ሌላ ኢየሱስ፥ ል ዩ መ ን ፈ ስ ፥  ል ዩ ወ ን ጌ ል

ዘላለም መንግሥቱ

በጥቂቱ ሞኝነቴ ብትታገሡኝ መልካም ይሆን ነበር፤ ቢሆንም በእርግጥ ታገሡኝ። በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፥ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፤ ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። የሚመጣውም ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክ፥ ወይም ያላገኛችሁትን ልዩ መንፈስ ወይም ያልተቀበላችሁትን ልዩ ወንጌል ብታገኙ፥ በመልካም ትታገሡታላችሁ። 2ቆሮ.11፥1-4

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን ምን እየሆነች ናት? ምን እየተመገብን ነን? ምን እየሆንን ነን? ብዬ ስጠይቅ የመጨረሻው ዘመን እየሮጠብን እንደሆነ ይታየኛል። ቤተ ክርስቲያን ሳታውቀው የበሰበሰ ፍሬ እየበላች ናት። የበሰበሰ ብቻ ሳይሆን የተመረዘ ፍሬ እየበላች ናት። ቃሉ ተትቶ የሰው ቃል እየተበላ ነው። ሌላ ኢየሱስ እየተሰበከላት፥ ልዩ መንፈስ እየተቀበለች፥ ልዩ ወንጌል እየሰማች ናት። “ሰይጣን በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት” የተባለው ይህ ቃል ሔዋን የተከለከለችውን፥ ያልተፈቀደላትን ፍሬ በመጋበዝ የጠለፋትና የጣላት ታሪክ ነው። ክፉ ሥራ እየሠራ መራራ ብቻ ሳይሆን መርዘኛ ፍሬ ያበላት ታሪክ ነው። ከፍሬውም ወሰደችና በላች፤ ዘፍ.3፥6። ለምን በላች? ፍሬው ለመብላት ያማረ፥ ለዓይን የሚያስጎመጅ፥ ለጥበብ መልካም ፍሬ ነበረ። ዛሬ ሰዎች እየቀጠፉ የሚበሉአቸው ወይም ሌሎች እየቀጠፉ የሚያቀርቡላቸው ለመብላት ያማሩ፥ ለዓይን የሚያስጎመጁ፥ ለጥበብ መልካም የሚመስሉ ፍሬዎች አሉ። መብል መሆኑን ብቻ ነው የሚያዩት፤ እና መብላታቸው ላይ ብቻ ነው የሚያተኩሩት። የሚብበላ ሁሉ ምግብ አይደለም። ምግብ ብዙ ቦታ ይከፈላል፤ ከጠቃሚ እስከ ጥቅም የለሽ፥ እስከ ጎጂና እስከ ገዳይ።

  1. አልሚ ምግብ አለ፤ ይህ ለአካል እድገትና ጥንካሬ እጅግ አስፈላጊ ነው። የተመጣጠነ ምግብ መብላት ለሰውነት፥ ለጤና፥ ለጥንካሬ፥ በጥቂቱ ደግሞ ከአካላችን አልፎ ለማይታየው ማንነታችን አንዳንድ ክፍሎችም አስተዋጽዖ ያደርጋል። እንደተቻለን ጤናማና የተመጣጠነ መብል አካላችንን እንደሚያዳብረው አውቀን ጤናማና የተመጣጠነ መብል ላይ መሳተፍ አለብን። መንፈሳዊ መብልም መንፈሳዊ ሕይወታችንን ያዳብረዋል። አልሚ፥ አጠንካሪ፥ ከጣዕሙ ይልቅ ጥቅሙ ያደላበት መብል ለነፍሳችን ተገቢዋ ነው።
  2. ምግብነት ያለው ግን ጉዳትም ያለበት ምግብ፥ አንዳንዱ ጮማነት ቅባትነት የበዛበት፥ ሌላው ስኳርነት፥ ጣፋጭነት የበዛበት ከጥርስ ጀምሮ እስከ ውስጥ ድረስ እየጣፈጠና እያጣፈጠ የሚያበላሽ ምግብ ነው፤ ግባሶ ምግብ ማለት ነው። እውነትም ግባሶ! ዛሬ ተለፍቶ የተሠራ የቤት መብል፥ አልሚነት ምግብነት ያለው የእናት መብል፥ የማይጥማቸው ልጆች በዝተዋል። እና ማንትስ በርገር ቤት ሄደው በተንጨረጨረ ዘይት የተጠበሰ ድንችና ሥጋ ካልበላን ይላሉ። በቤተ ክርስቲያንም እየሆነ ያለው ይህ ነው። የሚያስፈልገንን ስለሚያውቁ መጋቢዎቻችንና አስተማሪዎቻችን ተግተው አዘጋጅተው የሚያመጡት ግባሶ ለለመደ ሆድ አይጥመንም። እናዛጋለን፥ ሰዓት እናያለን፥ እንቁነጠነጣለን፤ እናንቀላፋለን። ያልሆነውን ግን አውዝተው፥ ቀብተው፥ ስኳርና ማር አልሰው 'እንደወረደ' ብለው ሲያመጡልን እንሰለቅጠውና እናንጎላጃለን። ሆድ ጮማ መፍጨት ስለማይችል ሌላ ቀን ሊፈጨው ቦታ ለማስለቀቅ ወደ ሰዋራ ቦታ ይገፋዋል። እና ከወገባችንና ከሆዳችን መስፋት እንጀምራለን። አንዳንዶቻችን ተሸክመነው እንዞራለን፤ ለአንዳንዶች ኋላ መጥፊያችን ይሆናል።
  3. ምግብነት የሌለው ምግብ። ለምሳሌ፥ ጎመን ጉልበት አይሆንም። ከነተረቱ፥ ሆድን በጎመን ቢደልሉት ጉልበት በዳገት ይለግማል ይሏል። በመንፈሳዊው አመጋገብም ምግብነት የሌለውን ነገር ምግብ ብለው የሚያቀርቡልን በዝተዋል። አረፋ እያበሉ አምቦ ውኃ እንደጠጣ ያስገሱናል። አየር እያበሉን ሆዳችንን ኳሸርኮር እንደያዘው ልጅ ያስመስሉናል። ሆዳችን ተቆዝሮአል፤ ጡንቻ የለንም። ምግብነት የሌለው ምግብ ተብዬ ሆዳችን ውስጥ ስላለ ራቡ አይታወቀንም፤ ግን በጠኔ ውስጥ ነን። ደግሞም ጠኔ የያዘን ከሆንን የሚሰብኩንን ሰባኪዎች ማጣጣም አንችልም። የሰጡንን ሁሉ እንበላለን። እንደ ጎመን እና የወርካ ወተት ያሉትን መብላት ጥቅም የለውም፤ ለዘለቄታው ቀጣይ ከሆነ እንጂ ለጊዜው ጉዳትም የለውም። ምግብ የሚመስሉ ግን ጉዳት ያለባቸው ነገሮች ደግሞ አሉ።
  4. መርዘኛ ምግቦች፥ አካልን የሚመርዙ፥ የሚጎዱ፥ የሚገድሉ ደግሞ አሉ። በቅርብ በደቡብ አፍሪቃ የአይጥ መርዝ ያበላው ነቢይ ነኝ ባይ ጉዳይ በዜና ማሰራጫዎች ናኝቶ ነበር። በዚህ የአይጥ መብል የሞቱም የተጎዱም ነበሩ። ይህን መሰል ቅሌታም ወንጀል ለመፈጸም ይህ ሰው የመጀመሪያው አይደለም፤ ከእርሱ በፊት አያሌ ኖረዋል። የመጨረሻውም አይሆንም። በ1970ዎቹ ከ900 በላይ ሰዎችን በአንድ ቀን የፈጀውን ጂም ጆንስን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ አይዘነጋውም። ከካሊፎርኒያ እስከ ጋያና ድረስ እንደ ዕውር አምነው ለተከተሉትና በአንድ ቀን ለፈጃቸው ሰዎች ያጠጣቸው ለስላሳ መጠጥ ውስጥ ሳያናይድ የተባለ ገዳይ መርዝ መደባለቁን አልነገራቸውም። ጆንስ ሥጋቸውን የገደለበትን መርዝ ብቻ ሳይሆን ለነፍሳቸውም መርዝ ነበር ሲመግባቸው የኖረው።

በ1992 ከሴሚነሪ ትምህርቴ ለበጋ ዕረፍት ወደ አገር ቤት ተመልሼ ነበር። ያደግሁበት ገጠር ሄጄ የተለያዩ የመንደሬን ሰዎች ስጠይቅ በአንድ ሰሞን የሞቱ የአንድ ሠፈር ሰዎች በዙብኝ። እገሌ? ስል ሞተ፤ እገሌስ? እርሱም ሞተ። መቼ? ስል እሱም ሌላውም፥ ሌላውም፥ ሌላውም የሞቱት በሰሞን አንድ ነው። ምን ሆነው ነው ሁሉም በአንድ ሳምንት ውስጥ የሞቱት? ብዬ ስጠይቅ ደርግ ወድቆ ኢሕአዴግ ገና ሥልጣን ሳይይዝ፥ መንግሥት ወድቆ መንግሥት ገና ሳይቆም በነበረው የግርግር ጊዜ የሰፈሩ ሰዎች የገበሬ ማኅበሩን መጋዘን ሰብረው ገብተው ዱቄት ዘርፈው ወስደው ነበር። ያንን ዱቄት ጋግረው፥ አገንፍተው በልተው ግማሹ በዚያው ቀን፥ ግማሹ በማግስቱና በሳልሥቱ ሞተው አለቁ ተብሎ ተነገረኝ። እየጋገሩ የበሉት ዱቄት ለካስ ዱቄት ሳይሆን የበቆሎ ወይም የገብስ ዱቄት የሚመስል 'ዳፕ' የሚባል የአፈር ማዳበሪያ ነው!

በመንፈሳዊው ረገድም እንዲሁ ነው። ታዲያ የዚህ ሰለባ ሆነው አንዳንድ መጋቢዎች መጋቢዎች በመሆን ፈንታ አስመጋቢዎች ሆነዋል። ራሳቸው መብል አዘጋጅተው በማብላት ፈንታ ስንፍናም፥ መሰልቸትም፥ ሰዎችን ለማስደሰት ብለውም፥ ፈንድሻ የሚያበሉንን ነቢያትና ሐዋርያት የሚባል ቆብ የተሰፋላቸውና የተደፋላቸው ሰዎች ይጋብዙልናል። ፈንድሻው በሰፌድ ይቀርብልናል። እናም ፈንድሻ በልተን ፈንድሻ የምናገሳ ክርስቲያኖች ሆነናል። ፈንድሻስ ፈንድሻ ነው፤ አረፋውም አረፋ ነው፤ በግሳት ይወጣልናል። ጎመን ነው ብለው ሰንሰል ሲያበሉንስ? ዱቄት መስሎን 'ዳፕ' እየበላን ከሆነስ? እነዚያ የአይጥ መርዝ የጠጡትስ ተነግሮአቸው ነው የጠጡት፤ ያልተነገረን ሳያናይድ ያለበት ኩሌይድ ቀርቦልን ከሆነስ? አንዳንድ ሰዎች ምግብ ይለምናሉ። አንዳንዶች ግን በምግብ ስም ሌላ ይለምናሉ።

በቅርብ ብሔራዊ ቴያትር አጠገብ ሳር ላይ የተጋደመ ወጣት፥ 'ነፍሱ ራበኝ' አለኝ። ቆምኩና፥ 'እውነት ርቦሃል? ና ምሳ ልግዛልህ' አልኩት። ሰዎች ራበኝ ሲሉኝ ገንዘብ አልሰጥም። ካለኝ ምሳ ነው የምገዛላቸው። ምሳ ገዝቼላቸው አብረን እየበላን ስለጌታ ያካፈልኳቸው ጥቂት ያልሆኑ ሰዎች አሉ። ይህኛው ልጅ ግን ምሳ ሳይሆን ገንዘብ ነበር የራበው። ምሳ ልገዛለት ስጋብዘው፥ 'አቦ፥ ሂድልኛ' አለኝና ሄድኩለት። የሚጠይቀው አንድ ነገር ነው፤ የሚፈልገው ግን ሌላ ነው። ከጥቂት ዓመታት በፊት አንድ ቀን የአንድ ጓደኛችን ልጅ ከትምህርት ቤት እንደመጣች፥ 'ማሚ ጠማኝ' ትላታለች። 'ሃኒ፥ ይኸውልሽ' ብላ ውኃ በመሰለ ብርጭቆ ቀዝቃዛ ኩልል ያለ ውኃ ትሰጣታለች። 'ማሚ ውኃ አይደለም፤ የጠማኝ ኮካ ነው' አለቻት። 'የኔ ቆንጆ፥ ኮካ ያምራል እንጂ አይጠማም፤ የሚጠማው ውኃ ነው' አለቻት። እቅጭ!  ዛሬ በመንፈሳዊው ዓለምም እየመረጡ የሚራቡና የሚጠሙ የበዙበት ፌርማታ ላይ ደርሰናል። የሚቀጥለው ፌርማታ የትኛው መሆኑን ስንደርስ እናያለን። ብቻ አሁን ያለንበት መስቀለኛ መንገድ ይመስላል። ተመጋቢዎች፥ መጋቢዎች፥ አስመጋቢዎች፥ ምንድርን ነው እየበላን፥ እያበላን፥ እያስበላን ያለነው? 

“ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት” (2ቆሮ. 11፥1-4) ሲል የማሳቻውን መሣሪያ አብሮ ጠቅሶአል። በተንኮሉ ነው የተባለው። ስለ ሰይጣን ተንኮል ነው የሚናገረው፤ ግን በዘመኑ ስለነበሩት አሳቾችም ነው የሚነግራቸው። እባብ በተንኮሉ ሔዋንን ያሳታት አትብሉ የተባሉትን ፍሬ በማሳየትና በማስጎምጀት እንደሆነ አሳቾችም ያንኑ ስልት ነው በተንኮል የሚጠቀሙት። ሰይጣን ይህን ፍሬ ሔዋንን ለማብላት የተጠቀመው መንገድ አንድ ነው፤ እርሱም ተንኮል ተብሎአል። ሁላችንም ምክር ጠይቀንም ተጠይቀንም፥ ሰጥተንም ተቀብለንም እናውቃለን። ራሳችን ሌሎችን ምክር ስንጠይቅ ሰዎቹ መልካም መሆናቸውን፣ ሁነኛ መሆናቸውን አውቀን ወይ ገምተን ነው የምንሄደውና የምንጠይቀው። እንደ ሰሎሞን ልጅ እንደ ሮብዓም የስንፍና ምክርን ሆን ብለን የምናግበሰብስ ካልሆንን በቀር (1ነገ. 12 እና 2ዜና 10)። ሰዎች ለምክር ፍለጋ እኛ ጋ ሲመጡም ያንን አድርገው መሆን አለበት። መካሪ እንደሆንን አምነው ወይ ገምተው ነው መጥተው የሚጠይቁን። አንዳንዶች መካሪዎች ደግሞ አሉ፤ ሳንጠይቃቸው በራሳቸው አነሣሽነትና ተነሣሽነት፥ በፈቃደኝነትና በፈቃዳቸው ምክር የሚለግሱ መካሪዎች። ከነዚህ ለጋሾች ዘንድ ምክር ሲመጣ እንቁም። ምክራቸውን ከመስማታችን በፊት የቆምንበትን ስፍራ እንይ። ስናይ፥ በስፍራችን ኖረን ከሆነ እነዚህ መካሪዎች ቀና መካሪዎች ሳይሆኑ የእባብ መካሪዎች መሆናቸው ቁልጭ ብሎ ይታየናል። ሔዋን ያልጠየቀችው የፈቃድ ምክር፥ ማመልከቻ ያላስገባችለት ምክር ሲመጣላት የቆመችበትን ስፍራ ብታየው ያ ቦታ መገኘት ያልነበረባት ስፍራ መሆኑ ይገባት ነበር። ያ ምክር ምክር ሳይሆን ተንኮል መሆኑ ይገባት ነበር።  

“የሚመጣውም ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክ፥ ወይም ያላገኛችሁትን ልዩ መንፈስ ወይም ያልተቀበላችሁትን ልዩ ወንጌል ብታገኙ፥ በመልካም ትታገሡታላችሁ” 2ቆሮ.11፥4። እርሱን ነኝ የሚል ሌላ ኢየሱስ እንደሚመጣ ጌታ ራሱ አስተምሮአል። በማቴ. 24፥5 ብ ዙ ዎ ች ፦ እ ኔ ክ ር ስ ቶ ስ ነ ኝ እ ያ ሉ በ ስ ሜ ይ መ ጣ ሉ ና ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። ብሎአል። እነዚህ ራሳቸው፥ 'እኔ እርሱ ነኝ' እያሉ የሚመጡት ናቸው። ከዚህ በፊት ብዙዎች ተነሥተዋል፤ በአገራችንም ጭምር። አንዳንዶቹ ግን 'እኔ ነኝ' የሚል በሌለበት፥ 'ይህ ኢየሱስ ነው' ብለው ከምናባቸው ውጪ ያልኖረና ኖሮ የማያውቅ ኢየሱስ ፈጥረው ያስተዋውቁናል። ለምሳሌ፥ በኢስላም የምናገኘው ኢየሱስ በወንጌል ውስጥ የማናገኘው ሌላ ኢየሱስ ነው። ምንም መለኮትነት የሌለው፥ ሰው ብቻ የሆነ፥ በአላህ እንዲያምኑ ሰዎችን ያስተማረ፥ በመጨረሻም ሌላ እርሱን መሳይ ሰው ሰው በፈንታው፥ በምትኩ ተሰቅሎ እርሱ ሳይሞት ወደ ሰማይ የተወሰደ ነቢይ ነው። አንዳንድ ሰዎች የምናባቸው ፍጡር የሆነ ኢየሱስ ይሰብካሉ። ኢየሱስ ያልሆነ ኢየሱስ፥ ሌላ ኢየሱስ ሲሰበክ እየሰማን ነን። ስለ ኢየሱስ ማንነት የተሳሳቱ ግንዛቤዎች ከጥንትም ጀምሮ ነበሩ። ከጥንት የነበሩት ባመኑቱ ላይ ያሉትን ትግሎች የሚያሳዩ ናቸው። “ሌላ ኢየሱስ” ሲል እርሱ ጳውሎስ የሰበከው ኢየሱስ አለመሆኑን የበለጠ ግልጽ ለማድረግ፥ 'ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክ' ነው ያለው። ግልጽ ነው፤ ጳውሎስ የሰበከውን ኢየሱስ በ1ቆሮ. 1፥23 ሲገልጥ፥ 'እኛ ግን የ ተ ሰ ቀ ለ ው ን ክ ር ስ ቶ ስ ን እ ን ሰ ብ ካ ለ ን ፤ ይ ህ ም ለ አ ይ ሁ ድ ማ ሰ ና ከ ያ ለ አ ሕ ዛ ብ ም ሞ ኝ ነ ት ነ ው' ነበር ያለው።

የጳውሎስ ኢየሱስ ይህ በመስቀል ላይ የተሰቀለው ኢየሱስ ነው። “የአይሁድ ንጉሥ፥ የናዝሬቱ ኢየሱስ” ተብሎ የክሱ ጽሕፈት በመስቀሉ ላይ የተጻፈበት የተሰቀለው ኢየሱስ ነው። ጳውሎስ እላይ የተመለከትነውን ቃል ለሰበከላቸው ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በ1ቆሮ. 2፥2 “በመካከላችሁ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደተሰቀለ ሌ ላ  ነ ገ ር  እ ን ዳ ላ ው ቅ ቆ ር ጬ  ነ በ ር ና”  አለ። የጳውሎስ የስብከቱ ብቻ ሳይሆን የጠቅላላ ኹነቱ ማዕከል የክርስቶስ መስቀል ነበረ። ጳውሎስ ክርስቲያኖችን እያሳደደ ከኢየሩሳሌም ወደ ደማስቆ ሲሄድ በመንገድ ላይ በምድር ላይ እስኪወድቅና ዓይኖቹ እስኪታወሩ ያየው አስደናቂ ኢየሱስ ከሞት የተነሣው ባለ ግርማ ጌታ ነው። ግን ዐይኖቹ ላይ ተስሎበት የቀረው በመስቀል ላይ የተሰቀለው ክርስቶስ ነው። ስብከቱም ይኸው ነበር። በአንዳንድ ቤተ ክርስቲያኖች መስቀል መሰበኩ ቀርቶአል። የሚሰበከው ኢየሱስ ሌላው ነው። በቅርብ አንድ 'ተንባይ' ኢየሱስን ከተጸነሰበት እስከ ትንሣኤው ድረስ ሰው ብቻ ነው። እንዲያውም እስከ መሰይጠን፥ ሰይጣን እስከመሆን፥ ደርሶአል። ደግሞም ታጃቢ ነበረ ሲል ተናግሮ ነበር። ይህ የወንጌሉ ኢየሱስ አይደለም። ይህ ጳውሎስ የሰበከው ኢየሱስ አይደለም። ይህ ሌላ ኢየሱስ ነው። አሳቾች እንዲህ ያለ ቃል እያበሉ፥ የዋሆችም አፋቸውን ከፍተው እየበሉ ናቸው። ዘመናዊዎቹ አሳቾች በኢየሱስ ላይ ሳይሆን በራስ ላይ ለማጠንጠን ምክንያት ፈላጊ ናቸው።

ኢየሱስ ሌላ የተባለው፥ ምንም እንኳ ከዚህ በፊት ጥቂቶች፥ 'እኔ ኢየሱስ ነኝ' እያሉ ቢመጡም፥ ገና ወደ ፊት ደግሞ ሐሰተኛው ክርስቶስ በአዋጅ እርሱ መሆኑን እያስነገረ ቢመጣም፥ እስካሁን ብዙ አሳቾች ለውጠውና በውዘው፥ ቀናንሰውና ቀያይጠው የሚያቀርቡት ያንኑ ኢየሱስ ነው። ስለዚህ ከልዩ ይልቅ ሌላ መሰኘቱ አግባብ ነው። ኢየሱስ ነኝ የሚል ሌላ ሰው ይኖራል እንጂ ሌላ ኢየሱስ ሊኖር አይችልም። መንፈስ ግን ልዩ መባሉ አንድ ዓይነት ያልሆነ ሌላ መንፈስ በመኖሩ ነው። “ያላገኛችሁትን ልዩ መንፈስ . . . ብታገኙ” ያለው ቀድሞ ያገኙት አንድ መንፈስ መኖሩንም ያሳያል። ያ መንፈስ አማኞች ሲድኑ በውስጣቸው ገብቶ የሚኖረው፥ ወደ አካሉ የሚያጠምቃቸው፥ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሚያደርጋቸው፥ ዳግም ልደትን የሚያቀዳጃቸው፥ የሚቀድሳቸው፥ የሚሞላቸው መንፈስ መንፈስ ቅዱስ ነው። አማኞች ሲያምኑ ይህን መንፈስ አግኝተዋል። በዚህ መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ተጠምቀዋል።” 1ቆሮ. 12፥13 እንዲህ ይላል፥ “አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እ ኛ ሁ ላ ች ን በ አ ን ድ መ ን ፈ ስ አ ን ድ አ ካ ል እ ን ድ ን ሆ ን ተ ጠ ም ቀ ና ል ና ። ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል። በዚህ መንፈስ እየተሞላን፥ እርሱ እየተቆጣጠረንና እየገዛን ልንኖር ደግሞ ተነግሮናል፤ መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ ይህ ማባከን ነውና፤” ኤፌ. 5፥ 18። መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር መንፈስ እንደሆነ ያስተምረናል። መንፈስ ቅዱስም ቅዱሱ መንፈስ ነው።  ከእግዚአብሔር መንፈስ ሌላ ደግሞ የሰው መንፈስ መኖሩን እና ርኩስ መንፈስም መኖሩን ቃሉ አስረግጦ ያስተምራልና ይህን እናውቃለን። እንግዲህ መንፈስ ቅዱስን የሚመስል ግን ከቶም ያልሆነ ልዩ ሌላ መንፈስ አለ ማለት ነው። እነዚህ የቆሮንቶስ ሰዎች ያላገኙትን ልዩ መንፈስ እያገኙ ነው። የእግዚአብሔርን መንፈስ መንፈስ ቅዱስን ሳይሆን እርሱን የሚመስለውን ግን ያልሆነውን ልዩ መንፈስ እያገኙ ነው። ይህንን ገለባውን የሚያቃጥል፥ ልብን የሚያሞቅ፥ በእሳት የተመሰለውን መንፈስ ቅዱስ ሳይሆን፥ ያ ያኔ ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ የመጣውን፥ ወንጌልን ለመስበክ ወደ ኋላ የማያስብል፥ ቅሌን ጨርቄን የማያሰኝ ወደ ወደደበት የሚመራ በነፋስ የተመሰለውን መንፈስ ቅዱስ ሳይሆን፤ ጴጥሮስን በድፍረት ያሰበከውን፥ በዚያ የበዓለ ኀምሳ ቀን የጠጣሮችን ልብ የነካውንና ያሟሟውን፥ ያን የድፍረትና ራስን የመግዛት መንፈስ ሳይሆን ልዩ መንፈስ እየተቀበለች ናት፤ የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን። የሚመስል ግን ያልሆነ ሰው ሠራሽ እሣት እየተቀበለች ናት! የመንፈስ ቅዱስ ያልሆነ የነዳታንና አቤሮን እሣት! የሚመስል ግን ያልሆነ። ሰይጣን አስመስሎ መሥራትን ያውቃል። ስለማስመሰል ወይም አስመስሎ ስለመሥራት ጥቂት ነጥቦች እንይ፤

  1. የሚመስለው የሚሠራው እውነተኛው ባለበት ነው። እውነተኛው ከሌለ መሳዩም አይኖርም። መቶ ብር የሚሠራው አሻጥረኛ፣ መቶ ብር የሚሠራው፣ እውነተኛ መቶ ብር ሲኖር ነው። የሌለ ነገር ውሸታም አምሳያ አይሠራለትም። 
  2. ውሸተኛ ነገር የሚፈበረከው ነገሩ፥ እውነተኛው ነገር፣ ተፈላጊ ሲሆን ነው። የማንትስን ፎቶ አስመስዬ ልሠራ እችላለሁ። ግን ማንትስን ማን ይፈልገዋል። መቶ ብር አስመስዬ ብሠራ ግን ይፈለጋል።
  3. ውሸተኛው ነገር የሚፈበረከው እውነተኛው መገኘቱ ሲጎድል ነው። ባንክ እውነተኛውን ብር ካላቀረበ እነ አጅሬ አስመስሎ አምራቾች ውሸተኛውን ሠርተው ያቀርባሉ። እኛ እውነተኛውን ኢየሱስ ካላቀረብን ሐሰተኞች ሐዋርያትና ሐሰተኞች ነቢያት ሌላውን ኢየሱስ በፍላጎታቸው መጠንና በልካቸው ቀርጸው ቢያቀርቡ ምን ያስደንቀናል? ዛሬም ይህ እየሆነ ነው። ቤተ ክርስቲያን አምልኮ የሚመስል ግን ከክብር የወረደ፥ ከሞገስ የወረደ፥ የቀለለ፥ የኮሰሰ ነገር እያደረገች ናት። የድል ነሺ የድል መዝሙር ወይም የድል ተነሺ እዬዬ ሳይሆን የዘፈን ድምጽ በጉባኤ እየተሰማ ነው። እስክስታ በጉባኤ ከታየ፥ በጥበብ ስም የሆታ ጭፈራና ባሕላዊ ውዝዋዜ ከታየ፥ ምሕዋራችንን ለቅቀን ልንንከራተት ከመስመር ወጥተናል። ሙዚቃውና ተጫዋቾቹ፥ መዝሙሩና ተወዛዋዦቹ፥ ትርዒት ነው የሚሠሩት፤ ሙያተኞች በገንዘብ ለማያውቁትና የማያገለግሉት ጌታ እያጋፈሩ ናቸው።

እንደ ዔሊ ዘመን እግዚአብሔርን የማያውቁ ምናምንቴዎች በመድረክ መሥዋዕት እያሳረጉ ናቸው። የዔሊ ልጆች በመቅደስ ከሚያገለግሉ ሴቶች ጋር ይተኙ ነበር፤ ለነዚህኛዎቹ ሰዎች ግን፥ አይደለም ከሴት ጋር፥ ከሴቶች ጋር መተኛት ምንም ማለት እየሆነ ነው። ያደፈ ሰውነታቸውን እንኳ ሳይታጠቡ መጥተው ይቆማሉ። ቅድስናን የማያውቅ ልዩ መንፈስ ተቀብለዋላ! ለዘፈን ጥብቅና ሽንጣቸውን ገትረው የሚቆሙና የሚከራከሩም መጥተዋል። እግዚአብሔር የሚመለከው በእውነትና በመንፈስ ሲሆን ልዩ መንፈስ ባለበት ግን ሰዎች ለአምልኮ ሳይሆን ለትርዒትና ለመዝናናት ይመጣሉ ሰዎች፤ በቅድስናና በንጽሕና፥ በአክብሮትና በፍርሃት ሳይሆን ቁርስ ሊበሉ ወደ ካፊቴሪያ እንደሚሄዱ፥ ሸቀጥ ሊገዙ ወደ ሱቅ እንደሚሄዱ፥ ምናልባት ሊጠጡ መሸታ ቤት እንደሚሄዱ ሆነው ይመጣሉ። የት እንደመጡ ሳያውቁ፥ ምን እንደሆነ ሳያውቁ ትርዒት እያዩ ሲዝናኑ ቆይተው ወደ መጡበት ይመለሳሉ። በስሜት ግለት ውስጥ ቆይተው አካላቸው ብቻ እንጂ ከስሜታቸው በታች ነፍሳቸው፥ መንፈሳቸው ከቶም ሳይዳሰስ ተሟሙቀው ቆይተው ወደ ቀዘቀዘ፥ ወደ በረደ ኑሮአቸው ይሄዳሉ። በቀጣዩ እሑድ እና በቀጣዮቹ እሑዶችም የሚደጋገምላቸው ይህ ነው። እሑድ ጣራ  ላይ ይወጣሉ፤ ከእሑድ እስከ እሑድ ከመሬቱ በታች ናቸው፤ ወይም የት መሆናቸውን ማን ያውቀዋል? በአንዳንድ አምልኮዎች ስፍራዎች ሰው የእውነት እንስሳ እየተደረገ ነው፤ የአፍሪቃ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን መሳለቂያም እየሆነች ናት። አንዱ እውጭ አውጥቶ ሳር አስግጦአቸው ነበር፤ ሌላው ከጉባኤው ሰዎች ወደ መድረክ አውጥቶ እንደ አህያ እየጋለበ፥ ሌላው እነርሱ እንደ ጋሪ ፈረስ ሆነውለት በጀርባቸው ቆሞ ይሰብካል። ይህ እኮ ጌኛነት ነው። አንዳንዶቹ እንደ አንበሳ ያገሳሉ፤ ሰው አንበሳ ሲሆን ከሰው በላይ መሆን ይመስላቸዋል፤ እንስሳነት እኮ ነው ይህ። ሰው ክቡር ነው፤ ግን ክቡር ሰው እንደ እንስሳ ሲሆን እየታየ ነው። "ክቡር ሆኜ ሳለሁ፤ አምላኬን ረስቼ እንደሚጠፉ እንስሶች መሰልኩ" ብለው ዘመሩ የቆሬ ልጆች (ተስፋዬም "ከቆሬ ልጆች" አንዱ ይመስለኛል፤ በማስተዋል የሚዘምር፤ ጥበብ የሚቀኝ።) ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አያውቅም፤ እንደሚጠፉ እንስሶች መሰለ። (መዝ. 49፥12)። ልዩ መንፈስ በሚገኝበት የአዶ ከብሬ አሠራር አለ። የሰከነ አምልኮ የለም። ልዩ መንፈስ ባለበት አስተማሪዎችና ሰባኪዎች አንድ ጥቅስ ይጠቅሱና ከእውነት ጀርባ ተደብቀው ወይም በእውነት ጀርባ ታዝለው እውነተኛ መስለው ይቆያሉ፤ አስተማሪው እንጂ ትምህርቱ አይታይም፤ ሳይፈተሹ ኬላ አልፈው ከማይክሮፎን ጀርባ ስለቆሙ ብቻ የእግዚአብሔር ወኪል ሆነዋል። ስምንት ወይ ዘጠኝ የማይታወቁና የማይተረጎሙ ቃላት ከተናገረ፥ ድምጹ ካስገመገመ፥ ካቅራራ፥ ከፎከረ፥ ደጋግሞ እንደ አገሬ ሸላይ 'እትትትት!' ካለ፥ ንዳድ እንደያዘው ከተንዘፈዘፈ፥ ለአላዋቂዎች ያ ነው ቁም ነገሩ። ጎል ጠባቂ መስሎ ከመድረክ ዳር እስከ ዳር ከሮጠ፥ ትምህርቱ ምን ይፈይዳል? ድራማው ነው ተፈላጊው። በየቃሉ ጣልቃ አጃቢ ሙዚቃ፥ እዚህ ቀጭ፥ ቋ፥ እዚያ ድው፥ ዷ ከተደረገ ያ ነው አሟሟቂው።

የሚያባብል ጥበብ ቃል! ጳውሎስ በ1ቆሮ. 2፥4-5፥ “እምነታችሁም በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ እንዳይሆን፥ ቃሌም ስብከቴም መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ ነበረ እንጂ፥ በሚያባብል በጥበብ ቃል አልነበረም።” አለ ያኔ። ዛሬ የሚያባብል የጥበብ ቃል ሰዎችን እያባበለ እየወሰደ ነው! ማባበል አለማስኮረፍ ነው፤ ማባበል አለማስቆጣት ነው፤ ማባበል ጠቃሚ ነገርን ሳይሆን እንዳያለቅሱ ዝም ለማሰኘት የማይረባ ነገርን ማስጨበጥ፥ በስኳር የተበጠበጠ ጡጦ ማጥባት ነው። የማይረባ ነገር በሚያስጨብጡን ከንቱ ሰዎች የቤተ ክርስቲያን መድረኮች እየተጣበቡ ነው! የማይረባንን ነገር፥ ብልጭልጭ ነገር፥ ፉሪሽካ ነገር፥ በሚያስጨብጡን ሰዎች ተሞሉ። ፈንድሻ በሚያበሉን ሰዎች! ኧረ ፈንድሻ በስንት ጣ'ሙ፤ አረፋ በሚያበሉንና አግሱ በሚሉን ሰዎች ግራ እየተጋባች ናት! አረፋ በልታችሁ ታውቃላችሁ? እኔ በልቼ አላውቅም፤ ጠጥቼ ግን አውቃለሁ፤ ጋዝ፤ አምቦ ውኃ። ምግብነት የለውም፤ ግን ያስገሳል! የማይረባቸውን ነገር ለመስማት የጆሮ እከክ የያዛቸው ሰዎች ቤቱን ሞልተዋል። የጆሮ እከካም የሆኑት በዙ! የቴሌፎን ኩባንያ የሰጣቸውን ቁጥር ነግረው፥ የጠርሙስ ውኃ፥ ጉማጅ ሳሙና፥ ቁራጭ ጨርቅ ሸጠው፤ እናታቸው ያወጣችላቸውን፥ ጎረቤትና አገር ሁሉ የሚጠራቸውን መታወቂያቸው ላይ የተጻፈውን ስማቸውን ነግረዋቸው፥ አስደንቀው፥ አስገርመው፥ አስደምመው ይልኳቸዋል። ጌታ ቀበሌ የሚያውቀውን ስማቸውን ማወቁ ያስገርማቸዋል? 'እንዲህ ያለ እስከዛሬ አይተን አናውቅም፤ እንጃ ይህ ሰው ክርስቶስ ይሆንን?' እንዳሉት እንዲሉ ያደርጓቸዋል። መቼ ይሆን የጆሮ እከካችን የሚፈወሰው? መቼ ነው መጽሐፍ ቅዱስን ከቴሌፎን ማውጫ ለይተው በማያውቁ ሰዎች እግር ስር ተቀምጠን ቀና ብለን በአድናቆት እያየናቸው መገረማችን የሚያበቃው? ልዩ መንፈስ በሚገኝበት ይህም አለ።

ቤተ ክርስቲያን እመድረኳ ላይ የወደቀችው ኬላ ላይ ያልቆሙና ያልተፈተሹ ሰዎች ከማይክሮፎን ጀርባ የቆሙ ዕለት ነው። ዓለም ሰተት ብላ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብታለች። ያኔ የጌታን መቅደስ ታቦት ነበር ወስደው ዳጎን ቤት ያስቀመጡት፤ ዛሬ ዳጎን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብቶአል። ዳጎን የአሞራውያንና የፍልስጥኤማውያን የሥጋዊ በረከት አምላክ ነው። የሥጋ በረከት፥ የገንዘብ መውደድ፥ የንዋይ ፍቅር፥ የቁስ ናፍቆት በቤተ ክርስቲያን መድረክ ተደርድሮ እየተሸጠ ነው። ሸቀጣም ትውልድና ዳጎናም ትውልድ ልዩ መንፈስ በሚገኝበት በዚያ አለ። ትንቢቱ ይሸጣል፤ በረከቱ በጆንያ ይሸጣል፤ ፈውሱ፥ ጤንነቱ ይሸጣል፤ ቪዛው ጥርመሳው ይሸጣል፤ የተከፈተ ማኅጸን፥ የተከፈተ ሰማይ ይሸጣል፤ እርከኑ፥ መለዮው፥ ማዕረጉ ምኑ ቅጡ፤ ሁሉ ይሸጣል። ይሸጣል፤ ይቸረቸራል።

ስጡ ይሰጣችኋል ሳይሆን ስጡኝ ይሰጣችኋል የሚሉ ደፋሮች የት ነው ያሉት ቢባል ልዩ መንፈስ ባለበት ነው። በሕንጻ ማሰሪያ ስም፥  በእንግዳ ማረፊያ ስም፥ በወንጌልም እንኳ ስም ገንዘብ ይሰበሰባል፤ ደብተር ላይ መዝገብ ላይ ሳይደርስ ይጠፋል። አንዳንዴ መንግሥት ለሕጋዊ ሌብነት ፈቃድ የሰጣቸው ይመስላል። ዛሬ ሐዋርያ ሹም ነው፤ ነቢይም ሹም ነው። ላኪ የሌለው፥ የሚሄድበት አድራሻ የሌለው፥ ራሱ ላኪ፥ ራሱ ተላኪ፥ ራሱ ተቀቢ፥ ራሱ ቀቢ፥ እንደ ናፖሊዮን የራሱን ዘውድ በራሱ እጅ የደፋ፥ ጠያቂ የሌለው፥ ተጠያቂነት የሌለበት ሹመት። የቀደሙት ነቢያት በዚህ ዘመን ቢኖሩ ምን እንደሚሉ ለማወቅ ያኔ ምን እንዳሉ ሄደን ማንበብ ብቻውን የነቢይ ተግባር ምን መሆኑን ሊያሳውቀን ይችል ነበር። እውነተኛው መንፈስ ያንን ነበር ያስደረጋቸው። ዛሬ ልዩ መንፈስ በተገኘበት ግን 'አትውቀሰን' አይባልም፤ ወቀሳ የለማ! ሸቀጡ ውስጥ ላልዳልዳኑት ወንጌል መስበክ የለም፤ ጠላትን መውደድ የለም፤ ቅድስና የለም፤ መስቀል የለም፤ 'ዋጋ ያስከፍላልና፥ ክርስትና' የለም፤ ተግሳጽ የለም፤ እርማት የለም፤ ኃጢአትን አክ እንትፍ በል ማለት የለም፤ ዓለምን ናቅ የለም፤ በኩርነትህን ለምስር ወጥ አትሽጥ፥ ጸጋን በገንዘብ አትለውጥ፥ ጠጉርህን አትላጭ፥ . . . እነዚህ የሉም። እነዚህ ነገሮች አይሰበኩም። እነዚህ አይሸጡማ፤ ዋጋ አያወጡማ! የሚገዛቸው ከኖረም ጥቂት ነው። ጥቂት ሰው የሚፈልገውን ነገር በገፍ ማቅረብ አይቻልም፤ ቢቻልም ትርፍ የለውም። ዋናው ጉዳይ ትርፍ ነዋ! አዲስ ፍጥረትነት ሳይሆን አዲስ ቤት ያዩልሃል፤ አዲስ መኪና ያዩልሻል። ኧረ አዲስ ባልም ያዩልሻል! አሮጌውን ባል የሚያስጥል። ስንት ትዳር አፍርሰዋል እነዚህ መሰሪዎች። ልዩ መንፈስ ባለበት ይህም አለ። 

“ልዩውን” ወንጌል ከማየታችን በፊት እውነተኛውን ወንጌል እንይ። ወንጌል ማለት የቃሉ ቀጥተኛ ትርጉም፥ የምሥራች፥  መልካም ዜና፥  አስደሳች ቃል ማለት ነው። ቃሉን የምናገኘው በአዲስ ኪዳን ይሁን እንጂ አሳቡ በብሉይ ኪዳንም አለ። በአዲስ ኪዳን ቋንቋ፥ ማለትም በግሪክ፥ ቃሉ “ዩዋንጌሊዮን” የሚለው ጥምር ቃል ከሁለት ቃላት የተሠራ ነው፤ መልካም እና መልእክት ከሚሉ። መልካም መልእክት ማለት ነው። በብሉይ ኪዳን ቃሉ “ብሦራህ” የሚለው ነው። ብስራት ማለት ነው። ማብሰር፥ የሚያበስሩት፥ የሚበሰር ነገር ማለት ነው። አንድን ዜና መልካም ዜና ወይም የምሥራች የሚያሰኘው የፍርድ ቃል፥ መርዶ፥ አሳዛኝ ዜና፥ አስደንጋጭ፥ አሸባሪ ወሬ ሲኖር ነው። ያንን የሚቀለብስ፥ የሚቀይር፥ የሚለውጥ፥ የሚተካ ዜና ከኖረ፥ ያ የምሥራች ነው። አዳም ኃጢአት ከሠራ በኋላ፥ ሰውና እግዚአብሔር ተለያዩ። ከዚያ በኋላ ሰውና እግዚአብሔር ግንኙነታቸው ተለወጠ፤ ተለያዩ። እግዚአብሔር ቅዱስ ስለሆነ ፍጹም የሆነው ቅድስናው ኃጢአትን ሊቀጣና ሊበቀል እንጂ ሊቀበል የማይችል ባህርይ ነው።

ለአዲስ ኪዳን ሰዎች የምሥራች ወይም መልካም ዜና፥ ወይም ወንጌል የሆነልን ይህንን የመሰለው የቤዛነት ሥራ ነው። ይህ ነው ወንጌል። መስቀሉ የኃጢአት ዕዳ ተከፈለ ማለት ነው። እንኳን የኃጢአት የገንዘብ ዕዳ ሲከፈልልን እንዴት ያሳርፋል! አሥመራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለሁ ግቢያችን እየመጣ ተማሪዎችን ፎቶ የሚያነሣ አንድ ፎቶ አንሺ ነበረ። አንድ ቀን ሌሎች ልጆች ሲነሡ እኔም ተነሣሁ። ከጥቂት ቀናት በኋላ ፎቶዎቹን አትሞ አመጣና ገንዘቡን እየተቀበለ ማደል ጀመረ። የምንማርበትና የምናድርበት ግቢ የተለያየ ነውና አንድ ቀን ከምንማርበት ግቢ ወደምናድርበት ስመለስ ግቢው በር ላይ አየሁት። ሁለት ወይ ሦስት ብር ነው ዕዳዬ፤ ግን የለኝም። ከሩቅ እንዳየሁት ወደ ኋላ ዞሬ ተመለስኩ። ስንቀዋለል ቆይቼ ስመለስ ሄዷል። እሰይ ብዬ ገባሁ። በማግሥቱ ደግሞ እንደገና መጥቶ እበር ላይ ከካምፓስ ፖሊሶች ጋር ሆኖ ሲያወራ አየሁትና ታጥፌ አሁንም ሳልፈልግ የእግር ጉዞ ሳደርግ ቆይቼ ተመለስኩ። በሳምንቱ ውስጥ በሌላ ቀን ከትምህርት ግቢያችን ስመለስ ሰውየው አለመኖሩን አረጋግጬ ስገባ፥ ከግቢ ፖሊሶቹ መካከል የነበረች አንዲት ክርስቲያን እኅት፥ 'ዘሌ ሓወይ ቆይ. . .' አለችና ከመሳቢያ ውስጥ አውጥታ ፎቶዎቼን ሰጠችኝ። ተቀብዬ፥ በሚቀጥለው ወር ገንዘብ ሲላክልኝ እንደምሰጠው ነገርኳት። 'ዋእ! የምን ገንዘብ? ባለፈው ሰሙን ያመጣ ጊዜ አነ ከፍዬዋሎህ፤ በቃ ውሰድ ተኸፊሉ!' አለችኝ። ፎቶ አንሺውን ከሩቅ ሳየው ተሳቅቄና ተሸማቅቄ ሁለት ቀን ሰፈር ለሰፈር የዞርኩት ለካስ ዕዳዬ ተከፍሎ ፎቶዬ በክብር ተቀምጦ እያለ ነበር! ይህች ትንሽ አመልካች ዕዳ እንደሚያሳቅቅ እና ሳናውቅ የተከፈለ ዕዳ መኖሩን ታሳያለች።  ትልቁ የኃጢአታችን ዕዳ በክርስቶስ መስቀል ተከፍሎአል። መሳቀቅ አበቃ። የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው። ሞት ዕዳችን ነበር፤ የሥጋ ሞት አይደለም፤ ዘላለማዊ ሞት። ግን ሞታችንን እንዱ ክርስቶስ ወሰደውና የዘላለም ሕይወትን ሰጠን። ይህ ነው ወንጌል።

በገላትያ 1፥6-9፣ ይህን በደሙ የተፈጸመውን ኪዳን ወንጌል ሳይሆን ሌላ ወንጌልን የሰበከ የተረገመ ይሁን ይላል ጳውሎስ። በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ ወደ ልዩ ወንጌል እንዲህ ፈጥናችሁ እንዴት እንዳለፋችሁ እደነቃለሁ፤ እርሱ ግን ሌላ ወንጌል አይደለም፤ የሚያናውጡአችሁ የክርስቶስንም ወንጌል ሊያጣምሙ የሚወዱ አንዳንዶች አሉ እንጂ። ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን። አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን። እንዲህ ያለ ትምህርት ሌላ ትምህርት፥ ልዩ ወንጌል ነው። ሰዎችም ጳውሎስ፥ 'ያልተቀበላችሁትን ልዩ ወንጌል ብታገኙ፥ ትታገሡታላችሁ' ያለው ባለፉት ክፍሎች ያየነውን ሔዋንን ያሳተበትን ዓይነት ማሳት ነው። ይህንን በመፈጸም አበላሽቶ፥ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ያዘነበለውን አሳይቶ እያስጠነቀቃቸው ነው። የቆሮንቶስ ሰዎች እየታገሡ ነበሩ። ጳውሎስ ይህን ወንጌልነት የሌለበት ልዩ ወንጌል የሚሰብክ የተረገመ ይሁን አለ። ወንጌል ማለት የምሥራች፥ መልካም ብሥራት ማለት ነው። ወሬውን፥ ዜናውን መልካም ያደረገው አስቀድሞ የነበረ መልካም ያልሆነ፥ መርዶ የሆነ፥ አሳዛኝ፥ አስደንጋጭ፥ የሆነ ዜና መኖሩ፤ ያም ውድቀት፥ ኃጢአት፥ ሞት፥ መለየት፥ ፍርድ፥ ነበረ። ዛሬም በተንኮል የተሠራ ልዩ ወንጌል በዘመናችን መልኩን አሳምሮ እየቀረበልን ነው። ከዚህ ወንጌል፥ ከዚህ መልካም ዜና ፈቀቅ የሚያደርጉ፥ ልዩ ወንጌል፥ የተጣመመ፥ የተወላገደ ወንጌል የሚሰብኩልን ሰዎች አሉ። ያኔ እንደነበሩ ዛሬም አሉ።

ይህን ጽሑፍ ላነበቡ፣ ላላነበቡ እንዲያስተላልፉና በየቤተ ክርስቲያኑ ለመወያያ አባዝተው እንዲጠቀሙ እናሳስባለን። ጽሑፉ ለህትመት እንዲያመች አጥሯል፤ ሙሉውን ጽሑፍ የሚሹ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ይጠይቁ።