መታመን ብርቅ ሲሆንና ኪሳራዎቹ
የመጨረሻው ክፍል


መታመን እንደ አለመታመን በቃልና በድርጊት ይገለጻል። መታመንና አለመታመን ወዳጅነትና አገርን ያለማል ወይም ያፈርሳል። እምነት እንዲጣልበት ከፈለገ ሰው፦ በስውር የሚያየውን እግዚአብሔርን መፍራት። ሕግ የሚያስከትለውን ቅጣት መፍራት። ኃፍረትን ማወቅ። የዛሬን ብቻ ሳይሆን የነገን ማሰብ ይኖርበታል። ሕግ ግን ለሁሉም እኩል ካልሠራ፣ በሁሉም ላይ እኩል ተጽእኖ ካላሳደረ የማኅበረሰብን ደጅ ምስጥ አንክቶ ሊበረግደው ነው። እምነት ማጉደልና ቀምቶ ማደር ሲለመድ፣ እምነት ያጎደሉ አደባባይ መውጣት ሳያስፈራቸውና ሳያሳፍራቸው ሲቀር፤ እምነት ያጎደሉ መልሰው መካሪ ሲሆኑ። ያልታመኑ ተሹመው የታመኑ ሲከሥሩ። መታመን ብርቅና መሳለቂያ ሲሆን። የአምላክ ፍርዱ በደጅ ነው። ፍርኃትና ኃፍረትን ሲጥል ክቡር ሰው እንደ እንስሳ ይሆናል። ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ሊደርስ ይችላል፤ ከፍተኛ ዕውቀት ሊገበይ ይችላል፤ ባለሥልጣን ሊሆን ይችላል። ፍርኃትና ኃፍረትን ስለጣለ ግን ሰብአዊነቱን ተቀምቷል፤ ይህ ሰው ክብር የለውም።

ለሰው አክብሮት በሌለበት መታመን ሊኖር አይችልም። አክብሮት የሌላኛውን ሰው አሳብ ለመስማትና እንዳስፈላጊነቱ ለመቀበል፣ የራስን ለማለዘብና ለመተው መፍቀድን ይጨምራል። ስላልተስማማ ብቻ ግለሰቡና አሳቡን ውድቅ ማድረግ በደል ነው። የሌላውን አሳብ ሳያከብር ሌሎች የርሱን እንዲያከብሩለት መጠበቅ ሞኝነት ነው። መታመን በውዴታ እንጂ በግዴታ አይመሠረትም።

አንድ ሰሞን አንዲት ሰው ኢትዮጵያ አየር መንገድ መንገደኛ መሳፈሪያ ወለል ላይ አምስት መቶ ብር ወድቆ አግኝታ አስረከበች ተብሎ እንደ ጉድ ሲወራ ከረመ። “ይቺ ቂል፣ ይቺ ጴንጤ ሳትሆን አትቀርም” ሲሏት፣ “ኧረ እግዜር ይባርካት” ሲሏት። ዛሬ መታመን ብርቅ ሆኗል። አንድ ነገር ግልጽ እናድርግ፦ አገርና ሕዝብ የሚጠበቀው እርስ በርስ በመተማመኑ መጠን እንጂ በኢኰኖሚ እድገት ብቻ አይደለም። ካልተማመነ አሳቡን በነጻነት መግለጽ ይፈራል፤ አሳቡን መግለጽ ከፈራ አይሳተፍም፤ ካልተሳተፈ አስተዋጽዖው ይጓደላል፤ ከተጓደለ የአገር ጉዳይ የጥቂቶች ጉዳይ ይሆናል። “በመካሮች ብዛት ግን ደኅንነት ይሆናል …ምክር ከሌለች ዘንድ የታሰበው ሳይሳካ ይቀራል፤ መካሮች በበዙበት ዘንድ ግን ይጸናል፤ ምሳሌ11፡14፤ 15፡22” በበለጸጉና በደኸዩ አገራት መካከል የሚታየውን ልዩነት፣ በመተማመን፣ በሕግ የበላይነትና መከበር መጠን ማስረዳት ይቻላል። የመሪ ብቃቱ መተማመንን መፍጠሩ፣ ተጠያቂነትን ማጽናቱና ያንኑ ለሚመራው ተግቶ ማስረዳቱ ላይ ነው። የሕዝብ ቅርስ ምዝበራ ሲንሠራፋ፣ ለሚመዘብረውና ለሚመዘበረው ሁለት ዓይነት ፍትኅ ሲታደል፣ አለመተማመን ሥር ሰዷል ማለት ነው። ዳኝነት የርሱ ነውና፣ እግዚአብሔር ለተገፋው ብይን የሚሰጥበት ሰዓት ተቃርቧል።

የቀድሞ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል አንድ ጊዜ እንዲህ አጫወቱኝ፦ አንድ ሰው ከአራዳ ንግድ ባንክ ረብጣ ብር ወጪ አድርገው መንገድ እንደጀመሩ ብሩ ከኪሳቸው ሾልኮ ይወድቅባቸዋል። ከኋላቸው ይጓዝ የነበረ መንገደኛ ያነሳና፦ “ሼኪ! ሼኪ!” ብሎ ይጣራል። ቆም ሲሉ፣ ደርሶ ብሩን እንዳ-ለ ያስረክባቸዋል። “ሼኪም” ረብጣውን ኪሳቸው ይከቱና ጉዞአቸውን ይቀጥላሉ። መንገደኛው ጉርሻ ጠብቆ ኖሮ፣ “ምነው ሼኪ፣ ትንሽ እንኳ አይሉኝም?” ቢላቸው፤ “ምን ትንሽ እልሃለሁ፣ አላህ ሁሉን ሰጥቶህ አልፈልግም አልከው እኮ” አሉት አሉኝ። የሼኪን መልስ ሳይሆን የመንገደኛውን ታማኝነት እናስተውል።

እንኳንስ ሌላውንና ራሱን የሚጠረጥር አለ። መታመን እንደ አለመታመን የሚለመድ ባህርይ ነው፤ ደጋግሞ በማድረግ ውስጥ ልማድ ይሆናል። መታመን የመንፈስ እርካታና ቀና ብሎ መሄድን ያጎናጽፋል፤ አለመታመን ደግሞ የቅጣት ስጋትና አንገት ማቀርቀርን፤ ለልጅ ልጅ የሚተርፍ አሳርና ኃፍረትን። የሌባ ልጅ ቸርነቱ እንደ ተጠረጠረ ይኖራል። መታመንና አለመታመን ከቤት ይጀምራል። በትምህርት ቤት ይኰተኰታል። ትምህርት ቤቶች ከቀለሙና ከዕደ ጥበቡ ጋር ምን ዓይነት ሥነ ምግባር በማስተማር ላይ ይገኛሉ? መምህራን በጎ ሥነ ምግባር ይታይባቸዋል? የፈተና ውጤትና ዲፕሎማ የሚሠጠው በሃቅ ተሠርቶ ወይስ በዘመድና በአልባሌ መንገድ? መታመን ደግሞ በሥራ ዓለም ይደረጃል። ቅጥር እድገትና ደመወዝ ጭማሪ የሚገኘው በትጉ ሠራተኛነት ወይስ ከአለቃ ጋር በመመሳጠርና በመዛመድ? መተማመን ደግሞ በቤተ አምልኮ ይበለጽጋል። አማንያንና የቤተ እምነት መሪዎች ምን እየዘሩ ይሆን?

በበለጸጉ አገሮች ዕለታዊ ጋዜጦችን በየመንገዱ ከቆሙ ሣጥኖች ገዝቶ ማንበብ የተለመደ ነው። አብዛኛው አንባቢ አራት ስሙኒ ያክል ጨምሮ ከክምሩ ላይ አንዲት ጋዜጣ ብቻ ይወስድና ሣጥኑን መልሶ ይዘጋዋል። ይኸ የሚያሳየው አገራቱ በህግ አምላክ የሚተዳደሩና፣ መታመንም የዜግነትና የማኅበረሰብ መሠረታዊ እሴት መሆኑን ነው። በቃል ወይም በጽሑፍ ይዋዋላል፣ ይገበያያል። ዛሬ በአገራችን እንኳንስ በቃልና፣ በፊርማም መተማመን እያቃተ፣ ፊርማ በፊርማ፣ ፊርማ በቃል እየተሻረ ነው። አንባቢ ከሣጥኑ ውስጥ አስር ጋዜጣ ቢወስድስ ኖሮ? ጋዜጣ አቅራቢው ከሠረ ማለት ነው። እንዳይከሥር ዘብ ቀጥሮ ማቆም ወይም ስውር ካሜራ መትከል ይኖርበታል። ሥራ ፈትቶ ፍርድ ቤት ሊጓተት ነው። ለጠበቃ ወጪ ሊያወጣ ነው። ወጭውን ማን ይሸፍን? ጋዜጣ አንባቢ። አራት ስሙኒ የነበረ ጋዜጣ አምስት ስሙኒ ይሆናል። ሻጭ ማትረፍ ስለሚኖርበት የስፖርቱን አምድ በሦስት ስሙኒ፣ የፖለቲካውን አምድ በሦስት ስሙኒ መሸጥ ይጀምራል። ቀን ያለፈበትን በሁለት ስሙኒ መሸጥ ይጀምራል። ከአቅም በላይ ይሆንበትና አንዳንዱ አንባቢ ማንበብ ያቆማል። ባያነብስ? ተሳትፎው ይገታል፤ የአሳብ ድህነት ይስፋፋል። ነጋዴ በዘበዘኝ ብሎ ዜጋ ተቃውሞ ያሰማል። መንግሥት አራት ስሙኒ ይበቃል የሚል ህግ ያወጣል። ያን የሚያስፈጽም ተቆጣጣሪ ይመድባል። ተቆጣጣሪ ትንሽ ጉርሻ ይሻል፤ አለዚያ ሻጩን በቅጣት ያስፈራራል። ሻጭ ንግዱ እንዳይቋረጥ ጉርሻ ይሰጣል፤ ያን ለማካካስ ያደረ ጋዜጣ ከዕለቱ ጋር ያሰባጥራል ወይም ሸሽጎ በውድ መሸጥ ይጀምራል፤ የሚያጓጉ “ትኩስ ሰበር” ጉዳዮችን ማተም ይጀምራል። መንግሥት “ሰበር ዜና” ማተም “ሽብር” እንዳያስነሳ ጋዜጠኛውን ያስራል፤ ጋዜጣውን ያግዳል። አንባቢውም አሳቡን የሚገልጽበትን ስውር ብልሃት ይፈጥራል። መንግሥት ነጭ ለባሽ ያሠማራል። የሕዝብን ጉዳይ ከሕዝብ መደበቅ ይጀምራል። ፍርኃት ይነግሣል። አለመታመን ማህበራዊ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊና መንፈሳዊ ቀውስ ያስከትላል ማለት ነው። በሌላ አነጋገር፣ የህግ ብዛት፣ መታመንን አያስገኝም። ዜጋ ድምጹ ሲታፈን፣ ብሶቱ ይገነፍላል፣ ችግሩ አይወገድም።

በአሜሪካ ቃል ሰጥቶ ካፈረሰ ወይም ከዋሸ፣ ማንነቱ ሳያግደው ህግ የሚገባውን ቅጣት ያከናንበዋል። አባቶቻችንና እናቶቻችን በእግዚአብሔር ፍርኃት ያካበቱትን ውርሳችንን “ንጉሥ አምላክ ነው” “ፓርቲ አምላክ ነው” “እግዚአብሔር የለም” በማለትና በማሰኘት፤ “ለኔ”፣ “ለክልሌ” በማለት፣ ለሌላው ያለብንን ግዴታ ችላ ብለን እየበተንን ነው። የአለመታመን ጎርፍ በህግ አምላክ አልተገደበምና ከርክሮ ሠርሥሮ የተያያዝንበትን ገመድ አላልቶታል። አለመታመን ማኅበራዊ ምስጥ ነው። ከደርግ በፊት፦ ልዑላን መሳፍንት ጪሰኛ ዘላን ባለእጅ ኋላ ቀር፤ መሪ አምልኮ ነበሩ። በዘመነ ደርግ፦ ተራማጅና አድኃሪ፣ ቡርዧና ሠርቶ አደር ተባሉ። ደርግ የሕዝቡን የእምነት ጥንካሬ ባለማጤኑ በአንድ ጀንበር “እግዚአብሔር የለም” ለማሰኘት አለመ። እግዚአብሔር ከሌለ ማን ሊኖር ኖሯል? ያኔ መልሱ፦ አብዮተኛ፤ ማዕከላዊ ኮሚቴ፤ ነጭና ቀይ ሽብር፣ ሊቀመንበሩ ነበረ። ልጅ አባቱን፣ ወንድም እህቱን አጋለጠ፤ ወዳጅ ወዳጁን አሳልፎ ሰጠ። አለመታመን፣ ፍርኃትና ጥርጥር፤ መሪ አምልኮ ነገሠ። ያ የማያልፍ የመሰለ ሳይታሰብ በአንድ ጀንበር አለፈ። ከደርግ ወዲህ፦ ብዙ አማልክት ቢኖሩህ ባይኖሩህ በየቀዬህ ተባለ። ማኅበራዊ ግዴታ የላላበት “ነፃነት” ታወጀ። አዳዲስ አማልክት ተደረደሩ። የጎሣ አማልክት። የአብዮታዊ ዲሞክራሲ አማልክት፤ የፓርቲ አማልክት፤ የትልቅነት አማልክት፤ የውጭ እርዳታ አማልክት፤ የጦር ኃይል አማልክት፤ የሽብር አማልክት፣ የዲፕሎማ አማልክት፤ የብልጽግና አማልክት፣ ወዘተ። እያንዳንዱ እንደመሰለው ለማይረቡ ለማያድኑ አማልክት አጠነ። ወጣቱና ሕጻኑ በደርግ ዘመን እንኳ በማይፈቀዱ ማኅበራዊ ጠንቆች ተለከፈ፤ ወጣቱ ባገኘው አጋጣሚ አገሩን ጥሎ ኮበለለ። ለራሳቸው እንጂ ለሕዝብ የማይገዳቸው መሪዎች በዙ፤ በሥጋ ዝምድና በጥቅም በጎሣና በሃይማኖት ተያያዙ። ዕድሜአቸውን ለማራዘም ከእውነት ይልቅ ጥላቻን መረጡ። በየዘመናቱ ተሞክሮ የከሠረ አሠራር አንሠራሩ። የዘሩትን እንደሚያጭዱ ግን አልተገነዘቡም።

ምትኩ አዲሱ