የአገልግሎት ስኬት

ነቢዩ ኢሳይያስ

ስኬት በተሰጠን የእድሜ ዘመን በትክክለኛ መንገድ እውቀታችንን፣ ገንዘባችንን፣ ልምዳችንን በማቀናጀት ትውልድን የምንለውጥበትንና የምንጠቅምበትን ሕያው ቅርስ በመተው ውጤታማ መሆን ማለት ነው። በቤተ ክርስቲያንም ሆነ ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ስለ ስኬት ብዙ ነገር እንሰማለን። በጣም የሚያሳዝነው ግን ዓለም ከዳር እስከ ዳር የተመታችበት አስተሳሰብ በአማኞች ሕይወት ውስጥ ግጥም ብሎ መገኘቱ ነው። መጽሓፍ ቅዱስ ስለ ስኬት ምን ያስተምረናል? ብለን ወደ ቃሉ መመለስ ይገባናል። አገልጋዮች በእግዚአብሔር መንግሥት ሥራ ስኬታሞች ሆነው እንዲቀጥሉ፣ የከለከላቸውን ነገሮች ለይተው በማወቅ፣ መጽሓፍ ቅዱስ ስለዚህ የሚናገረውንና አስፈላጊ ናቸው የሚላቸውን ነገሮች ማድረግ ይኖርባቸዋል። የአገልግሎት ስኬታማነት ምን ይጠይቃል? ቢያንስ ሦስት ነገሮችን እንመልከት።

1. ዘመንን፣ ያለንበትን ሁኔታና ግባችንን ለይቶ ማወቅ። የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ከሞተ በኋላ እግዚአብሔር ለነዌ ልጅ ለኢያሱ፦ባሪያዬ ሙሴ ሞቷልበማለት ተናገረው። ኢያሱ እስራኤላውያን በምድረ በዳ አርባ ዓመት በተንከራተቱበት ወቅት የሙሴ የቅርብ ሰው፣ ታማኝ ወዳጁና ረዳቱ፤መንፈስ ያለበትሰው ነበረ (ዘኁ 2718-23) እግዚአብሔር ይህንን ሰው የኪዳኑን ሕዝብ መርቶ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዲያስገባ ጠርቶታል። እግዚአብሔር ኢያሱን ወደ ተጠራበት ሥራ ሊያሰማራው በፈለገ ጊዜ ግን በቀጥታ ያለውባሪያዬ ሙሴ ሞቷልነው። ይህን ሲለው ግን መርዶ እያረዳው አልነበረም፤ እርሱ ሊነግረው የፈለገው ዋና ነገር ጊዜው፣ ዘመኑንና ያሉበትን ሁኔታ እንዲለይ ነበር። ከዚህም የተነሳ ነው በመጽሐፈ ኢያሱ .1 ቁጥር 2-3 ባለው ክፍል ላይአሁንም አንተና ይህ ሕዝብ ሁሉ ተነሥታችሁ ለእስራኤል ልጆች ወደምሰጣቸው ምድር ይህን ዮርዳኖስ ተሻገሩያላቸው። ከያዝነው ርዕሰ ጉዳይም ሆነ ከዐውደ ምንባብ አኳያ ዘመንን ማወቅ ማለት የት እንዳለንና ወዴት እንደምንሄድ ማወቅ ማለት ነው። በክፍሉባሪያዬ ሙሴ ሞቷልየሚለው አባባል የኪዳኑ ሕዝቦች የት እንዳሉ ወይም አሁን ያሉበትን ሁኔታ ለማሳየት ጥቅም ላይ የዋለ ሓሳብ ሲሆን፣ዮርዳኖስ ተሻገሩየሚለው ደግሞ ወዴት መሄድ እንዳለባቸው ወይም ግቡን አመልካች ቃል ነው። የመንፈሳዊ አገልግሎት ስኬትአሁን የት እንዳለን፣ ነገ ደግሞ ወዴት እንደምንሄድ ወይም ግባችንን ጠያቂ በመሆኑ ዘመንን፣ ጊዜንና ያለንበትን ሁኔታ ጠንቅቆ መለየትን የሚጠይቅ ነገር ነው።ግብ የሌለበት ተግባር እንቅስቃሴ ብቻ እንጂ ስኬት አይደለም። እግዚአብሔር ኢያሱን የኪዳኑን ሕዝብ እየመራ ከነዓን እንዲያስገባ ከማድረጉ በፊት ያሳየው እርሱና የእስራኤል ሕዝብ ያሉበትን የአገልግሎት ዐውድ ነበር።

በዚህ ዘመን ሁሉም ቤተ ክርስቲያን፣ ሁሉም አገልጋይ ስኬት ይፈልጋል። ከስኬቱ ጥያቄ በፊት ግን ዛሬ የእግዚአብሔር ሕዝብ ምን ይመስላል? አብያተ ክርስቲያናትስ በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ? የእግዚአብሔር ሕዝብም ሆነ ባጠቃላይ ቤተ ክርስቲያን ያለችበትን ዐውድ ሳናውቅና ሳንረዳ ለአገልግሎት ብንነሳ ምን አናልባት እንቅስቃሴ ኖሮን በአገልግሎታችን ግን ስኬት ላይኖረን ይችላል። አገልጋዮች ያለነው የትና እንዴት ነው? የምናገለግለውስ ሕዝብ በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ይገኛል? እግዚአብሔርስ ምን ይፈጋል? እነዚህ ጥያቄዎች በትክክል መልስ ባላገኙበት ሁኔታ ዝም ብለን ለአገልግሎት ብንነሳ ምናልባት መለኮታዊ ስኬት እንደ ሰማይ የሚርቀን ይሆናል። የት እንዳለንና ወዴት እንደምንሄድ ካላወቅን ዓላማና ግባችንን ማወቅ አንችልም። ግባችንንም ለመወሰን እንቸገራለን። ስኬታማ አገልግሎት ያልታሰበበትን ፕሮግራም እያካሄዱ፣ ያልታሰበበት ስብከት እየሰበኩና እያሰበኩ፣ ያልታሰበበት የቡድን የመጽሓፍ ቅዱስ ጥናት እያስጠኑና ፕሮግራም አያሸፈኑ እንዲሁም ያልታሰበበት መንፈሳዊ ኮንፍራንስ እያካሄዱ የሚዞርበት የቀለበት ዓይነት መንገድ አይደለም። ስኬታማ አገልግሎት ዘመንን ማወቅ፣ ዓላማንና ግብን መወሰንን የግድ ይላል። እነዚህ ነገሮች የሌሉበት አገልግሎት ድምር ውጤት ኪሳራ እንጂ ውጤት አይደለም። የእግዚአብሔርን ሕዝብ ወደ ታሰበለት የብስለት ልክ ማድረስ የሚቻለው ዘመንን ስንለይ፣ ግባችንን ስንወስንና ዓላማችንን ለይተን ስናውቅ ብቻ ይሆናል። በ1ኛዜና 12፣32 ላይ “እስራኤል የሚገባውን ያደርግ ዘንድ ዘመኑን የሚያውቁ፣ ጥበበኞች ሰዎች የይሳኮር ልጆች አለቆች ሁለት መቶ ነበሩ፤ ወንድሞቻቸውም ሁሉ ይታዘዟቸው ነበር” ይላል። በየዘመኑ እግዚአብሔር በሉዓላዊ ፈቃዱና ሓሳቡ መሠረት ሓሳቡንና ምክሩን በሰው ልጆች መካከል ይፈጽማል፤ ይህም በተፈጥሮና በመንግሥታት ዘንድ በሚከናወነው ነገሮች ተለይቶ ይታወቃል፤ ይሁን እንጂ ከእግዚአብሔር ሕዝቦች መካከል ይህንን ለይተው የሚያውቁ ግን እጅግ በጣም ጥቂቶች ናቸው። ለምሳሌ እስራኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ መሲሁ የዓለም መድህን ተደርጎ መላኩንና የተላከበትን ዘመን አላስተዋለችም ነበር። ለዚህ ነገር ታውራ ነበር ማለት ይቻላል። በተመሳሳይ መልኩ ቤተ ክርስቲያንም እግዚአብሔር እያደረገ ያለውን ነገርና በቅርብ ጊዜ ሊፈጽም ያለውን ነገር የማታስተውልበት ጊዜ አለ። ወደ ተነሳንበት የመጽሓፍ ቅዱስ ጥቅስ ስንመለስ ግን፣ የይሳኮር ልጆች በዚህ ክፍል ለየት ባለ መልኩ ተጠቅሰዋል፤ ምክንያቱም ከእስራኤል ነገዶች ውስጥ እነርሱ እግዚአብሔር ዳዊት ለእስራኤል የተቀባ ንጉሥ አድርጎ ወደ ዙፋን ሊያመጣው እንዳለ በዚያን ዘመን ተረድተዋልና ነው፤ ወይም ደግሞ እግዚአብሔር በዚያን ዘመንና ጊዜ ምን ሊሠራ እንዳሰበ ለይተው አውቀዋል። ዓላማ ባለው ሥራ ላይ ከእግዚአብሔር ጋር ለመተባበር ወይም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለውጥ በሚመጣበት ጊዜ ከእግዚአብሔር የተሰጠ እይታን ለማሳደግ ዘመንና ጊዜን መለየት ያስፈልጋል። ታዲያ ይህ ዓይነቱ ነገር ከሌለ እንዴት በመንፈሳዊ አገልግሎት ውስጥ ስኬት ይኖራል?

በአገልግሎት ስኬታማ ለመሆን፣ የምናገለግልበትንዘመንለይቶማወቅ የሚለው ሓሳብ አጽንዖት ይሰጠው። ያለንበትን ዘመንና የእግዚአብሔር ሕዝብ ያለበትን ሁኔታ ለይተን ማወቅና መረዳት ካልቻልን፣ እግዚአብሔር ባለንበት ዘመን ሊሠራ የሚያስበውንና ለትውልዱ የሚሆነውን የእግዚአብሔርን ምክር ማምጣት አንችልም። በምዕራባውያን ዘንድ ታዋቂ የነበሩትና አሁን በጌታ እረፍት ውስጥ ያሉት ታላቁ የነገረ-መለኮት ምሁር ጆን ስቶት እንደሚሉት “በአንድ እጃችን ወንጌልን በሌላው እጃችን ደግሞ ያለንበትን የወቅቱን ተጨባጭ ሁኔታ ልንይዝ ይገባናል፣ ከዘመን ርቆ ትውልድን ማገልገል፣ ተግዳሮቶቹንም ለይቶ በማወቅ መፍትሔ መስጠት አይቻልም።” በየትኛውም የማዕረግ መጠሪያ የሚጠሩ አገልጋዮች በዚህ ዘመን በአገልግሎታቸው ውጤታሞችና የሠመረላቸው እንዲሆኑ ከተፈለገ ዘመኑን፣ ያሉበትን ሁኔታና ግባቸውን ማወቅ ይጠበቅባቸዋል። የሕዝቡን ተግዳሮት ምን እንደሆነ የሚረዱና ለትውልዱ የእግዚአብሔርን ሓሳብ አውቀው የሚያሳውቁ፤ የወንጌልን ማዕከላዊ መልእክት ሳይበርዙ፣ ሳይቀይጡና ሳይሸቅጡ የሚያገለግሉ በአገልግሎታቸው ስኬት ይኖራቸዋል።

2. እግዚአብሔርን መታመን። ኢያሱ ምዕራፍ 13-5 ባለው ክፍል ላይተሻገሩ።” “በሕይወትህ እድሜ ሁሉ ማንም አይቋቋምህም” “ለእናንተ ሰጥቻለሁ” “ዳርቻችሁ ይሆናልየሚሉት አባባሎች ኢያሱ በእግዚአብሔር ካልታመነና ካልተደገፈ በስተቀር የኪዳኑን ሕዝብ ማሻገር እንደማይችልና የተመሸጉ ከተሞችን በመቆጣጠር ከነዓንን ማውረስ እንደማይችል አመልካች ቃላትና ሐረግ ናቸው። እግዚአብሔር ግን እኔከአንተ ጋር እሆናለሁይለዋል። ኢያሱን ተልዕኮውን በውጤታማነት እንዲያጠናቅቅ የሚያደርገው የእግዚአብሔር ከእርሱ ጋር መሆን ነው። በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ የሚከናወኑ የትኛውም ዓይነት ነገሮች በእግዚአብሔር መታመንን፣ የእርሱን ሀልዎት መለማመድንና እርሱን መደገፍን ይጠይቃል። በየትኛውም እውቀት፣ የላቀ የሕይወት ልምምድና ደረጃ ላይ ብንሆን እግዚአብሔርን ከመታመንና ከመደገፍ ውጭ የአገልግሎት ስኬት የለም። የእግዚአብሔር ቤት ሥራ በቤቱ ባለቤት መደገፍ ይጠይቃል። አገልግሎት እርሱ በእኛ ሆኖ የሚሠራው ነው፤ ደግሞም ብቻችንን ሳይሆን ከእርሱ ጋር የምንሠራ ነን (1ቆሮ 39) ስለዚህም ስኬት እርሱን ሙጥኝ ማለትን ይጠይቃል። ኢያሱ የመሪነት አገልግሎቱን የጀመረው በእግዚአብሔር መንፈስ ኃይል ተሞልቶ ነበር (ዘዳ 3412) በብሉይም ሆነ በአዲስ የእግዚአብሔር ሥራ የእግዚአብሔርን መንፈስ ኃይል የግድ ይላል። በሰብአዊ ኃይልና ድካም ዳር የሚደርስ መንፈሳዊ አገልግሎት የለም። ኢየሱስና ሐዋርያቱ የእግዚአብሔር መንፈስ ኃይል ካስፈለጋቸው ለእኛማ ምን ያህል? (ሉቃ4 1-11 ሐዋ 1 8)

በመጀመሪያው ምዕተ ዓመት ይኖሩ የነበሩ አብያተ ክርስቲያናት የአገልግሎታቸው ስኬት ምስጢር የሊቃውንት ትምህርትና ጥበብ፣ ድርጅታዊ አሠራራቸውና ጥንካሬያቸው ሳይሆን የእግዚአብሔር መንፈስ ነበር። እርሱን መጠማታቸውና ከእርሱ ጋር የነበራቸው ትሥሥር በዘመናቸው ተልዕኮአቸውን ከዳር እዲያደርሱት ረድቶአቸዋል። ለመጀመሪያው ዘመን አብያተ ክርስቲያናት፣ መንፈስ ቅዱስ በፍሬ አልባ ፍልቅ ስሜታዊነት የሚያፍነከንክና በየአምልኮው ስፍራ መዝናናትን የሚፈጥር መንፈስ ሳይሆን የሚቀድስ፣ የሚመራ፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ለዓለም ለማድረስ ኃይልን የሚሰጥ፣ እንዲሁም የሚያስታጥቅ፣ የሚናገርና በስብሰባቸው ላይ አብሮ የሚወስን አምላክ መሆኑን በሐዋርያት ሥራ ተጠቅሷል። ለእኛም ከእርሱ ውጭ የአገልግሎት ስኬት የለም። ዛሬም የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ያስፈልገናል። ወደ እዚህ ነገር ለመምጣት ግን ስሜትን ከመንፈስ ቅዱስ ሥራ መለየት ያስፈልጋል።

መንፈስ ቅዱስን በተመለከተ በእኛ በኢትዮጵያውያን የወንጌል አማኞች ዘንድ ሁለት የጎሉ ችግሮች አሉ። የመጀመሪያው በየአብያተ ክርስቲያናቱ ባሉ የአምልኮ ፕሮግራሞች ላይ በመንፈስ ቅዱስ ሳይነኩና ሳይዳሰሱ ልክ እንደ ተነኩና እንደተዳሰሱ ሆኖ በመቅረብ በሙዚቃ መሣሪያ ኃይል የተቀሰቀሰን ስሜት እንደ መንፈስ ቅዱስ ሥራ የመተርጎሙ ችግር ሲሆን፣ እንዲህ ዓይነቱ መረዳትና ችግር በመንፈሳዊ ሕይወታቸው በሳል ያልሆኑ አማኞችን፣ አልፎ አልፎ አገልጋዮችን ስለ መንፈስ ቅዱስ ማንነት፣ እግዚአብሔርም ለምን ዓላማ የመንፈስ ቅዱስን ኃይል እንደሚሠጠን ያለማወቅና የግንዛቤ ችግር ውስጥ ከቷቸዋል። ይህ ሁኔታ ታዲያ በሥላሴ የምናምን ሆነን ሳለን “የመንፈስ ቅዱስ ብቻ” ኃይማኖት የተፈጠረ ይመስል፣ መንፈስ ቅዱስ፣ መንፈስ ቅዱስ እያሉ ክርስቶስን ማዕከል ወደ አላደረገ እንቅስቃሴ ውስጥ ከቷቸዋል። በእነዚህ ወገኞች ዘንድ ያለው ችግር ይህ ብቻ አይደለም፤ ከሥህተታቸው ላለመታረም ራሳቸውን የመንፈስ ቅዱስ እንደራሴ አድርገው ይከራከራሉ፤ በሌላ መልኩ ደግሞ፣ “ለቤዛ ቀን የታተማችሁበትን ቅዱስን የእግዚአብሔር መንፈስ አታሳዝኑ” የተባልንበት ባህርይ ጎልቶ ይታዩባቸዋል። ውሸት፣ ቁጣ፣ መራርነት፣ ጩኸት ወዘተ.... ቀላል ልምምዳቸው ናቸው (ኤፌ 4፣ 25- 32)። ለዚህ ምክንያቱ ስለ እርሱ ማንነት ያለማወቃቸውና ክርስቶስን ማዕከላዊ ያላደረገ እንቅስቃሴ በየአብያተ ክርስቲያናቱ መበራከቱ ይመስላል። ሁለተኛው ደግሞ የለዘብተኛ የነገረ መለኮት አቋም ሲሆን፤ የመንፈስ ቅዱስ የጸጋ ሥጦታ በዚህ ዘመን አይሠራም የሚለው አመለካከት ነው፤ ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ለሚከተሉ ያለኝ መልስ ያለ መንፈስ ቅዱስ ኃይልና ያለ ሀልዎቱ ልምምድ በነገረ መለኮት እውቀት ክምችት ብቻ ወንጌሉን እየሰበኩ የእግዚአብሔርን መንግሥት ማስፋትና ዓለምን መለወጥ አይቻልም የሚል ነው። ይህም ብቻ አይደለም ለግል መንፈሳዊ ሕይወት ለውጥና እድገትም የእግዚአብሔር መንፈስ ኃይል ያስፈልገናል። በአገልግሎት ውስጥ እርሱን ቀንሶ መንፈሳዊ ስኬት የለም። ዛሬ የእግዚአብሔር መንፈስ ያስፈልገናል። በየዕለቱም መሞላት፣ በየእለቱም ከእውቀታችን ይልቅ ፊታችንን ወደ እርሱ ረድኤት ማዞር አለብን።

3. ለእግዚአብሔር ቃል መገዛት። ኢያሱ ጠላቶቹን ድል እያደረገ የኪዳኑን ሕዝብ ወደ ተገባለት ተስፋ ያደረሰው፣ እግዚአብሔር አስቀድሞባሪያዬ ሙሴ ያዘዘህን ሕግ ሁሉ ጠብቅ፥ አድርገውም፤ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲከናወንልህ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል። የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፥ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም፣ [ኢያሱ 17]” ብሎ እንደ ተናገረው የሕጉን መጽሓፍ በማንበቡ፣ በማሰላሰሉና በመጠበቁ ነበር። ስኬታማ አገልግሎት ለእግዚአብሔር ቃል መገዛትን ይጠይቃል። ቅዱሳንን ወደ ታሰበላቸው መንፈሳዊ ብስለት በማምጣት ሂደት ውስጥ ያለእግዚአብሔር ቃል ስኬት የለም። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አገልግሎት ቀናና የተሳካ የሚሆነው ለቃሉ ሥልጣን የሚገዛ ሕይወት ሲኖር እንጂ ቃሉን እንደ ፍልስፍና መርህ አድርገን ስንወስድ አይደለም። የእግዚአብሔር ቃል በቤተ ክርስቲያን ሕይወት የመጨረሻ ባለ ሥልጣን ነው፤ ሆኖም ይህ ቃል የአገልግሎታችን ስኬት ምክንያት የሚሆነው በአስተምህሮአችን ላይ፣ በኑሮአችን ላይ፣ በክርስቲያናዊ ምግባራችን ላይ፣ በመንፈሳዊ ሥጦታዎችና ልምምዳችን ላይ እንዲሁም በቤተ ክርስቲያን አመራራችን ላይ የመጨረሻ ባለ ሥልጣን መሆኑን አምነን ስንቀበል ነው።

ከቅርብ ዘመናት ወዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ሥልጣን የማጣጣል አባዜ በዓላማችን ላይ በፈጣን ሁኔታ እያደገና እየተስፋፋ የመጣ ተግባር ሆኗል። የሌሎች እምነት ተከታዮች፣ መጽሓፉ ሲዖልና የገሃነመ እሳት ፍርድ አለ እያለ ሰዎችን የሚያስፈራራ፣ ደስታቸውንና ነፃነታቸውን የሚነፍግ መጽሓፍ እንደ ሆነ በማሰብ የተጠላ መጽሓፍ በማለት ሰይመውታል። አዲሱ ትውልድም እንዲጠላው ከፍተኛ ተጽዕኖ እየተደረገ ነው። የምስስለ ጾታንም ጋብቻ የማይቀበል መጽሓፍ በመሆኑ የዚህ እኩይ ምግባር ተከታዮች ይነቅፉታል። ክርስትና ከሩቅ ምስራቅ ኃይማኖት ጋር ካልተዳቀለም በራሱ ምንም ዓይነት ኃይማኖት መሆን የማይችልበት ጊዜ ይመጣል እያሉ የሚናገሩም አልታጡም። የዚህ ሁሉ ምክንያቱ ሰዎች የመጽሓፍ ቅዱስን ሥልጣን ያለመቀበላቸው ችግር ነው። እኛም ብንሆን ለዚህ መጽሓፍ ሥልጣን ካልተገዛን እንዲህ ዓይነት አመለካከት ካላቸው ሰዎች በምን ተለየን? በዚህ መጽሓፍ ላይ ጠላትነት በውጭ ብቻ ሳይሆን በውስጥም እንዳይሆን ያስፈራል። በእግዚአብሔር ቃል ላይ ወንጀል የሚሠራው ከውጭ ይልቅ በቤተ ክርስቲያን ነው።

በአንድ ወቅት “ጉድ ኒውስ” በሚል ርዕስ በሚዙሪ ሲኖዶስ ሉትረን ቤተ ክርስቲያን እየታተመ የሚሰራጭ መጽሔት አነብብ ነበር። በመጽሔቱ ላይ በዓለማቀፋዊቱ የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን መካከል ተፈጥሮ የነበረው መከፋፈል ሠፊ ሽፋን ተሰጥቶታል። የመከፋፈሉ ምክንያት የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች የእግዚአብሔርን ቃል ሥልጣን በግልጽ በመካድ ግብረ ሰዶማዊ ጳጳስ መሾማቸው ነበር። በተፈጠረው መከፋፈል ውስጥ የነገረ-መለኮት ምሁራን ሹመቱን አጥብቀው ይቃወሙ የነበረው የእግዚአብሔር ቃል ስለ ግብረ-ሰዶማዊነት የሚናገረውን ቀጥተኛ ነገር በግልጽ በመናገር ሲሆን፣ ሹመቱን ለማጽደቅ የተነሱት ግን ነገሩን አደረግነው የሚሉት ከመንፈስ ቅዱስ ምሪት ተቀብለን ነው በሚል ነበር። በዚህ ጉዳይ ላይ በዋሽንግተን ዲሲ የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን አገረ ስብከት ዋና መሪ የሆኑት ጳጳስ ብራይሰን ቼን ሰኔ 9 ቀን 2003 ዓ.ም ባሰራጩት ጽሑፍ፣ ለግብረ ሰዶማዊው ጂን ሮቢንሰን የጵጵስና ማዕረግ መሰጠት የመንፈስ ቅዱስ ቀጥተኛ የሥራ ውጤት ሆኖ አግኝተነዋል፤ ስለዚህ ይህንን የጵጵስና ሥልጣን ያለመቀበልም ሆነ መቃወም መንፈስ ቅዱስን መገዳደር ነው ሲሉ ገልጸዋል። በመጨረሻም እያንዳንዱ አገረ ስብከት የራሱን ጳጳስ የመሾም መብትና ለመንፈስ ቅዱስም ሥራ ክፍት የመሆን ሥልጣን አለው በማለት ተናግረዋል። እዚህ ላይ አንድ መሠረታዊ ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይሆናል፤ ይኸውም እነዚህ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ግብረ ሰዶማዊውን ጂን ሮቢንሰንን ጳጳስ አድርጎ ለመሾም እንዴት ተነሱ? የሚለው ነው። የአንግሊካንን ቤተ ክርስቲያን ለሁለት ለመክፈል ያደረሰው ችግር ምክንያቱ መሪዎቹ የእግዚአብሔርን ቃል ሥልጣናዊነት በመካድ መንፈስ ቅዱስ መርቶናል የሚሉት አባባል ነው። መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያንን የሚመራት በቃሉ ስለሆነ ከቃሉ ጋር የሚቃረን ነገር አያደርግም። መገለጥ እንኳን ቢሰጠን ቃሉን የሚያጸና እንጂ የሚያፈርስ አይደለም። በቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ የእግዚአብሔር ቃል የመንፈስ ቅዱስ የመገለጫ መንገድ ነው የሚል ትምህርት አለ። መንፈስ ቅዱስን ከቃሉ ሥልጣን መለየት ትልቅ ኑፋቄ ነው።

ከወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ውጭ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት የእግዚአብሔር ቃል ለመሠረተ እምነት የመጨረሻና የተሟላ ምንጭ ነው ተብሎ አይወሰድም። ከመጽሓፍ ቅዱስ ላይ በተጨማሪ የተቀደሱ ልማዶች መወሰድ እንዳለባቸው ይታመናል። ጥቂት የማይባሉ ሰዎች በእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ባሉ አንዳንድ ምዕመናን ሕይወት ውስጥ ለሚታየው የአስተምህሮ፣ የክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ዝብርቅርቆሽና ኃይማኖታዊ ቅይጥይጣዊነት ምክንያቱ ከቃለ እግዚአብሔር ይልቅ ሌሎችን መጽሓፍት በማስተማራቸው ነው የሚል እምነት አላቸው። የዚህ ጽሑፍ ጸሓፊም ይህንን ሓሳብ ይጋራል። እስትንፋሰ-መለኮት ያልሆኑ መጽሓፍት ሕይወትን ለመለወጥና የሰዎችን ሕይወት በጽድቅና በቅድስና የመሙላት ኃይል የላቸውም። ወደ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያና ስንመጣ ደግሞ በቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔርን ቃል ብቻ ማስተማር ሲገባን፣ ቃሉን በልምምዳችንና በሌሎች ርባና የለሽ ተረት ተረቶች ተክተናል። በዚህ ዘመን በቃሉ ስብከትና ትምህርት ውስጥ ማዕከላዊውን ሥፍራ በመያዝ ሠፊ ቦታ የሚሰጠው ሰዎችን ነፃ የሚያወጣው የቃሉ እውነት ሳይሆን፣ ኩምክናና የኮሜድያኖች ሥራ ክምችት አይደለም እንዴ? ምዕመኑም “ተሰበከ” የሚለው የእግዚአብሔርን ቃል በመንተራስ ኮሜድያን ሰባኪዎች በሳቅ ሲያንከተክቱት እንጂ የክርስቶስ ባለ ጠግነት በቤተ ክርስቲያን ሲሰበክ አይደለም። ከዚህ የተነሳ ስብከቱም እየተሰበከ፣ መዝሙሩም እየተዘመረና ጸሎቱም እየተጸለየ ሰው በባህሪው አይለወጥም። ከቅዱሳን ሕይወት የሚጠበቀው ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ጠፍቷል ቢባል ማጋነን አይሆንም። ከመድረኩ ላይ አዘውትረን የምንሰማው መልዕክት የወንጌሉን ሙሉ መልዕክት ሳይሆን ጎዶሎ መልዕክት ነው። ከዚህም የተነሳ ክርስትና ተብሎ የሚኖረውም የሕይወት ዓይነት መስቀል አልባና ጎዶሎ ክርስትና ነው። ምናልባት ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ መጥቀስ ያስፈልግ ይሆናል። ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ያለው ሐሜት፤ ጥላቻ፣ ስም ማጠልሸት፣ መስቀል ያልሞረደው ጠባይ፣ የእግዚአብሔር ቃል ትምህርትና ሕሊና የማይዳኘው ፈንጠዝያና ዝላይ፣ የሥነ ምግባርን ሕግ የሚጻረር ትምህርትና መርሆ አልባ ኑሮ፣ እንዲሁም እርቅ የማይፈታው ጥላቻና አፍቅሮተ ነዋይ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንብንም።

እኛ ከመኖራችን በፊት በራሱ ሕልውና ይኖር የነበረ እግዚአብሔር ብቻ ነው። እርሱ በሥልጣኑ የማይታየውን ነገር ሁሉ ወደማኖር አምጥቷል። ይህንንም ሥልጣኑን የገለጸው በልዩ ልዩ ወኪሎቹ በኩል ሳይሆን፣ በሕያው ቃሉ አማካይነት ነው። ይህም ሕያው ቃል ባለሥልጣን ነው የምንልበት ምክንያት መገኛው እግዚአብሔር በመሆኑ ነው። ምን ጊዜም ቢሆን በሚበልጠው ላይ የሚሰለጥን ባለሥልጣን ነው። እግዚአብሔር በሁሉም ላይ ባለሥልጣን ስለሆነ የመጨረሻው ባለሥልጣን የእግዚአብሔር ቃል ነው። ለዚህ ቃል የሚገዛ ማንነት ሲኖረን፣ በአገልግሎታችንም ሆነ በምንኖረው ሕይወት ስኬታሞች እንሆናለን። እንደ እውነቱ ከሆነ ልምምዳችን ከእግዚአብሔር ቃል ትምህርት ጋር የማይቃረንና የማይጣረስ መሆን አለበት። ለእግዚአብሔር ቃል ሥልጣን የማይገዛ ልምምድ በግልም ሆነ በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ተፋልሶን ያመጣል። እግዚአብሔር ቃሉ በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በግል ሕይወታችን ማዕከላዊ እንዲሆን የፈቀደበት ምክንያት አለ። ይኸውም የቤተ ክርስቲያንንም ሆነ የግል ሕይወታችንን የሚሠራበት ብቸኛ መንገድ ቃሉ በመሆኑ ነው። መጽሓፍ ቅዱስ የተጻፈበት ቀዳማይ ዓላማ እግዚአብሔር ሰዎችን ሁሉ ያለ ምንም መደናገር የነፍሳቸው ጠባቂና እረኛ ወደ ሆነው ወደ አዳኙ ኢየሱስ ክርስቶስ ለማስጠጋትና በእርሱም ወደታሰበላቸው የሕይወት ሙላት እንዲመጡ ነውና ቃሉን እንመገብ፣ ለሥልጣኑም የሚገዛ ሕይወት ይኑረን (ዮሐ 14፣ 4 ፤ 2ጢሞ 3፣ 14- 17)። ይህን ስናደርግ ብቻ ስኬታማ አገልግሎት ይኖረናል።

የዚህን ጽሑፍ ረዘም ያለ ቅጂ ለማግኘት This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ይጠይቁ።