የኪነጥበብ መገኛዋ ወዴት ነው?

ምህረት ማስረሻ

mihret

ኪነጥበብ በአጭሩ ሲተረጎም በሰውነት እንቅስቃሴ፤ በቁስ፤ በድምጽ፣ በጽሑፍ፣ በአቀማመጥ፤ በብልሀት ተቀናብሮ የሚቀርብ የሚታይ፣ የሚደመጥ፣ የሚዳሰስ ውበት ነው። ኪነጥበብ በብልኃት፣ በዝርዝርና በጥልቀት ከማከናወን የሚገኝን ውበት ይወክላል። የኪነ-ጥበብ ዓላማውም ተግባሩም ውበትን በውበት ማቅረብ ነው። መጥኖና ቆጥቦ አሳምሮና አቀናብሮ ማሳየት፣ ማስደመጥ - ኪነጥበብ ነው። በውበትና ውብ አድርጎ በመስራት፣ የሰራውንም ለሰው ልጆች በመግለጥ እግዚአብሔርን የሚስተካከለው የለም። የሰው ልጅ ኪነጥበብን የሚማረው ከእግዚአብሔር ነው። ዙሪያችንን ስናስተውል፤ ራሳችንን ስንመረምር የእግዚአብሔርን ማስተዋልና ጥበቡን እንማራለን። መጽሐፍ ቅዱሳችን ወደር የማይገኝለት የኪነ-ጥበብ መዝገብ ነው። ዛሬ በአለማችን ላይ የመጠቁ ቴክኖሎጂዎች የስኬት ምስጢር በዙሪያችን ያለውን የእግዚአብሔር ጥበብ ጠንቅቆ በማጥናትና በመቀጸል የተገኙ ናቸው። የኪነጥበብ ሂደቱም ሆነ ትግበራው ማስተዋልና ዕውቀትን ይጠይቃል። “እግዚአብሔር በጥበብ ምድርን መሠረተ። በማስተዋልም ሰማያትን አጸና። በእውቀቱ ቀላያት ተቀደዱ፤ ደመናትም ጠልን ያንጠባጥባሉ" ምሳሌ3:19-20።

የኪነጥበብ ዘርፎች፡፡ ሥነ-ግጥም፣ ሥነ-ጽሁፍ፤ ድራማና ቲያትር፣ የመልዕክት አጻጻፍ፣ ሙዚቃ፣ ታሪክ መንገር፣ ውዝዋዜና አቋቋም፣ ፎቶግራፍና ፊልም፤ ንድፍና ስዕል፤ መፈልፈልና ቅርጽ፣ መፋቅና መጥረብ፤ ሥነ-ህንጻና የቅጥር ውበት፤ ቤት ውስጥን ማስዋብ፤ ጥልፍ፣ ሽመናና ስፌት፤ ሸክላ ስራ። መኳኳልና መሸላለም፤ የጌጣጌጥ ስራ የመናገርና የመግለጽ ጥበብ፤ የህዝብ ግንኙነትና የመገናኛ ብዙሀን ሥራዎች፣ ጋዜጠኝነት፣ የፋሽን ትርኢት፣ . . . በሙሉ ኪነጥበብ ማዕቀፍ ውስጥ ሊካተቱ የሚችሉ የሙያና የስልጠና ዘርፎች ናቸው።

የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን፤ ኪነጥበብና ዓለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከዓለም ይልቅ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል እምቅ የኪነ-ጥበብ መዝገብና ሀብት ይዛለች። በውበት ፈጣሪነት እጹብ ድንቅ የሆነ ችሎታ ያለው እግዚአብሔር አምላክ የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው። ተበልቶ የማይጠገበው የእግዚአብሔር ውብ ቃሉ የቤተ ክርስቲያን መመሪያ ነው። ከእግዚአብሔር የተነገረን የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ የሆነው እግዚአብሔርን መፍራት በምዕመኑና በቤተ ክርስቲያን የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች ዘንድ አለ [ኢዮብ 28፡28]። ሙያው የሚፈልጋቸው ዲሲፕሊኖች ደግሞ ከዓለማውያን ይልቅ በክርስቲያኖች ዘንድ ስለሚገኝ ቤተክርስቲያንን ለኪነጥበብ መተግበሪያ አመቺ ስፍራ ያደርጋታል። ታዲያ ምንድነው የሚቀረን? ሙያውን ዋጅተን በቤተ ክርስቲያን በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል።

በአሁኑ ወቅት ኪነጥበብ በዓለም ውስጥ ያለአግባብ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ነው። ብዙዎቹ የኪነጥበብ ዘርፎች በጠላት ዲያቢሎስ ይዞታ ስር ሆነው ትውልዱን እያረከሱ ወደ ሲኦል የሚያደርገውን ጉዞ በድምቀት እያጀቡት ናቸው። ለምሳሌ ሙዚቃው ለዘፈን፤ ስዕልና ቅርጻቅርጹ ለጣኦት ማስመለኪያ፤ ፊልሙና የፋሽን ትርዒቱ ለዝሙት ንግድና በዚህ አለም ለሚገኝ ክብር ማግበስበሻ እየዋለ ነው። የኪነ-ጥበብ ሙያዎች በአገራችንም ሆነ በውጪው ዓለም የእግዚአብሔርን መንግስት ለማስፋት ከሚሰጡት ጥቅም ይልቅ ለዓለም የሚሰጡት ግልጋሎት ይጎላል። በዚህም ምክንያት ብዙዎቹ የኪነ-ጥበብ ሙያዎች በዓለም ተወርሰው ለእግዚአብሔር ክብር መዋል የማይችሉ እስከሚመስለን ድረስ ዓለምና ገዢዋ የሰውን ልጅ ለማታለያ ዓላማ በባለቤትነት ወርሰው ይዘውታል። የአገራችንንም ባህል አሳድፈውታል።

የኪነ-ጥበብ ውጤቶች የክርስቶስ ኢየሱስን ወንጌል ለፍጥረት ሁሉ የምናደርስባቸው ሁነኛና ውጤታማ ዘዴዎች ናቸው። ለሰው ጥልቅ ስሜት ቅርብ በመሆናቸው በአቀራረባቸው ሰዎችን የሚማርኩት የኪነ-ጥበብ ሥራዎች የክርስቶስ ኢየሱስን ወንጌል በዚህ ትውልድ መካከል በቀላሉና ልብ በሚደርስ መልኩ ለመንገር ተመራጭ ናቸው። የኪነ-ጥበብ ውጤቶች በእግዚአብሔር ቃልና በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ሲሠሩ በጌታ ቤት ያለነውን ካለንበት የዛሬ ክርስትናችን እልፍ አድርገው አዲስ መረዳት ውስጥ ሊያስገቡን የሚችሉ መሳሪያዎች ናቸው። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እስከ ዛሬ ድረስ የተከናወኑት የኪነ-ጥበብ እንቅስቃሴዎች እጅግ አበረታች ውጤት ያስገኙ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። በበቂ ዝግጅት በስፋት ቢከናወን ኪነጥበብ ብዙ ፍሬ ማፍራት የሚቻልበት መስክ መሆኑንም አመላክተዋል። ሙያዎቹን ዋጅቶ ለጌታ ክብር ማስገዛት ከክርስቲያን ባለሙያዎች የሚጠበቅ የመጀመሪያው ተግባር ነው። ባለሙያዎች ከዓለምና ከዓለማውያን ተጽእኖ ውጭ እንደየዝንባሌአቸው የሚሰለጥኑበትና እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በነጻነት ተሰጥኦአቸውን ለእግዚአብሔር ክብር የሚያውሉበት ሥርአት በቤተክርስቲያን መፍጠር ያስፈልጋል። ህጻናት በኪነጥበብ ሙያ ውስጥ ሲያድጉ የግንዛቤና የአመለካከት አድማሳቸው ይሰፋል። የኪነ-ጥበብ ሥራዎች ሰዎችን ከእግዚአብሔር ቤት እያስኮበለሉ ማስወጣታቸው ቀርቶ ሰዎች ከዓለም ኮብልለው ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚመጡባቸው ሁነኛ መሳሪያዎች እንዲሆኑ ያስፈልጋል። መንፈሳዊ መረጃዎች ከአንዱ ወደ ሌላው፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ በኪነ-ጥበብ ሙያ እየተከሸኑ መተላለፍ አለባቸው። የኪነ-ጥበብ ሙያ ቤተክርስቲያን የተሰጣትን መለኮታዊ ተልዕኮ እንድታሳካ አጋዥ ሆኖ መቀረጽ አለበት። ኪነጥበብ የኢትዮጵያን ባህላዊ እምነት የማደስና ወደ ትክክለኛው ስፍራ የመመለስ ኃላፊነት ያለበት ሙያ ነው።

የባለሙያዎች ጥቆማ፡፡ ጌትዬ ተፈራ ከአዲስ አአበባ ዩኒቨርስቲ ሥነ-ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት በሚውራል አርት (የግርግዳ ላይ ስዕሎች) ተመርቆ ለ14 ዓመታት ያህል በባህልና ቱሪዝም መስሪያ ቤቶች በማሠልጠን፣ በጥናትና ምርምር፤ በቅርስ ጥገናና እድሳት ላይ የሠራ ወንድም ነው። በኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን በአንድ አጥቢያ ሽማግሌ ነው። ጌትዬ ከሁሉ አስቀድሞ የኪነጥበብ ሥራና ጠቢባኑ ከእግዚአብሔር የተሰጡ ለመሆናቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ አጣቅሶ ትምህርቱን እንደሚከተለው አቅርቦልናል፦

rembrandtየጽሑፍ ጥበብና የድንጋይ ጥርብ ሥራ ቀድሞ በእግዚአብሔር ዘንድ ያለ ለመሆኑ ማስረጃው እግዚአብሔር ድንጋይ አስተካክሎ ጽሑፍን በእጁ ጽፎ ለህዝቡ መስጠቱ ነው። “እግዚአብሔር ከሙሴ ጋር የተናገረውን በፈጸመ ጊዜ በእግዚአብሔር ጣት የተጻፈባቸውን ከድንጋይ የሆኑ ሁለቱን የምስክር ጽላቶች ሰጠው … ጽላቶቹም የእግዚአብሔር ሥራ ነበሩ። ጽሕፈቱም በጽላቶች ላይ የተቀረጸባቸው የእግዚአብሔር ጽሕፈት ነበረ" ዘጸአት 32፡16፤ 31፡18። ንድፍ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይሰጣል። እግዚአብሔር የማደሪያ ድንኳኑን ልክ፤ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን አይነትና መጠን በዝርዝርና በተሟላ ሁኔታ ነው ለሙሴ ያሳየው። “በመካከላቸውም አድር ዘንድ መቅደስ ይስሩልኝ፤ እኔ እንደማሳይህ ሁሉ፤ እንደ ማደሪያው ምሳሌ፤ እንዲሁ ሥሩት" ዘጸአት 25፡8-9። ልጁ ሰለሞን የሚሰራውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ እግዚአብሔር ራሱ ለንጉስ ዳዊት በዝርዝር በጽሑፍ አሳውቆታል። “ዳዊትም፦ ‘የሥራውን ሁሉ ምሳሌ አውቅ ዘንድ ይህ ሁሉ በእግዚአብሔር እጅ ተጽፎ መጣልኝ’ አለ" 1ዜና 28፡19። እግዚአብሔር ባለሙያዎችን ከሚያስፈልጋቸው ዕውቀትና ችሎታ ጋር አዘጋጅቶ ለአገልግሎት ይለያል። “እግዚአብሔርም እነሆ ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ እይ ከይሁዳ ነገድ የሚሆን የሆር የልጅ ልጅ፤ የኡሪ ልጅ ባስልኤልን በሥሙ ጠርቼዋለሁ። በሥራ ሁሉ ብልሀት በጥበብም፣ በማስተዋልም በእውቀትም የእግዚአብሔርን መንፈስ ሞላሁበት። የጥበብን ሥራ ያስተውል ዘንድ በወርቅና በብር በናስም ይሠራ ዘንድ ለፈርጥ የሚሆነውን የዕንቁ ድንጋይ ይቀርጽ ዘንድ፤ እንጨቱንም ይጠርብ ዘንድ፤ ሥራውንም ሁሉ ይሠራ ዘንድ። እኔም እነሆ ከእርሱ ጋር ከዳን ነገድ የሚሆን የአሂሳሚክን ልጅ ኤልያብን ሰጠሁ፤ያዘዝሁህን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ በልባቸው ጥበበኞች በሆኑት ሁሉ ጥበብን አኖርሁ" ዘጸአት 31፡1-6። በእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እግዚአብሔር ራሱ ጥበበኛ፤ ጥበብንም የሚሰጥ እርሱ መሆኑን እንረዳለን። ከዚህ በተጨማሪ እሱ የሚሰጠንን ጥበብና እውቀት ለትዕዛዙና ለክብሩ ለሆኑ ነገሮች እንድንጠቀምበት ያዛል።

የሥዕልን ጥበብ እግዚአብሔር በሚከብርበትና እንደ እርሱ ፈቃድ በሆነ መልኩ መሥራትና ጥቅም ላይ ማዋል እንችላለን። ሥዕል በቀላሉ ገላጭና አመላካች፤ ከጽሑፍና ከንግግር ይልቅ መልዕክትን ለማስተላለፍና ለማስተማር የተሻለ አቅም ያለው በመሆኑ በዘመናት መካከል የሥነ መለኮትን ትምህርት ለማስተማር በሥፋት ጥቅም ላይ ውሏል። ከእነኚህ መካከል የሊዮናርዶ ዳቬንቺና የሚካኤል አንጀሎ ስዕሎችን መጥቀስ ይቻላል። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነትና፤ መንፈሳዊ መረዳቶችን አጉልቶ ከማውጣት አንጻር በሥፋት የሚጠቀሰው እ.ኤ.አ. ከ1606 ዓ.ም. እስከ 1669 ዓ.ም. የኖረው ኔዘርላንዳዊው ሬምብራንት ነው። ሬምብራንት ቀለም ቅብን፤ ጭረትን፤ ብርሃንና ጥላን ለሥዕል ሥራዎቹ በሥፋት የሚጠቀም ሲሆን በተለይ በጨርቅ ላይ በሚሰራቸው ህትመቶቹ ይታወቃል። ከሥራዎቹ መካከል ሙሴ ጽላት ሲሰብር (1659ዓ.ም.)፦ ሙሴ ከእግዚአብበሔር የተሰጠውን ጽላት በቁጣ ከእጁ ሲጥለው የሚያሳይ (ዘጸአት 32፡19)፤ የብልጣሶር ግብር (1635ዓ.ም.)፦ የባቢሎኑ ንጉስ ብልጣሶር ታላቅ ግብዣ አዘጋጅቶ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ እቃዎች ጥቅም ላይ ይውሉ ዘንድ ባልተፈቀደበት ቦታ በመጠቀሙ ምክንያት አረከሳቸው። በዚህም እግዚአብሔርን ባለማክበሩ ከእግዚአብሔር የተላከች የሰው ጣት በግርግዳው ላይ ወጥታ በአረማይክ ቋንቋ “ማኔ፣ ቴቄል፣ ፋሬስ” ብላ ስትጽፍ የሚያሳይ (ዳንኤል 5፡6) ሦስቱ መስቀሎች (1653ዓ.ም.)፦ የክርስቶስ ኢየሱስንና በቀኝና በግራው አብረውት የተሰቀሉትን ሰዎች ስቅለት የሚያሳየው የህትመት ሥራው (ሉቃስ 23፡32) የሚጠቀሱት ናቸው። በቤተክርስቲያን ያለውን ገሀድ እውነት በሥዕል ማሳየት ይቻላል። በአዲስ አበባ ሥነጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ከ1984 ዓ.ም ተመራቂዎች አንዱ የሆነው ወንድም ቴዎድሮስ አድማሱ ለመመረቂያው ስሎ ያቀረበው ሥዕል ቤት የሚበረብሩ ወታደሮችንና ተገነጣጥሎ የወደቀ አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የመሳሪያ አፈ ሙዝ ተደቅኖበት ያሳያል። ይህንን ሥዕል የተመለከተ ሰው ሌላ አስረጂ ሳያፈልገው በዘመነ ደርግ በቤተክርስቲያን ላይ የደረሰውን ስደት በቀላሉ መገንዘብ ይችላል።

ይሁን እንጂ አንድ የሥዕል ሥራ ከሚያስተላልፈው መልዕክት ባለፈ ለሥዕሎቹ የሚኖረን የፍቅር፤ ወጣ ያለ አክብሮትና በልብ ውስጥ የተለየ ሥፍራ የመስጠት ዝንባሌ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት። ሥዕሎቹ የማንም ይሁኑ የማን፤ የቱንም ያህል ይዋቡ ከብሩሽ፤ ከጨርቅና ከሸራ ወይንም ከሌላ ቁስ ተሰርተው በፎቶ ኮፒ ማሽን አልያም በሌላ ዘዴ ተባዝተው እኛ ጋር የደረሱ መሆናቸውን እንዳንዘነጋ። የአሳሳል ጥበቡን ማድነቅ የአባት ነው። ይህንን ይመስል ነበር ብለው ወቅቱንና ሁኔታውን ከማሳየት በቀር ስዕሎቹ የተሳለውን ተክተው በልባችን ውስጥ ስፍራ ሲይዙ መንፈሳዊ ነገራችንን ልንመረምር ይገባል። ጠላት ሊያጠቃን ሸምቆ የሚጠብቀው ለተዋቡ ነገሮች በቀላሉ የሚሸነፈውን ደካማ ጎናችንን ስለሚያውቅ ነው። የሥዕሎቹን ውበትና የመወከል አቅማቸውን ብቃት ተመልክተን ልንስማቸው፣ ልንሳለማቸው፣ ልናወጋቸው . . . ከዳዳን ክፉው መሹለኪያ ቀዳዳ አግኝቶ ወደ ልባችን ለመግባቱ ምልክቶች ናቸው። መረሳት የሌለበት የአምላካችን ጽኑ ትዕዛዝ አለ፦ “በላይ በሰማይ ካለው፤ በታች በምድር ካለው፤ ከምድርም በታች በውኃ ካለው የማናቸውንም ምሳሌ፤ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ፤ አትስገድላቸው፣ አታምልካቸውም" ዘጸአት 20፡4-5። ሥዕላሥዕሎችን ማሽሞንሞን፤ ማጠን፤ መሳምና መሳለም ከጣዖት አምልኮ ጋር ዝምድና ያለው እግዚአብሔር የሚጠላው ተግባር ነውና ከዚህ አይነቱ ልምምድ ፈጥነን ልንርቅ ይገባል።

ሠዓሊያን፣ ቀራጽያን ሌሎችም የኪነጥበብ ባለሙያዎች እንደ ሌላው ሰው ሁሉ ክርስቶስ ኢየሱስ የሞት ዕዳ ጽሕፈታቸውን ሰርዞ የዘላለምን ህይወት ሊያወርሳቸው ሞቶላቸዋል። በክርስቶስ ኢየሱስ አምነው በእግዚአብሔር ልጅነት በተሰጣቸው የከፍታ ደረጃ መመላለስ ይገባቸዋል። በሥራዎቻቸውም የእግዚአብሔርን መንግስት ምሥጢር ለፍጥረታት ሁሉ መግለጥ ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ ከሚጠፋ ዓለም ጋር ሊጠፉ የተገቡ ሥራዎቻቸውን እያመረቱ እነሱም ጠፍተው እንዳይቀሩ ሳይውሉ ሳያድሩ ማንነታቸውንና ጊዜአቸውን ከተቆጣጠረው የአዕምሮ መጠበብና የእጅ ሥራቸው ለአፍታ ያህል እረፍት ወስደው መንገድም፣ እውነትም፣ ህይወትም ከሆነው ከክርስቶስ ኢየሱስ ተርታ ሰልፋቸውን ያስተካክሉ። ቤተ ክርስቲያን ይህንን ለመሳሰሉት የሙያ ዘርፎች ሥፍራ መስጠት፤ በጌታ ቤት ላሉት ባለሙያዎች ጆሮዋን ማዋስ ይገባታል። ሙያውንና ሙያተኞችን በክርስቶስ ኢየሱስ ደም ዋጅታ በቅዱስ መንፈሱ ቀድሳ ለወንጌሉ ሥራ የምታውልበትን አዲስ አተያይ በመሪዎቿ ዘንድ ማንሸራሸር፤ ዕቅድ መተለምና ሳትውል ሳታድር ወደ ተግባር መሸጋገር ይጠበቅባታል።

ያሬድ ተሾመ ገጣሚና የቲያትር ጥበባት ባለሙያ ነው። “ሞኙ ምስጢረኛ”፣ “ፍለጋ” የተሰኙ የግጥም መድብሎችን አሳትሟል። ያሬድ አንድ ግጥሙንና ኪነጥበብ ለወንጌል ሊኖር የሚገባውን ግልጋሎት አስመልክቶ ቀጥሎ ያለውን ሀሳብ አካፍሎናል፦

የመስታወት ገበያ፡፡ እንዲያ ባቶቢሱ፣ በጐኑ መስታየት /  እንዲያ በመሂና፤ በጐኑ መስታየት /  እንዲያ ‘ዳልተጋፋን፤ መልካችን ለማየት /  እንዲያ 'ዳልተሳልን፤ እሱኑ ለመግዛት /  ቀን ወጣለትና፣ መስታወት ረክሶ /  አሁን ጥንቡን ጥሎ፣ አገናው ቀንሶ /  አይን ኩል ተኩሎ፣ ፀጉር ተተኩሶ /  ሁሉ አበጣሪ ሁሉ ባለ ጋርሶ /  ሁሉ ሆነ መልከኛ፣ ሁሉ ከማን አንሶ /  ጉድፉን ተመልካች አቁሞ ምሰሶ።  [ሰኔ 2000]

ኪነጥበብ ለዛ ባለው አቀራረቧ ዓለምንና ዓለማውያንን የመማረክ ጸጋ አላት። ኪነጥበብ የእግዚአብሔርን ምስጢር እንድናውቅ ከላይ የተሰጠን ችሎታ ነው። ኪነጥበብ ለተለመደው የወንጌል ሥብከት አማራጭ፣ የሚስብና ማራኪ ዘዴ ሆኖ መቅረብ ይችላል። በምንሰራቸው የሚስቡ የኪነጥበብ ሥራዎቻችን የሰዎችን ትኩረት ማግኘት እንችላለን፤ ቀጥሎም በምንኖረው ኑሮና በምንናገረው መልዕክት ሰዎችን በወንጌል እንገዛለን። የኪነ-ጥበብ ሥራዎች ቤተክርስቲያን ወደ ዓለም ከምትዘረጋቸው እጆች ዋናዎቹ ሆነው መቀረጽ ይችላሉ። ወንጌል በኪነጥበብ ተሰብኳል። ክርስቶስ ኢየሱስ በርካታ ትምህርቶቹን በምሳሌ አቅርቧል። የተለያዩ የትረካ ሥልቶችንም ተጠቅሟል። መጽሐፍ ቅዱስ የተሳካለት የሥነ-ጽሑፍ ሥራ ነው። የሥነ-ጽሑፍ ሥራዎች በውበታቸውም ሆነ በአቀራረባቸው ሰዎችን የማዕዘን ራስ ወደ ሆነው ወደ ክርስቶስ ኢየሱስ የማዳን ሥራ የሚጠቁሙ ከሆነ የመንፈሳዊነታቸው የመጀመሪያው መስፈርት ነው። ተራው ሰው ዕለት ዕለት ከሚኖረው ኑሮ ላይ በመነሳት፤ ሁሉም የሚነጋገረውንና የሚያግባባንን ቋንቋ በመጠቀም፤ በገሀድ የሚታየውን እውነት ሳንክድና ሳንሸሽ እጅግ ጥልቅ የሆነ መንፈሳዊ መልዕክት ማስተላለፍ ይቻላል - በኪነጥበብ። ዓለም ከነሥርዐቷ ምንኛ ፍትህ አልባ እንደሆነች ለሌሎች የምናሳውቅበት በምትኩም የእግዚአብሔርን መንግስት ውበትና ደስታ የምንገልጽበት፤ አለምና ዓለማውያንን የምንወቅስበት፤ ዘላለምን በሕይወት ለመኖር ዘዴው በክርስቶስ ኢየሱስ አዳኝነት ማመን ብቻ እንደሆነ የምንመሰክርበት፤ ትውልድን ከሚሄድበት የተሳሳተ ጎዳና እንዲመለስ የማንቂያ ደወል ማቃጨል የሚቻልበት፤ መርገምን ሊያሰብር የሚችል መረዳት ውስጥ ገብተን ሌሎችን የምናስገባበት ውጤታማ ዘዴ ኪነጥበብ ነው። ይህ ደግሞ ለኪነጥበብ የተሰጠ ጸጋ ነው። በኪነጥበብ ሥራዎች ውስጥህን ትገልጻለህ። በኪነጥበብ ራስህን ትተህ የሌሎችን ጩኸት መጮኽ ትችላለህ። በውበት ውስጥ የዚህን ዓለም አላፊነትና ከንቱነት ማንጸባረቅ ትችላለህ። የክርስቲያንም የዐለማዊም የጋራ መለኪያ የሆነውን ሞራልና ግብረገብ መንፈሳዊ መነሻቸውን በማጉላት ተቀባይነታቸውን ታጠናክራለህ። የዘመኗ ቤተክርስቲያን ኪነጥበብን በተገቢው መጠን ጥቅም ላይ ስታውለው አትስተዋልም። ኪነጥበብን ከዓለም መማረክና ወደ ሥፍራው መመለስ ያስፈልገናል።

ቤተክርስቲያን በተለምዶው እየሄደችበት ባለው ባህላዊ መንገድ ብቻ ፍልሚያውን መምራት የውጊያው ስትራቴጂ ከመኸሩ ብዛት ጋር እንደማይጣጣም ያሳየናል። በዚህ ረገድ ብዙ እየተሠራ አይመስለኝም። ቤተክርስቲያን ከለመደችው አካሄድ ጎን ለጎን ኪነጥበብን እንደ ሌላ አማራጭ የወንጌል መልዕክት ማስተላለፊያ መንገድ ጥቅም ላይ ማዋል ይጠበቅባታል፡፡ ቤተክርስቲያን የላቀ ብቃት ያላቸውን የኪነጥበብ ሥራዎች እየያዘች ወደ ሰፊው አውድ መዝለቅ አለባት። እውነቱ የእግዚአብሔር ቃል ነው። ቃሉ በእጃችን ነው። ውበቱንና ህያውነቱን አጉልተን በሥነ-ግጥም፤ በፊልም፣ በቲያትር . . . ይዘን ልንወጣ ይገባል።

ወንድም ከበደ መርጊያ የፊልም ባለሙያ ነው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የብዙኃን መገናኛ መምህር ሆኖ አገልግሏል። አሁን “የመዳን ቀን” የተሰኘ መንፈሳዊ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ያቀርባል። ከበደ መገናኛ ብዙኃንን ለወንጌል ሥራ ለማዋል ሊደረግ የሚገባውን ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንደሚከተለው ይጠቁመናል፦

ሚዲያ ስንል በርካታ ነባርና አዳዲስ የብዙኃን መገናኛ ዘርፎችን፦ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ ሕትመት፤ የጥበብ ዘርፎች፦ ሥነጽሑፍ፣ ሙዚቃ ወይንም ዝማሬ፣ ድራማ፣ ፎቶግራፍና ፊልም፤ እንዲሁም ዘመኑ ያፈራቸው አኒሜሽንና ኢንተርኔት ብሎም እዚህ ውስጥ ያልተጠቀሱትን ሌሎች የመረጃ ማስተላለፊያ ዘዴዎችንና አውታሮቻቸውን ያጠቃልላል። በእነኚህ የሙያ ዘርፎች ረገድ ቤተክርስቲያን ተልእኮዋን እንድትፈጽም ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት የሚዲያ ጥምረት መመስረት ግድ ይላል። ጥምረቱ የመቋቋሙ አስፈላጊነት ያለንን ዕውቀት፣ ልምድ፣ ገንዘብና መሣሪያ በመጋራትና በመደጋገፍ የእግዚአብሔርን መንግስት ሥራ ለማፋጠን የሚካሄደውን ጥረት ማገዝ፤ የሚዲያንና የብዙኃኑን ሥሜትና ትኩረት መሳብና ከተፈለገው ዓላማ ጎን እንዲቆሙ ለማድረግ ያለውን ኃይል ለወንጌል ትምህርትና ስርጭት በሙላት መጠቀም ማስቻል ነው። በተለይ ህጻናትና ወጣቶች በእግዚአብሔር እምነትና ፍቅር ውስጥ እንዲያድጉ የሚረዱ፤ በአሁኑ ጊዜ ቴሌቪዥንና ኢንተርኔት የሚያራግፉባቸውን የማደናገሪያ ፊልሞች የሚተኩ ፕሮግራሞችን ተረባርቦ ማዘጋጀት ያስፈልጋል። የሚዲያ አገልግሎቶችን በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት በዲኖሚኔሽን ደረጃ፤ በክልል፣ በአጥቢያዎች፣ በሕብረቶች፣ በገጠርና በከተማ በዓለም አቀፍ ደረጃ አስተባብሮ አሁን የተጀመረውን ራዕይ ማሳደግ ያስፈልጋል። በሚዲያ አገልግሎት ውስጥ የሚያገለግሉ ወገኖችንም ሙያዊ ብቃት ማሳደግ። የዚህ ቅንጅት ግብ መሆን ያለበት ሙያዊ መስፈርቶችን ያሟሉ ስብከቶችን፣ ትምህርታዊ ፕሮግራሞችን፣ ቃለ መጠይቆችን ወዘተ፤ በተንቀሳቃሽ ምስል ወይንም በቪዲዮ፤ በአኒሜሽን፣ በፎቶግራፍ፣ በድምጽና በጽሑፍ ቀርጾና አቀነባብሮ በዲቪ፣ በዲቪዲ፣ በቪሲዲ፣ በሲዲ በተፈላጊው ፎርማት ማዘጋጀት። ይህንን ውጤት ለማምጣት መጋቢዎች፣ ወንጌላውያን፣ መምህራን፣ ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ መዘምራን . . . ሌሎችም አገልጋዮች ሰዎችን በወንጌል ለመድረስ በሚያቅዱበት ጊዜ ራዕያቸው ላይ በመመስረት መወያየት፣ በየደረጃው ጥናት ማድረግ፣ መጸለይ፣ ለአሠራር አመቺና ከአገልግሎቱ ባህርይና ሊደረሱ ከታቀደላቸው ወገኖች አንጻር አመቺ የሆኑትን የመገናኛ ብዙኃን አይነቶች መምረጥን ይጠይቃል። ክርስቲያን ባለሙያዎች የሙያ ሥነምግባርን አሟልተው መገኘት፤ መንግስት ለሚያወጣቸው ህጎች ተገዢ ሆኖ መገኘት፤ ከሁሉ በላይ በቅድስና ማገልገልን መርህ አድርገው መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል። በሚገኙት የሥልጠና እድሎች እራሳቸውን ከዘመኑ ቴክኖሎጂዎች ጋር ማስተዋወቅም ተወዳዳሪ ሆኖ ለመስራት ይጠቅማል። ውጤቶቹን ለሬዲዮና ቴሌቪዥን፣ ለህትመት፣ ለግለሰቦች በነፍስ ወከፍ፣ በድረ ገጾች በማሰራጨት የወንጌል ሥርጭትን ማገዝ ይቻላል።

 ስዕሉ፦ በኔዘርላንድስ ተወላጁ ሬምብራንት፤ [1598 ተወለደ – 1661 ዓ.ም ሞተ፤ 1645 ዓ.ም. ተሳለ]