ኢየሱስ ሊቀ ካህናትም አማላጅም ነው

ነቢዩ ኢሳይያስ

“እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዓት አንተ ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ፥ እግዚአብሔር ማለ አይጸጸትም …እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ ሊቀ ካህናት ሊሆን ራሱን አላከበረም፤ ነገር ግን አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ ያለው እርሱ ነው፤ እንደዚህም በሌላ ስፍራ ደግሞ። አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ይላል …በዚያም ኢየሱስ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ሊቀ ካህናት የሆነው፥ ስለ እኛ ቀዳሚ ሆኖ ገባ፤ መዝሙር 110፣4፤ዕብ 5፡5-6፤6፣20።”

በአይሁዶች ሕግም ሆነ ታሪክ ውስጥ ንጉሥ ካህን ሆኖ የሚያውቅበት ታሪክ የለም ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ካህን እንደሚሆን ተተንብዮለት ነበር (መዝ 110)። ይሁን እንጂ ይህ ትንቢት በዘመኑ በምን ሁኔታ ተግባራዊ እንደሚሆን ወይም መሲሁ እንዴት ካህን እንደሚሆን ለሕዝቡ ግልጽ አልነበረም (1ሳሙ 2፣35)። የዕብራውያን መልእክት ጸሓፊ ግን መሲሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ካህን መሆን የቻለበትን መንገድ አሳይቶናል። ኢየሱስ ክርስቶስ የክህነት አገልግሎት የተሰጠው ራሱን መስዋዕት አድርጎ በማቅረቡ ነው (ዕብ 5፣10፤ 6፣19-20)። ዛሬም ኢየሱስ ክርስቶስ ብቸኛው ንጉሥና ካህን ሆኖ ሳለ በእርሱ ስለሚያምኑቱም ሆነ በእርሱ በኩል ወደ አብ ለሚመጡቱ ይማልዳል (ዕብ 7፣25፣ ሮሜ 8፣34)።

ኢየሱስ ብቸኛ ንጉሥና ካህን ሆኖ ስለ እኛ ይማልዳል ማለት ምን ማለት ነው? የሚለው ጥያቄ ይነሳ ይሆናል። ሓሳቡን ለመረዳት ወደ ትርጓሜው ሓሳብ እሄዳለሁ። “ማማለድ” ማለት ምን ማለት? “ማማለድ” ወይም “መማለድ” ማለት ስለ ሌላው ሆኖ፥ የሌላውን ጉዳይ ይዞ መፍትሔና ብያኔ ለማግኘት ሲባል የሚደረግ ተተኪ መሆን ማለት ነው። ምልጃ የሚለው ቃል ደግሞ ስለ ሌላው መጸለይ ሲሆን፣ ይህም ማንም ሰው ስለ ሌላ ሰው የሚጸልየውን ጸሎት ያሳያል። ይህ ቃል በአዲስ ኪዳን ልመናንና ጸሎትን ለማሳየት በጥቅም ላይ ውሏል (ፊልጵስዩስ 4፥6፤ 1ጢሞ 2፥1-2)። የደስታ ተክለ ወልድ የአማርኛ መዝገበ ቃላትም በበኩሉ ከዚህ ቃል ጋር ተያያዥ ስለ ሆነው ሓሳብ ብዙ ማብራሪያን ሰጥቷል። ከዚህ በታች የማነሳቸውን ቃላት ትርጓሜ ሓሳብ በመመልከት ወደ ትርጓሜው ዋና ሓሳብ መሄድ ይቻላል። “ማማለድ” የሚለው ቃል “ማለዳ” ከሚለው የተገኘ ሲሆን፣ ትርጉሙም፦ “በማለዳ ገስግሶ ፍርደኛውን ማዳን” ማለት ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተቀመጠው ደግሞ “አማላጅ” የሚለው ቃል ሲሆን፣ ይህም “ያማለደ፣ የሚማልድ፣ የነፍስ የሥጋ አስታራቂ፣ መካከለኛ” የሚለውን ሓሳብ ያሳያል (1ዮሐ 2፣1)።[1] “ማማለድ” ማለት ደግሞ “ፍርደኛውን ነፃ ማውጣት” ማለት ነው። በዘመናችን ግን ከዚህ የተለየ ትርጉም ተሰጥቶት “ማማለድ” ማለት “ስለ ሌላው ሰው መጸለይ (መለመን)” የሚል ትርጉም ብቻ የተሰጠው ይመስላል። “አማላጅ” ማለት ደግሞ “ስለ ሌላው ሰው ልመና የሚያደርግ” ማለት ነው። ይህም፣ በራስ ማድረግ የማይቻል መሆኑን ያንጸባርቅልናል።

ከአማርኛው መዝገበ ቃላት ሓሳብ ወጣ ስንል ደግሞ “ማማለድ” በመሠረተ ሓሳቡ “መስዋዕትን ማቅረብ፣ ሥርየትን መስጠት፣ የምሥራችን ማወጅና ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነትን መፍጠር” ላይ የሚያተኩር ተግባር ሆኖ እናገኘዋለን። የሰዎችን ድነት በመስቀሉ ላይ በትኪ ሞት መስዋዕት በመሆን የፈጸመው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመሆኑ፣ ይህንን የማማለድ ተግባር ማለትም የኃጢአትን ይቅርታ የመስጠትና ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነትን የመፍጠር ሥራ የሚሠራ አሁንም አዳኛችን፣ ንጉሣችንና ካህናችን የሆነው ጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሆኖ እናገኘዋለን። ዮሐንስ በመልእክቱ ስለዚህ ሁኔታ ሲናገር እንዲህ ይለናል፦ “ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ፤ 1ዮሐ 2፣1-2።”

ኢየሱስ ክርስቶስ በካህንነቱ ፍጹም ነው። አገልግሎቱም ለሕዝቡ ምልጃን ማቅረብ ትልቅ ሥፍራ ነበረው። ለጴጥሮስ አማለደ (“እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ አማለድሁ፣” ሉቃ 22፣31-32)። አብን እንደሚለምንና ሌላ አጽናኝ እንደሚሰጣቸው ለደቀ መዛሙርቱ ቃል ገባ (ዮሐ14፣16)። ለመስቀል ሞት አልፎ ከመሰጠቱ በፊት በሠፊው ለተከታዮቹ ጸለየ (ዮሐ 17)። ሞቱን የአዲስ ኪዳንን ደም እንደ ማፍሰስ አድርጎ ገለጸው (“ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው፣” ሉቃ22፣20)። ከትንሣኤ በኋላም ደቀ መዛሙርቱን እንደ ካህን ቡራኬ ሰጣቸው (“እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው፣” ሉቃ 24፣ 50-51)።

ኢየሱስ ክርስቶስ በአገልግሎቱ የመልከ ጼዴቅን ክህነት ፈጽሟል። ለዚህ የበቃው ደግሞ ራሱን ለእግዚአብሔር የመዓዛ ሽታ አድርጎ በማቅረቡ ነው (ኤፌ 5፣1-3)። በዚህም ምክንያት ስለ እኛ የሚማልድ ሆኗል። እዚህ ላይ ግን ቀደም ሲል ወዳነሳነው የጥያቄ መልስ ከመሄዳችን በፊት ምልጃን ከወንጌላውያን አማኞች ውጭ ካሉ መምህራን እምነትና አመለካከት አኳያ እንመለከተዋለን። በዚህ ዘመን አንዳንድ መምህራም ምልጃን አስመልክቶ የሚሉት አለ።ይኸውም፦ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመስቀል ሞቱ በፊት በግብረ ትስብእት እያለ “ለምኗል” ወይም በአሁኑ ትርጉም “ጸልዩአል፣” ከትንሣኤ በኋላ ግን እርሱ አይለምንም፤ ምክንያቱም በሰዎችና በእግዚአብሔር መካከል ለተፈጠረው ጥል የማስታረቅን ሥራ በግብረ ትስብዕት በማጠናቀቁ ነው ብለው ያምናሉ። እንደ እነዚህ መምህራን እምነት ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በሥጋ እያለ ይህንን የመማለድ (የመለመን) ተግባር ጨርሷል ወይም አጠናቅቋል። እርሱ አሁን በአብ ቀኝ ከተቀመጠበት ተነሥቶ እንደገና እንዴት ይጸልያል? ያኔም እንኳን መለኮት በሥጋ አማልዷል፤ ሥጋ ለመለኮት መልስ ሰጥቷል ይላሉ።[2] እንግዲህ ከእንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ሊሆን ይችላል አንዳንዶች ኢየሱስ ክርስቶስ አሁን ባለበት ሁኔታ ፈራጅ እንጂ አማላጅ አይደለም በማለት የሚያስተምሩት።

ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር እያለ ስለ ሰዎች ይማልድና ይለምን ነበር? ለሚለው ጥያቄ መልሳችን፣ “አዎን” ነው። እንደ ገናም ፈራጅ ነው? በሚገባ። አሁን ባለበት ሁኔታ ደግሞ ንጉሥ በመሆኑ አሁንም ሆነ ዳግም በመምጣቱ በንጉሥነት ዓለምን ይገዛል፤ ደግሞም የፍርድን ተግባር ያከናውናል። በእርግጥ በአንዳንድ መምህራን ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ አሁን ባለበት ሁኔታ ፈራጅ እንጂ አማላጅ አይደለም የሚል ትምህርት ይሰማል። እኛ ደግሞ በእርግጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ፈራጅ ብቻ ሳይሆን አማላጅስ አይደለም? የሚል ጥያቄ እናነሳለን። ወደ ቅዱሳት መጽሓፍት ትምህርት ስንመለስ የዕብራውያንና የሮሜ መጻሕፍት በዚህ ጉዳይ ምን ያስተምሩናል? በዚህ ጉዳይ ላይ ሊኖረን የሚገባው ነገረ መለኮታዊ ምልከታ እንደሚከተለው ሊሆን ይገባል።

የኢየሱስ ክርስቶስ አማላጅነት፦ “እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው፥ የሚኰንንስ ማን ነው? የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፥ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፥ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው (ሮሜ 8፣ 32-33)።” “እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል። እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤ እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል (ዕብ 7፣22-25)። እንደ አዲስ ኪዳን ትምህርት ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህናችን ነው። ሊቀ ካህናት ማለት አስታራቂ ማለት ነው። የሊቀ ካህናትን ሥራ ያላወቀ ሰው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ሊረዳ አይችልም። ይህንን የተረዳ ሰው ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥራ ሊክድ አይችልም። በቀደመው ኪዳን የሊቀ ካህን ዋና ሥራ በዓመት አንድ ጊዜ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የእንስሳት ደም ይዞ በመግባት የእርሱንና የሕዝቡን ኃጢአት ማስተሰረይ እንደ ነበረ እነዚህ የመጽሓፍ ቅዱስ ንባባት ያስረዳሉ (ዘሌ 1611-34 ዕብ 96-10) ይህ ማለት የሊቀ ካህናቱ ሥራ ሕዝቡን ከእግዚአብሔር ጋር ማስታረቅ ነው ማለት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ አስታራቂ ነው ስንል በአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናትነቱ ባቀረበው መስዋዕትና ምልጃ ሰውንና እግዚአብሔርን ያስታረቀ ብቸኛው ሊቀ ካህን ነው ማለታችን ነው። ከዚህ እውነታ በመነሳት የቀደመውን ኪዳንና የአዲሱን ኪዳን ሊቀ ካህን እናነጻጽር፦

የቀደመው ኪዳን ሊቀ ካህን ሰው ብቻ ነው (ዕብ 5፣1)፤ የአዲሱ ኪዳን ሊቀ ካህን ግን ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ነው (ዮሐ 1፣1፤2፤ ዮሐ 5፣20)። የቀደመው ኪዳን ሊቀ ካህን ክህነቱ ከሌዊ ነገድ በመወለድና የአሮን ወገን በመሆን በዘር የሚገኝ ሲሆን ያለ መሐላ የተሰጠ ክህነት ነበር (ዕብ 7፣ 1)። ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ከይሁዳ ነገድ የተወለደና ክህነቱ እንደ አሮን ሳይሆን፣ እንደ መልከ ጼዴቅ የሆነ ከመሓላ ጋር የተሰጠ ክህነት ነው (ዕብ 7፣11-14)። የቀደመው ኪዳን ሊቀ ካህን ኃጢአተኛ ስለ ሆነ በእግዚአብሔር ፊት ስለ ራሱም መስዋዕት ማቅረብ ያስፈልገው ነበር (ዘሌ 11፣14፤ ዕብ 5፣1-4)፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ኃጢአት የሌለበት ስለ ሆነ ስለ ራሱ መስዋዕት ማቅረብ አላስፈለገውም (ዕብ 7፣26)። የቀደመው ኪዳን ሊቀ ካህን አገልግሎቱ በሞት የተገደበ ስለ ነበረ ሲሞት ክህነቱ በሌላ ይተካል ወይም ክህነቱ ይሻራል፣ በአስታራቂነቱም አይቀጥልም። ስለዚህ ምክንያት ካህናት የሆኑ ብዙ ነበሩ (ዕብ 7፣23)። ኢየሱስ ግን ህያውና ዘላለማዊ ስለ ሆነ የማይሻር ክህነት አለው፤ የሚተካው አያስፈልገውም። ስለዚህ አስታራቂነቱ ወይም ምልጃው ዘላለማዊ ነው (ዕብ 9፣12)። የቀደመው ኪዳን ሊቀ ካህን ለመስዋዕት የሚያቀርበው የእንስሳትን ደም ነበር (ዘሌ 16፣11-34፤ ዕብ 9፣6-10)፤ ኢየሱስ ግን መስዋዕት አድርጎ ያቀረበው የራሱን ደም ነው (ዕብ 9፣12)። ለመማለድ ወይም ለማስታረቅ በቀደመውም ሆነ በአዲሱ ኪዳን ደም ያስፈልጋል። ያለ ደም ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ ይህንን ማድረግ ስለማይቻል ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ማድረግ ማን ይችላል? የቀደመው ኪዳን ሊቀ ካህን መስዋዕትን በእግዚአብሔር ፊት የሚያቀርበው ዕለት ዕለት ወይም በተደጋጋሚ ነበር (ዕብ 7፣27፤10፣11)፤ ኢየሱስ ግን ለዘላለም ስላቀረበ በተደጋጋሚ ማቅረብ አላስፈለገውም፣ መስዋዕቱ ዘላለማዊ ነው (ዕብ 7፣27፤ 9፣25፤10፡12-14)። የቀደመው ኪዳን ሊቀ ካህን በክህነቱም ሆነ በሚያቀርበው መስዋዕት ፍጹም ድነት አልተገኘም (ዕብ 10፣11)፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ዘላለማዊና ፍጹም ድነት አስገኝቷል (ዕብ 7፣25)። የቀደመው ኪዳን ሊቀ ካህን ያገለገለው ለሰማያዊቱ መቅደስ ምሳሌ በሆነችውና በሰው ልጅ ባልተሠራችው ምድራዊ መቅደስ ውስጥ ነበር (ዕብ 9፣6-7)። ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ያገለገለው በማታልፈውና ሰማያዊት በሆነችው መቅደስ ነው፤ እርሷም በሰው እጅ ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት (ዕብ 8፣2፤9፣11፣12፣28)።

ከዚህ በላይ በንጽጽር እንደ ተመለከትነው ኢየሱስ ክርስቶስ በማይሻር ክህነቱ አንድ ጊዜ ብቻ ባቀረበው ዘላለማዊ መስዋዕት ዘወትር ሲማልድና ሲያድን ይኖራል (ዕብ 5፣7-10፤7፣25)። የእግዚአብሔር ድንቅ ጥበብ ከሚመሰከረበት ነገሮች ውስጥ አንዱ ይኸ ነው። “እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ ይበልጣል።” ዓለምን ለመፍጠርም ሆነ ዓለምን ለማዳን ችሎታ ያለው ሁሉም የማይሳነው አምላክ ብቻ ቢሆንም አፈጻጸሙ ሲታይ ግን እውነትም ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ ይበልጣል። የቀደመው ኪዳን ሊቀ ካህናት ከተሾመበት ጊዜ አንስቶ እስከሚሞትበት ጊዜ ድረስ በየጊዜው መሰዋዕት እየሠዋ ይማልድ ነበር። በሕጉ መሠረት የአንድ ጊዜ መስዋዕት ይቅርታን የሚያስገኘው አንድ ጊዜ የተሠራን ኃጢአት ነው። በዚሁ መሠረት በዚያ ኪዳን ውስጥ የሚያልቁትም እንስሳት ስፍር ቁጥር አልነበራቸው ። እንዲህም ሆኖ የሚገኘው ድነት ፍጹም ድነት አልነበረም። የአዲሱ ኪዳን ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ኃጢአተኞች በተደጋጋሚ በግ፣ ፍየልና የመሳሰለውን መስዋዕት በመጎተት መጨነቅ ሳያስፈልጋቸው አንድ ጊዜ ለዘላለም ትኩስ ሆኖ የሚኖረውን የኢየሱስን ደም ሠውቶ ለዘላለም በዚያው መስዋዕት ሲማልድ ይኖራል። አንድ ጊዜ እግዚአብሔር “ይሁን” ብሎ የፈጠረው ፍጥረት እንደገና “ይሁን” ተብሎ ሳይፈጠር እየተባዛ ይኖራል። አንድ ጊዜ ስለ ኃጢአት ሥርየት የፈሰሰው የክርስቶስ ደምም፣ እግዚአብሔር “ይሁን” ብሎ በወሰነው መሠረት በድጋሚ መፍሰስ ሳያስፈልገው ዘወትር ሲማልድና ሲያድን ይኖራል።

በሊቀ ካህናት አገልግሎት ያለ ደም ምልጃ አይፈጸምምና ሊማልድ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ሲገባ ደም ይዞ ነው። ይህ በየዓመቱ ይከናወናል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ወደ ሰማያዊቱ ቤተ መቅደስ የራሱን ደም ይዞ የገባው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። የሚገርመው ደግሞ መስዋዕቱና ምልጃው የቀረበው አንድ ጊዜ ብቻ መሆኑ ነው። ያ አንድ ጊዜ የቀረበው ግን ዘወትር ይሠራል። የቀረብነውም ከአቤል ደም ይልቅ ወደሚናገር ደም ነው። የአቤል ደም ፍትህ ፍለጋ ለፍርድ ወደ እግዚአብሔር ይጮህ እንደ ነበር፤ በቀራኒዮ መስቀል ላይ የፈሰሰውም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ለሰው ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ምህረትን ይጠይቃል። ይህ ደም የፈሰሰው አንድ ጊዜ ነው፣ ምህረትን የሚጠይቀው ግን ለዘላለም ነው። እዚህ ላይ ግን አንድ ነገር ልብ ማለት ያስፈልጋል። ይኸውም “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወትር ሊማልድ ይኖራል” ማለት በምድር ላይ ይኖር በነበረበት ጊዜ እንዳደረገው አሁንም በአባቱ ፊት በመደፋት ይጸልያል ማለት አይደለም፤ በምድር እንዳደረገው በአባቱ ፊት በመደፋት ይጸልያል የምንል ከሆነ በየጊዜው መከራን እየተቀበለ ነው እንደ ማለት ነው። የዕብራውያን ጸሓፊ “ሊቀ ካህናቱም በየዓመቱ የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት እንደሚገባ ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም” ካለ በኋላ በመቀጠል “እንዲህ ቢሆንስ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ መቀበል ባስፈለገው ነበር። አሁን በዓለም ፍፃሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጧል” በማለት መስዋዕቱና ምልጃው አንድ ጊዜ ለዘላለም የተፈጸመ እንጂ በየጊዜው የሚከናወን ያለመሆኑን ያስረግጥልናል (ዕብ 9፣ 25- 26)።

በቀደመው ኪዳን ሕዝቡ ኃጢአቱ እንዲሠረይለት በየዓመቱ አዳዲስ የእንስሳት ደም ማየት ነበረበት። በየጊዜው ኃጢአትን የሚሠራ ሰውም የእንስሳን ደም እያቀረበና ኃጢአቱን በሚታረደው የእንስሳ ላይ እያደረገ ደሙን ማየት ነበረበት (ዘሌ 4፣29)። ያም መስዋዕት ሰውን ፍጹም በማድረግ ከሕሊናው በደልን እንዲረሳ አያደርገውም ነበር (ዕብ 10፣1-4)። በአዲስ ኪዳን ግን እንዲህ አይደለም። አንድ ጊዜ የተሠዋውን የእግዚአብሔርን በግ በቀራኒዮ ላይ ማየታችን ብቻ በቂ ነው። አንድ አይሁዳዊ ኃጢአት በሠራ ቁጥር ኃጢአቱን ለማስተሰረይ እንስሳ ይዞ እንዲመጣ፣ ሕዝቡም በዓመት አንድ ጊዜ እንዲሁ እንዲያደርጉ ሕጉ ያዝ[ዝ] ነበር። ማንም ሰው ዛሬ በግ ነገ ፍየል ሳያስፈልገው ድነት ለማግኘት ቀድሞ ወደ ተሠዋው በግ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ በዓይነ ልቦናው መመልከት ብቻ በቂ ነው።

ማጠቃለያ። የክርስቶስን “በአንድ ጊዜ መሥዋዕትነት የዘወትር አማላጅነት” በሥነ ፍጥረት ምሳሌ ብንመለከት፣ አንድ ጊዜ እግዚአብሔር ይሁን ብሎ የፈጠረው ፍጥረት እንደገና ይሁን ተብሎ ሳይፈጠር እየተባዛ ይኖራል። አንድ ጊዜ ስለ ኃጢአት ሥርየት የፈሰሰው የክርስቶስ ደምም፣ እግዚአብሔር “ይሁን” ብሎ በወሰነው መሠረት በድጋሚ መፍሰስ ሳያስፈልገው ዘወትር ሲማልድና ሲያድን ይኖራል። ጥንታዊቷም ቤተ ክርስቲያን ይህን የክርስቶስን አማላጅነት ተቀብላ ስታስተምር ኖራለች። የሚከተሉት የአዋልድ መጻሕፍት ጥቅሶች ይህን ያስረዳሉ። ዮሐንስ አፈወርቅ (ጆን ክሪሶስተም) የዕብራውያንን መልእክት በተረጎመበት ድርሳኑ እንዲህ ብሏል፦ “ባሕርያችንን ስለ ተዋሀደ ሰው የመሆኑን ነገር ያስተምረን ዘንድ ይህን ተናገረ። ሰው ለመሆን ያበቃው ለማስታረቅ፣ ኃጢአትን ለማስተሠረይ ብቻ ነው እንጂ ሌላ ምክንያት የለውም። ከእርሱ በቀር ራሱ ብቻውን ኃጢአት ማስተስረይ የሚቻለው የታመነ አስታራቂ ማነው? ለማስታረቅ ኃጢአትን ለማስተሠረይ ያቀረበው መሥዋዕትስ ምንድን ነው? መሥዋዕት ለመሆን የነሳው (የያዘው) ሥጋው ብቻ ነው እንጂ። እርሱ ተመልክቶን እነሆ ለእግዚአብሔር ጠላቶች ሆነን ተገኘን። ሀብትን (ልጅነትን) ለማግኘት ኪዳንም ቢሆን፣ መስዋዕትም ቢሆን፣ ወደ እርሱ ያቀርበን ዘንድ የሚችል ፈጽሞ አልነበረንም። እርሱ አንዱ ወደ እዚህ ዓለም ወርዶ ባሕርያችንን ባህርዩ አድርጎ ሊቀ ካህናት (አስታራቂ) ሆነን እንጂ። ከመላእክት፣ ከኃያላትም ወገን ሊቀ ካህናት (አስታራቂ) አልሾመልንም።”[3] ይህ “ኃይማኖተ አበው” የተባለው መጽሐፍ ቤተ ክርስቲያን ለትምህርት የምትጠቀምበት በግዕዝና በአማርኛ ተርጉማ የያዘችው መጽሐፍ ነው። ሌሎች አዋልድ መጻሕፍትም ይህን ሐቅ ይመሰክራሉ። ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁሉ በላይና ለዘላለም የሆነ ሊቀ ካህናታችን ነው። ኢየሱስ ሊቀ ካህናት ነው ማለት አማላጅ ነው ማለት ነው።[4]

[1] ደስታ ተክለ ወልድ፣ የአማርኛ መዝገበ ቃላት፣ ገጽ 775። [2] መላከ ገነት አፈወርቅ፣ ሕዳር 12/1993፣ ቃለ መጠይቅ። [3] ኃይማኖተ አበው፣ በዮሐንስ አፈወርቅ፣ 63 ቁ.14-16፣ ገጽ 222። [4] መልከ ኢየሱስ።