ሱስ አምጪ መድኃኒቶች፤ ዕጽዋትና ጎጂ ኬሚካሎች

ወርቁ አበበ

በዚህ በአሜሪካ ከምኖርባት ትንሽ ከተማ ወጣ በማለት ብዙ ኢትዮጵያውያን ወደሚኖሩባቸው ትላልቅ ከተማዎች ብቅ ባልኩ ቁጥር በርከት ያሉ ኢትዮጵያውያን ሲጋራ ሲያጨሱና የአልኮል መጠጥ በገፍ ሲጠጡ ተመልክቻለሁ። ከዘመድና ከጓደኛም ጋር ምን አዲስ ወሬ እንዳለ ጨዋታ ሲጀመር፤ በወሬ መሃል አንዳንድ የአገራችን ሰዎች በሱስ አምጪ መድሃኒቶች፤ እጽዋትና ተመሳሳይ ኬሚካሎች አንደተነካኩ ብዙ ጊዜ ሰምቻለሁ። ከትንሽዋ ከተማዬም ሳልወጣ፤ በተለያዩ የዜና ማሠራጫዎች አማካኝነት ኢትዮጵያውያን አልፎ አልፎ ከጫት ጋር በተያያዙ የወንጀል ድርጊቶች እንደተሠማሩ ለመገንዘብ ችያለሁ። በአሁኑ ወቅት ሱስ አምጪ በሆኑ ነገሮች መለከፍ የኢትዮጵያውያን ችግር ብቻ ሳይሆን የዓለም አጠቃላይ ችግር እንደሆነ በስፋት ይነገራል። በተለይም ወጣቱን ትውልድ አስመልክቶ። ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ ስለዚህ ችግር የምሰማውና የማነበው ስላሳሰበኝና አዝማሚያውም ሰላላማረኝ፤ የሚመለከታቸውን ለማሳሰብ ያህል ይህንን አጭር ጽሑፍ ብዙዎቻችን በይበልጥ በምናውቀው ቋንቋ ለመጻፍ ተነሳሁ። አንዳንድ ቴኪኒካዊ የሆኑ ጉዳዮችን በብቃት ለመግልጽ አስቸጋሪ ቢሆንብኝም፤ አንባቢያን የጽሑፌን አጠቃላይ መልእክት ይረዳሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

ለመሆኑ “ሱስ” ሲባል ምን ማለት ነዉ? ባጭሩ፣ ሱስ አምጪ የተባለው ነገር ተደጋግሞ እንዲወሰድ የሚገፋፋ መጥፎ ልምድ ወይም ሁኔታ ማለት ነው። እንደሚወሰደው ነገር አይነትና እንደ አወሳሰዱ ሁኔታ እንደዚሁም እንደ ወሳጁ የአዕምሮና የአካል አቋም የሱሱ አይነት ወይም ደረጃ ሊለያይ ይችላል። ለምሳሌ ያህል የሱሱ ሁኔታ ከፍተኛ ከሆነ፤ ሱሰኛው ለሱስ አምጪው ነገር የአዕምሮም ሆነ የአካል ተገዥ ሊሆን ይችላል። በዚህን ጊዜ ሱሰኛው ፍላጎቱን ለሟሟላት ብዙ የማይጠበቁ ነገሮችን ለማድረግ ይገደዳል። በድርጊቱም ራስን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ሊጎዳ ይችላል። በሱስ ለመያዝ ዋና መነሻ ተብሎ የታመነው፤ ሱስ አምጪው ነገር ከተወሰደ በኋላ በአዕምሮ ላይ በቅድሚያ የሚፈጥረው “የደስታ”፤ የእርካታንና “የድል” ስሜትን ነው። ይህ የአዕምሮ ሁኔታ ሱስ አምጪው ነገር በማከታተል እንዲወሰድ ይገፋፋል። ሁኔታው በዚህ ብቻ ሳያበቃ የሚወሰደው ነገር መጠን እየጨመረ እንዲወሰድ የሚያስገድድ ስሜት ይፈጠራል። ሱሰኛው በዚህ ከቀጠለ የሚወሰደው መድኃኒት፤ ዕጽ ወይም ሌላ ተመሳሳይ ኬሚካል በሰውነቱ ውሰጥ ረዘም ላለ ጊዜ በመቆየት በአካል ላይ አይነተኛ ለውጥ በማምጣት በመጨረሻ ሱስ አምጪው ነገር እንደሚፈለገው ካልተወሰደ ሰውነት በትክክል ለመሥራት ይሳነዋል። ሰለዚህ ይህንን ተደራቢ ችግር ለመቋቋም ሱሰኛው የለመደውን ነገር ላለማቋረጥ አስፈላጊውን ሁሉ ያደርጋል። ከላይ የተሰጠው ምሳሌ ከፍተኛ ለሆነ የሱስ ዓይነት ሲሆን፤መለስተኛ የሆኑ የሱስ ጸባዮችም የሚታዩባቸው ብዙ ሁኔታዎች አሉ።

በብዙ አካባቢዎች ሱስ ሊያመጡ የሚችሉ በርካታ ነገሮች ሲኖሩ፡ በስፋት ከታወቁት መካከል ጥቂቶቹ ቀጥሎ የተዘረዘሩት ናቸው። ማርዋና፡- ይህ ከዕጽ የሚገኝ ሱስ አምጪ የሆነ ነገር ነው። ካናቢስ በመባልም ይጠራል። የማርዋና የተለያዩ የሚወሰዱ ዝግጅቶች ሲኖሩ፤ በብዙዎች ዘንድ የታወቀዉ “ሀሽሽ” እየተባለ የሚጠራው ነው። ማርዋና የአዕምሮን ቦታና ጊዜን የማገናዘብ ችሎታንና የቅርብ ጊዜን ድርጊቶች የማስታወስ አቅም ይቀንሳል። በአንዳንድ ተጠቃሚዎች ላይ መደናገጥን፤ ጥርጣሬንና ቅዥትን ያመጣል። ብዙውን ጊዜ ማርዋና በማጬስ የሚወሰድ ነው። ሱስ ከማምጣት ባሻገር ማርዋና ሳንባን፤ ልብንና የርቢ አካላትን ሊጎዳ የሚችል ነው። ኮኬን፦ የዚህ ሱስ አምጪ ነገር ምንጩ እንደገና ዕጽ ነው። ከማርዋና ጋር ሲወዳደር ኮኬን ከፍ ያለ ሱስ የሚያመጣና በይበልጥ የሚጎዳ ነው። መረበሸን፤ መጠራጠርን፤ መቃዠትን፤ ፋታ ማጣትንና ቁጡነትን ያመጣል። በተጨማሪም ኮኬን የልብ መታወክን፤ የደም ብዛትን፤የሆድ ህመምን ይፈጥራል። ኮኬን በተለያዩ መንገዶች የሚዘጋጅና የሚወሰድ ነው። ሂሮይን፦ ይህ ኬሚካል በከፊል አመጣጡ ከዕጽ ነው። ሂሮይን ከባድ ሱስ ከሚያመጡ ነገሮች መካከል አንዱ ነው። ሲወሰድ ከሚያመጣቸው የጤንነት ቀውሶች መካከል መፍዘዝን/መደንዘዝን፤ መምታታትን፤ ማቅለሽለሽን፤ የሆድ ድርቀትን፤ የመተንፈስ ጭንቀትንና ዝግተኝትን ይፈጥራል። ሱሰኞች ሂሮይንን የሚወስዱት በመርፊ መልክ በመወጋት ነው። የአልኮል መጠጥ፦ ይህ ሱስ አምጪ ነገር ለመጀመሪያ ጊዜ ወይም በመጠኑ ሲወሰድ የሚያነቃቃና አዝናኝ ሲሆን፤ መጠጣቱ ግን ሲቀጥል አደንዛዥ ብሎም ሰውነትን የመቆጣጠር ችሎታን የሚያሳጣ ይሆናል። ረዘም ላለ ጊዜ በብዛት ሲወሰድ የጉበት በሽታን፤ የልብ በሽታን፤ የደም ብዛትን፤ የአዕምሮና የነርቭ ህመምን እንደዚሁም ሌሎች ችግሮችን ያስከትላል። በተለይ የአልኮል ተገዢ የሆነ ሰው ብዙ ችግሮች የሚታዩበት ነው። ከችግሮቹ መካከል ጠጪው አልኮልን በማይወስድበት ወቅት ከሞላ ጎደል ሁሉንም ሰውነቱን በመነካካት የሚታዩ እንደ ቅዥት፤ ትኩረት ማጣትን፤ የምግብ ፍላጎት መቀነስን፤ መንቀጥቀጥን፤ የልብ ትርታና የደም ብዛት መጨመርን የመሳሰሉ ህመሞች ይንጸባርቃሉ። በነዚህ ችግሮች ላለመሰቃየት ሱሰኛው መጠጣቱን ይቀጥላል።

ጫት፦ ጫት በተለያዩ ህገ ወጥ በሆኑ መንገዶች እዚህ አሜሪካ እንደሚገባ ብዙ ጊዜ ተገልጿል። ለሚፈለገው አገልግሎት ጫት ብዙውን ጊዜ ቅጠሉን በማላመጥ ነው የሚወሰደው። ጫት ለአዕምሮ ጊዜያዊ ንቃትን የሚሰጥ ነው፤ ስለሆነም ብዙውን ጊዜ የሚወሰደው ለዚሁ ሲባል ነው። ጫት ለረጅም ጊዜ በተለይም በብዛት ሲወሰድ በቀላሉ ተናዳጅነትን፤ መሸበርን፤ ቅዠትን፤ መንቀዥቀዥን፤ መደንበርን፤ በፍጥነት ተለዋዋጭ መሆንንና እንቅልፍ ማጣትን ያመጣል። በአንጎል ላይ ከሚያመጣው ችግር በላይ ጫት የደም ብዛትን ይጨምራል፤ የልብ መምታትን ያፋጥናል፤ የሆድ ድርቀት ያመጣል፤ የምግብ ፍላጎትን ይቀንሳል፤ መተንፈስን ያዳክማል፤ ጉበትን ይጎዳል፤ ጥርስንም ያበላሻል። ስለጫት በይበልጥ ለማወቅ ካስፈለገ፤ ደራሲው ከዚህ በፊት የጻፋቸው ጽሁፎች በተለያዩ የኢትዮጵያዊያን ድህረ ገጾች ላይ ይገኛሉ። ትንባሆ፦ ባጭሩ ትንባሆ አዕምሮ ላይ ከሚያመጣው የንቃት ስሜትና ሱስ በተጨማሪ፤ የደም ብዛትን፤ የልብ ህመምን፤ የሳንባ በሽታን፤ የተለያዩ የካንሰር ዓይነቶችንና የጥርስ መበላሸትን ሊፈጥር እንደሚችል ተመዝግቧል። ትንባሆ በኢትዮጵያውያን በብዛት የሚወሰደው በሲጋራ መልክ በማጨሰ ነው።

በሳንባ በኩል የሚወሰዱ ሌሎች ኬሚካሎች፦ እነዚህ ሱስ አምጪ ኬሚካሎች በአፍ ወይም በአፍንጫ ተስበው በሳንባ በኩል ሰውነት ውሰጥ የሚገቡ ናቸው። ኬሚካሎቹ በብዙ መንገድ በሰውነት ውስጥ የሚሠሩ ወይም ጉዳት የሚያመጡ ናቸው። ብዙዎቹ እንደ ተወሰዱ ወዲያውኑ የአዕምሮ ንቃት ይሰጡና ቀጥሎም ማደንዘዝን፤ ራስምታትን፤ ማቅለሽለሽን፤ መንገዳገድን፤ መደንበርን፤ መርሳትንና የልብና የነርቭ መታመምን ያስከትላሉ። በስፋት ከሚገኙት ከእነዚህ ኬሚካሎች መካከል በምሳሌነት፣ የዕቃ ማጣበቂያ (ግሉ)፤ የግድግዳ ቀለም መበጥበጫ፤ የጸጉር ሰፕሬይ፤ ቤንዚን (ጋዝ)፤ እንደ ቡቴን ጋዞችና አንዳንድ ተናኝነት ያላቸው የላቦራቶሪ ወይም የኢንዱስትሪ ፈሳሽ ኬሚካሎች የሚጠቀሱ ናቸው። አስፈላጊው ጥንቃቄ ካልተወሰደ እነዚህ ነገሮች የልብንና የሳንባን አሠራር በማቃወሰ ድንገተኛ ሞት ሊያመጡ የሚችሉ ናቸው። ለረጅም ጊዜ ሲወሰዱ ደግሞ የአዕምሮን የማሰብ ችሎታና የዐይንን የማየት ብቃት ይቀንሳሉ፤ በሰውነት ላይ ክሳት ያስከትላሉ፤ የአጥንት ቅልጥምም እንዲበላሽ በማድረግ በደም አሠራርና አገልግሎት ላይ ችግር ይፈጥራሉ። በሐኪም የሚታዘዙ ሱስ ሊያመጡ የሚችሉ መድሃኒቶች፦ ለጭንቅላት/ለራስ በሽታዎች ተብለው ሐኪም የሚያዝዛቸው ብዙ መድኃኒቶች በትክክል ከጥቅም ላይ ካልዋሉ፤ ሱስንና ሌሎች ብዙ ችግሮችን ሊያመጡ የሚችሉ ናቸው። ከነዚህም መካከል አደንዛዥ መድኃኒቶች፤ እንቅልፍ አምጪ መድኃኒቶች፤ አንቂ መድኃኒቶች፤ መንቀዥቀዥን ማረጋጊያ መድኃኒቶች፤ የስጋት ማስታገሻ መድኃኒቶችና የህመም ስሜት ማብረጃ መድኃኒቶች ይገኙባቸዋል። መድኃኒቶቹ ያለአግባብ ከተወሰዱ፤ እንደ ዓይነታቸው የተለያዩ የአዕምሮና የሌላ የአካላት ችግር ያመጣሉ። በዚህ ርዕስ ሥር ሊጠቃለሉ የሚችሉ እንደ ባርቢቹሬት፤ ቢንዞዲያዜፕን፤ ኦፒዮይድስ አምፊታሚን የመሳሰሉ መድኃኒቶች ናቸው።

ከላይ ከተዘረዘሩት መሠረታዊ ጉዳዮች በተጨማሪ ሱስ አምጪ ስለሆኑ ነገሮች ቀጥሎ የተመለከቱት ተያይዘው መታወቅ ይኖርባቸዋል። ማናቸውም መድኃኒት ወይም ኬሚካል በብዛትና ለረጅም ጊዜ ሲወሰድ ጉዳቱ ከፍተኛ ይሆናል። የተለያዩ መድኃኒቶች/ኬሚካሎች ተደባልቀው ሲወሰዱ ደግሞ ያለተጠበቀ ጉዳት ሊያመጡ ይችላሉ። ሱሰኞች የሚወስዷቸው ብዙ ሱስ አምጪ ነገሮች ቁጥጥርና ጥራት ስለሚጎላቸው፤ ያልታወቁ ተጨማሪ ጉዳቶች ይኖራቸዋል። በተጨማሪም በመርፌ መልክ የሚወሰዱት መድኃኒቶች/ኬሚካሎች በወሳጁ ላይ እንደ ኤቻአይቪ/ኤይድስና ሄፓታይቲስ የመሳሰሉ በሽታዎችን ሊያስተላልፉ ይችላሉ።

በዚህ ጽሑፍ የተገለጹትንም ሆነ ሌሎች ሱስ አምጪ የሆኑ ነገሮችን ለመቆጣጠርና በአግባብ ከጥቅም ለማዋል ወይም ጥቅም የሌላቸውን ለማስወገድ፤ በተለያዩ አገሮች የወጡ መመሪያዎች አሉ። በአሜሪካ እነዚህ መድኃኒቶች/ኬሚካሎች በአንድ ላይ “ቁጥጥር የሚደረግባቸው ቁሳቁሶች” በመሰለ ስያሜ ታውቀው በሚያመጡት የሱስ ዓይነትና በሌሎች መለኪያዎች ተገምግመው በአምስት ክፍል ተዋቅረዋል። ከዚህ አመዳደባቸው ጋር በማገናዘብ መድኃኒቶቹን/ኬሚካሎቹን ከህግ ውጪ ለሚጠቀሙ፤ ለሚሠሩ ወይም ለሚያሠራጩ ሰዎች ተመጣጣኝ የሆኑ ቅጣቶች ተመድበዋል። ሰለዚህ ከእነዚህ ሱስ አምጪ ነገሮች ራስን በተቻለ መጠን ማራቁ፤ በሰውነትም ሆነ በኢኮኖሚ ላይ ሊያመጡ ከሚችሉት ጉዳት መትረፍ ብቻ ሳይሆን ከወንጀልና ከቅጣትም መዳን ሊሆን ይችላል። በመድኃኒቶችና በሌላ ተመሳሳይ ነገሮች ሱስ ላለመጠመድ እነዚህን ነገሮች መውሰድ አለመጀመሩ ከሁሉ በላይ የሚመረጥ እርምጃ ነው። ለዚህም ነገሮቹ ከተወሰዱ በወሳጁ ላይ ሊያመጡ የሚችሉትን ችግሮች በቅድሚያ ማወቁ የሚረዳ ነው። ስለዚህ ችግሩን በቅድሚያ ለመከላከል ቅድመ-ትምህርት ወሳኝ ነው ለማለት ይቻላል። በቁሳቁሶቹ ሱስ ለተጠመደ ሰውም ቢሆን ሊረዱ የሚችሉ ልዩ ልዩ አገልግሎቶች አሉ። ፈቃደኛ ለሆነ ሱሰኛ የባለሞያ ስነልቦናዊ ምክር ማግኘት፤ የድጋፍ ክለብ አባል መሆንና የሕክምና ባለሞያ እርዳታ ማግኘት የሚቻል ነው። እነዚህና ተመሳሳይ የሆኑ እርምጃዎች በየፈርጁ መልካም ውጤት ያስገኙ ናቸው። አሁንም እንደገና የተጠቀሱትን አገልግሎቶች በትክክል ለማወቅና ለመጠቀም፤ ስለ ሱስ አምጪ ቁሳቁሶች ቢያንስ የተወሰነ ትምህርት ማግኘቱ እጅግ ጠቃሚ ነው። ጥረት ከተደረገ ከሱስ ተገዢነት ነጻ መውጣት የሚቻል ነው። ችግር ያለባቸው የመጪው አዲስ ዓመት ይህ አንዱ አላማቸው እንዲሆን በመጠየቅ፤ 2013 መልካም ዓመት እንዲሆንላቸው እመኛለሁ።

ዶክተር ወርቁ አበበ የፋርማሲና የፋርማኮሎጂ ባለሞያና ፕሮፌሰር ሲሆኑ በስኳር በሽታ፤ በደም ብዛት፤ በጥርስ ሽታና በባህል መድኅኒቶች ላይ መሠረታዊ ምርምሮችንና በርከት ያሉ ሳይንሳዊ ጽሑፎችን ያሳተሙ ምሁር ናቸዉ። በዚህ ኢሜይል ሊያገኟቸው ይችላሉ፦ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.