በክፍል አንድ፣ ዲያብሎስን ለመቃወም እንዳንችል 1/ ተናዝዘን ያልተውነው ኃጢአት 2/ ማናቸውም ጥንቆላ ነክ (ዕቃዎችን) ወደ ቤት ማስገባት 3/ ይቅር የማይል ልብ 4/ ማንኛውም ክፉ ሃሳብ ያግደናል የሚሉ ነጥቦችን ወንድም ተድላ ሲማ ዘርዝሮልን ነበር። በዚህ ክፍል ደግሞ የቀሩትን አሳቦችና መፍትሔዎችን ያቀርብልናል።

መንፈሳዊ ዉጊያ [2]

ተድላ ሲማ

5. ሐዘንተኛ ልብ። ሁል ጊዜ የሚተክዝ ልብ ለሰይጣን ይመቻል። ቃሉ "ሁል ጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ" ይላል (ፊል 4፡4)። የጌታ ደስታ ልባችንን ሊሞላው ይገባል። "የእግዚአብሔር ደስታ ኃይላችሁ ነውና (ነህምያ 8፡10)።" የእግዚአብሔር የሆነው ደስታ ወደ ልባችን ሲገባ ኃይልን እንሞላለን። ጌታ ኢየሱስ ወደ ምድር ከመጣባቸው ምክንያቶች አንዱ "በሐዘን መንፈስ ፋንታ የምስጋናን መጎናጸፊያ፤ በልቅሶ ፋንታ የደስታን ዘይት" (ኢሳ 61፡3) ሊሠጠን ነው። በመሆኑም ዘመናችንን ሁሉ በመተከዝ ዕድሜያችንን በሰይጣን ማስዘረፍ የለብንም። ሰይጣን ትናንት ስለ ሠራነው ስህተትና ስለ ደረሰብን ችግር፥ ዛሬ እያስተከዘ ዛሬን ይቀማናል። ይህ የጠላት ስልት ነው። ዛሬን ሳናጣጥም ነገ ይመጣብናል። ቃሉ "እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት፤ ሐሴትን እናድርግ፥ በእርስዋም ደስ ይበለን" ይላል [መዝ (118):24]። አንድ ሰው እንዲህ አለ፣ "ዘጠና በመቶ ትኩረታችንን ማድረግ ያለብን በዛሬ ላይ ወይም ዛሬ ልንሠራቸው ባሰብናቸው ነገሮች ላይ ሊሆን ይገባል፤ አምስት በመቶ ደግሞ ስለ ትናንት በማሰብ ከስህተታችን ልንማር ከመልካም ተሞክሯችንም ልንበረታታ እንችላለን። አምስት በመቶ ደግሞ ስለ ወደፊት ሕይወታችን የምንተልምበት ሊሆን ይገባል።" ሰይጣን ግን ከዚህ በተቃራኒ ዘጠና በመቶ ስላለፈው ውድቀታችንና ስህተታችን በማሰብ በጸጸት እንድንቃጠልና በተስፋ መቁረጥ እንድንሞላ ሊያደርገን ይፈልጋል። ብዙ ቅዱሳን ትናንት ያመለጣቸውን ዕድል በማሰብ፣ በትናንት ላይ ቆመው በመተከዝ ዛሬ ሊያደርጉ የሚገባቸውን ሳያደርጉ ፍሬ አልባ ሕይወት እየመሩ ይገኛል። የሰይጣንን ዘዴ ልንነቃበት ይገባል። እግዚአብሔር ኢያሱን "ባሪያዬ ሙሴ ሞቷል፤አሁንም አንተና ይህ ሕዝብ ተነሥታችሁ ...ተሻገሩ" አለው (ኢያሱ 1፡2)። ስለ ትናንቱ የሙሴ ታሪክና ገድል ቆሞ ማሰብ ለኢያሱም ሆነ ብዙ አሕዛብን ድል ነሥቶ የተስፋይቱን ሀገር የመውረስ የቤት ሥራ ላለበት የእስራኤል ሕዝብ አንዳችም የሚፈይደው ነገር የለም። ሁል ጊዜም ሕያው ሆኖ ከሚኖረው ጌታ ጋር የዛሬውን የእግዚአብሔር አጀንዳ ለመፈጸም ልንተጋ ይገባል፣ "በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ (ፊልጵስዩስ 3፡11)።" ያለፈውን ታሪክ ብቻ በመዘከር መኖር የለብንም። ጌታ ለእኛና ለቤታችን፥ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለምድራችን ያለውን የዛሬ አጀንዳና ፈቃድ እያስተዋልን በጌታ ጸጋ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል። ያን ጊዜ ነው ጸጸት የሌለበት ሕይወት የምንመራው። እግዚአብሔር ኩብኩባና ተምች የበላቸውን ዓመታት ሊያድስ ይችላል (ኢዮኤል 2:25)። "ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም (ኤር 29፡11)።" "በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንዲፈጽመው ይህን ተረድቻለሁና (ፊል 1፡6)።"
ስለዚህ መስቀሉ ሥር ተንበርክከን ሐዘናችንን፥ ትካዜያችንንና ጸጸታችንን በጌታ ላይ ጥለን ጌታን ለማመስገንና ለማክበር እንነሳ። ትካዜያችንን በእግዚአብሔር ላይ ስንጥል ጌታ ይደግፈናል (መዝ 55፡22)። ሁልጊዜ የሚተክዝ ልብ ለጠላት ሥራ የተመቸ ነው። በአንጻሩ በመንፈስ ቅዱስ ደስታ የተፍለቀለቀ ሰው ሌሎችን ወደ ጌታ የመሳብ ኅይል አለው። የመስቀሉ ሥራ የሐዘናችንን ቀንበር ሊሰብር ይችላል። ጌታ በመስቀል ላይ ሲሞት ስለ እኛ ሁሉን ዕዳ ከፍሏል። በጌታ ደስ ይበለን።

6. ትዕቢት። "እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፣ ለትሑታን ግን ጸጋ ይሰጣል (ያዕቆብ 4፡6)።" "ትዕቢት" ን በሁለት መልክ ልናየው እንችላለን። አንደኛው፣ የእግዚአብሔርን ቃል አለመስማት /አለመታዘዝ/ ነው፤ የጌታን ቃል መናቅ ትዕቢት ነው (ዘዳግም 1፡43)። በአንፃሩ ትሕትና ደግሞ ለእግዚአብሔር ቃል መንቀጥቀጥ (መታዘዝ) ነው፣ "ወደዚህ ወደ ትሑት በቃሌም ወደ ሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ (ኢሳ 66፡2)።" ሁለተኛው፣ የትዕቢት መገለጫ ሌሎችን መናቅ ነው፤ማለትም ራስን አግዝፎ ማየትና ሌሎችን አሳንሶ ማየት ነው። የትዕቢት ኃጢአት ስውርና እንዴት እንደያዘን ሳይታወቅ የሚሰለጥንብን በመሆኑ ሁልጊዜ ራሳችንን ባዶ በማድረግ በትሕትና ለመመላለስ መጣር አለብን። ቃሉ "በጊዜው ከፍ እንዲያደርገችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ" ይላል (1ኛ ጴጥ 5፡6)። "ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፣ ራሱንም የሚያዋርድ ከፍ ይላል" በማለት ቃሉ ያስጠነቅቀናል (ሉቃ 14፡11)። በአንድ ሥፍራ እንዲህ የሚል አባባል ማንበቤ ትዝ ይለኛል፣ "እኛ የራሳችንን ሥራ ካልሰራን (ራሳችንን ካላዋረድን) እግዚአብሔር የእኛን ሥራ ይሠራል (ያዋርደናል)።" ራሳችንን ማዋረድ የእኛ ድርሻ ሲሆን ከፍ ማድረግ ደግሞ የጌታ ድርሻ ነው። ጌታ ኢየሱስ ራሱን ባዶ በማድረግ ሰው ሆነ። ዝቅተኛውን ሥፍራ ወሰደ፤ በበረት ተወለደ፤ በእንጨት ላይ ተሰቀለ፤ እግዚአብሔር ግን ያለ ልክ ከፍ ከፍ አድረገው፤ "ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው" (ፊልጵስዩስ 2፡9)። ራሳችንን ስናዋርድ እግዚአብሔር ያከብረናል። የእግዚአብሔር ቤት የትዕቢተኞች ቤት ሊሆን አይገባም፤ የትሁታን ቤት እንጂ። ስለዚህ ሁል ጊዜ በጌታ ፊት ራሳችንን ማዋረድ አለብን። እርስ በርስም በትሕትና ልንከባበርና ባልንጀራችን ከእኛ እንዲሻል ልንቆጥር ይገባል። ቃሉ "ዓይኖቼ በምድር ምዕመናን ላይ ናቸው፣ በቀና መንገድ የሚሄድ እርሱ ያገለግለኛል፣ ትዕቢትን የሚያደርግ በቤት መካከል አይኖርም" ይላል (መዝ 101፡6-7)።መዘንጋት የሌለበን ትዕቢት ሰይጣን እራሱ የወደቀበት ኃጢአት መሆኑን ነው (ኢሳ 14፣12-16)። በምንታበይበት ጊዜ በሰይጣን የአሠራር መርህ ውስጥ እንገባለን። ስለዚህ ሁል ጊዜ ከትዕቢት እንጠንቀቅ፤ እግዚአብሔርም እንዲረዳን እንጸልይ። "እግዚአብሔር ከፍ ያለ ነውና ወደ ችግረኞች ይመለከታል፣ ትዕቢተኞችንም ከሩቅ ያውቃል" (መዝ 138፡6)።
7. ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ቁጣ። "ተቆጡ ግን ኃጢአት አታድርጉ" ይላል ቃሉ (መዝ 4፡4)። በሌላ ስፍራ ደግሞ "በቁጣችሁ ላይ ጸሐይ አይግባ፥ ለዲያቢሎስም ፈንታ አትስጡት" ይላል (ኤፌ4፡25)። መቆጣት በራሱ ኃጢአት አይደለም፤ ነገር ግን ቁጣ ወደ ንዴት፣ ብስጭትና ኩርፊያ ሲሄድ ግን ኃጢአት ይሆናል። በምንበሳጭበት ጊዜ ወይም መራራ ቁጣ በምንቆጣበት ጊዜ ውስጣችን የሚያድረው የእግዚአብሔር መንፈስ ያዝናል። በመሆኑም በምንቆጣበት ጊዜ ራሳችንን ልንገዛ ይገባል። አንደበታችንን ልንገራ ይገባል። እንደዚያ ሲሆን ጠላት ዕድል ፈንታ ያጣል። መራራነትና ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ቁጣ መንፈስ ቅዱስን ከማሳዘኑ በተጨማሪ ለሰይጣን በር ይከፍታል። "ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ። መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ (ኤፌ4:30-31)"
8. ዓመፅ። ለሰይጣን በሕይወታችን በር የሚከፍተው ሌላው ዓመፀኝነት ነው። ለተለያዩ የሥልጣን ተዋረዶች ልንገዛ ይገባል። ልጆች ለወላጆቻቸው፥ ሚስት ለባሏ፥ተማሪ ለአስተማሪ፥ አስተማሪ ለርዕሰ መምህሩ፥ የጸሎት አገልጋይ ለጸሎት ቡድን መሪው፥ምዕመናን ለመጋቢው ወይም ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሊታዘዙ ይገባል። የሥልጣን ተዋረድ መኖር ከብጥብጥ ይጠብቃል። ከሥልጣን ክፍተት የተነሣ ሶማሊያ ውስጥ ያለውን ብጥብጥ፥ውከትና ያስከተለውን መዘዝ ስንመለከት የሥልጣን ጠቃሚነት ይገባናል። ዓመፅ ሕይወታችንን እንዳይገዛው ልንጠነቀቅ ይገባል። ዓመፀኛ የሆኑ ሰዎች በየደረሱበት ከኃላፊዎች ጋር የመጣላት ዝንባሌ አላቸው። የሥራ ኃላፊን እንደ ባላንጣ የማየት ዝንባሌ ይታይባቸዋል። በየደረሰበት መሥሪያ ቤት ከአለቆች ጋር የሚጣላ ሰው ዓመፀኛ መሆኑን ልንጠራጠር አይገባም፣ እንደዚህ ዓይነቱ ሰው ለሥልጣን መታዘዝ የሚቸገር ሰው ነው። እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ከህፃንነት ጀምሮ ለሥልጣን የመታዘዝ ክፍተት የገጠማቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ምናልባት ወላጆች የሌላቸውና ቢኖሯቸውም ተገቢውን ሥርዓት ሳያስይዙ ያሳደጓቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ሰይጣን ራሱ ዓመፀኛ መሆኑን ልንዘነጋ አይገባም። ለእግዚአብሔር አልገዛም ብሎ ያመፀ ነው። አጋንንትም እንደዚሁ ከእርሱ የዓመፅ ጎራ የተሰለፉ ናቸው። ሰይጣንም በዓመፁ ምክንያት የነበረውን ሥፍራ አጥቷል (ኢሳ 14:12-15፤ ሕዝ 28:11-18፤ ራእይ 12:7-10)። በምናምጽበት ጊዜ በሰይጣን የአሠራር ጎራ ውስጥ እንገባለን። ዳታንና ቆሬ በሙሴ ላይ ያመፁትን ዓመፅ እግዚአብሔር አልታገሰውም፤ ተቀጥተዋል። ስለዚህ ዓመፅን ልንጸየፍ ይገባል።
9. እኔነት። ሌላው የሰይጣን መቆሚያ እኔነት ነው። ራስ ወዳድነት፥ የራስን ክብር መፈለግና ራስ ተኮር ብቻ የሆነ የሕይወት አካሄድ ለሰይጣን አሠራር የሚመቹ ክፍተቶች ናቸው። ጌታ ኢየሱስ ራሳችንን በመካድ መስቀላችንን ተሸክመን እንድንከተለው አዞናል። ራሳችንን ስንክድ ብቻ ነው በእውነት እግዚአብሔርን የሚያስከብር ኑሮ መኖር የምንችለው። ሃያ አራት ሰዓት ሙሉ ስለ ራሳችን ብቻ እንድናስብ አልተጠራንም። እግዚአብሔር ከራስ ወዳድነት እንዲገላግለን እንለምነው። ያን ጊዜ የተትረፈረፈውን ሕይወት መኖር እንጀምራለን። ለሌሎች መኖር ስንጀምር ሕይወት ጣዕም ይኖራታል። ራስን መውደድ ኃጢአት ባይሆንም እንኳን ሌሎችንም እንደ ራሳችን እንድንወድ ታዘናል። ራስን መውደድ ኃጢአት አይደለም። ራስ ወዳድነት ግን ኃጢአት ነው። "ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶች ሆነው ይመላለሳሉ፤ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ አልኋችሁ፣ አሁንም እንኳ እያለቀስሁ እላለሁ፤መጨረሻቸው ጥፋት ነው፤ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፤ ክብራቸው በነውራቸው ነው፤ ሃሳባቸው ምድራዊ ነው (ፊልጵስዩስ 3፡18-19)።"
ከላይ የተዘረዘሩት 9 ነገሮች ሰይጣን ወደ ሕይወታችን ክፉ ተጽዕኖ እንዲያመጣ መንገድ ሊሆኑ የሚችሉ በመሆናቸው ከሕይወታችን ልናስወግዳቸው ይገባል። ከመንፈስ ፍሬ ጋር የሚቃረኑ የሥጋ ስራዎች ሁሉ ሰይጣን በሕይወታችን ሥፍራ እንዲያገኝ የሚያግዙ ናቸው (ገላትያ 5:16-24)። የሰይጣንን መግቢያ ከእነዚህ አቅጣጫ ከዘጋን፥ የእሱን ክፉ ተጽ ዕኖ ሁሉ ከሕይወታችን ማራቅና የድል ሕይወት መምራት እንችላለን።
ለ. በምስጋናና ውዳሴ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ። ጠላትን የመዋጊያው ሌላው ስልት ደግሞ በምስጋናና በውዳሴ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ነው። "ከሕፃናትና ከሚያጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀ ስለጠላትህ፣ ጠላትንና ቂመኛን ለማጥፋት" ይላል (መዝ 8፡2)። "ቅዱሳን በክብር ይመካሉ፤ በምንጣፋቸውም ላይ ሐሴትን ያደርጋሉ። የእግዚአብሔር ምስጋና በጉሮሮአቸው ነው። ሁለት አፍ ያለው ሰይፍ በእጃቸው ነው በአሕዛብ ላይ በቀልን፥ በሰዎችም መካከል ቅጣትን ያደርጉ ዘንድ፥ ንጉሦቻቸውን በሰንሰለት፥ አለቆቻቸውንም በእግር ብረት ያስሩ ዘንድ፥ የተጻፈውን ፍርድ ያደርጉባቸው ዘንድ ለቅዱሳን ሁሉ ይህች ክብር ናት፤ ሃሌሉያ (መዝ 149፡5-9)።" "ምስጋናን የሚሰዋ ያከብረኛል፤ የእግዚአብሔርን ማዳን ለእርሱ የማሳይበት መንገድ ከዚያ አለ (መዝ 50፡23)።" "እንግዲህ ዘወትር ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ በእርሱ እናቅርብለት (ዕብ13፡15)።" እግዚአብሔርን ስለ ታላቅነቱ ልንወድሰው ይገባል፤ ስለቸርነቱ ልናመሰግነው ይገባል፤ አንደበታችንን በመክፈት "ትልቅ ነህ፥ ኃያል ነህ፥ ኤልሻዳይ ነህ፥ ታማኝ ነህ፥ ንጉሥ ነህ፥ ጌታ ነህ፥ አምላክ ነህ፥ እፁብ ድንቅ ነህ፥ ክቡር ነህ፥ ቅዱስ ነህ፥ የሚመስልህ የለም፥ የነገሥታት ንጉሥ ነህ፥ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ውስጥ ትኖራለህ፥ መጀመሪያና መጨረሻ አልፋና ኦሜጋ ነህ" ልንለው ይገባል። በሌላም ብዙ ቃላትና ዜማ ልናወድሰው ይገባል። ይህ ውዳሴያችን ለጌታ ጣፋጭ መሥዋዕት ሲሆን ለሰይጣን ግን መራራ ነው፤ አስደንጋጭ ነው። በተጨማሪም እግዚአብሔር ስላደረገልን ነገር ዘወትር ልናመሰግነው ይገባል፤ "ልጅህ ስላደረግኸኝ አመሰግንሃለሁ፤ በጌታ በኢየሱስ ሞትና ትንሳኤ ዳግም ልደትን ስለ ሰጠኸኝ ተመስገን፤ የዘላለም ሕይወት ስላገኘሁና ስሜን በሕይወት መጽሐፍ ስለ ጻፍከው ክበር ተመስገን፤ ከዘላለም ሞት ስላዳንከኝ ተመስገን፤ ከሰይጣን የጨለማ መንግሥት ወደ ልጅህ የፍቅር መንግሥት ስላፈለስከኝ አመሰግንሃለሁ፤ ኃጢአቴን ሁሉ ይቅር ስላልከኝ ተመስገን፤ በጌታ በኢየሱስ ክቡር ደም ስላነፃኸኝ አመሰግንሃለሁ። በመንፈስ ቅዱስ ስለሞላኸኝ ተመስገን፤ ኃይልንና ብርታትን ስላበዛህልኝ ተመስገን፤ ስለ ሰጠኸኝ ጤንነት ተመሰገን፤ ስለ ሰጠኸኝ ቤተሰብ ተመስገን፤ አንተ ፈዋሼ ነህ፤ ብርሃኔ ነህ፤ መድኃኒቴ ነህ፤ክብሬ ነህ፤ ምስጋናዬ ነህ፤ተስፋዬ ነህ፤ጌታዬ ነህ፤ሰላሜ ነህ፤አምላኬ ነህ፤ጉልበቴ ነህ፤እረኛዬ ነህ፤መታመኛዬ ነህ፤ ዕረፍቴ ነህ፤ጥበቤ ነህ፤ንጉሤ ነህ፤ጽድቄ ነህ፤ኃይሌ ነህ" ልንለው ይገባል። በምስጋናና ውዳሴ የተሞላ ሕይወት የሚመራ ክርስቲያን ለጠላት ድንጋጤ ነው የሚሆነው። ስለዚህ ወደ እግዚአብሔር ፊት በምንቀርብበት ጊዜ ሁልጊዜ በውዳሴና በምስጋና መቅረብ ተመራጭ መሆኑን አንዘንጋ።
ሐ. ቃሉን ማንበብና ማሰላሰል። የእግዚአብሔር ቃል የመንፈስ ሰይፍ ነው። ጌታ ኢየሱስ እኔ የነገርኳችሁ ቃል መንፈስ ነው፥ሕይወት ነው (ዮሐ 6፡63)" ብሏል። የእግዚአብሔርን ቃል ስናነብ ወይም ስንሰማ የቃሉ መንፈስ ወደ ሕይወታችን ይገባል፤ በጎ ተጽዕኖ ይፈጥርብናል። እምነትን በውስጣችን ይፈጥራል። በቃሉ ውስጥ የእግዚአብሔርን ድምፅ ለሁኔታችን እንሰማለን። አእምሯችን ሥራ መፍታት የለበትም፤ ቃሉን ማሰላሳል አለብን። "ሰው በልቡ እንዳሰበ እንደዚሁ ነውና" ይላል (ምሳሌ 23፡6)። የሽንፈት ሃሳብ የምናስብ ከሆነ ተሸናፊዎች እንሆናለን። የድልን ሃሳብ የምናስብ ከሆነ ድል እናደርጋለን። ስለዚህ ማሰላሰል ያለብን የአግዚአብሔርን ቃል ነው። የአስተሳሰብ ክፍላችንን በእግዚአብሔር ቃል እንሙላው። ከተቻለም ተንበርክከን እናንብበው። በየቀኑ አራት ምዕራፎችን ብናነብ፥መጽሐፍ ቅዱሳችንን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንጨርሳለን። በየእለቱ ስምንት ምዕራፍ ካነበብን ደግሞ በ ስድስት ወር መጽሐፍ ቅዱሳችንን አንብበን መጨረስ እንችላለን። አዲስ ኪዳን 260 ምዕራፎች አሉት። በየእለቱ 10 ምዕራፎችን ብናነብ፥አዲስ ኪዳናችንን በ26 ቀናት ውስጥ መጨረስ እንችላለን። በየዕለቱ ከአዲስ ኪዳን 5 ምዕራፍ ብናነብ ደግሞ በ2 ወር ጊዜ አዲስ ኪዳንን አንብበን መጨረስ እንችላለን። አሉታዊ ነገሮችን በመስማት ጊዜያችንን የምናጠፋ ከሆነ ለሰይጣን በር እንከፍታለን። የምንሰማቸው፥የምናነባቸውና የምናያቸው ነገሮች በጎ ወይም አፍራሽ ተጽእኖ በሕይወታችን ላይ የመፍጠር ዓቅም አላቸው። የእግዚአብሔር ቃል ይሻለናል፤ የቅድስና ተጽእኖ ይፈጥርብናል፤የበጎ ነገር ተጽእኖ ይፈጥርብናል። "የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ (ቆላ 3፡16)።"
የእግዚአብሔርን ቃልና መንፈሳዊ መልዕክቶችን የምናነብና የምንሰማ ከሆነ የታደሰ አእምሮ ይኖረናል። እግዚአብሔር የታደሰ አእምሮ ባለው/ባላት ክርስቲያን ሕይወት በጣም ይጠቀማል። አንድ ሰው "ዳግም የሚወለደው መንፈሳችን ነው፤ አእምሯችን ግን ይታደሳል" ብሏል። አእምሯችን ከአሮጌው አስተሳሰብና ከኃጢአተኝነት የሚላቀቀው በእግዚአብሔር ቃል ሲታደስ ነው። ሰውን ለመቀየር ከፈለግን አስተሳሰቡን መቀየር አለብን። የሰው አስተሳሰብ በእግዚአብሔር ቃል ሲቃኝና ሲታደስ አስተሳሰቡ የተለወጠ ሰው ይሆናል። የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላል፦ "የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሳፅ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል (2ኛጢሞ 3፡16-17)።" ብዙ አማኞች በዳግሞ ልደት አዲስ ሕይወት አግኝተዋል። ሆኖም ግን አስተሳሰባቸው እንደ ቀድሞው አሮጌ ነው፤አልታደሰም። እንደ ቀድሞው ያስባሉ። ይህ ደግሞ ለጠላት በር ይከፍታል። "ሰው በልቡ/አእምሮው/ እንዳሰበው እንዲሁ ነውና (ምሳሌ 23፡6)።" ስለዚህ እንደ እግዚአብሔር ቃል እናስብ፤ ደግሞም እንደ እግዚአብሔር ቃል እንናገር፤ ያንጊዜ ሰይጣን ዕድል ፈንታ በሕይወታችን ውስጥ ያጣል፤
መ. መቀደስ። የተቀደሰ ሕይወት ለጠላት ጸር ነው። በተቀደሰ ሕይወት ውስጥ ሰይጣን ዕድል ፈንታ አይኖረውም፤ "እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ" ብሏል ጌታ (ዘሌዋውያን 19፡2)። የተቀደሰ ሕይወት ለጌታ መጠቀሚያ ይሆናል። የአስተሰሳብ፥የንግግርና የአካሄድ ቅድስና ሲኖረን ጌታ በሕይወታችን ይከብራል። ዕለት ዕለት ለመቀደስ መፈለግ አለብን። "ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ፤ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና (ዕብራውያን 12፡14)።"
ሠ. በልብ አንድነት መጸለይ ወይም ኅብረት ማድረግ (መዝ 133፡1-3፣ ሮሜ 15፡5፣ ኤፌ 4፡3፣ ቆላ 3፡14)። በአንድ ልብ መጸለይና ኅብረት ማድረግ በጠላት ላይ ድልን ለማግኘት ዓይነተኛ መንገድ ነው። ሰይጣን "ከፋፍለህ ግዛ" የሚለውን የቀድሞ ቅኝ ገዢዎች መርህ በጣም ይጠቀማል። የልብ አንድነታችንና ጤናማ ኅብረታችንን በእጅጉ ይዋጋል። በአንድ ልብ ስንሆን ጸሎታችን ስለሚሰማ ለጠላት ሥራ ትልቅ እንቅፋት እንሆናለን። በአንድ ልብ ስንጸልይ መንፈሳዊ ጉልበታችን ስለሚጨምር የጠላት ኃይልና ሥራ ይፈርሳል። "አንዱ ሺህ ሁለቱ አስር ሺህ ያሳድዳሉ ይላል ቃሉ (ዘዳግም 32፡30)።" በአንድ ልብ ስንሆን ከመደመር ስሌት ወጥተን ወደ ብዜት ስሌት ወይም ወደ ስኬት ነው የምንገባው። አንድ ልብ እንዲኖረን የተቻለንን ሁሉ ጥረት ልናደርግ ይገባል። በአንድ ልብ መጸለይ፥በአንድ ልብ ማገልገልና በአንድ ልብ አብሮ መኖር የድል ሕይወት መለማመጃ ምስጢር ነው። የእግዚአብሔር ቃል "እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱና ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ" ይላል (ገላትያ 5፡15)። የልብ አንድነት አለመኖር ለጠላት ሥራ አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል። በመሆኑም በመቀባበል፥በመከባበርና በትሕትና የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ሁላችንም የበኩላችንን ድርሻ ልንወጣ ይገባል። ይህም በመንፈሳዊ ውጊያ ባለድል ያደርገናል።
ረ. የኢየሱስ ስም። "የእግዚአብሔር ስም የጸና ግንብ ነው፤ጻድቅ ወደ እርሱ ሮጦ ከፍ ከፍ ይላል (ምሳሌ 18፡10)።" ጠላትንና ሥራውን ለማፍረስ የጌታ ኢየሱስን ስም በእምነት ልንጠራው ይገባል። ስሙ ዓለታችን ነው። ስሙን ጠርተን አናፍርም። ከስም ሁሉ በላይ የሆነ ስም ስለሆነ በጠላት ኃይል ላይ ፈጥኖ ከአንደበታችን ሊወጣ የሚገባ ስም ነው። ዘጸአት 20፡7፣ "የአምላክህን የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ አትጥራ" ስለሚል የጌታን ስም ስንጠራ በአክብሮት ሊሆን ይገባል።
ሰ. የኢየሱስ ደም። በዕብራውያን 11፡28 ላይ "አጥፊው የበኩሮችን ልጆች እንዳይነካ ፋሲካንና ደምን መርጨትን በእምነት አደረገ" ይላል። እኛ ካህናት ነን (1ኛ ጴጥሮስ 2፡9፣ራእይ 1፡6)፤ የጌታን የኢየሱስን ደም በእምነት በቤታችን ላይ ልንረጭ ይገባል። የጌታ ደም የዘላለም ኪዳን ደም ነው። "ከበጉ ደምና ከምስክርነታቸው ቃል የተነሳ ድል ነሱት" ይላል (ራእይ 12፡11)። መንፈሳዊ ውጊያ ስናደርግ ከላይ የተዘረዘሩትን የውጊያ ስልቶች ብንከተል እጅግ ውጤታማ እንሆናለን። ሆሴዕ 4፡6 "ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል እንደሚል ለመንፈሳዊ ውጊያ ተገቢው መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውቀት ያስፈልገናል። ስለ መንፈሳዊ ውጊያ ስናስብ "በኢየሱስ ስም" ብቻ ማለት እንደሆነ ልናስብ አይገባም። ለጠላት ሥፍራ ሰጥተን፥በኢየሱስ ስም ስንል ብናድር ምንም ለውጥ ላይመጣ ይችላል። ለጠላት የከፈትነውን በር መጀመሪያ መዝጋት አለብን። ሌሎችንም የውጊያ ስልቶች ማለትም፥በምስጋናና በውዳሴ መቅረብ፥ቃሉን ማንበብና ማሰላሰል፥መቀደስ፥በአንድ ልብ መጸለይና የኢየሱስን ደም በመንፈሳዊ ውጊያ ውስጥ ልንጠቀም ይገባል።
መንፈሳዊ ውጊያና የመንፈስ ቅዱስ ምሪት። መንፈሳዊ ውጊያ ስናካሂድ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ሊሆን ይገባል። ከመንፈስ ቅዱስ ውጪ መንፈሳዊ ውጊያ ማድረግ የለብንም። "ጠላትህን ከፊትህ አውጥቶ አጥፋው ይላል" (ዘዳ 33፡27) እንደሚል መንፈስ ቅዱስ የሚጠቁመንን ጠላት ልናጠፋ ይገባል። ነፋስ እንደሚጎስም መዋጋት የለብንም። ጌታ የተለመልንን ውጊያ ልንዋጋ ይገባል። ምድራዊ የሆነ ጦርነት ለማካሄድ እንኳ ዳዊት የጌታን ምሪት ይጠይቅ ነበር። ኢያሱንም ስንመለከት በጌታ ምሪት ነበር የሚዋጋው። መንፈሳዊ ውጊያ ደግሞ ከዚያ እጅግ የረቀቀና የጌታ ምሪት ሙሉ ለሙሉ የሚያስፈልገው ነው። ዳዊት የጌታን ምሪት ጠይቆ ለጦርነት ይወጣ ስለነበር በሄደበት ሁሉ እግዚአብሔር ድል ይሰጠው ነበር (2ኛ ሳሙ 2፡1)። ጌታ ኢየሱስ "እውነት እላችኋለሁ፣ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፤ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና" ብሏል (ዮሐ 5፡19)። ጌታ ኢየሱስ ሁልጊዜ በእያንዳንዱ ነገር ከአባቱ ሰምቶ የአባቱን ፈቃድ ብቻ ያደርግ እንደነበር ሁሉ፥እኛም መንፈሳዊ ውጊያ ስናደርግ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ብቻ ሊሆን ይገባል። "እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል (ዮሐ 16፡1)።"
ያለ ጌታ ምሪት ያደረጉት ውጊያ ብዙ ዋጋ እንዳስከፈላቸው ከባለቤታቸው ከፓስተር ኤዲ እስሚዝ ጋር የአሜሪካው የጸሎት ማዕከል መስራች የሆኑት ዶ/ር አሊስ እስሚዝ ከጥቂት ዓመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ለአገልግሎት በመጡ ጊዜ የሚከተለውን መስክረውልናል። "በምኖርበት የዩስተን ከተማ፣ ገዢ የሆኑት መናፍስት የትኞቹ እንደሆኑ እንዲነግረኝ ጌታን በጸሎት ጠየኩት። ጌታም የስድስት ገዢ መናፍስትን ስሞች ጠቆመኝ። ከዚያም ወዲያውኑ ጾም ጸሎት በመያዝ ከመናፍስቱ ጋር ውጊያ ገጠምኩኝ። ከዚያም በዚያ ዓመት ብቻ በቤተሰባችን ውስጥ ስድስት ሰዎች የቀዶ ጥገና ሕክምና በሚያስፈልገው ሕመም ተመታን። በሁኔታው ግራ በመጋባት ጌታን "ምነው ይሄ ሁሉ ሲሆንብን እያየህ ዝም አልከን?" ብዬ ጠየኩት፣ ጌታም "የስድስቱን ገዢ መናፍስት ስም ጠየቅሽኝ፤እኔም ነገርኩሽ። ከዚያ በኋላ ግን ምን ማድረግ እንዳለብሽ እኔን አልጠየቅሽኝምኮ ልጄ" አለኝ። ከዚያን ጊዜ ወዲህ የጌታን ምሪት ሳንጠይቅ እኔና ባለቤቴ ምንም ዓይነት መንፈሳዊ ውጊያ አናደርግም፤ ለድላችን ቁልፉ ያለው ጌታን ሰምተን መዋጋቱ ላይ መሆኑን ከደረሰብን መንፈሳዊ ጥቃት ትምህርት ወስደናል።" የመናፍስት አሰራር ረቂቅ በመሆኑ በሥጋና በደም ልንረዳው አንችልም። የመንፈስ ቅዱስ ምሪት እጅግ ያስፈገናል። የትኛውን መንፈሳዊ የጦር ዕቃ መቼ መጠቀም እንዳለብን ከጌታ ምሪት መቀበሉ አስፈላጊ ነው። አንዳንድ ጊዜ በኢየሱስ ስም መቃወም ውጤታማ ሊያደርገን ይችላል፤ሌላ ጊዜ ደግሞ በምስጋናና በውዳሴ ብቻ በጌታ ፊት መቅረብ ጠላትን ሊመታው ይችላል፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ ቃሉን በመጥቀስ መዋጋት ውጤታማ ሊያደርገን ይችላል። አንዳንዴ ደግሞ የኢየሱስን ደም በመጥቀስና በእምነት በመርጨት መዋጋቱ ሊመረጥ ይችል ይሆናል። ሌላ ጊዜ ደግሞ ከወገናችን ጋር በአንድ ልብ ሆኖ መጸለይና ማምለክ የጠላትን ሥራ ለማፈራረስ ወሳኝ ይሆናል። ስለዚህ የትኛውን መንፈሳዊ የዉጊያ ስልት መቼ መጠቀም እንደሚገባን ጌታ እንዲመራን እንጠይቀው።
ለጠላት መቆሚያ የሚሆኑ ነገሮችንም ከሕይወታችን ማስወገድ አንዱ ጠላትን የመቃወሚያው ዋና መንገድ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። አንዳንድ ወገኖች ወደ ጠንቋይ ቤት ሄደው መንፈሳዊ ውጊያ ለማካሄድ እንደሞከሩ የሰማኋቸው ታሪኮች አሉ። ጌታ ብሏቸው ከሆነ የሄዱት መልካም ነው፤ በቅንአት ብቻ ተነሣሥተው ያለ ምሪት ከሄዱ ግን አላስፈላጊ ዋጋ ከመክፈል ውጪ ውጤታማ ሊሆኑ አይችሉም። ሆሴዕ 4፡6 "ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሳ ጠፍቶአል" እንደሚል የእውነት እውቀት እጅግ አስፈላጊ ነው። "የማያስተውል ሕዝብ ይገለበጣል" የሚለውን ቃል (ሆሴዕ 4፡14) ልብ በማለት በመንፈሳዊ ማስተዋልና ጌታን በማድመጥ መንፈሳዊ ውጊያ ልናደርግ ይገባል። "በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም፤ በዚያን ቀን ብዙዎች ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህስ አጋንንት አላወጣንምን? በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንምን? ይሉኛል። የዚያን ጊዜም ከቶ አላወቅኋችሁም! እናንተ ዓመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ" (ማቴ 7፡21-23) በማለት ጌታ ያስጠነቅቀናል። ዋናውና ጠቃሚው ነገር አጋንንት ማውጣት፥ትንቢት መናገር ወይም ብዙ ተአምራት ማድረግ ሳይሆን የአብን ፈቃድ ለይተን ማድረግ ነው። እነ ጳውሎስ ቃሉን እንዳይናገሩ መንፈስ ቅዱስ እንደ ከለከላቸው እናነባለን (የሐዋ 16፡6)። ከዚያም ወደ ቢታንያ ይሄዱ ዘንድ ሲሞክሩ የኢየሱስ መንፈስ አልፈቀደላቸውም፤ ከዚያም በራእይ እና በምሪት ወደ መቄዶንያ እንደሄዱ እንገነዘባለን። እነዚህ ሰዎች በሌላ ጊዜ ወደ እስያ ሄደው ወንጌል ሰብከዋል። መቼ ምን ማድረግ እንዳለብን ጌታ ምሪት ይሰጠናል። በአንድ ወቅት ጊዜው ባለ መሆኑ የከለከለንን ነገር በሌላ ጊዜ ሊፈቅድልን ይችል ይሆናል። ስለዚህ ጌታን የሚሰሙ የተከፈቱ የልብ ጆሮዎች ያስፈልጉናል። ዎች ማን ኒ የተባሉ ቻይናዊ አገልጋይ ምሪትን በተመለከተ የሚከተለውን ብለዋል፣ "እግዚአብሔርን የሚፈሩና ራሳቸውን የካዱ ሰዎች ጌታ ያልከለከላቸውን ነገር ሁሉ እንደ ተፈቀደ አስበው ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ። ጌታ የማይፈቅደውን ነገር በመከልከል ወይም ባለመፍቀድ የሚያሳውቃቸው ሲሆን ፈቃዱ የሆነውን ነገር ሲያደርጉ ግን ምንም የተዐቅቦ ድምፅ በውስጣቸው አይሰሙም። እነ ጳውሎስን ጌታ በዚህ መንገድ ነበረ የሚመራቸው።" እንዲያው በዘፈቀደ እየተነሱ "ጌታ እንዲህ አለኝ" የሚሉ ሰዎችን ይህ አይመለከትም።
እግዚአብሔርን ለሚፈሩ፣ ራሳቸውን ለካዱና የጌታን ፈቃድ ብቻ ለሚፈልጉ በዚህ ዓይነት መንገድ ሊመራቸው ይችላል። "ጌታ ሆይ ድምፅህን መስማትና መለየት አስተምረኝ" ብለን እንጸልይ። ጌታ ዳቦ ብንለምነው ድንጋይ አይሰጠንም፤ ዓሳ ስንለምነው እባብ አይሰጠንም። ድምጹን መለየት ያስተምረናል፣ ያሳድገናል። በቃሉ መሞላትና ከጌታ ጋር በጸሎት ሰፊ ጊዜ ማሳለፍ ድምጹን ለመለየት እጅግ ይጠቅማል።
መንፈስ ቅዱስንም ዕለት ዕለት መሞላት የጌታን ድምፅ ለመለየት ይረዳል። ጌታ ጥበብንና ማስተዋልን እንዲሰጠንም በጸሎት ልንጠይቀው ይገባል። ያንጊዜ ስኬታማ የሆነ መንፈሳዊ ውጊያ ልናካሄድ እንችላለን።