ውስጥ ከመቶ እጅ ሃምሳ አምስት ያህሉ ሴቶች የጡትና የማህፀን ካንሰር በሽተኞች መሆናቸውንም አረጋገጡልን። ሆሰፒታሉ ለዚህ ሁሉ በሽተኛ ማከሚያ የሚሆን አንድ ሬዲዮ ቴራፒ መስጫ ብቻ ስላለው፣ የካንሰር ማዕከሉ ሀኪሞች ረጅም ሰዓት እየሠሩም እንኳ በሽተኞችን ለማከም የስድስት ወር ቀጠሮ ማስያዝ ግዴታ ሆኖበታል። ያም ሆኖ ከመቶ እጅ አሥራ አራቱ የካንሰር ህሙማን ያንን ስድስት ወር እየጠበቁ ህክምናም ሳያገኙ እንደሚሞቱ ገልጸውልናል።

cancercntrበዚህ አድፍጦ ገዳይ በሽታ፣ በባላገር የሚኖሩ ስንቶች ባካባቢያቸው ወዳለው ጤና ጣቢያ እንኳን ለመሄድ ዕድል ሳያገኙ በዚያው ለዘላለም እንደቀሩ ቤቱ ይቁጠረው። በሌላ በኩል ደግሞ ትንሽ የተስፋን ስንቅ ሰንቀው እንደምንም ጥረው የሆስፒታሉን ደጅ የረገጡ፤ ረጅም እና ተስፋ አስቆራጭ ቀጠሮ እየጠበቁ፤ ያለ እንቅልፍ እያደሩ፣ ዋ! እያሉ የጣር ጩኸት እየጮሁ፣ በመሣሪያ እጦት እርዳታ ሳያገኙ፣ ከልጆቻቸው፣ ከትዳራቸውና ከወዳጆቻቸው በሞት የተነጠቁ የእናቶች፣ የአባቶች፣ የልጆች፣ የወንድም እና የእህቶች ቁጥር ቀላል አለመሆኑን ከሃላፊው ገለጣ ከተረዳን በኋላ ልባችን አዝኖ፣ ወደ ለንደን ተመለስን።

ወገኖቼ! ስለ ካንሰር በሽታ ከማንበብና ከመስማት ባለፈ ታምሜ በእግዚአብሔር ምህረትና ቸርነት በህክምና እርዳታ የተፈወስኩ በመሆኔ የህመሙ ጉዳትና ክብደት ምን ያህል እንደሆነ በጣም የገባኝ ሰው ነኝ። በሽታው እንኳን አለህክምና በህክምናም ታግዞ ቀላል አደለም። ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን ከጎበኘን በኋላ ሁኔታው ተስፋ አስቆራጭ ቢሆንም በተለያዩ አህጉራት በተለይም ደግሞ በሠለጠኑት አገሮች የምትኖሩትን ወገኖቼን ሁሉ አስቤ ተጽናናሁ። “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” ይባል የለ? አዎን፣ ሁላችንም ተባብረን በኢትዮጵያ ለሚገኙ የካንሰር በሽተኞች ለህክምና ጠቃሚ የሆነውን ነገር ማድረግ እንደምንችል በሙሉ ልቤ ተማመንሁባችሁ። ስለዚህ እንደምንም ብለው ከህመማቸው እፎይታን ለማግኘት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ካንሰር ማዕከል ድረስ መጥተው ግን በማከሚያ መሣሪያ እጥረት ምክንያት በረዘመ ቀጠሮ ያለህክምና የሚሞቱትን ህሙማንንና ቀንና ሌሊት ቆጥረው፣ ማዕከሉ ደርሰው ህክምናቸውን ሳይጨርሱ የሚያልፉትን ስቃይ ይዘን ልግስናችሁን ለመጠየቅ አምስት ሰዎች (ሁለታችን በበሽታው ያለፍን፣ ሶስቱ ደግሞ አብረውን የቆሙ) “ፍልሚያ ከካንሰር ጋር በኢትዮጵያ” (Battling Cancer in Ethiopia, BCE) በሚል ስም በጎ አድራጎት ድርጅት መሥርተናል። ይህ የበጎ አድራጎት ድርጅት በእንግሊዝ አገር ሕግና ደንብ መሠረት የተመዘገበ ነው። ድርጅቱ ከፖለቲካና ከሀይማኖት ነፃ ሲሆን ከለጋሶች የሚሰበስበውን ገንዘብ መቶ በመቶ ለህክምና መሣሪያ መግዣ ብቻ ያውላል። የ BCE ሥራና ዓላማው፡- በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና የሰው ሕይወት ግድ ከሚላቸው ገንዘብ አሰባስቦ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የካንሰር ማዕከል የጠየቀውን ለካንሰር ህክምና መስጫ CT Simulator መግዛት ነው።

መሣሪያውን ለመግዛት፤ ማዕከሉ ድረስ ወስዶ ለማስገጠም፣ ሠራተኛ ለማሠልጠንና ለሦስት ዓመት የጥገና ወጪ ለመሸፈን የሚያስፈልገው አንድ ሚሊዮን የእንግሊዝ ፓውንድ ነው። ወገኖቼ፡ ሁሉ በሞላበት ምድር ስንኖር፣ መርጠን የምንበላና መርጠን የምንለብስ፣ ከአብዛኛው የአገራችን ሕዝብ በተሻለ ሁኔታ የምንገኝ መሆናችን እሙን ነው። ስለዚህ፣ ለካንሰር በሽተኞች ህክምና መስጫ የሚረዳውን CT Simulator ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሚገዛበትን ገንዘብ ለመርዳት እጃችሁን እንድትዘረጉ እማጸናችኋለሁ።

እስቲ አንድ አፍታ ራሳችሁንና የምትወዷቸውን ዘመዶቻችሁን አስቡ። በቂ ህክምና በሌለበት አገር ብኖር ኖሮ ብላችሁ። ስለገዳይ በሽታዎች እውቀት በሌለበት ብኖር ኖሮ። ጤና ጣቢያ ሄጄ የካንሰር በሽተኛ ነሽ ተብዬ ቤቴን ልጆቼን ትቼ ወደ አዲስ አበባ ለህክምና የምሄድ ቢሆን ኖሮ። ሆስፒታሉ አንድ የካንሰር ህክምና መስጫ መሣሪያ ብቻ ኖሮት ረጅም ቀጠሮ ሰጥቶ ሲሸኘኝ። ያለህክምና ቀጠሮ እየጠበቅሁ፣ ረሃብ እየጠበሰኝ፣ ህመሙ ሰውነቴ ውስጥ እየተሠራጨ እርዳታም ሳላገኝ የመሞቻዬን ቀን ስቆጥር ብላችሁ አስቡ። እግዚአብሔር ረድቶኝ ህክምና ካለበት ምድር ባልገኝ ኖሮ፣ እኔም የሞት አልጋ ላይ ሆኜ ሞቴን የምጠብቅ ነበርኩ። ይህን ማስታወሻ ልጽፍላችሁ ባልበቃሁ። ዛሬ በኢትዮጵያ ምድር ያለው ሁኔታ ይህን ይመስላል። ወገኖቼ! ለካንሰር ህመምተኞች እኛ ካልደረስንላቸው ለልጆቻቸው እናቶች እንዲሆኑ ሁለተኛ እድል  ካልሰጠናቸው የሚጠብቃቸው ሞት ነው። ከሞት ባናስጥላቸው እንኳ ታክመው የመዳንን ተስፋ እየጠበቁ እንዲሞቱ እንርዳቸው። ጥቂቶችንም ቢሆን ከሞት አልጋ ቀና ቢሉ ለሁላችንም ደስታ ስለሚሆን ካለመቆጠብ እጃችሁን ትዘረጉ ዘንድ ታክማ እንደ ዳነች የካንሰር ህመምተኛ፣ ህክምና ባጡ ህመምተኞች ስም ሆኜ ደግሜ ደጋግሜ እለምናችኋለሁ። ስለትብብራችሁ በቅድሚያ አመሰግናለሁ። ሰላምና ጤና ይብዛላችሁ።

ስጦታችሁን በሚከተለው አድራሻ ገቢ ማድረግ ትችላላችሁ፡- Battling Cancer in Ethiopia; Off-line: HSBC Bank; IBAN: GB45MIDL40040721450675; SWIFT/BIC: MIDLGB22; On-line: PayPal: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.; Registered Charity no. 1146052; በተጨማሪ ድረ ገጻችንን በዚህ አድራሻ ይጎብኙ። http://www.bcethiopia.org/ 

የእህት ጽጌ ባለቤት፣ በለንደን ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በስታቲስቲክስና ማትማቲክስ ሲኒየር ሌክቸረር ናቸው።