ኢየሱስ ሙዚቃ አይጠላም
ዘሪቱ ከበደ

የቤተክህነትና የዓለም ሙዚቃ በልማድ አይዋሃዱም። ሽብሸባ ለቤተክህነት ነው፤ ጭፈራ ለዓለም። በገናና ቅኝቱን ለዳዊት የገለጠለት እግዚአብሔር ነው ይባላል፤ ክራር የሰይጣን ነው፣ ወዘተ። ዓለማዊና መንፈሳዊ ፈጽሞ ይራራቃሉ ማለት ግን አይደለም። ብዙ ዓለማዊ ዘፈኖች በያሬዳዊ ዜማ ስነምግባርን የቤተሰብን ፍቅር አብሮነትን ሲያስተምሩ ኖረዋል፤ የቅኔ አወራረዳቸውና ቅኝታቸው ከብዙ ዛሬ ከምንሰማቸው “መንፈሳዊ ዝማሬዎች” ይልቅ የተዋበ ነው። ዘመናዊነት ሲስፋፋ ድንበር ደበዘዘ። ደርግ “መንፈሳዊ” ዜማዎችን ለአብዮታዊ ተግባር አዋለ። በሰማንያዎቹ መባቻ ደርግና ሶሻሊስታዊ ድንበር ፈረሰ፤ ኢንተርኔት ዓለም ምድሩን ወረሰ። ጃፓኖች ጸናጽል፣ ከበሮ፣ ክራርና በገና በኪቦርድ ጭነው ላኩልን። በአገራችን ሙዚቃና የሙዚቀኛ ልምድ ብዙ ለውጥ የታየው ከዚያ ወዲህ ነው። “አባታችን ሆይ” በተስፋዬ ጋቢሶም በቴዲ አፍሮም ተዘፈረ። ማንም ይዘምር ማን ለውጥ አያመጣም እንበል? “በይቅርታ ተቀበለኝ” መዝሙር የቴዲ አፍሮ ላለመሆኗ አጠራጠረ፣ አከራከረ፤ የጥላሁን ጎአ ገቢ እንዳልተጎዳ መገመት አያዳግትም። ይህም የደብዛዛ ዘመን ተምሳሌት ነው። እንደ ጥቁር ፈረንጆች ከመድረክ ጥግ ጥግ መዝለል መጣ። ሆሆታ እስክስታ ዳንኪራ መጣ። ሽብሸባ ጭፈራ ቀረርቶ መጣ። ዘማሪ ይከራይ ጀመር፤ ታዋቂ ዘማሪ ዋጋው አላስቀምስ አለ። ለውድድርና ለሽልማት መሠዊያ ተሠራ። ቀስ በቀስ ከዝማሬ ወደ ዘፈን ቀረሹ ተሻገረ። በዚህ መሓል ዘሪቱ ከበደ ብቅ አለች። ከሁለት ዓመት በፊት ከኢየሱስ ጋር መንገዴን አድርጌአለሁ አለች። እምነቴን በቤተክርስቲያን አልወስነውም አለች። ከዘፈን ወደ ዝማሬ ጉዞዋን አስመልክቶ ከቪኦኤ ጋር ያደረገችው ቆይታ ለውይይት የሚጋብዝና እንደ እድሜዋ ሳይሆን ጥልቅና ጠቃሚ ሆኖ ስላገኘነው በከፊል አትመነዋል። እነዚህን ጥያቄዎች እያሰብን መጠይቁን እናንብብ፦ ዝማሬና ውዳሴን ዘፈንና መዝሙርን ምን ይለያቸዋል? ዘማሪና ዘፋኝ አንዱ በሌላው ተግባር ቢሠማራ ምን አለበት? ኢየሱስ ማነው? ኢየሱስን የማይስማማው ሙዚቃ አለ? ኢየሱስ 'ምንም አይደለም' የሚለው ምን ዓይነቱን ዝማሬ ወይም ዘፈን ነው? ኃጢአት ምንድነው? መጽሐፍ ቅዱስ እንደ አንባቢው ነው? ልክ በሆነውና ልክ በሚመስለው መሓል እንዴት መለየት ይቻላል? ቃል ሳይጨመርበት በሙዚቃ ብቻ ሐዘንን፣ ደስታን፣ ፍትወትን፣ ወዘተ፣ ማነሳሳት መቻሉ ስለ ሙዚቃ ምን ይነግረናል?           - ኢትዮፕያንቸርች አዘጋጅ

“በዘመን በጊዜ”ን [እንዴት ጻፍሽው?] ይመስጠኛል በጣም ንገሪኝ ...
zerituእሱን እንግዲህ አይ ቲንክ [እንደሚመስለኝ] ወደ ሰባት ዓመት አካባቢ ነው ከጻፍኩት፣ ያኔ ኢየሱስን መከተል ስጀምር፣ ነውና የመጀመሪያው ሰሞን ላይ የገቡኝ ነገሮች ነበሩ፤ እ እ መጀመሪያ ኢየሱስን ለመከተል ስወስን ራሴን ይዤ እንደምከተለው ነበር የማስበው፤ በመጀመሪያው መረዳቴ ማለት ነው፤ ምክንያቱም ፋስኔቲንግ ነው [አስገራሚ ነው] የኢየሱስ ትምህርት ደስ ይላል፤ይወደዳል፤ ከእሱ ጋር ጊዜ ማሳለፍ፤ ግን ዋት ምን ደግሞ እንደሚጠይቅ አልተረዳሁም ነበር፤ እና ያንን መረዳት የጀመርኩበት ሰሞን ነው፤ እ እ ራስን መካድ ይጠይቃል ለካ ኢየሱስን መከተል ራስን መካድ ይጠይቃል የኔን መንገድ ብሎ የሱን መንገድ መሄድ አይቻልም፤ ኢየሱስን መከተል ማለት ደግሞ መንገድ እሱ ነው ብሎ ማመን ነው። ስለዚህ ቀላል አይደለም ያንን ማወቅ ስትመጣ፤ አንተ ዝም ብለህ አልመጣህም፤ በአንድ ቀን አልተሠራህም፤ ብዙ ነገር አልፈሃል፣ ቀለም አለህ እምነት አለህ፣ እይታ አለህ፣ ብዙ ስለራስህ የምትረዳው ነገር አለህ፤ በተለይ አርቲስት ስትሆን ደግሞ ብዙውን አስተሳሰብ እየጣልክ የራስህን መንገድ እያየህ ያልተቀደደውን እየቀደድክ ምናምን ነው የምትመጣው እና በዚያ ሥፍራ ላይ አንተ የምታየው እይታ የተሻለው እይታ አይደለም፣ ያንተ አስተሳሰብ የተሻለው አስተሳሰብ አይደለም፤ ያንተ መንገድ ምንም አይሠራም፤ በቃ ያው አስተሳሰብም ጥበብም መንገድም በዚህ ነው፤ ስለዚህ ራስንም ነገርንም ጉዳይንም መካድ ይጠይቃል የሚለውን መረዳት ልክ ሲገባኝ ነው፤ ሲገባኝ አቺቭ አላረግሁትም አሁንም አላረግሁትም፣ በየቀኑ ምን ያህል እንዳልካድኩ ራሴን ነው የምረዳው፣ ግን እ እ ፍቅር ብዬ ለጠራሁት ለርሱ ራሴን ቦታ መልቀቅ እንዳለብኝ፣ ምክንያቱም እኔን ይዤ እሱን ልከተል ብል አይሆንም፤ እየሸነገልኩት ነው የምቆየው፤ እኔን ትቼ እሱን ብከተል ግን ለኔም ለሰውም እሆናለሁ እ እ የሚለው መረዳት ሲገባኝ ነው፣ አሁንም በየቀኑ የሚሠራልኝ ዘፈን ነው በየቀኑ ይሠራልኛል፤ እና በጣም እወደዋለሁ። እ እ ብትፈቅዱልኝ፣ ለፍቅር አስተማሪ የጻፍኩት የፍቅር ዘፈን ነው።

ፍቅር አየሁና ፍቅር የጠለቀ / ፍቅር አወቅሁና ፍቅር የጠለቀ

ዓለሜ ተናጋ አቋም መሠረቴ / ስሆነው የኖርኩት እኔነት ክበቴ ...

በዘመን በጊዜ የሆንኩትን ትቼ / ይሁን እኔን ጣልኩኝ አንድ እሱን ፈርቼ

ግን ሃሳቡ፣ አሁን ያነሳሽልኝ ሃሳብ ከሙዚቃ ጋር በተለይ በኛ አገር፣ በውጭው የተለመደ ነው፤ በተለይ በኛ አገር ክላሽ ያደርጋል [ይጋጫል]፣
ዘሪቱ፣ ሊሆን ይችላል፣ ግን ምን መሰለህ፣ ኢየሱስን መከተልን የጀመርኩት ኢትስ ኢን ምዩዚክ ስቱዲዮ ውስጥ ከሙዚቀኞች ነው፣ እነ ኤልያስ እነ ኢዮብ እነ ዘካሪያስ እነ ዘሩባቤል ሲከተሉ አይቼ ነው ኢየሱስን፤ ከሰው ስለተለዩብኝ ከማቃቸው ሰዎች የተለዩ ናቸው፤ እ እ የወንድማማች ፍቅር አብሮ የመሆን ፍቅር የሚዛን ልዩነት የሕይወት ልዩነት አትራክት አድርጎኝ [ስቦኝ] ነው ወደዚያ መንገድ የገባሁት፤ ያ መንገድ ደግሞ እንድቆፍር እግዚአብሔር አለበት ብዬ የማምነውን ከልጅነቴ ጀምሮ የማምነውን መጽሐፍ ቅዱስ እንድቆፍርና መንገዱን እንዳገኝ አደረገኝ፤ ስለዚህ ያ ፍለጋ ደግሞ የእውነት እውነቱ ከእግዚአብሔር ቃል ውጪ የትም የለም፤ የእግዚአብሔር ቃል እስካሁን እንዳስተማረኝ ደግሞ ኢየሱስ ሙዚቃ አይጠላም፤ ሰዎች ደስ እንዲላቸው ይፈልጋል፤ ሰዎች አስቆዛሚ አይደለም ኢየሱስ፤ ኃጢአት ብቻ ነው የሚጠላው፤ ኃጢአት ምክንያቱም ከሥርዓቱ ይጋጫል። እና ስለሚወደን የሰው ልጆችን ሁሉ ይወዳል፤ ስለሚወደን በዚያ መንገድ እንድንባክንበት አይፈልግም። ስለዚህ በመንገዱ እንድንሄድለት ይፈልጋል፤ ኃጢአት ይጠየፋል። የሚወዳቸው ልጆቹን የሚያበላሽበትን ነገር አይፈልግም፤ ኃጢአት በቃ ጠላቱ ነው። ከዚያ ውጭ ሂ ወንትስ አስ ቱ ቢ ሃፒ፣ ደስ እንዲለን እንድንዝናና ይፈልጋል። ምግብ ሰርቫይቭ ለማድረግ [ለመኖር] ብቻ አይደለም የምንበላው፤ እንጂ በታብሌትም መቆየት እንችላለን። ኪኒን እየዋጥክ በሕይወት ለመቆየት የሆኑ ነገሮች እየወሰድክ የሆነ ፖርሽን እየወሰድክ [የተለካ መጠን እየወሰድክ] መቆየት ትችላለህ፤ ግን እንደዚያ አይደለም ሕይወት የምንኖረው፤ አይደል? ቁርሳችንን የሆነ ነገር እንበላለን በቃ፣ ደስ እንዲለን ሕይወት ስለሆነ ሙዚቃም ኢትስ ፓርት ኦፍ ዛት [የተያያዘ ነው]። ሕይወታችን ውስጥ ያለውን ነገር እንገልጽበታለን፣ እንማማርበታለን፤ እንዋደድበታለን፤ እንዝናናበታለን፤ ስለዚህ እንደሱ የሚል አላስተማረኝም መጽሐፍ ቅዱስ፤ የምከተለው ደግሞ እኔ ራሱን ኢየሱስን ነው። ተከተሉኝ ነዋ ያለው።

[ስለዚህ ሳውንድ ትራክ ነው ነው የምትዪኝ?...]
መንጠቅ ነው ከሰዎች ሕይወት ውስጥ ዜማውን ውበትን መንጠቅ ነው፤ ይኸ ደግሞ የኢየሱስ ዓላማ አይደለም፣ ሰዎችን ማዳን ሰዎችን መውደድ ነው የሱ ዓላማ በቃ፤ ስለዚህ እኔ እንደሚጋጭ ቢታሰብም፤ እኔ በተረዳሁት መንገድ እግዚአብሔር ባስተማረኝ መጽሐፍ ቅዱስ ባስተማረኝ፣ አይጋጭም፤
[ስለዚህ ወደፊት አልበም እሠራለሁ እያልሽኝ ነው?...]
ደፍነትሊ ደፍነትሊ [በርግጥ፣ በርግጥ] ማለት ፕላን አለኝ፤ ስከተል አንድ መልኩ መከተል፤ መከተል ነው፤ መከተል መከተል ነው፤ አንተ መንገድህን ሁሉ አትገልጥም እርግጠኛ የምሆንበት ፕላን የለኝም ሂጂ ባለኝ ነው የምሄደው፣ ምክንያቱም ተከታይ ነኝ እኔ አሁን መንገድ የለኝም፤ የኔ እቅድ ምናምን የለኝም ተከታይ ነኝ አሁን አልበም አውጭ ስባል ሥሪ ስባል ቫለንታይን፤ ሂጂ ዲሲ አካባቢ ያሉ ሰዎች ይፋቀሩ ስባል ጥሩ ጊዜ ያሳልፉ አዝናኚአቸው ስባል ሄጄ አዝ አዝና አዝናናለሁ ...እና እንደዚያ ነው ስለዚህ እቅዴ ውስጥ አለ ...

እስቲ ንገሪኝ ስለዚህ በቻሌንጆች [በሕይወት ትግል] ውስጥ ስለማለፍ፣ ሼር የምታደርጊው [የምታካፍዪው] ስቶሪ [ታሪክ] ካለ …
እኔ ብዙ ቻሌንጆች አልፌ [ፈተናዎችን] እንደማውቅ ነው፤ እግዚአብሔር ብዙ ረድቶኛል… ከረዳበት ውስጥ ደግሞ ቤተሰብህ በትዳር በሱ አካባቢ፣በእውነተኛ ሰዎች መከበብ፣ አንተን ራስህን የሚወድዱ ሰዎች፣ ላንተ ጥሩ ነገር የሚፈልጉ ሰዎች፣ እውነተኛ እውነት የሚነግሩህ ሰዎች፣ ስታጠፋ አጥፍተሃል የሚሉህ ሰዎች፣ ተስፋ ታደርጋለህ፣ ተስፋ በጣም ጥሩ ነገር ነው። ተስፋ ታደርጋለህ፤ እንደማታንስ ያንተ ነገር እንዳለህ፣ የታሰበልህ ነገር እንዳለ እያመንክ መንገድህን መቀጠል … የመውደቅ የመነሳት ደግሞ ህመም ቢኖርም ደግሞ ውበት አለው፤ መጨረሻ ብዙ ውበት ነው የሚያመጣው፣ ውበት ጥልቀት ያመጣል፤ ስለዚህ እሱን እየተረዳህ በብዙ ተስፋና በብዙ እምነት እንዳለፍኩ አምናለሁ፣ እና እግዚአብሔር በጣም ስለረዳኝ እንደዚያ ነው የማስበው።

ቪኦኤ [ከ13:40 ደቂቃ ይጀምሩ] ሚያዝያ 7/2008 / አቅራቢ፦ ዲጄ ፋትሱ          በቅንፍ የተደረጉ ማብራሪያዎች ተጨማሪ ናቸው።